Skip to main content
x
አገር ችግር ውስጥ የምትገባው ሕዝብ በመንግሥት ላይ ያለው አመኔታ ሲነጥፍ ነው!

አገር ችግር ውስጥ የምትገባው ሕዝብ በመንግሥት ላይ ያለው አመኔታ ሲነጥፍ ነው!

ሕዝብ በመንግሥት ላይ ያለው መተማመን ሲነጥፍ በቅርቡ እንደታየው አገርን ትርምስ ውስጥ የሚከት ሁከት ይቀሰቀሳል፡፡ የሥልጣኑ ባለቤት እንደሆነ ከሚታመነው ሕዝብ ጋር መደማመጥ ያቃተው መንግሥት ራሱን ለአደጋ፣ አገርን ደግሞ ለመተንበይ ለሚያዳግት ውድመት ያጋልጣል፡፡ አገሪቱን ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በዳረገውና በርካቶች ሕይወታቸውን ባጡበት ሁከት ማግሥት አንፃራዊ መረጋጋት ቢታይም፣ ይህንን መረጋጋት የሚያደፈርሱ ክስተቶች ገጽታቸውን እየለዋወጡ ናቸው፡፡ በዚህች አገር ለዘመናት ሕዝብን ሲያማርሩ የነበሩ ድርጊቶች መልካቸውን እየቀያየሩ ሲቀጥሉ እንጂ፣ መፍትሔ ተፈልጎላቸው መግባባት ሲፈጠር አይታይም፡፡ የ2009 በጀት ዓመት ተዘግቶ አዲሱ በጀት ዓመት ሲጀመር እየተንከባለሉ የመጡ ችግሮችን ተሸክሞ መጓዝ የማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡ ከዓመት ዓመት አገርን የሚያተራምሱና ሕዝብን ለምሬት የሚዳርጉ ጉዳዮች አሁንም እንደተጣቡን መቀጠል አይኖርባቸውም፡፡ አንድ በአንድ እያነሱ መነጋገር ተገቢ ነው፡፡ መንግሥት ራሱን ችግር ውስጥ እየከተተ የሕዝብ አመኔታ ያጣባቸውን ውስን ማሳያዎች እንጠቃቅሳለን፡፡

በአሁኑ ጊዜ የአብዛኞቹ የከተማ ነዋሪዎች አንገብጋቢ ጥያቄ መጠለያን ይመለከታል፡፡ በተደጋጋሚ በዚህ ርዕሰ አንቀጽ ላይ ለማመልከት እንደተሞከረው፣ መንግሥት የሕዝብን አመኔታ እያጣበት ያለው የመኖሪያ ቤት ጉዳይ ነው፡፡ መንግሥት ቃል በገባው መሠረት ቤቶችን ገንብቶ ማስረከብ ባለመቻሉ ምክንያት፣ በቤት ኪራይ መከራ የሚያዩ ዜጎች ቁጥር ከመቼውም በላይ አሻቅቧል፡፡ ከመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በፊት በተጀመረው የቤቶች ልማት መርሐ ግብር የተመዘገቡ በርካታ ዜጎች ላለፉት 13 ዓመታት እየጠበቁ ነው፡፡ ባለፉት አራት ዓመታት ተመዝግበው እየቆጠቡ ያሉ ዜጎች መቼ እንደሚደርሳቸው አይታወቅም፡፡ በ40/60 መርሐ ግብር ተመዝግበው ሙሉ በሙሉ የከፈሉና እየቆጠቡ ያሉ ዜጎች ደግሞ ሰሞኑን ተስፋ አስቆራጭ መልክዕት ተላልፎላቸዋል፡፡ ባለአንድ መኝታ ክፍል ቤቶች አለመገንባታቸው፣ ተመዝጋቢዎች ከተዋዋሉት ስምምነት ውጪ ባለአራት መኝታ ክፍል ቤቶች መገንባታቸውና ለሌላ አካል የሚተላለፍበት ዕድል መኖሩ መሰማቱ፣ መንግሥት ለተሿሚዎቹ ገንብቶ ወይም ከሪል ስቴቶች ገዝቶ ማቅረብ ሲገባው የ40/60 ፕሮግራም ላይ አነጣጥሯል መባሉ ከፍተኛ ቅሬታና ውዥንብር ፈጥሯል፡፡ በዚህም ሳቢያ ሕዝብ በመንግሥት ላይ ያለው እምነት እየጠፋ ነው፡፡ በ40/60 የቤቶች ግንባታ መርሐ ግብር አንድ ሺሕ የማይሞሉ ቤቶች ለዕጣ ሲቀርቡ ይህንን ሁሉ መራኮት ምን አመጣው? ሕዝብ ይህንን ድርጊት እያየስ እንዴት መንግሥትን ያምናል? መንግሥት የሕዝብን አመኔታ እያጣ እስከ መቼ ይቀጥላል?

