Skip to main content
x

እውነትም ያሳፍራል!

ጉዟችን ሊጀመር ነው። እነሆ ጉዞ ከፒያሳ ጳውሎስ መድኃኔዓለም። ሾፌራችን የታክሲዋን ሞተር እያስጓራ ልባችንን አንጠልጥሎታል። ‹‹እንዴት ነው ነገሩ? ‘ሔሊኮፕተር’ ላይ ነው እንዴ የተሳፈርነው? ወደፊት ለመሄድ ይኼ ሁሉ ነዳጅ ማባከን ከሙስና ይተናነሳል?›› ሦስተኛ ወንበር ከአጠገቤ የተቀመጠ ‘ጆከኛ’ ይለፈልፋል። ‹‹ምን ይታወቃል ዘንድሮ የሚወስድህንም ሆነ የምትሄድበትን እኮ መለየት ይከብዳል፤›› ስትል መጨረሻ ወንበር የተቀመጠች በስላቅ ታብራራለች። ‘ቀ… ቀ… ቀ… ቀ…’ ይላል ማርሹ አልገባ ብሎ። ‹‹ወይኔ! ‘ፈርስት ክላስ’ በተሳፈርኩ ኖሮ›› ማኅበራዊ ድረ ገጽ ውስጥ ገሀድ ማኅበራዊ ትዕይንቱን ሰልችቶ ከተመሰጠው ወጣት አጠገብ የተሰየመች ወጣት ትቆጫለች። ‹‹እዚህ ሕዝባዊ ‘ክላስ’ የጎደለ ነገር አለ?›› ፌዘኛው ጎረቤቴ ይጠይቃታል። ‹‹አትሰማም እንዴ ሸንኮራ ሲቆረጥ? እዚህ አገር ከፊት ካልተቀመጥ ወይም ካልተወለድክ መረቁ የተመጠጠለት ደረቁ ነው የሚታደልህ እኮ። እሱንም ቅን ሾፌር ካጋጠመህ፤›› ትለዋለች።

‹‹ኧረ ሰላማዊ ሠልፍ ጠርተው ያዋከቡን ይበቃል። ደግሞ በተቀመጥንበት ልታሳፍሱን ነው?›› ሻሽ ካሰረች ቀዘባ አጠገብ፣ መጨረሻ ወንበር ላይ የተሰየመች ወይዘሮ ትናገራለች። ይኼን ጊዜ ሾፌሩ በሩን ከፍቶ ይወርዳል። ወይዘሮዋ፣ ‹‹የፈራሁት ሊደርስ ነው መሰል፤›› ስትል በራሷ የፈጠረችውን አጉል ፍርኃት አንዳንድ ተሳፋሪዎች ላይ ታጋባለች። የሾፌሩን መውረድ ተከትሎ ወያላውም ወርዶ ወደ ሾፌሩ አመራ። ‹‹ምን ይማከሩብናል አይዘውሩትም? ሃሎ አትሄዱም?›› ከወያላው ጋር የተናቆረችው ደርባባ ትጮሃለች። ‹‹እስኪ ቢያልፍብንም ጊዜ እንስጣቸው የመኪናውን ችግር እያጣሩ ይሆናል?›› ሲል ከአጠገቤ ሊያረጋጋት ይጥራል። ‹‹አደራ ሰው መሆናችንም አብሮ ይጣራ?›› ብሎ ደግሞ ‘የመኪናው ችግር ይጣራ’ የተባለውን የብሶት ማስተንፈሻ የሚያደርገው ጎልማሳው ነው። ‘ሆድ የባሰው ብቻ ነው የሚሳፈረው?’ እስክንል ድረስ የማንሰማው የለም!

