Skip to main content
x
አንዱን አምሮት ሌላውን አንቆት እንዴት ይሆናል?

አንዱን አምሮት ሌላውን አንቆት እንዴት ይሆናል?

ሰላም! ሰላም! በሬ ስም በሚወጣለት አገር ‘ሥጋ ስም አነሰው’ ብሎ ሃሜት መቼስ አይኖርም። ይኼን ብሎ አንድ በቅርብ የማውቀው ወዳጄ ለሠፈራችን ሕፃናት መዋያ ያከራየውን ግቢውን ወደ ሥጋ ቤትነት ማሸጋገሩን በሩ ላይ ያሰረው ባለሻኛ በሬ ነገረኝ። መዋለ ሕፃናቱ ሲዘጋ ግን የነገረኝ አንድ ውሪ የለም። ሕፃን አዋቂው ‘ቆራጭ’ በሆነበት ጊዜ አንተስ ምንቆርጦህ የሰው ልጅ ታማለህ አትሉኝም? ከደላላነት የሚብስብኝ ዘልዛይነቴ መስሎኝ። ይኼም ሥጋ፣ ያም ሥጋ። ልዩነቱ የእኔ የሥጋት፣ የዚያኛው የአምሮት መሆኑ መሰለኝ። ካላመናችሁ ላመሳክርላችሁ። እኔ ሠፈር የተዘጋው መዋለ ሕፃናት ነው። የተከፈተው ደግሞ ሥጋ ቤት ነው። እንግዲህ የእናንተን ሠፈር አላውቅም። ግን ልገምት። ትናንትና መለስተኛ ክሊኒክ የነበረው ምናልባት ስጠረጥር ዛሬ ጫት ቤት ሆኗል። ወይም ደግሞ መለስተኛ መጻሕፍት አከፋፋይ የነበረ ከሆነም ዛሬ ወይ መጠጥ ቤት ነው ወይም ማሳጅ ቤት ሆኗል። ባይሆን እንኳ በዚህ አያያዛችን ከቀጠልን እመኑኝ ይሆናል። ‘ሳያዩ የሚያምኑ መልካም ዜጎች ናቸው’ እንዳልላችሁ እኔም እንደ እናንተው በሚመጣ በሚሄደው ስም ያጠረው ነገር ተገዢ ነኝ። ታዲያ ሌላ ምን እላለሁ? ብቻ እንዲያው ሲገርመኝ ሰነበተ። ‹‹ኤድያ ያንተ ግርምት ነው እኔን ያስቸገረኝ፤›› ይሉኛል ባሻዬ።

‹‹እንዴት?›› ስላቸው፣ ‹‹ምን አገባኝ ብለህ ነው እንዲህ የምትብሰከሰከው?›› ሥልጣን የለህ። ድምፅ የለህ። ወይ ጉልበት የለህ። ምን ብትጠግብ ነው በዚህ የኑሮ ውድነት ላይ የትም ለፍተህ የምትቆርሰውን እንጀራ አንጀትህ ሳይደርስ የምታበነው?›› ይሉኛል። ቆይ ግን ልክ አይደለም ወይም ኧረ ይኼ ነገር ሲል አድማጭ ቢጠፋ ቢያንስ የመገረም መብቱን ይገፈፋል? ሌላው ሁሉ ቢቀር የተገራሚ ታዛቢ ለመሆን ሲባል ብቻ በሥጋ ተሟሽቶ በቅጠል ተብላልቶ በገብስ የሚታጠብ የዕለት ተዕለት የኑሮ ዘይቤ ከተማችንን አገራችንን ማኖ ሲያስነካው ኧረ ፋውል ነው የሚል ይጥፋ? ለስሙ ግን ኳስ ስንተነትን አንደኛ ነን! ድንቄም ተመልካች አያ!