የተመልካችን ዓይን የሚያስደምሙ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልዩ ትኩረት ተሰጥቷቸው እየተገነቡ እየተመረቁ ነው፡፡ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት እየተከናወነ ያለው ተግባር የሚያስመሰግን ነው፡፡ በአንድ ወገን በልዩ ትኩረትና ትጋት በዓይን የሚታዩ አስመስጋኝ ተግባራት ሲከናወኑ፣ በሌላ በኩል ደግሞ አገርን አንገት የሚያስደፉ ድርጊቶች ይንሠራፋሉ፡፡ በመንግሥት ከሚካሄዱ ግዙፍ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ የስኳር ፕሮጀክት ነው፡፡ ይህንን የአገር ከፍተኛ ሀብት የሚፈስበትን ግዙፍ ፕሮጀክት መንግሥት በአግባቡ ማስኬድ ባለመቻሉ የተነሳ በሕዝብ ዘንድ አመኔታ ጠፍቷል፡፡ ከመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎትሜሽን ዕቅድ በፊት የጀመረው የተንዳሆ ስኳር ፕሮጀክትና ከዚያ በኋላ የተጀመሩ ሌሎች የስኳር ፕሮጀክቶች በጊዜያቸው አለመጠናቀቅ፣ በሕዝቡ ውስጥ የሚብላሉ በርካታ ጥያቄዎችን ያስነሳል፡፡ መንግሥት የማስፈጸም ብቃቱ ጥያቄ ውስጥ ገብቶ በተለያዩ መድረኮች መነጋገሪያ ሲሆን ለምን አይባልም እንዴ? እነዚህ ፕሮጀክቶች በጊዜያቸው ተጠናቀው ማምረት ቢጀምሩ የሕዝቡን ፍጆታ ሸፍነው ለአገር የውጭ ምንዛሪ የሚያመጡ ነበሩ፡፡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች እየተገነቡ ባሉበት አገር ውስጥ እነዚህን ፕሮጀክቶች አጠናቆ ሥራ ለማስጀመር አለመቻል በሕዝብ ዘንድ ከነቀፌታ በላይ አመኔታም ያሳጣል፡፡ እየሆነ ያለውም ይኼ ነው፡፡

መንግሥት ለዓመታት መልካም አስተዳደር ለማስፈን፣ የፍትሕ ሥርዓቱን ለማስተካከል፣ ሙስናን በፅናት ለመታገል፣ ወዘተ. በማለት በተደጋጋሚ ቃል ገብቷል፡፡ ተሃድሶ ውስጥ በመግባትም እንቅስቃሴ መጀመሩን ወትውቷል፡፡ አሁን ግን ከወረዳ ጀምሮ እስከ ላይኛው መዋቅር ድረስ ሕዝብን ማስመረር ተባብሷል፡፡ በስብሰባ ምክንያት ሹማምንትን ማግኘት አዳጋች ሆኗል፡፡ በሥራ ገበታቸው ላይ ሆነው ሕዝብን ማገልገል የሚገባቸው የመንግሥት ሠራተኞች አይገኙም፡፡ ሕዝብ ግብር እየከፈለ በጀት የሚመድብላቸው መንግሥታዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሥራቸው ስብስባ ሆኗል፡፡ በቀጥታ አገልግሎት ከማግኘት ይልቅ ጉዳይ አስፈጻሚ በሚባሉ ደላሎች አማካይነት በክፍያ ጉዳይን መፈጸም የዘወትር ተግባር ሆኗል፡፡ ሙስና እንደ ሰደድ እሳት ተስፋፍቶ ሕዝቡን እየለበለበ ነው፡፡ አገልግሎት ማግኘት የሚቻለው በሕገወጥ መንገድ ጉቦ እየተከፈለ ነው፡፡ አሁንማ በግልጽ የተደነገገ እስኪመስል ድረስ ተቋማት የጉዳይ አስፈጻሚ ደላሎች መፈንጫ እየሆኑ ነው፡፡ ሕዝብ ምሬቱ ከሚቆጣጠረው በላይ እየሆነበት ነው፡፡ በወረዳና በክፍለ ከተማ ጉዳይ ያላቸው ዜጎች በመንግሥት ላይ ያላቸው እምነት እየተሟጠጠ ነው፡፡ በየደረጃው ያሉ አስፈጻሚዎች ብቃት ማነስ ተጨምሮበት መልካም አስተዳደር ማስፈን ቀርቶ መግባባት አልተቻለም፡፡ ከአንዱ ቦታ በብቃት ማነስ ተገምግሞ የተባረረ ተሿሚ ሌላ ቦታ እየተሰየመ በለመደው መንገድ ማተራመሱን ቀጥሏል፡፡ በዚህም የሕዝቡ ምሬት ንሯል፡፡ በመንግሥት ላይ ያለው እምነት ተሸርሽሯል፡፡