‹‹1—2—3›› ሾፌሩና ወያላው ተጋግዘው አንደኛ ማርሽ ያስገባሉ። ለካ ወያላው የወረደው አንደኛ ማርሽ በጉልበት ስለሚገባ ኖሯል። አንዳንዱ ከት ብሎ ይስቃል። ሳቅ እንዲህ በቀላሉ ድርሽ የማይለው ደግሞ ያላየውን፣ ‹‹ኧረ ባቡር ይግደለኝ፤›› ሲል ሌላ ነገር ይመስልበታል። ደርባባዋ፣ ‹‹አይዞህ አይገልህም። አንዱ ፌርማታ ላይ አስመድበንህ ወፍ ታባርራለህ፤›› ትለዋለች እየሳቀች። ‹‹አግኝቼ ነው? ሰው በአገሩ ተምሮ ዲግሪ ይዞ ሥራ መቀጠርን ተይውና ወፍ የማባረር ዕድል እየራቀው መስሎን የሚሰደደው፤›› ይላታል ተለሳልሶ። ‹‹መጀመሪያ ነዋ ዲግሪ እይዛለሁ ሲል ወፎች ስጡን የሚጨርሱት፤›› አጠገቤ የተቀመጠው ነገረኛ ጣልቃ ይገባል። ‹‹ኧረ ኤዲያ!›› ነገሩ ያላማራት ወይዘሮ ትርበተበታለች።

ይኼን ጊዜ ወያላው እየተንደረደረ ገብቶ በሩን ይዘጋል። ሾፌሩ አስጓርቶ እንደ መንኮራኩር ታክሲዋን ማንደርደር ጀምሯል። ‹‹ጥድፊያው የተቃጠለብን ጊዜ ለመካስ ነው? ወይስ ከአንደኛ ማርሽ ለመሸሽ?›› ሲል ገጹ ላይ ሊለጥፈው ያሰበውን በቃል ይለዋል ‘ፌስቡከሩ።’ ጋቢና የተቀመጡት ወጣቶች ደግሞ፣ ‹‹እኛን አግዙኝ ብትል እኮ እናግዝህ ነበር፤›› ሲሉ አጠገቡ  ተቀምጠው ወያላው ዞሮ መምጣቱ ቅር እንዳሰኛቸው ያስረዳሉ። ከመጨረሻ ወንበር ደግሞ፣ ‹‹ጋይስ’ ሰው መንጃ ፈቃድ ለማውጣት ኪሱ አልችል ሲለው ታክሲ በመግፋት ለማካካስ ሙከራ ጀመረ እንዴ? የሙከራ ሥርጭቱን ከዋናው መለየት አስቸገረን እኮ?›› ብላ አንዲት ቆንጆ ብቻዋን በሳቅ ትፈርሳለች። ‹‹እንዲህ ስቀሽ ስቀሽ ትን ያለሽ እንደሆን፣ ደቂሽ እኔ ነኝ አትራፊሽ ማን ይሆን?›› ሲል ጎልማሳው ያሽሟጥጣታል። ጉድ እኮ ነው!

‹‹ይታይሃል? ይታይሃል ይኼኛው? እርግጠኛ ነኝ የእዚህ ሕንፃ ካርታ በደንብ ተነቦ አይደለም የተሠራው። ተመልከት የፍሳሽ መስመሩ በውጭ በኩል አድርገው እንዴት እንደሠሩት?›› ትለዋለች ቦርሳ አንጋቿ ታዳጊ ለጓደኛዋ። እርሱም ሐሳቡንና ግምቱን መልሶ ይነግራታል። ‹‹እኛ እኮ እንዲያው ነው ተማርን የሚባለው፡፡ ዘመኑ ከተራቀቀበት የግንባታ ንድፍ አንፃር ስንተያይ አለን ይባላል?›› ቢላት፣ ‹‹ትቀልዳለህ? እዚህ አገር ምንም ነገር ብትችል እንድታስብ የምትገደደው ሌላው ማሰብ እስከቻለበት ደረጃ ብቻ ነው። አለቀ ደቀቀ፤›› አለችው። በአነጋገራቸው እየተገረምን ጨዋታቸውን ስናዳምጥ ብዙ ቆየን። ድንገት፣ ‹‹ተመልከት እንግዲህ፣ ገና በዚህ ደረጃ አቃቂር ማውጣቱን እንዴት እንደሚችሉበት፤›› ይላሉ ወይዘሮዋ በታዳጊዎቹ ላይ ንዴታቸው አልበርድ ብሎ።

