Skip to main content
x

ኢትዮጵያ በ‘ዴማጎጊዝም' እንዳትታለል

የእንግሊዝኛው መዝገበ ቃል 'ዴማጎጊን' ሲያብራራ የሕዝብን ስሜት ኮርኩሮ በመጠምዘዝ ተደናቂ መሪ ለመሆን መሻት  ነው፡፡ በታዋቂነት ወይም በዴማጎጊዝም ከመጠን በላይ ሥልጣን የሚጠሙ ሰዎች በሐሳብ ብስለትና በዕድሜ ታላላቆቻቸው የሚሆኑ ሰዎችን ለማስወገድ፣ ጎሳ ጠቀስ ፌዴራሊዝሙ አልበቃ ብሏቸው የዕድሜ ፌዴራሊዝም ሊያቋቁሙ ይፈልጋሉ፡፡  

በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ስለኢኮኖሚ ጉዳይ በሪፖርተር ጋዜጣ ካወጣኋዋቸው ሃያ አምስት ጽሑፎች ዕረፍት ወስጄ የጻፍኳቸውን በማደራጀት መመርመር ላይ እያለሁ፣ ሚያዝያ 9 ቀን 2009 ዓ.ም. በኢኤንኤን ቴሌቪዥን ጣቢያ ‘ፊት ለፊት' በሚባል ዝግጅት ከአቶ ልደቱ አያሌው ጋር የተደረገ ቃለ ምልልስ አየሁ፡፡ ከ1960ዎቹ ወጣት ታጋዮች እስከ ዛሬ ድረስ በመታገል ላይ ያሉት አዛውንቶቹ ፖለቲከኞች ለአገር የሚጠቅም ሐሳብ እንደሌላቸው አድርገው በማንኳሰስ ሲናገሩ ስለሰማሁ፣ መልስ መስጠት እንደሚገባኝ ተሰማኝ፡፡  

ለነገሩ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊም የፓርላማ ስብሰባ ላይ ስለ60ዎቹ ሊያወሩ ሲከጅሉ ባልተወለድክበት ዘመን ስለሆነው የምታውቀው ነገር የለም ዝም በል ብለዋቸዋል ሲባል ሰምቼአለሁ፡፡ የማይረባውን ትናንትን እንርሳው ከባዶ ተነስተን ነገን እንገንባ በሚል ሐሳብ የ1960ዎቹ ሰማዕታት ሲብጠለጠሉ ዝም ማለት አልቻልኩም፡፡ ‹‹የነበረ ይናገር የቀበረ ያርዳ›› ነውና በጊዜውና በቦታው በመኖሬ የማውቀውን እናገራለሁ፡፡

 

በተማሪነት ጊዜዬ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ውስጥ ከመሳተፍ የዘለለ የአመራር ሚና የተጫወተ ፖለቲከኛ አልነበርኩም፡፡ በአባልነትና በደጋፊነት ግን ለተማሪዎች ትግል ዓላማ በ1964 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጀምሬ ወጣ ገባ እያልኩ ለሦስት ዓመታት የተከታተልኩትን የኢኮኖሚክስ ትምህርት ያለ ውጤት እስከማቋረጥ ደርሼ መስዋዕትነት ከፍዬአለሁ፡፡ ፖለቲከኛነትን አሁን በጣም ጠላሁት፡፡ ምክንያቱም በሐሳብ ተቀባይ መሆን አለመሆን ሳይሆን በጅምላ በዕድሜ መግፋት ምክንያት ሐሳቡ ዋጋ የለውም የሚባልበት ሙያ ሆነብኝ፡፡

