Skip to main content
x
አሰልቺ ስብሰባዎች የሰነፎች መደበቂያ ዋሻ እየሆኑ ነው!

አሰልቺ ስብሰባዎች የሰነፎች መደበቂያ ዋሻ እየሆኑ ነው!

ሥራን በተገቢው መንገድ ለማቀላጠፍ በተለያዩ እርከኖች መነጋገር ወይም ሐሳብ መለዋወጥ የነበረ፣ ያለና ወደፊትም የሚቀጥል ነው፡፡ የሥራ ዕቅዶችን ለማዘጋጀት፣ በተዘጋጁ ዕቅዶች ላይ ለመነጋገርና ለመወሰን መወያየት ተገቢ ነው፡፡ ከዚያ ባለፈም ከቤተሰብ ጀምሮ እስከ አገር ሁለንተናዊ ጉዳዮች ድረስ መወያየት ትልቅ ጥቅም አለው፡፡ ትልልቅ ስብሰባዎችን በማዘጋጀት ወሳኝ በሚባሉ አገራዊ ጉዳዮች ላይ መወያየት ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር ከመጥቀሙም በላይ፣ የዘመኑ ሥልጣኔ መገለጫ ነው፡፡ በጋራ የወሰኑት ጉዳይ አፈጻጸሙ የተቀላጠፈ እንዲሆንም፣ በየጊዜው በመገናኘት የምክክር ግምግማ ወይም ክትትል ማድረግ ፋይዳው ብዙ ነው፡፡ አንድ ዘመናዊ ኅብረተሰብ በሥርዓት ለመኖሩ ማረጋገጫ ከመሆኑም በላይ፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲኖርም ይረዳል፡፡ ከእዚህ ውጪ የሚደረጉ ግልጽነት የጎደላቸውና ፋይዳ የሌላቸው የተንዛዙ ስብሰባዎች ለምንም አይጠቅሙም፡፡ በአሁኑ ጊዜ በአገሪቱ በተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማት የተለያዩ አገልግሎቶችን ለማግኘት የሚሄዱ ዜጎች፣ ከዝቅተኛ የሥራ መደብ እስከ አመራር ድረስ የተሰማሩ ሠራተኞችንና ኃላፊዎችን ማግኘት አይችሉም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ‹‹ስብሰባ ላይ ናቸው›› ስለሚባል ነው፡፡ አሰልቺ ስብሰባዎች ከመብዛታቸው የተነሳ እየተንዛዙ ነው፡፡

በተለያዩ ሚኒስትር መሥሪያ ቤቶች ወይም በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጉዳይ ያላቸው ሰዎች የሚመረሩት አታካችና የማያቋርጡ ስብሰባዎች በመብዛታቸው ነው፡፡ ምንም እንኳ ተቋማቱ በተወሰኑ ጊዜያት ከአገልግሎት አሰጣጣቸው ባህርያት አንፃር ስብሰባ ቢኖርባቸው ባይደንቅም፣ ዓመቱን ሙሉ በአሰልቺ ስብሰባዎች መወጠራቸው ትልቅ ችግር እየፈጠረ ነው፡፡ ስብሰባዎች ቀነ ገደብ ተደርጎባቸው አገልግሎት ፈላጊዎችን በማይጎዳ መንገድ ቢከናወኑ ይመረጣል፡፡ ተቋማቱ በሚያወጡት ዕቅድ መሠረት በሕግ በተሰጣቸው ኃላፊነት እየተመሩ በጣም አስፈላጊ የስብሰባ ጊዜያትን ቢወስኑ፣ አገልግሎት ፈላጊው ሕዝብ አይንከራተትም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ስብሰባዎች ሲከናወኑ ባለጉዳዮችን የሚያስተናግዱ ሠራተኞችና የሥራ መሪዎች ሊኖሩ ይገባል፡፡ ያለምንም ማስጠንቀቂያ ወይም ማሳሰቢያ ለበርካታ ቀናት ተቋማቱን ሥራ አስፈትቶ ሕዝብ ማጉላላት የተለመደ ተግባር ሆኗል፡፡ ብዙዎቹ ስብሰባዎች ለሠራተኞችም ሆነ ለተቋማቱ ፋይዳ የሌላቸው፣ ሥራ በታቀደው መሠረት እንዳይከናወን እንቅፋት የሚሆኑ፣ ያላግባብ የመንግሥት በጀት ለአበልና ለተለያዩ ወጪዎች የሚባክንባቸውና የሰነፎች መደበቂያ ዋሻ ናቸው፡፡

