Skip to main content
x

ከሕገ መንግሥት የራቁ ፖሊሲ፣ ሕግና ተግባር የነገሡበት ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት

በአውሮፓውያን አቆጣጠር በየዓመቱ ግንቦት ሦስት ዓለም አቀፍ የፕሬስ ቀን ነው፡፡ በኢትዮጵያ ደግሞ ብዙ ጊዜ ሚያዝያ ሃያ አምስት ቀን ላይ ይውላል፡፡ በዚህ ዕለት፣ ከፕሬስ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች አርዕስት ይሆኑና ውይይት ይደረጋል፡፡ ፕሬስ በየአገሮቹ ስላለበት ሁኔታም ደረጃ ይወጣል፡፡ የየአገሮቹ መንግሥታትም ያጣበቧቸው፣ የገደቧቸውና የጣሷቸው መብቶች ይፋ ይደረጋሉ፡፡ ምናልባት ገበናቸውን ሌሎች ሲያውቁባቸው ኃፍረት ተሰምቷቸው እንዲያሻሽሉ የተሻሉ አገሮችና አካላትም ጫና እንዲያደርጉባቸው ይረዳል፡፡ ዕለቱን በማሰብ ሌሎችም በርካታ ነገሮችም ይደረጋሉ፡፡

በዚሁ ዓመትም በኢትዮጵያም ይህንኑ ዕለት በማሰብ ጥናቶች ቀርበዋል፡፡ ውይይትና ምክክርም ተደርጓል፡፡ መነሻው የመገናኛ ብዙኃን ለዴሞክራሲ እያደረጉት ያለው አስተዋጽኦ ዝቅተኛ ነው ከሚል ነው፡፡ በእርግጥ ስለዚህ ጉዳይ የኢፌዴሪ የፖሊሲ ጥናት ተቋምም ተመሳሳይ መደምደሚያ ያለው የጥናት ሪፖርት ይፋ ማድረጉን ልብ ይሏል፡፡

ዓለም አቀፍ ተቋማትም የፕሬስ ነጻነት ባለፈው ዓመት ስለነበረው ሁኔታ ደረጃ ካወጡላቸው ከ180 አገሮች ውስጥ ኢትዮጵያ 150ኛ ደረጃ ላይ አስቀምጠዋታል፡፡ ፕሬሱ ለዴሞክራሲ ካለው አስተዋጽኦም ይሁን ከሌሎች ግቦችና አድራጎት አንጻር፣ በዓለም አቀፍ ተቋማትም ይሁን በአገሮች ሪፖርት ዞሮ ዞሮ የኢትዮጵያ መንግሥት ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን ከማክበር፣ ከማስከበርና መሟላት ያለባቸውን ሁኔታዎች ከማሟላት አንጻር በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ስለመገኘቱ አከራካሪ አይደለም፡፡

መረጃ ማግኘትን ሳይሆን፣ ሐሳብን በነጻነት መግለጽን በሚመለከት በሕገ መንግሥት ላይ በመጻፍ ጥበቃ ከማድረግ አኳያ በጣት ከሚቆጠሩ ገደቦች በስተቀር እጅግ በጣም ሰፊ ነጻነትን ለማስፈን በሚመች መልኩ ተቀምጧል፡፡ ይሁን እንጂ ከሕገ መንግሥታዊው እጅግ ሰፊ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ጥበቃ በተጻራሪው በተግባር በዝቅተኛ ሁኔታ ላይ ይገኛል፡፡

ቁምነገሩ ያለው ሕገ መንግሥቱ የሰጠው ጥበቃ ሰፊ ከሆነ በተግባር እንዲህ እንዲጠብ ያደረጉት ምክንያቶች ምንድን ናቸው? የሚለው ነው፡፡ እነዚህን እንከኖች ነቅሶ ማውጣቱ ደግሞ ለማስተካከልም አንድ ዕርምጃ ይሆናል፡፡ ይህ ጽሑፍ የሐሳብ ነጻነትንም ሆነ ፕሬስና ሌሎች መገናኛ ብዙኃንን የሚመለከቱና እንቅፋት የሆኑ ፖሊሲና ሕግጋትን በመጠቆም ይህንን መብት ለማስጠበቅና ለመተግበር ይረዳሉ የሚባሉትን ተቋማት ያለባቸውን የመዋቅር ችግር በመጠቆም ሕገ መንግሥቱን የሚቃረኑ መሆናቸውን ማሳየት ነው፡፡ በመሆኑ በቅድሚያ በሕገ መንግሥቱ ላይ የተቀመጠውን የዚህን መብት ይዘት ላይ መጠነኛ ማብራሪያ ይቀርባል፡፡