የፍትሕ ሥርዓቱ ላለፉት 26 ዓመታት ብዙ ተብሎበታል፡፡ መንግሥት የፍትሕ ሥርዓቱን ለማስተካከል፣ ሰብዓዊ መብቶችን ለማስከበር፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲገነባና ፍትሕ ለሁሉም ዜጎች ተደራሽ እንዲሆን አደርጋለሁ ሲል በተደጋጋሚ  ተሰምቷል፡፡ በዚህ በኩል የአንድ ትውልድ ዕድሜ ተቆጥሯል፡፡ ነገር ግን የፍትሕ ሥርዓቱ ዜጎችን በአንድ ዓይነት መነጽር እያየ አይደለም፡፡ ዜጎች በነፃነት ሐሳባቸውን መግለጽ እየፈሩ፣ በሚፈልጉት የፖለቲካ ድርጅት ለመደራጀት እየተሸማቀቁና ተሳትፎአቸው እየተገደበ ይበሳጫሉ፡፡ የፍትሕ ሥርዓቱ መብታቸውን ስለማያስከብርላቸው ይማረራሉ፡፡ የሕግ የበላይነት አለ በሚባልበት አገር ውስጥ በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጡ መብቶች ባለመከበራቸው ብቻ የአገሪቱ የፖለቲካ ዓውድ ተዘጋግቷል፡፡ ፍትሕ ለመጠየቅ የወጡ ዜጎች በገንዘብ እንዲገዙ ተገደዋል፡፡ መለስተኛ ቅራኔዎች መሠረታዊ አየሆኑ መደማመጥ ጠፍቷል፡፡ በገዛ አገራቸው ባይተዋርነት የሚሰማቸው ብዙ ናቸው፡፡ ከነፃ ውይይቶች ይልቅ መገለማመጥ የሰፈነበት ጊዜ ውስጥ በመገባቱ፣ ሕዝብና መንግሥት የተለያዩ ይመስላሉ፡፡ በዚህ ሁኔታስ እስከ መቼ መቀጠል ይቻላል?

መንግሥት ከሕዝብ ጋር የሚቀያየመውና የሚጣላው ሕዝብን በአንክሮ ማዳማጥ ባለመቻሉ ነው፡፡ ወጣቶች በሥራ አጥነትና በሌሎች የመብት ጉዳዮች ሳቢያ ብሶታቸው ገንፍሎ አደባባይ ሲወጡ ምን እንደተከሰተ የቅርቡ ብጥብጥ ትልቅ ምስክር ነው፡፡ ሕዝብ ብሶቱ ከመጠን በላይ ሆኖ ለመንግሥት ጀርባውን በመስጠቱ የተፈጠረው ምስቅልቅል አይዘነጋም፡፡ መንግሥት አገርን በአግባቡ መምራት የሚችለው ከሕዝብ ጋር ሲነጋገር ብቻ ነው፡፡ ሕዝብን በሚገባ ማዳመጥ ሲችል ነው፡፡ መንግሥት ራሱን ሲገመግም መቼ ነው ከሕዝብ ጋር በጋራ መክሬ መፍትሔ ማምጣት የምችለው ማለት አለበት፡፡ የራሱን አጀንዳ ብቻ ለማስፈጸም ሲሯሯጥ ግን ከሕዝብ ጋር ይጋጫል፡፡ ለዓመታት ፈራቸውን በሳቱ ውሳኔዎች ምክንያት መንግሥት ከሕዝብ ጋር ሲጋጭ ነበር፡፡ አሁንም አገሪቱን የተበተቧት በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ የሕግ የበላይነት እንዲከበርና ሁሉም ዜጋ በሕግ ፊት እኩል መሆኑ እንዲረጋገጥ፣ መንግሥት ለሕዝብ ፈቃድ ተገዥ መሆን ይኖርበታል፡፡ የሕዝብን ፍላጎት በመጋፋት ግን ከጥፋት በስተቀር ምንም አይገኝም፡፡ ሕዝብን ለችግር አገርን ለትርምስ ከመዳረግ በስተቀር፡፡ አሁንም በተለያዩ መስኮች ሕዝብን የሚያስከፉና ብሶቱን የሚጨምሩ ድርጊቶች ይቁሙ፡፡ ሕዝብ ፍትሕ፣ እኩልነትና ነፃነት ይፈልጋል፡፡ ይህ ፍላጎት በተግባር ይረጋገጥ፡፡ አገር ችግር ውስጥ የምትገባው ሕዝብ በመንግሥት ላይ ያለው አመኔታ ሲነጥፍ መሆኑ ይሰመርበት!