ብዙዎቹ አሰልቺ ስብሰባዎች ተደጋጋሚ ከመሆናቸውም በላይ፣ ለተቋማቱም ሆነ ለአገር የሚሰጡት ጥቅም የለም፡፡ በስመ ግምገማ የሚካሄዱት እነዚህ ስብሰባዎች በዕቅድ ያልተያዙ፣ ሌላ ቦታ ላይ ስለተደረጉ ብቻ በየተቋማቱ በትዕዛዝ የሚካሄዱ፣  በርዕሰ ጉዳዮቻቸው የተለየ አጀንዳ ይዘው የማይመጡ፣ የታሰበላቸው ዓላማ ቢኖር እንኳ የማይሳኩ ናቸው፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹ ስብሰባ በአቋም መግለጫ የሚጠናቀቁ በመሆናቸው፣ የተለመደውን ውጤት አልባ የዘመቻ ሥራ ያስታውሳሉ፡፡ እነዚህ ስብሰባዎች ውጤት እንደሌላቸው ዋነኛ ማመላከቻዎች በዕድቅ ያልተያዙ መሆናቸው፣ ተደጋጋሚነታቸው፣ የተሳታፊዎችን ቀልብ አለመያዛቸው፣ ውሳኔያቸው ተፈጻሚ ለመሆን አቅም የሌለው መሆኑና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ በሌላ በኩል አገልግሎት ፈላጊዎችን የሚያጉላሉ፣ በሠራተኞች ላይ የሥራ ጫና እንዲፈጠር የሚያደርጉ፣ ዓመታዊ አፈጻጸምን የሚጎዱና የሥራ ባህልን የሚያበላሹ ናቸው፡፡ በዚህ ሳቢያ አገር ትጎዳለች፡፡ ለሥራ ተነሳሽነት የሌላቸው ሰነፎች ደግሞ ሰበብ ስለሚያገኙ ይደበቁባቸዋል፡፡

ስብሰባዎች ከመብዛታቸው የተነሳ መረጃ የሚፈልጉም ሆኑ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ መድበው ትልልቅ ኢንቨስትመንቶችን የሚመሩ ባለሀብቶች ጭምር እየተጎዱ ነው፡፡ የአንድ የመሥሪያ ቤት ኃላፊን ውሳኔ የሚጠብቁ በርካታ አቤቱታዎችን ዞር ብሎ የሚያያቸው በመጥፋቱ ብቻ፣ በየቀኑ ለኪሳራ የሚዳረጉ የግሉ ዘርፍ ማኅበረሰብ አባላት ብዙ ናቸው፡፡ ከራሳቸው ጀምሮ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል የፈጠሩ አገልግሎት ሰጪዎች፣ አምራቾች፣ አስመጪዎች፣ አከፋፋዮችና ቸርቻሪዎች ሥራ ሲፈቱ አገር ማግኘት የሚገባትን ቀረጥና ግብር ታጣለች፡፡ የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶችን በፍጥነት ማግኘት ያለባቸው ባለጉዳዮች፣ ኃላፊው ወይም ሠራተኛው ለቀናት በስብሰባ ምክንያት ሲጠፋባቸው ለችግር ይዳረጋሉ፡፡ ጊዜ ገንዘብ እንደመሆኑ መጠን በረባ ባልረባው የሚሰበሰቡ የመንግሥት ኃላፊዎችና ሠራተኞች ከሥራ ገበታቸው ሲጠፉ፣ ከግለሰብ እስከ አገር ጉዳቱ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ይህንን ባለመገንዘብ የተፋጠነ ዕርምጃ አለመውሰድ የሰነፎች ተባባሪ መሆን ነው፡፡