የመሰለውን ሐሳብና አመለካከት የመያዝ መብት

የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29 ሙሉ በሙሉ ሐሳብን በነጻነት ከመግለጽ ጋር የሚያያዙ መብቶችንና ግዴታዎችን የሚገልጽ ነው፡፡ በመጀመሪያው ንዑስ አንቀጹ ላይም ማንም ሰው የመሠለውን አመለካከት የመያዝ መብት ያለው መሆኑን አረጋግጧል፡፡ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን ለማስጠበቅ በመንደርደሪያነት የሚያገለግል ነው፡፡ ከዚያ ውጭ ማንም ሰው የመሰለውን ሐሳብና አመለካከት የመያዝ ወይም የመጣል መብትን በተመለከተ ጥበቃ ቢደረግለትም ባይደረግለትም ብዙም ለውጥ አያመጣም፡፡ ምክንያቱም አንድ ሰው የመሰለውን፣ ያመነበትን፣ የፈለገውን ወዘተ አመለካከት ቢይዝና ሌላውን ቢተው ሌላ አካል በግዳጅ በተቃራኒው የሆነን ሐሳብና አመለካከት እንዲይዝ ወይም እንዲጥል ማድረግ የሚቻል ባለመሆኑ ነው፡፡ በዋናነትም ውስጣዊ ነው፡፡ መቼም ቢሆን መገደብ የሌለበት መብት ነው፡፡

በዓለም አቀፍና አኅጉራዊ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶችም በአስቸኳይ ጊዜም ቢሆን እንኳን ዕገዳ የለበትም፡፡ ከገደብም ከዕገዳም ነጻ የሆነ ነው ማለት ነው፡፡ በእርግጥ በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከሚታገዱት ውጭ አልሆነም፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ መንግሥታት የሚፈለጉትን ያለዜጎች ፍላጎት አንድን ሐሳብ  የማስረጽ ተግባር ውስጥ እንዳይሰማሩ መከላከያም በመሆን ያገለግላል፡፡ ማስረጽ ከፈለጉት ሐሳብ ውጭ የተለየ ሐሳብ የሚይዙ ሰዎችን በመለየት ምንም ዕርምጃ እንዳይወስዱ ወይም አግላይ የሆነ ድርጊት እንዳይፈጽሙ ለመቀየድ የሚያስችሉ ሕግጋትን ለማውጣትም ይረዳል፡፡

መንግሥታዊ ሐሳብን ብቻ እንዲከተሉ ወይም እንዲይዙ ማስገደድ ለሐሳብ ብዙኃነት ተቃራኒ በመሆኑ ለዴሞክራሲያዊ ኅብረተሰብም ግንባታም ፀር ነው፡፡ ራሳቸው ባያደርጉ እንኳን ሌላ ሐሳብ እንዳይንሸራሸር የሚያግድም አሠራር ማስፈን ለዚህ መብት ተቃራኒ ነው፡፡ በደርግ ዘመን ይደረግ እንደነበረው የካፒታሊዝምና የሊበራሊዝም ይዘት የነበራቸውን መጻሕፍት ወደ አገር እንዳይገቡ የማገድ አድራጎት ማለት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ማንም ሰው ምን እንደሚያስብ ወይም አቋም እንዳለው እንዲገልጽ ከመገደድም የመጠበቅ መብትንም ያካትታል፡፡

ሐሳብን የመግለጽ መብት ሦስት ፈርጆች

ማንም ሰው የመሰለውን አመለካከት ከመያዝ ቀጥሎ የሚመጣው የማካፈሉ፣ የመቀበሉና የመግለጹ ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም ተጨባጭ ዋስትና መስጠት የሚቻለውና ጥበቃ የሚያስፈልገውም ይኸው መብት ነው፡፡ ይህ መብት ለዴሞክራሲ እምብርት ነው፡፡ ሕዝብ ራሱን በራሱ ለማስተዳደርና አማናዊ የምርጫ ሥርዓት ይተገበር ዘንድ፤ መራጩ ስለሚመርጠው ሐሳብም ወኪልም መረጃ ያስፈልገዋል፡፡ የፈለገውንና የሚበቃውን ዕውቀት ለማግኘት ደግሞ የትኛውም ዓይነት ሐሳብ ያለገደብ የሚሠራጭበት ሥርዓትን ይጠይቃል፡፡