‹‹የሕንፃ ግንባታ የዕድገት ጫፍ ይመስል ታዳጊው ሁሉ የሚመለመለው ለዚሁ ሆነ በቃ?›› ብሎ ከሾፌሩ ኋላ የተቀመጠ ወጣት አጠገቡ የተቀመጠችውን ቀዘባ ሲጠይቃት ሰማን። ‹‹እሱስ ድልድዩንና የባቡር መስመሩን ጭምር የሚዘረጉ ለማግኘት ታስቦ ነበር። ለእንጀራ እንጂ ለሙያ ፍቅር የሚማር እየጠፋ መንግሥትም የጥራቱ ነገር ችላ ብሎት ቻይና ተንሰራፋችብን እንጂ፤›› ብላ መለሰችለት። አንዱ እውነት ሌላውን እየመዘዘና እያወያየን ታክሲያችን እየገሰገሰች መንገዳችን እያጠረ እንጓዛለን። ሒደት ነውና ካለፈው መማር ለሚመጣው መዘጋጀት ግድ እየሆነብን!

ታክሲያችን አሁንም ትንሽ ከመንደርደሯ መልሳ ቀዝቀዝ አለች። ይኼኔ ወራጅ ልታወርድ ወይም ተሳፋሪ ልትጭን አልነበረም። ከፊታችን ያሉ የሠርግ ሥነ ሥርዓት አድማቂ ‘መርሰዲሶች’ መንገዱን ስለዘጉት እንጂ። ‹‹ተመልከት  የሰውን  ልጅ መጨረሻ፤›› አለ ወያላው ለመጀመሪያ ጊዜ ሳቅ እያለ። ‹‹መጀመሪያ ማለትህ ነው?›› አለው ሾፌሩ ዞር እንደ ማለት ብሎ። ‹‹የለም መጨረሻ ነው ያልኩህ። በቃ እኮ ከዚህ በኋላ ስለሕይወት የምታስበው ነገር አከተመ። ለምን? ተከርቸም ነዋ ትዳር። ሰው ይወለዳል፣ ያድጋል፣ ይጋባል፣ ይወልዳል፣ ይሞታል ሲባል አልሰማህም?›› እያለ ይቀልዳል። ‹‹ኧረ እይልኝ ሙሽሮቹን፤›› ከሾፌሩ ኋላ ያለው ወጣት። ሙሽሮቹ ከመኪናቸው ወርደው መኪና ሲገፉ በካሜራ እየተቀረፁ ነው። ‹‹እርፍ! ደግሞ ከየት የታየ ‘ስታይል’ ይሆን ይኼ?›› ይላል ወያላው።

ከወይዘሮዋ አጠገብ የተቀመጠው ጎልማሳ በበኩሉ ‹‹ተዋቸው ይለማመዱት። ጉድና ጅራት ከበስተኋላ አይደል? ዛሬ እየሳቁ ነገ ደግሞ እያለቀሱ የኑሮን መከራ መግፋታቸው የት ይቀራል?›› ብሎ ከማለቱ አጠገቤ የተቀመጠች ረዘም የምትል ሴት፣ ‹‹ሟርተኛ ሁሉ!›› ስትል ሰማኋት። እንደሰማኋት አውቃለች መሰል ፊቷን ወደ እኔ አዙራ፣ ‹‹አይገርምህም? ምናለበት ደህና ነገር ማሰብ ብንወድ? በቃ እዚህ አገር ቀና አስተሳሰብ ህልም ሆኖ ሊቀር ነው? ዛሬ ተደራጁ ሲባል ነገ ይፈርሳሉ፣ ዛሬ ተፋቀሩ ሲባል ነገ ይጣላሉ፣ ዛሬ ወጠኑ ሲባል ነገ ይከሽፋሉ የማይልህ ሰው ጠፋ እኮ!›› ስትለኝ ትከሻዬን ሰብቄ ‘ምን ይደረግ?’ አልኳት። ሁሉን አጣመን እያሰብን ሁሉ ሲጣመምብን ለምን እንደማንነቃ እነጃ!   