ማንኛውም ሌላ ሙያ አንባቢ ከሆንክ ዕድሜህ ሲጨምር ዕውቀትህም ይጨምራል እንጂ አይቀንስም፡፡ ከአንተ በታች ያለው ልምድና ዕውቀት ከአንተ ይማራል እንጂ አንተን ሊያስተምርህ አይልም፡፡ እንደሚመስለኝ በፖለቲካውም ለሥልጣን የሚቋምጡ ዴማጎጎች በዕድሜ ፌዴራሊዝም ስብስብ ሰውን ከሰው የሚከፋፍሉበት ሥልት እንጂ የጤናማ ሰዎች አስተሳሰብ አይደለም፡፡ የእነዚህ ሰዎች ዓላማና ተልዕኮ የጎሳ ፖለቲካው አልበቃም፣ እንደርብ የተወሳሰበውን የባሰ እናወሳስበው የሚል ነው፡፡

የኢትዮጵያን ነፃነት ያስከበሩት የዓድዋና የማይጨው ጀግኖች ወጣቱም አዛውንቱም በአንድነት እንደነበሩ የማያውቅ ሰው የለም፡፡ ካለም የቴዲ አፍሮን ወይም የእጅጋየሁ ሺባባውን ክሊፖች ይመልከት ወይም እነ ባልቻ አባ ነፍሶ የስንት ዓመት ሰው እንደነበሩ ይጠይቅ፡፡ የዕድሜ ፌዴራሊዝም ፈጥረው ቢሆን ኖሮ ይህችን አገር እስከ ዛሬ ድረስ አያቆዩልንም ነበር፡፡  

የትናንቱንና የዛሬውን የናቀ ነገን አያያትም፡፡ በዓድዋና በማይጨው ተዋግተውና ወጣቱን አዋግተው ለድል ያበቁት የ70 እና የ80 ዓመት አዛውንት የነገዋ ኢትዮጵያ እናንተ ናችሁና እናንተ ተዋጉ አላሉም፡፡

ከዚህ በፊት ባቀረብኳቸው ጽሑፎች ውስጥ ከአዲስ አበባ ተማሪዎች እንቅስቃሴ ከጥቂቱ በቀር አብዛኞቹን የትግል መሪዎች በአካል እንደማውቃቸው፣ ስማቸውንና የማውቅበትን ሁኔታ ጠቅሼ ጽፌአለሁ፡፡    

በ1960ዎቹ ወጣቱ በሙሉ በሁለት ጎራዎች ተሠልፎ ሲፋለም መሪዎቹ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ብርሃነ መስቀል ረዳ፣ የመላው ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ (መኢሶን) ኃይሌ ፊዳ የሁለት ብሔረሰቦች አባላት ቢሆኑም፣ ያሰባሰቧቸው አባላት በአገሪቱ ሁሉንም ብሔረሰቦች የሚወክሉ ነበሩ፡፡ ከደርጉ ዋና ሊቀመንበር ጄኔራል ተፈሪ በንቲ እስከ የ12 ዓመት ልጆች ድረስ የኢሕአፓ አባልና ደጋፊ ነበሩ፡፡ ከተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበሩ ሻለቃ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም እስከ የ12 ዓመት ልጆች ድረስ የመኢሶን አባልና ደጋፊ ነበሩ፡፡

በሁለት መሪዎችና በሁለት ሐሳቦች ዙሪያ ተሰባስቦ መሣሪያ ተማዞ ሕይወቱን እስከ መለገስ የደረሰን የ1960ዎቹን ወጣት ከመኮነን በፊት፣ 22 ቦታ ተበጣጥሶ የግል አጀንዳና የምፅዋት ኮሮጆ ይዞ ከመዞር መንፃት ያስፈልጋል       

በሐሳብ ማሸነፍ ማለት ይህን ዓይነት ልጅ አዋቂ ሳይሉ፣ የዚህ የዚያ ብሔር ሳይሉ፣ ሰውን በሰውነቱ ብቻ አሳምኖ የሐሳብ ተጋሪ ማድረግ እንጂ፣ ከደቡብና ከአማራ ብዙ አባላት አሉን ከሌሎቹ ብሔረሰቦች ሊመጡልን አልቻሉም ማለት በኃፍረት የሚያሸማቅቅ የሐሳብ ሽንፈት ነው፡፡ የኦሮሞ ልጆችን ያልያዘ ምን ዓይነት ኅብረ ብሔር ፓርቲ ነው? ኃይሌ ፊዳና ብርሃነ መስቀል ረዳ ከ40 ዓመታት በፊት ያደረጉትን እኔ ዛሬ ማድረግ ለምን አልቻልኩም ብሎ ራሱን መጠየቅ ያቃተው፣ ለሽንፈቱ የሚሰጠው መልስ አዛውንቶቹ የምነግራቸውን አይሰሙኝም የሚል ተመፃዳቂነት መሆኑ ይገርማል፡፡