በሥልጣን ላይ ያሉ ወይም የማድረግ አቅም ያላቸው የማይፈልጉትን ሐሳብ እየነጠሉ የሚያስቀሩ መሆን የለባቸውም፡፡ እንዲህ ከሆነ የሐሳብ ፍሰት ይገደባል፡፡ በበቂ ሁኔታ የማይታወቅን ለመምረጥም ሆነ ሳያውቁ ለመጥላትና ላለመምረጥም ያጋልጣል፡፡ ዴሞክራሲም ይጫጫል ወይም ጭራሹኑ አይኖርም ማለት ነው፡፡ የሚመረጥ ከሌለ ደግሞ ዴሞክራሲ የለም፡፡

የሐሳብ ፍሰትንና ሥርጭትን መጠምዘዝ የዴሞክራሲ ተቃራኒ ነው፡፡ እየፋፋ ሲሔድም የተረጋጋ ነገር ግን ቀጣይነትና ተያያዥነት ያለው ለውጥንም ያመጣል፡፡ ማኅበራዊ ግንኙነትና መግባባትንም ይፈጥራል፡፡ ካልሆነ አለመረጋጋት ይከሰታል፡፡ በአንድነት ሊኖሩ የሚችሉ፣ ጤናማ የሆኑ ልዩነቶች አይኖሩም፡፡ አገራዊ መግባባትም ይነጥፋል፡፡ የዚህ ውጤቱም ከለውጥ ይልቅ አብዮት ይሆናል፡፡

የንግግር ነጻነት ወይም ሐሳብን የመግለጽ መብት ሲባል የራስን አመለካከትንና ሐሳብን፣ ያለመንግሥታዊ ብቀላና ዕቀባ (ሳንሱር) እንዲሁም ያለማኅበረሰባዊ ክልከላ፣ የማንጠርና የማስተላለፍን መብትን ይመለከታል፡፡ ይህንን ለማከናወን ደግሞ ሐሳብን በነጻነት የመሰብሰብ፣ የመቀበልና የማሠራጨት ድርጊቶችን ማስጠበቅ ይገባል፡፡ በመሆኑም ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ሲባል እነዚህ ሦስት ፈርጆችን ይይዛል ማለት ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 29(2) ላይ የተገለጹ ናቸው፡፡

ሐሳብን የመሰብሰብ ወይም የመሻት ነጻነት የሚመለከተው መረጃ መሰብሰብን፣ መፈልግን፣ ማግኘትን ነው፡፡ ከየትም ቦታ የሚተላለፍን የሚዲያ ስርጭቶችን መከታተልንና መረጃ ማግኘትንም ማረጋገጫና ዋስትና ነው፡፡

ሐሳብን መቀበል ደግሞ በዋናነት ሚዲያ ከመከታተል ጋር ይያያዛል፡፡ የመረጃ ምንጭ ላይ ገደብ መጣል ወይም እንዳይደርስ ማድረግን ይከለክላል፡፡ እንዲሁም ዜጎችን ከሆነ የመረጃ ምንጭ ሐሳብ እንዳያገኙ አለማስፈራራትን (ከፍርሃት ነጻ) መሆንን ይመለከታል፡፡

በሌላ በኩል ሐሳብን ማሰራጨት ለፖለቲካዊ መብቶች መከበርና በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ዋና መሠረት ነው፡፡ ትርጉም ያለው ምርጫ ከዚህ የሚቀዳ ነው፡፡ መንግሥት ላይ የሚኖር ቅሬታና ትችት ለመግለጽና ለሕዝቡ በማሳወቅ ደጋፊዎችን ማፍራት የሚቻለው ሐሳብን በማጋራት ነው፡፡ ሐሳብን ማሰራጨትና መቀበል የሚነጣጠሉ ነገሮች አይደሉም ማለት ነው፡፡ የሚያሰራጭ ነገር ካለ የሚቀበል አለ ማለት ነው፡፡