  ‹‹‘ፌስቡክ’ ላይ ‘ቫት’ ሊጀመር ነው አሉ፤” ብሎ አንዱ ቀልድ መሳይ ጨዋታ ጀምሯል። ታክሲዋ በድንጋጤ ጎርፍ ተጥለቅልቃለች። ‹‹አይደረግም ይህ የሙሰኞች ወሬ ነው፤›› ትላለች የቀይ ዳማ ወጣት ከወደ ፊት መስመር ጆሮዋን ደፍናበት የነበረውን ‘ኢር ፎን’ እየነቀለች። ተሳፋሪው ታዝቧት ‘እንዴ ‘ኢር ፎኑ ማስክ’ ነበር እንዴ?’ እየተባባለ ያማታል። የዛሬ ሰው እንደው ‘ማስከኛ’ ነው ዓይነት ወሬ ደርቶባታል። ‹‹እውነትህን ነው? እንዴት ሆኖ?›› አብዛኛው ተሳሪፋሪ የሚጠይቀው በጭንቀት ነበር። ልጁ ‘ፌስቡክ’ ማለት ከሦስቱ መሠረታዊ ፍላጎቶች መካከል ሊመደብ ምንም እንዳልቀረው ታዝቦ ሲያበቃ፣ ‹‹ኧረ እኔስ ለጨዋታ ነው፤›› ብሎ ተሳፋሪውን አረጋጋው። የእፎይታው ንፋስ ብርድ እንዳያሳምመን እስክንሠጋ ድረስ።

‹‹እኔ ደግሞ ሰሞኑን ለግድቡ የተዋጣው መዋጮ ከታሰበው በታች መሆኑ ስለተገለጸ በዚህ በዛም ብለው ‘ሊፈልጡን’ ነው ብዬ አስቤ ክው አልኩ፤›› ብሎ አጠገቤ የተቀመጠው ወጣት ሥጋቱ ከምን መንጭቶ እንደደነገጠ ሲያብራራ፣ ‹‹ለግድቡ የተዋጣው መዋጮ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም ተባለ ነው ያልከው? ያዋጣነው እኮ በስንት ፀሎት ወር ሲመጣ ከምናገኛት መናኛ ደመወዝ ነው እንጂ እንደ ደላቸው ሙሰኞች በልጃችን ስም ባንክ ካስገባነው የሕዝብ ገንዘብ አልነበረም። እንዴት ነው ግን የዚህ አገር ነገር ትንሽ አልበዛም?›› እያለች መነጫነጭ የጀመረችው ከሾፌሩ ትይዩ የተቀመጠች ወይዘሮ ናት። ‹‹እኔስ የምፈራው ኑሯችን በመዋጮ እንዳይሆን ነው፤›› የሚለው ከኋላዬ የተቀመጠ ጎልማሳ ነው። እንዲህ ነገር በፖለቲካ አዋዜ እየተጠቀሰ ይሰለቅ ጀመር። ‹‹ጀምሮ ማፈግፈግማ አይታሰብም ጎበዝ! ባይሆን የነጣቂና የቀማኛው ነገር አንድ እየተባለልን ከሄደ ሌላው ቀላል ይሆናል፤›› ሲሉ አንድ አዛውንት ነገሩን አለዘቡት። ወያላው ሒሳቡን ሰብስቦ ጨርሷል። የእኛ ነገር ‘የነብር ጭራ አይዙ ከያዙም አይለቁ’ ከሆነ ቆያይቷል!