እሺ ግድ የለም። የዓይኑን ተውትና ወደ ጆሮ ልውሰዳችሁ። መቼም በስሚ ስሚ የነገር ሐረጋችንን አንጠራጠርም። ዓይቶ ማመንማ ዘበት ሆኗል። ይኼ አባባሌ ፌስቡክን እንደማይመለከት አስምሩልኝ። ስምረቱን ስትጨርሱ ወደ ስልክ ጥሪ ልውሰዳችሁ። የወሩ መባቻ ላይ ደብረ ወርቅ አንድ የአክስት ልጅ አለችኝ። ባሏ ያለአመሉ ቢራ ለምዶ ቢራ ቢራ ሲል አንዷን ለመደና እንደወጣ ቀረ። ደግሞ ይኼን ስላችሁ የቢራ ፋብሪካ ኢንቨስትመንትን ልታጥላላ ነው በሉኝ። አልወጣኝም አደራ።  ገና ሁለት ዓመት ያልሞላት ልጅ አላት። ዘንድሮ እኮ? እና ቸጋግሯት የተወሰነ ገንዘብ ልኬላታለሁ። ስልኬ ሲጠራ ሳየው የእሷ ቁጥር ነው። ውሎ አድሮ ምሥጋና የለም። ‹‹ምን ልትለኝ ነው?›› ስል ማንጠግቦሽ ሰምታኝ፣ ‹‹አንተ ደግሞ…›› ብላ ስልኩን አነሳችው።

ከላውድ ስፒከሩ የምሰማው ድምፅ ጩኸት ነው። ‹‹ገደልኳት ገደልኳት…›› እያለች እሪ። ኋላ አንድ የተረጋጋ ሰው ስልኳን ነጥቆ ሲነግረን፣ ቴሌቪዢን ላይ ፊልም እያየች ዓይኗን ሳትነቅል ለሕፃኗ በጡጦ ወተት ስታቀብላት ሕፃኗ ፀጥ። ምን ሆኖ መሰላችሁ? ወተቱን ከነጡጦው ለብ አድርጋ ልትሰጥ የፈላ ውኃ ውስጥ ነክራው እሷ ቀልቧ ፊልሟ ላይ ነው። ሙቀቱን ሳትገምት እንደወረደ ስታወርድላት ፍግም። ይኼውላችሁ እንግዲህ። ቴሌቪዢን ፍርድ ቤት የምንገትርበት ጊዜ ሊመጣብን ነው። ነው ወይስ ዓይን ሊከሰስ ነው? ያዩት ‘በእኛ ይብቃ’ ሲሉ ሰሚዎች እንዳልሰሙ ኖረው ሌሎች በሚቀሰፉባት ዓለም ያተረፍነው ተረትና ንግርት ብቻ ሆነ። ጆሮ ለባለቤቱ . . .!

ሁሉ በደጃችን አልሆን እያለ ቢያስቸግረን የምናወራው ነገር መቼም አናጣ። እናላችሁ ብለን ብለን በ‘የምበላው አታሳጣኝ’ ፈንታ ‘የማወራው አታሳጣኝ’ የምንልበት ጊዜ ላይ ሳንደርስ አልቀረንም። ታዲያ ይኼ ምኑም አይገርምም! ምኑ ይገርማልና? በቃ መኖር ካቃተን መኖር ስለቻሉት ማውራቱ፣ ሌላው ቢቀር አኗኗሪነታችንን ሲያረጋግጥልን በዓይናችን በብረቱ ዓይተናል። (አባባል ስለሆነ እንጂ በተለይ በአሁኑ ጊዜ ብረት ይሁን አይሁን፣ ደረቅ ይሁን እርጥብ የተረጋገጠ አይመስለኝም) መብላት ሲያቅተን ወይ በግላጭ ወይ በድብቅ በልተው ስላደሩት ሆድ ባይሞላም ጨዋታ ሲያደምቅ ታዝበናል። ‹‹እሱ የለመኑትን የማይነሳ የምንጎርሰው ሲጠርብን (ስናጣ) የምናወራው ነገር ይለቅብናል። መፍጠር አይታክተው እሱ!›› የሚለኝ አንድ የሠፈሬ ጫት ነጋዴ ወዳጄ ነው። ለጫት ካለው የተለየ ፍቅር የተነሳ በማይቅሙ ሰዎች ይናደዳል። ‹‹ሰው እንዴት ኑሮን በምርቃና መፎረፍ ሲችል አበሳ ያያል?›› ይለኛል ባገኘኝ ቁጥር።