ሐሳብን የመግለጽ መብትና የሚዲያ ዓይነት

ሐሳብ ወይም አመለካከት ደግሞ በተለያዩ ዘዴዎችና ምንጮች ሊገኝ ይችላል፡፡ ከኅትመት ውጤቶች፣ ከሰዎች፣ ከሬዲዮና ቴሌቪዥን፣ ከማኅበራዊ ሚዲያዎች ወዘተ ሊሆን ይችላል፡፡ ምንጫቸውም ከአገር ውስጥ ወይም ውጭም መሆኑ ለውጥ የለውም፡፡ የሚተላለፍበት ዘዴ ምንም ይሁን ምን፣ ከየትም አገር ይሰራጭ ጥበቃው ተመሳሳይ ነው፡፡ በየትኛውም ዘዴና ከየትም አገር ከሚሠራቸው ሚዲያ ማንም ሰው ሐሳብ የመሰብሰብ፣ የመቀበልና የማሰራጭት መብቱ ሕገ መንግሥታዊ ዋስትና ተሰጥቶታል፡፡

ሕገ መንግሥቱ ለግለሰቦች ሐሳብን የመሰብሰብ፣ የመቀበልና የማሰራጨትን መብትን በንዑስ ቁጥር 2 ላይ ጥበቃ ካደረገ በኋላ እነዚህን መብቶች ተግባራዊ ለማድረግ ወይም ለማንሸራሸሪያነት ወሳኝ የሆኑትን የፕሬስና የመገናኛ ብዙኃንንና የሥነ ጥበብ የፈጠራ ነጻነት እንደ ተቋም በንዑስ ቁጥር 3 ላይ ጥበቃ ሰጥቷል፡፡ ስለሆነም ማንም ሰው በእነዚህ ተቋማት በመረጠውና በመሰለው ዘርፍ ውስጥ በመሠማራት ሐሳቡንና አመለካከቱን በነጻነት መግለጽ ወይም ማንሸራሸር ይችላል ማለት ነው፡፡

በፕሬስ አማካይነት ሰው ሐሳቡን መግለጽ ሲፈልግ በማናቸውም መልኩ ከራሱ ከሐሳቡ ባለቤት ፈቃድ ውጭ አስቀድሞ ሳንሱር አይደረግበትም፤ የአርትኦትም ሥራ አይደረግበትም፡፡ በወንጀል የሚያስጠይቅ ቢሆን እንኳን ከኅትመት በኋላ የሚመጣ ጉዳይ ነው፡፡ ከመሰራጨቱ በፊት የሚታገድ ወይም የሚያዝም ከሆነ ዞሮ ዞሮ ያው ክልከላ ነው፡፡ ስለሆነም፣ሕገ መንግሥቱ ይህንን ሲያጸናና ሲያስረግጥ፣ ሊያስከትል የሚችለውን ውጤት መሠረት በማድረግ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት በሕግ ገደብ እንዳይጣል ጥበቃ ተደርጎለታል፡፡  

ሚዲያ በዋናነት የሐሳብን ነጻነትን ለማስከበር የሚያገለግል ቢሆንም ከዚህ በተቃራኒው ለመገደብም ሊውል ይችላል፡፡ የተወሰኑ ሰዎች ወይንም ቡድኖች ብቻ የሚጠቀሙበት  ከሆነም ለአፈናም ሊውል ይችላል፡፡ ጥበቃ የሚፈለገው ከመንግሥት ብቻ ሳይሆን ከሌሎችም ጭምር ነው፡፡

ለፕሬስም ይሁን ለማንኛውም ዓይነት መገናኛ ብዙኃን የመረጃ ነጻነት መኖር እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 29(3) ሥር ዋስትና የሠጠው ‹‹የሕዝብን ጥቅም›› የሚመለከት መረጃን ብቻ ነው፡፡ ለዚሁም ቢሆን መረጃ የማግኘት ዕድል እንዲኖር እንጂ በመብትነት የተቀመጠ አይደለም፡፡ የሕዝብ ጥቅምን የሚመለከት ካልሆነ መረጃን መንፈግ ይቻላል ማለት ነው፡፡ የሕዝብ ጥቅምን የሚመለከትና የማይመለከት የሚለውን መለየት አስቸጋሪና ለባለሥልጣናትና መረጃውን ለያዘው ሠራተኛ መልካም ፈቃድ ላይ እንዲንጠለጠል ሊደርግ ይችላል፡፡ ካልሆነም የሕዝብን ጥቅም የሚመለከቱና የማይመለከቱ ብሎ በሕግ ለመዘርዘር ሰፊ ሥልጣን ይሰጣል፡፡