 

በብሔር መደራጀቱ አልበቃ ብሎ 'ወጣት ሽማግሌ' እያሉ የዕድሜ ፌዴራሊዝም ይፈጥራሉ፡፡ ወጣቱ የትናንቱንና የዛሬውን ረስቶ ስለነገ ብቻ ያስብ ይላሉ፡፡ የነገ ኢትዮጵያ በትናንቱና በዛሬው ወደ ነገው ትሸጋገራለች እንጂ፣ እንደ አዲሲቱ እየሩሳሌም ከባዶ ተነስታ አትገነባም፡፡ ለነገ የማይጠቅም ትናንት እንደነበረ ሁሉ ለነገ የሚጠቅም ትናንትም አለ፡፡

‹‹ዘር ከልጓም ይስባል›› እንዲሉ በዘር የተደራጁት አሸነፉ እንጂ፣ ከጥቂቶች በ20ዎቹ ዕድሜያቸው ሥልጣን ለመጨበጥ በሚስጥር የጆሴፍ ስታሊንን የብሔር ጥያቄ መንገድ ከመረጡት በቀር፣ የ1960ዎቹ ወጣቶች ትግልና መፈክር መሬት ለአራሹ የሚሉ ኢኮኖሚያዊ የመደብ ጥያቄዎች ነበሩ፡፡

ከሁለትና ከሦስት ብሔረሰቦች የተውጣጡ መሳፍንትና መኳንንት ጨቋኝ የገዢ መደቦችና አጋር የየብሔሩ ፊውዳል ባላቶች ይኑሩ እንጂ፣ በኢትዮጵያውያን መካከል ጨቋኝ ተጨቋኝ ብሔረሰብ የሚባል የሕዝብ ክፍፍል አልነበረም፡፡

መብራትና መንገድ ለማየት እስከ 21ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ የጠበቁት የሰሜን ሸዋ ገጠሮች የቅርብ ዘመን ነገሥታት የበቀሉባቸው ቢሆኑም፣ ሕዝቡ አልፎለት አያውቅም፡፡ ዋና ከተማ የነበረችው ደብረ ብርሃንም ሕንፃ የሚባል ነገር ካየች 20 ዓመት እንኳ አይሞላትም፡፡  

ወጣቱ ብልህ ስለሆነ በአገር ጉዳይ ማንም ይሁን ማን ሐሳቡ ብቻ ተቀባይ ይሁን እንጂ በዕድሜ አይከፋፍልም፡፡ ብዙ የዓለም መንግሥታት መሪዎችም ከወጣቱም ከአዛውንቱም አሉባቸው፡፡ በወጣትነታቸው ብቻ ለመሪነት እበቃለሁ ለሚሉ ዴማጎጎች አንድ ማስረጃ ቆጥሬ ማስረዳት እፈልጋለሁ፡፡

በተማርኩበት በሶቭየት ኅብረት፣ ሶቭየቶች ለእወደድ ባይ ዴማጎግ ወጣት ሥልጣን መስጠት አገር እንደሚያፈራርስ ያምኑ እንደነበር አውቃለሁ፡፡ እንደ አጋጣሚ ሆኖ አራተኛው የሶቭየት ኅብረት ኮሙዩኒስት ፓርቲ ሊቀመንበር የነበሩት አዛውንቱ ሊዮኔድ ብሬዥኔቭ እንደታመሙ አሜሪካ ነበርኩና ጋዜጦቹ ሁሉ የቀዮቹ ብሬዝኔቭ መሞቱ ነው እያሉ ሞታቸውን መጠባበቃቸውን ይጽፉ ነበር፡፡ ያሉት አልቀረም ብዙ ሳይቆዩ ሞቱላቸው፡፡