እና የሚጎረስ ሲጠፋ በወሬ አውርቶ መጥገብን ከልጅ እስከ አዋቂ ሁሉም ተግባራዊ ሲያደርገው ስታዩ ያስገርማችኋል። ላስረዳችሁ፡፡ እንደምናውቀው በከተማችን ሦስት የወሬ ዘርፎች አሉ። እነሱም ሴት፣ ኳስ፣ ፖለቲካ ይባላሉ። ሦስቱም ግን በቀጭን የነገር ትብታብ ከኑሯችን ዋና ጥያቄ ጋር የተያያዙ ናቸው። ግልጽ ሳደርገው ለምሳሌ ስለሴት ሲወራ እንዲህ ሲባል ትሰሙ ይሆናል። ‹‹ውይ! እሷማ ምን የመሰለ ባል አግብታ ህም፣ በደህና ጊዜ ይኼው እመቤት አድርጎ ያኖራታል፤›› ይባልልኛል። ቀጥሉ ደግሞ ስለኳስ፣ ‹‹‘ሊዮኔል ሜሲና ክርስቲያኖ ሮናልዶ ዛራጎዛ የሚባል የስፔን ከተማ ተገናኝተው ምርጥ ፒዛቸውን ግጥም አድርገው በሉ’ ተባለ፤›› ሲባል ትሰማላችሁ። ስለፖለቲካ እንደሆነ ‹‹እከሌ የሚባሉት ባለሥልጣን ጫማ ሰቅለው ሰንብተው ተመልሰው ጨዋታውን ተቀላቀሉ። ‘ሥልጣን እስከ መቃብር’ ማለት እንዲህ ነው፤›› የሚሉትን ትሰማላችሁ። እንግዲህ በእነዚህ ሦስት ዋና ዋና የጨዋታ አርዕስቶች ውስጥ ስንታዘብ፣ ለራሳችን ያጣናውን በሌሎች ሕይወት ስንቆጥረው መዋልን ሙያ ማድረጋችን ነው። የኗሪነት ስሜት ላልተሰማው አኗኗሪ ከመሆን ዘሎ ምን ምርጫ አለ?

ሰሞኑን እጅግ ቸግሮኝ የነበረ ነገር ቢኖር ያገኘኝ አላፊ አግዳሚ ሁላ ‘አንበርብር ምነው ከሳህ?’ ሲለኝ የሰነበትኩበት ቃል ነው። ‹‹አራት እንቁላል አሥር ብር እየተሸጠ እንዴት ብለን ልንወፍርላቸው አስበው እንደሆነ እግዜር ይወቀው? ባልበላ አንጀታችን ሠልፍ በየነገሩና በየቦታው በሆነበት አገር ቆመን ስናዛጋ እየዋልን ከሳህ ብሎ ሀተታ ምን ማለት ነው? ኪራይ ሰብሳቢ መሰልኳቸው እንዴ ይህን ያህል?›› እያልኩ ስነጫነጭ ማንጠግቦሽ ታዳምጠኝ ነበር። ውዷ ባለቤቴ እውነቴን ደግፋ እንዲህ ተናገረች። ‹‹ዝም አትላቸውም? ለነገሩ እንኳን ተራው ሰው መንግሥትስ በዚህ ዕድል መቼ ተጠቀመበት?›› ብላ ወደ እኔ እየተመለከች ጠየቀችኝ። ‹‹እንዴ? ደግሞ መንግሥትን እዚህ ምን ዶለው?›› አልኳት ትስስሮሹን እስክትገላልጠው እየተቁነጠነጥኩ።

‹‹መቼም በዚህ ጊዜ ሰው በደህና ቀን የሞላው ጎተራ ከሌለው በቀር አልያም ደህና የሰው ድጋፍ ካልኖረው ይዞ መገኘትና በምቾት መታየት አይታሰብም። መንግሥት ቢያውቅበት ኖሮ ‘ካልጠቆማችሁኝ የት አገኛቸዋለሁ?’ እያለ እኛ ላይ ማፍጠጡን ትቶ ‘ቪ8’ቶች እየተከተለ፣ በአንድ ምሽት በሺዎች በሚቆጠር ገንዘብ አልኮል የሚንቆረቆርባቸውን መሸታ ቤቶች እያሰሰ፣ የታዳጊ ሴት ወጣቶችን ሕይወት እየሰለለ ቢተጋ ስንቱን ሙሰኛ፣ ስንቱን ዜጋ በራዥ በመነጠረልን ነበር?›› አለችኝ። እንግዲህ በማንጠግቦሽ አገላለጽ ‘ሙስና፣ የኑሮ ውድነት፣ የሞራል ዝቅጠት ጉዳዬ የሚላቸው አካል ባጡበት ጊዜ ከሳህ ብሎ ቋንቋ ምን ይባላል? እንኳን ዜጋ አገር ከስታ ሳለ!’ ነው!