የሕዝብ ጥቅምን የሚመለከት ካልሆነ ፕሬሱ ከመብት አንጻር ሊጠይቅ የሚችልበት መነሻም የለውም ማለት ነው፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ‹‹የማግኘት ዕድል›› የሚለው መረጃውን ለሚፈልጉት በመብትነት ባለመቀመጡ መረጃውን የያዘውን የመንግሥት ባለሥልጣን በፍርድ ቤት ማስገደድም የሚቻል አይሆንም፡፡ ምክንያቱም መብት ስላልሆነ፡፡

መንግሥት የሚተዳደር መገናኛ ብዙኃን ሲሆን

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29(4) ላይ ፕሬስ በተቋምነቱ ጥበቃ እንደተደረገለት ይገልጻል፡፡ ለጥበቃው ምክንያቱ ደግሞ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ማስፈን አስፈላጊ በመሆኑ እንደሆነ እዚሁ ንዑስ አንቀጽ ላይ ተገልጿል፡፡ ፕሬስ በተቋምነቱ አሠራሩ ነጻነት እንዲኖረው በሕግ ጥበቃ ይደረግለታል፡፡ ይህ የግልም ይሁን የመንግሥት ወይም መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም ቢሆኑ ልዩነት የለውም፡፡ ሁሉም ላይ ተፈጻሚ ነው፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በመንግሥት የሚተዳደረው ላይ ተጨማሪ ግዴታ እንዲኖር ንዑስ አንቀጽ አምስት ይደነግጋል፡፡ በመንግሥት ሐብት የሚተዳደር መገናኛ ብዙኃን ሲሆን የሐሳብ ብዝኃነትን ለማስተናገድ በሚያስችል መንገድ መተዳደር እንዳበት ሕገ መንግሥቱ በግልጽ አስቀምጧል፡፡ መንግሥት ከመገደብ ወደኋላ ሊል እንደማይችል ቀድሞ በማሰብ የተቀመጠ መከላከያ ነው፡፡ ምንም እንኳን ተግባሩ የተገላቢጦሽ ቢሆንም፡፡

ስለተገላቢጦሽነቱ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽንን (ኢቢሲ) በምሳሌነት በመውሰድ እንዴት እንደሚተዳደር እንመልከት፡፡ ይህ ተቋም በቦርድ የሚመራ ነው፡፡ ከዚያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አለው፡፡ እስካሁን የነበሩትን የቦርድ አባላት ስንመለከት የቦርዱ ሰብሳቢ የሚሆነው የማስታወቂያ ወይም የመንግሥት የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ነው፡፡ ሌሎቹ፣ በዋናነት የመንግሥት ሹመኞችና የፓርላማ አባላት ናቸው፡፡ ከሃይማኖት ተቋማትም አንዳንዴ ይጨመራል፡፡ እንደቀድሞው ሁሉ አሁንም በሥራ ላይ ያለው ቦርድ ጥንቅር ተመሳሳይ ነው፡፡ ከሁለቱ አባላት በስተቀር ሁሉም ሹመኞችና የፓርላማ አባላት ናቸው፡፡ የፓርላማ አባላቱ ያው እንደሚታወቀው አንድ ዓይነት የፖለቲካ ሐሳብ የሚከተሉ ናቸው፡፡ ሥራ አስኪያጁም በሹመት እንጂ ክፍት የሥራ መደብ ወጥቶ የሚቀጠር አይደለም፡፡ ወይም ደግሞ ቢያንስ ለስሙ እንኳን እንደ ምርጫ ቦርድ፣ የሰብዓዊ መብትና የዕንባ ጠባቂ ኮሚሽኖች ገለልተኛ እንዲሆን የተዘረጋ አሠራር የለም፡፡ ሥራ አስኪያጁ የቦርድም ጸሐፊም ጭምር ነው፡፡ ከተቃዋሚ ፓርቲ አንድም አባል የለም፡፡

እንዲህ ዓይነት የቦርድ አባላት አመራረጥና የሥራ አስኪያጅ ሹመት በመንግሥት የሚተዳደር የመገናኛ ብዙኃን የሐሳብ ብዝኃነት ያረጋግጣል ማለት ዘበት ነው፡፡ በየክልሉ የሚገኙ የመንግሥት የመገናኛ ብዙኃን ተቋማትም አደረጃጀታቸውና አስተዳደራቸው ከፌደራሉ ብዙም ልዩነት የላቸውም፡፡