ሶቭየቶች አንድሮፖቭና ሱስሎቭ የተባሉ 80 ውስጥ የገቡ አዛውንቶችን በብሬዥኔቭ እግር ተራ በተራ ቢተኩም እነርሱም ተከታትለው ሞቱባቸው፡፡ ይኼኔ ነው በአንድሮፖቭ ዘመን ወደ ሥልጣን ከቀረቡት ወጣቶች መካከል በ50ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የነበሩት ሚካኤል ጎርባቾቭ ለሶቭየት ኅብረት ኮሙዩኒስት ፓርቲ መሪነት የታጩት፡፡

በውስጣቸው ሞቆ የገነፈለው የወጣት ባለሥልጣንነት ስሜት አርቀው ሳያስተውሉ ልዩ ልዩ ለውጦችን በየዋህነት እንዲተገብሩ አስገደዳቸው፡፡ ግላስኖስት  (ግልጽነት) ፔሬስትሮይካ (መልሶ ግንባታ ወይም ህዳሴ) የሚባሉ ሶቭየት ኅብረትን ያፈራረሱ ለውጦችን አካሄዱ፡፡

በወቅቱ የአሜሪካን ፕሬዚዳንት የነበሩት ሮናልድ ሬጋን የተቀጣጠለው ለውጥ እንዳይጠፋ ቤንዚን በማርከፍከፉ አልሰነፉም፡፡ ጎርባቾቭን አሜሪካ ድረስ እየጋበዙ የታላላቅ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ምርቃት ሸላሚ አደረጓቸው፡፡ ኒሻኖችንም በአንገታቸው ላይ አጠለቁላቸው፡፡

ጎርባቾቭም በደስታ እየፈነጠዙ በተሃድሶው ጉዞ ቀጠሉ፡፡ ታዲያ ምን ያደርጋል ለ15ቱ ሪፑብሊኮች በሰጡት የውስጥ ነፃነት በሩሲያ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ቦሪስ ዬልሲን ጀማሪነት በሌሎቹም ሪፑብሊኮች የፌዴራል መንግሥቱ አይመራንም ተብሎ ሶቭየት ኅብረት ፈራረሰች፡፡ ጎርባቾቭም የወሰዷቸው ዕርምጃዎች የእግር እሳት ሆነውባቸው በስደት ይኖራሉ፡፡

 

በየትም አገር ወጣቶች በወጣት ሊግ ማኅበራት ይደራጃሉ፣ ዴማጎጎች በሚያደራጁት የዕድሜ ዘረኝነት የፖለቲካ ፓርቲ አመሠራረት መሰባሰብ ግን አደገኛ ነው፡፡ በደም ሥራቸው ውስጥ የሚዘዋወረውን ሞቃት ደም ጡንቻ ለማድረግ ከሆነ በ21ኛው ክፍለ ዘመን አለመግባባቶች የሚፈቱት በሐሳብ መንሸራሸር በሰላምና በድርድር መሆኑን መዘንጋት ነው፡፡

ወጣት ሁሉ እንደ ጎርባቾቭ አገር እስከሚፈራርስ ያጠፋል የሚል እምነት የለኝም፡፡ በትልቁ ሥዕል ውስጥ ቦታ ያላገኙ ሰዎች ትናንሽ ሥዕሎች እየሳሉ በሥዕሎቹ ኮርማዎችና በሰላ ምላስ ታዋቂ ዴማጎግ ለመሆን እየጣሩ ነው፡፡ የእኔ ሐሳብ ካላሸነፈ እንቢ የሚሉ ዴማጎጎች የዕድሜ ፌዴራሊዝም ፓርቲ አቋቁመው፣ ከጎሳ ፌዴራሊዝም ጋር ተዳምሮ ኢትዮጵያን እንደ ሶቭየት ኅብረት እንዳይበታትናት እንጠንቀቅ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