በሉ እንሰነባበት። ተፍ ተፍ ብዬ ያጋለኝን ትዝብትና የፀሐይ ንዳድ በንፋስ ሽውታ፣ ደግሞም የምርጫ ምኅዳሩ ባንቦረቀቀው የቢራ ገበያ የመረጥኩትን ጠርሙስ ይዤ ላበርድ ሰፈር ስደርስ የባሻዬ ልጅ አገኘኝ። ከማን ጋር ልሂድ ስል አለማፈሬ ብሎ አጄን አፈፍ አደረገው። ወዴት ሊወስደኝ መሰላችሁ? ወደሚመረቀው የወዳጃችን ሥጋ ቤት። በሬው ታርዷል። የታረደው ደግሞ ለሠፈሩ ሰፋሪ አፍ ማስያዣ ነው። ይሁና ብዬ ተጎትቼ ስገባ ማንጠግቦሽ ቀድማኝ ታድማ ከባሻዬ አጠገብ ተቀምጣለች። በሩ ላይ በሬ የሚያህል ሞንታርቦ ስፒከር የዘመኑን አሰልቺ ሙዚቃዎች እየደጋገመ ማስደለቁ ሳያንስ፣ ሠፈሩን በድምፅ ብክለት ተቆጣጥሮታል። ከፊት ለፊቱ እኮ የንግድ ፈቃድ አውጥቶ መሸታ ቤት የከፈተ ደንበኛዬ ድምፅ በክለሃል ተብሎ ቤቱ ታሽጓል። እንኳን ነዋሪውን በቤቱ ጩኸት እንቅልፍ ሊነሳ ይቅርና ባይል ከያዘ ጀምሮ ያለቫይብሬሽን የመጥሪያ ድምፅ ለእጅ ስልኩም መርጦ አያውቅም። ብቻ ተውኝ።

የሁለም ነገር መፍትሔው የድምፅ አወጣጥ እንጂ ድምፅ ባልሆነባት አገሬ ይኼን ማውራት አይጠቅምም። እናላችሁ ገና ሳልቀመጥ ‘ከረሜላ’ ተቆርጦ መጣ። እያቅማማሁ እሱን በዳጣ ስውጥ ደግሞ ከሽንጡና ከዳቢቱ ሌላ ሥጋ ቀረበ። ሥጋ በሥጋ ላይ ሲደራረብ እኔ ሥጋቴ ባሰ። ሐሜተኛ ሁሉ የምሱን እየዋጠ ነገ እንደማያሽሟጥጥ ሆኖ አጀብ አጀብ ሲል እየገረመኝ፣ የተነቃብኝ ሲመስለኝ ሰላምታ ለማስመሰል አንገቴን ደፋ ቀና አደርጋለሁ። ተበልቶ ሲያልቅ ደግሞ ተራውን ውስኪ በውስኪ ላይ ተነባበረ። እነ በልተን እንሙት መብልና መጠጥ ዓይተው እንደማያውቁ እያየሁ ያቅረኝ ጀመር። የሙዚቃው ጩኸት የጆሮ ታንቡሬን ሊበጥሰው ሲሆን አላስችል ብሎኝ በራስ ምታት አሳብቤ አመስግኜ ልወጣ ስል፣ ነገ እንዳትቀር ሌላ በሬ ይታረዳል ተባልኩ። ምን ፈራህ በሉኝማ? በሌለ አቅማችን በሉ፣ ጠጡ፣ ሞቱም ተብሎ እንዳይጻፍ ነዋ ታሪካችን። ቆይ እስቲ? አንዱን አምሮት ሌላውን አንቆት እንዴት ይሆናል? መልካም ሰንበት!