የሚተዳደሩበት ሁኔታ እንዳለ ሆኖ በተግባርም የሐሳብ ብዝኃነት የነጠፈባቸው ናቸው፡፡ ‹‹የህዳሴና የብዙኃን ድምጽ›› የሚል መፈክር ያለው ‘ኢቢሲ’ም ምን ዓይነት የሐሳብ ብዙኃነት እንደሚያስተላለፍ ተቋሙ ብቻ ነው የሚያውቀው፡፡ አንድ ዓይነት ሐሳብ በማቅረብ የተጠመደን ተቋም የብዝኃነት ድምጽ ማለት የዛሬ አምስት መቶ ሃምሳ ዓመት ገደማ በአገራችን ሰዎች ወንጀል ፈጽመው ሲፈረድባቸው የሚታሰሩበት ቤት ስያሜ የሚያስታውስ ድርጊት ነው፡፡ በወቅቱ ጥፋተኛ የተባሉ ወንጀለኞች ሲታሰሩ ‘መድኃኒት ቤት’ ገቡ ይባል ነበር፡፡ እነዚህ ቤቶች በእርግጥ የእሥረኞች ቋንጃ፣ የደም ሥር፣ እጅ፣ እግር ወዘተ የሚቆረጥባቸው ናቸው፡፡ በመሆኑም የማቁሰያ ቤቶች ሆነው ሳለ የሚጠሩበት ግን በተቃራኒው መድኃኒት ቤት ተብለው ነው፡፡ ልክ እንደዚያው ሁሉ አሃዳዊ ድምጽ የነገሠበትን ተቋም የብዙኃኑ ድምጽ ነው ማለት የማቁሠያ ቤቶችን የመድኃኒት ቤት ብሎ ከመጥራት አይለይም፡፡ በአጭሩ ‘ኦርዌላዊ’ ነው ማለትም ይቻላል፡፡ ጆርጅ ኦርዌል ጦርነት የሚያውጅን የሠላም፣ ውሸትና ፕሮፓጋንዳ የሚነዛን  የእውነታ ሚኒስትር ብሎ እንደሠየመው ማለት ነው፡፡

አራቱ ገደቦችና ሌላ ገደብ አለመኖሩ

መብቶች ስለሚገደቡባቸው ቅድመ ሁኔታዎች በርካታ ፈላስፋዎች፣ የፖለቲካ ሳይንቲስቶች፣ የሕግ ባለሙያዎች የተለያዩ ንድፈ ሐሳቦችን ይከተላሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አንዱና በሰፊው የሚታወቀው የጉዳት መርሕ (harm principle) ነው፡፡ በዚህ መርሕ መሠረት መብት ሊገደብ የሚገባው የሌላን ሰው መብት የሚጎዳ ከሆነ ነው፡፡ የገደቡ ምክንያት ሌሎችን ከጉዳት ለመጠበቅ ሲባል ነው፡፡ የጆን ስቱዋርት ሚል ንድፈ ሐሳብ ነው፡፡ የራስን ሐሳብ በሚያስኬደው መጠንና ጥግ ድረስ ለመግለጽ እንጂ ሌላ ላይ ጉዳት ለማድረስ የሚሰጥ ጥበቃ መሆን እንደሌለበት ይገልጻል፡፡

ሌላው፣ የጥፋት መርሕ (offense principle) የሚባለው ነው፡፡ ለማኅበረሰቡ ጥፋት ወይም የወንጀል ባሕርይ ካለው ማለትም ንግግሩ የሚመለከተው ሰው መጠን፣ የተነገረበት ወቅት እንዲሁም፣ የተናጋሪውን ፍላጎት ከግምት በማስገባት ማኅበረሰቡን ማስቀየሙን ወይም ጥፋት መሆኑን ብሎም ከመገድብ በመለስ በሌላ መንገድ ማስቀረት የማይቻል ከሆነ ሊገደብ እንደሚገባው የሚያስረዳ መርሕ ነው፡፡ በመሆኑም እንዲህ ዓይነቱን ወንጀል ማድረግ ሌሎችን ይታደጋል፡፡