 ወደ መውረጃችን ለመድረስ የቀሩን ጥቂት ደቂቃዎች ናቸው። ከልክ በላይ ታክሲዋን የሚያስጋልባት ሾፌራችን ከምድር ለመጥፋት የወሰነ ይመስላል። ‹‹ቀስ በል እንዳንል እንደ ዘንድሮ ሰው አስተያየት፣ ምክር፣ ተግሳፅ የጠላ የለም፤›› ይለኛል አጠገቤ ያለው ወጣት። ከኋላችን የተቀመጡት ጎልማሳና ቆንጅዬዋ ወጣት እንዲህ ይጫወታሉ። ‹‹እኔ ምለው መንግሥት ለትላልቅ ፕሮጀክቶቹ ሥራ ማስኬጃ ኪስ ሳያጥረው አልቀረም የሚባለው እውነት ነው?›› ብላ ጎልማሳውን ስትጠይቀው፣ ‹‹ምን አውቃለሁ ብለሽ ነው? ግን እንዲያ ሲባል መቼም እዚህ አገር የማይባል ነገር የለም እያልኩ ነው እንጂ መስማቱን ሰምቻለሁ። ምናልባት ያለ ልማዱ ትልልቅ ሙሰኞችን የሚያድን ነው የሚመስለው፡፡ እንዳልሽውም ሆኖ ሊሆን ይችላል፤›› ይላታል።

ትንሽ እንደሄድን ‘ኢር ፎን’ ሰክታ አልሰማም አላይም ብላ ከተቀመጠችው ወጣት ሦስተኛ ተደርበው የሚጓዙ አዛውንት፣ ‹‹እውነት ሙስና ላይ እንዲህ ከበድ ያለ ዘመቻ ከተጀመረ እውነት ይቺ አገር ማን ሊቀራት ነው?›› ብላው ሳያስቡት ድምፃቸውን አጉልተው ጠየቁ። ‹‹እንዴት?›› ስትላቸው ወይዘሮዋ፣ ‹‹ከጥበቃ እስከ  ዋና ሥራ አስኪያጅ ያለምንም እጅ መንሻ መግባት፣ መውጣት፣ ጉዳይ ማስጨረስ፣ መከታተል የማይታሰብባት በሆነችው አገር ማን ሊማር? ሙስና ሥር ሰዷል ያልተዘፈቀበት የለም። በአጠቃላይ አገሪቷ ራሷ ተዘፍቃለች ማለት ይቀላል እኮ። ታዲያ አሁን እኔ እያልኩ ያለሁት ‘የቱ ተወዶ የቱ ሊጠላ?’ ነው?›› ሲሉን ‘ህም’ ብለን ‘ዝም’። በዚህ መሀል አንዱ፣ ‹‹ለመሆኑ ሰማችሁ?›› አለን፡፡ ሁላችንም ለወሬ አሰፍስፈን፣ ‹‹ምኑ?›› ስንለው፣ ‹‹የስቴዲየሙ ፓውዛ ለሃያ ምናምን ደቂቃ ጠፍቶ ኳስ ጨዋታ ተቋርጦ እንደነበረ ነዋ?›› አለን፡፡ ይኼኔ አዛውንቱ ተከዝ ብለው፣ ‹‹ለመሆኑ ተመልካቾች ምን አሉ?›› ሲሉት፣ ‹‹ተመልካቾችማ ‘ያሳፍራል፣ በጣም ያሳፍራል’ እያሉ ሲጮሁ እውነትም ያሳፍር ነበር…›› ሲል ወያላው በሩን ከፍቶ ‘መጨረሻ’ ብሎ ውረዱልኝ እያለ ነበር። መልካም ጉዞ!