በየመሥሪያ ቤቱ ‹‹ስብሰባ ላይ ነን›› እየተባለ ሥራን በአግባቡ አለመወጣት በሕግ ማስጠየቅ አለበት፡፡ እያንዳንዱ መንግሥታዊ ተቋም በሕግ ሲቋቋም የተሰጠው ሥልጣን፣ ኃላፊነትና ግዴታ አለ፡፡ በሕግ መሠረት ሥራን አለመሥራትም ሆነ ኃላፊነትን አለመወጣት ያስጠይቃል፡፡ ሕግ እየተጋፉ አሰልቺ ስብሰባዎችን መደጋገም አንድም ሕገወጥነት ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ኃላፊነትን ለመሸሽ መደበቅ ነው፡፡ ብዙዎቹ መንግሥታዊ ተቋማት በዕቅዳቸው መሠረት ውጤት ለምን አጡ? ተብሎ ጥያቄ ሲቀርብ መልሳቸው የተለመደ ነው፡፡ የማስፈጸም አቅም ማነስ፡፡ ይህ የማስፈጸም አቅም መጥፋት የሚፈጠረው በአግባቡ አቅዶ መሥራት ባለመቻል ነው፡፡ ሥራን በአግባቡ መሥራት ሲያቅት ደግሞ መደበቂያው ስብሰባ ነው፡፡ ያውም አሰልቺ፡፡ ብዙኃኑ ሠራተኞች በፍራቻ ወይም በተለያዩ ምክንያቶች ሥሩ ሲባሉ ይሠራሉ፡፡ ተሰብሰቡ ሲባሉ ደግሞ አንገታቸውን ደፍተው ይመጣሉ፡፡ ይህ ዑደት በአሰልቺነቱ በመቀጠሉ የጠቀመው ለደካሞችና ለሰነፎች መደበቂያነት ነው፡፡

የመንግሥትን የዕለት ተዕለት ሥራዎች በበላይነት የሚመራው አስፈጻሚው አካል ኃላፊነቱን መወጣት ሲያቅተው ፓርላማው ለምን ብሎ ሊያፋጥጠው ይገባ ነበር፡፡ ከላይ እስከ ታች ስብሰባዎች ሥራ እስኪመስሉ ድረስ ሕዝብ ሲመረር ዝም ብሎ ማየት ተገቢ አይደለም፡፡ ሠራተኞች በሥራ ላይ ከሚያሳዩት የአፈጻጸም ብቃት ይልቅ በስብሰባ ላይ በአፈ ጮሌነት ምዘና ሲደረግባቸው፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት ለመጥፋቱ ማረጋገጫ ይሆናል፡፡ አገልግሎት ፈላጊው ሕዝብ በፀሐይና በቁር እየተጠበሰ ለምሬት ሲዳረግ የመልካም አስተዳደር ዕጦት አንድ ማሳያ ነው፡፡ በግልባጩ ግን በመልካም አስተዳደር ማስፈን ስም በሚካሄዱ አሰልቺ ስብሰባዎች የበለጠ ምሬት ይፈጠራል፡፡ ከዘመኑ ሥልጣኔና አስተሳሰብ ጋር በፍፁም መራመድ የማይችሉ የተንዛዙ ስብሰባዎች ለምን አገልግሎት ሰጪ ሠራተኞችን ጭምር ሥራ ያስፈታሉ? ሥራን በሕጉ መሠረትና በዕቅድ መምራት የሥልጣኔ ማሳያ በሆነበት በዚህ ዘመን፣ ልማዳዊና ጎታች አሠራሮች ለምን አገር ይበጠብጣሉ? ለምንስ አደብ እንዲገዙ አይደረጉም? አሰልቺ ስብሰባዎች የሰነፎች መደበቂያ ዋሻ መሆናቸው ማብቃት አለበት!