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29(6) ላይ በማያሻማና በግልጽ ቋንቋ እንደተገለጸው ሐሳብን በፕሬስና በማናቸውም መገናኛ ብዙኃን ማንኛውም ሰው ሲገልጽ የሐሳቡ ይዘት ምንም ይሁን ምን፣ ሐሳቡ በመገለጹ የሚያስከትለው ውጤት ምንም ይሁን ምን፣ መከልከል አይቻልም፡፡ ወንጀል ማድረግማ ፈጽሞ አይታሰብም፡፡ በሕግ የሚገደብባቸው ‘የወጣቶችን ደህንነት የሚያናጉ፣ የግለሰብን መብት የሚጥሱና ሰብዓዊ ክብርን  የሚነኩ የአደባባይ መግለጫ ማድረግ፣ የጦርነት ቅስቀሳ ማድረግ’ ብቻ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ከአራቱ ውጪ በሌሎች ምክንያት ፈጽሞ ሐሳብን በነጻነት በማናቸውም የፕሬስ ውጤቶችም ይሁን በኤሌክትሮኒክ መንገድ እንዳይገለጹ መከልከል ወይም ወንጀል ማድረግ ፈጽሞ ከሕገ መንግሥቱ ውጭ  ነው፡፡ በመሆኑም የመንግሥትን ስም ማጥፋት፣ መንግሥትን መስደብ፣ አገራዊ አርማንና ባንዲራን መስደብ፣ ሌሎች አገሮችን፣ ዓለም አቀፍ ተቋማትን፣ አርማዎቻቸውንና ባንድራዎቻቸውን መስደብና ስም ማጥፋትና የመሳሰሉትን ድርጊቶች ወንጀል የተደረጉበት ሁኔታ ፈጽሞ ሕገ መንግሥታዊ መሠረት የላቸውም፡፡ እዚህ ላይ ነው የሕገ መንግሥቱ ከየትኛውም ዓለም አቀፋዊ የሰብዓዊ መብት ሰነድ የሚሰፋው፡፡

 

የብዙዎቹ መለኪያዎች በሕግ መደንገግና ለዴሞክራሲያዊ ማኅበረሰብ አስፈላጊ መሆን ሲሆኑ የሁለተኛውን መሥፈርት አስፈላጊነቱን የመወሰን በአብዛኛው የተተወው ለሚመለከታቸው አገሮች ነው፡፡ እነዚህ መሥፈርቶች፣ እንደፈለጉ ለመፈንጠዝ የተመቹ ሲሆኑ በተቃራኒው የእኛ ሕገ መንግሥት የመረጣቸው ደግሞ ጥብቅ እንዲሁም ለመለካት የማያስቸግሩ መሥፈርቶችን ነው፡፡

ከላይ እንደተገለጸው በሕግ ሊገደብባቸው የማይቻልባቸው ሁለት ሁኔታዎች አሉ፡፡ የመጀመሪያው ይዘቱን መሠረት አድርጎ የሐሳብን ነጻነት በሕግ መገደብ አለመቻሉ ነው፡፡ ከላይ ከተገለጹት አራት መሠረታዊ ገደቦች በስተቀር በአገሪቱ በየትኛውም ደረጃ ላይ የሚገኝ ሕግ የማውጣት ሥልጣን የተሰጠው አካል ይዘቱን መሠረት ያደረገ ሐሳብን በነጻነት መግለጽን የሚገድብ ሕግ ማውጣት አይችልም፡፡ አራቱ በተራቸው ወደ በርካታ ዝርዝር ክልከላ ሊመነዘሩ ይችላሉ፡፡ ሲመነዘሩ ቢኖሩም ግን የግለሰብን መብትና ሰብዓዊ ክብር፣ እንደ ቡድን የወጣቶች አስተዳደግን የሚመለከት፣ እንደ ተቋም ደግሞ ከጦርነት ቅስቀሳን የሚመለከቱ ብቻ መሆን አለባቸው፡፡   

ሁለተኛው ደግሞ የሚያስከትለውን ውጤት በማሰብ የሐሳብን ነጻነት በሕግ መገደብ አለመቻሉ ነው፡፡ በመሆኑም በኅትመትም ይሁን በሌላ መንገድ የሚገለጽ ሐሳብ መንግሥት ላይ አመኔታ እንዳይኖር ወዘተ በማለት ወንጀል ማድረግን ሕገ መንግሥቱ ፈጽሞ አይፈቅድም፡፡ ሕገ መንግሥቱ ባይፈቅድም ቅሉ በወንጀል ሕጉ በመከልከሉ በርካታ ጋዜጠኞችና ጦማሪያን በዚህ ወንጀል መከሰሳቸው ይታወቃል፡፡

ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትንና ሐሳብ የሚንሸራሸርባቸውን ሚዲያ በተመለከተ ሕገ መንግሥቱ ከላይ በቀረበው መልኩ ጥበቃ ያድርግ እንጂ የመንግሥት ፖለሲና ተግባር ግን ብዙም ለዚህ መብት መከበር ምቹ ስላለመሆኑ የሚከተለውን በምሳሌነት እንመልከት፡፡ በተለይም ደግሞ ስለግል ፕሬሱ፡፡

የመንግሥት ፖሊሲ ስለግል ፕሬሱ

መንግሥት በ1994 ዓ.ም. ያወጣው ስለ ዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ከሚያትትበት ሠነዱ ስለግል ፕሬሱም በርካታ ነጥቦችን አስቀምጧል፡፡ በገዥው ፓርቲ ግምገማ መሠረት የግል ሚዲያው መሠረታዊ የመዋቅር ችግሮች አሉበት፡፡ ‘የአየር በአየር ነጋዴ  ባሕርይ አለባቸው፤ ወይም ከዚህ የጸዱ አይደሉም፡፡’ የተለያዩ ዓላማ ያላቸው ባለሀብቶች ሊቆጣጠሩት እንደሚችሉም አመልክቷል፡፡ ‘የተለያዩ ድርጅቶች ዓላማቸውን እንዲያስፈጽሙላቸው ሊደግፏቸውም ሊያሽከረክሯቸውም ይችላሉም’ ይላል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አክራሪዎችና አሸባሪዎችም ሊሆኑ እንደሚችሉ ይገምታል፡፡

በሌላ መልኩ ደግሞ፣ ‹‹በመሠረታዊ አቅጣጫዎች ላይ አገራዊ የጋራ አመለካከት አለመኖርና ተሟልቶ አለመገኘቱ ለግል ሚዲያ መዳከም አንዱ ምክንያት ነው፡፡›› በመሆኑም ‹‹የግል ሚዲያዎች ሥርዓቱን የማደናቀፍና የመናድ ተግባር ውስጥ እየተሳተፉ ነው›› ይላል፡፡ በመፍትሔነትም የጋራ እምነት መገንባት፣ እንደ ነጋዴዎችም ጭምር ከጥገኝነት ለማላቀቅ መረባረብና መሥራት፣ እንዲሁም የግል ሚዲያው አፍራሽ ሚና እየተጫወተ ነው በሚል እምነት ማግለልና በከፋ ደረጃ ሕግ የጣሱትን የማስቀጣት አቅጣጫ መከተሉ ብዙ ርቀት ስለማያስኬድ ገንቢ የሆኑትን የማሳደግ ያልሆኑትን ደግሞ በአስተማማኝ አኳኋን የሚያስወግዱ ሥርዓት እንደሚያበጅ በግልጽ አስቀምጧል፡፡ በመሆኑም፣ በተለይ ከምርጫ 1997 በኋላ የወጡትንና ሐሳብን በነጻነት ከመግለጽ የሚገናኙ አዋጆች የዚህ ፖሊሲ ውጤት እንደሆኑ መገመት አይከብድም፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የልማታዊ ጋዜጠኝነት ጉዳይም አብሮ ከግምት የሚገባ ነው፡፡

ለማጠቃለል ያህል ሕገ መንግሥቱ የሐሳብ ነጻነት ሊገደብ የሚቻልባቸውን አራት ማዕቀፎች ቢያስቀምጥም በሌሎች አዋጆች ግን በይዘቱንም የሚያስከትለውንም ውጤት በማሰብ በርካታ ገዳቢ የወንጀል ሕግጋት ወጥተዋል፡፡ በዚህም መሠረት በርካታ ክሶች ቀርበዋል፡፡ ለዚህ አሠራር ደግሞ በተራው ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ፖሊሲም አለ፡፡ በፖሊሲው መሠረት ሕግ ሲወጣም ሊቃወም የሚችል ሕግ አውጪ የለም፡፡ የወጣውን ሕግ በትጋት የሚያስፈጽም ተቋም ግን አለ፡፡ ሕገ መንግሥቱን የሚታደግ ባይኖርም፡፡ በመሆኑም፣ በፕሬስም ነጻነት፣ በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን የተለያዩ ሐሳቦችን አሳታፊነት፣ በኢንተርኔት አገልግሎት ወዘተ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ በመገኘታችን ለአገሪቱ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታም የሚገባውን አስተዋጽኦ ሊያደርግ አልቻለም፡፡

አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው wuobishett@yahoo.com ማግኘት ይቻላል፡፡