Skip to main content
x
ከአገርነት ወደ አመድነት - ሶሪያ

ከአገርነት ወደ አመድነት - ሶሪያ

በዮሐንስ አልታሞ

የዓረብ ፀደይ ስድስተኛ አመቱን ይዟል፡፡ ወቅቱ እ.ኤ.አ. 2011 ነው፡፡  በዓረብ አገሮች አዲስ ክስተት የተባለለት ሕዝባዊ አመፅ ተቀሰቀሰ፡፡ ለበርካታ ዘመናት በመንበረ ሥልጣናቸው ቤተ መንግሥት የማያስነኩት የዓረብ ንጉሣዊ ቤተሰቦችና መንግሥታት ሥፍራቸውን እንዲለቁ ሕዝባቸው ቀጥተኛ ጥሪ አስተላለፈ፡፡ ለጥሪው የመንግሥታቱ ምላሽ አገሮቹን ወደ መቀመቅ ከተተ፡፡ ሰላማዊ በሆነ መንገድ የተጀመሩ ሰላማዊ ሠልፎች ወደ አመፅ ተቀየሩ፡፡ መንግሥታቱ የታጠቁትን መሣሪያ ወደ ሕዝብ አዞሩ፣ ሕዝብን የወገኑ የመንግሥት ወታደሮችም ከሕዝብ ጎን ተሠልፈው ወደ እርስ በርስ ጦርነት ገቡ፡፡ አጋጣሚውን ተገን በማድረግ በየአገሮቹ የውስጥና የውጭ ኃይላትም እጃቸውን አስገቡ፡፡ ጦርነቶቹ የእርስ በርስ፣ ቅዱስ ጦርነት፣ እንዲሁም የቀዝቃዛ ጦርነት መልክ መያዝ ጀመሩ፡፡ ለአንድ ወጥ ዓላማ የሚደረግ አንድ ዓይነትና ተለምዶዓዊ ጦርነት የሚባል ነገር ጠፋ፡፡ በጦርነት ላይ የተሰማሩት አካላት ጠላታቸውን ከወዳጆቻቸው መለየት እስኪሳናቸው ግራ ተጋቡ፡፡ በዚህም የበርካታ ንፁኃን ዜጎች ሕይወት እንደ ቅጠል ረገፈ፡፡ ለተካሄዱ አብዮቶች መነሻ የነበሩ ሁኔታዎች ግን ሳይለወጡ ቀጠሉ፡፡ አብዮቶቹ የተቀሰቀሱባቸው አገሮች ቀደም ሲል የነበራቸውን መረጋጋትና ሰላም ማስመለስ ተሳናቸው፡፡ በአንፃሩ አዳዲስ ችግሮች እንደ እንጉዳይ በቃቀሉ፡፡

ከሜድትራኒያን ባህር የምትዋሰነዋና ከአፍሪካዊቷ ግብፅ በቅርብ ርቀት የምትገኘዋ ሶሪያ ላለፉት ስድስት ዓመታት  ከሌሎቹ አመፅ ከተቀሰቀሰባቸው አገሮች ለየት ባለ ሁኔታ ለዜጎችዋ የሲኦል፣ ለዓለም መንግሥታትና ተቋማት ደግሞ የራስ ምታት ሆና ቆይታለች፡፡ ለስድስት ዓመታት በዘለቀው የሶሪያ ጦርነት ሃምሳ ሺሕ ሕፃናትን ጨምሮ አምስት መቶ ሺሕ ሰዎች አልቀዋል፡፡ በሶሪያ ምድር ሁሉም መንደር ጦር ሜዳ ነው፡፡ ትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታሎች፣ እንዲሁም የሃይማኖት ሥነ ሥርዓት የሚካሄድባቸው ሥፍራዎች በሙሉ፡፡ በሶሪያ የሚካሄደውን ጭፍጨፋ ማን እየፈጸመ ነው? ውጊያውን የሚያካሂዱ አካላት እነ ማን ናቸው? ማብቂያውስ መቼ ነው? የሚሉ ጥያቄዎችን በዚህና በቀጣይ በሚወጡ ጽሑፎች ላይ ለማብራራት ይሞከራል፡፡ 

በሶሪያ ጦርነት ቀጥተኛ ተሳታፊ የሆኑ ቢያንስ አራት አካላት ይገኛሉ፡፡ እነዚህም በፕሬዚደንት በሽር አል አሳድ የሚመራው የመንግሥት ጦር፣ የአማፅያን ጎራ፣ የኩርዶች ቡድንና አይኤስ ሲሆኑ ሁሉም የየራሳቸውን ዓላማ አንግበው የሚንቀሳቀሱ ናቸው፡፡ የበሽር አስተዳደር ከሥልጣን ለማውረድ ወደ ፍልሚያ የገባው የመጀመሪያው የመንግሥት አማፂ ቡድን ከመንግሥት ጦር እየከዱ ከነትጥቃቸው በሚኮበልሉ አባላት እየተደራጀና እየተጠናከረ፣ ቀደም ሲል በመንግሥት ቁጥጥር ሥር የነበሩ ሥፍራዎችን እያስለቀቀ ግስጋሴውን ቀጠለ፡፡ በዚህም ግስጋሴ የዓለም ሚዲያዎች የበሽር አስተዳደር ፍፃሜ መቃረቡን ደሰኮሩ፡፡ ሰውየው የሙአመር ጋዳፊ ዕጣ ፈንታ ይደርሰዋል ብለው አፋቸውን ሞልተው ተናገሩ፡፡ ከአማፅያኑ ጎን ተሠልፈው የሚዋጉት ኩርዶችና ከኢራቁ የአልቃይዳ ክንፍ ክፍፍል በመፍጠር ተገንጥሎ ወደ ሶሪያ የገባው አይኤስ አንደኛው የሌላኛው ጠላት በመሆን ትኩረታቸውን ከጅምር እንዳደረጉት ሙሉ ኃይላቸውን በመጠቀም መንግሥት ከመፋለም ይልቅ፣ አንደኛው የሌላኛው ጠላት በመሆን የእርስ በርስ ፍልሚያ ውስጥ ገብተው ሰነባብተዋል፡፡ ሆኖም መንግሥትን በአንድ በኩል በሌላ በኩል እርስ በርስ ፍጅታቸውን ቀጠሉ ፡፡

በሒደት የአማፅያኑ ጡንቻ የጠነከረበት የበሽር አል አሳድ አስተዳደር በእጁ የሚገኙ አውዳሚና ጅምላ ጨራሽ የኬሚካል መሣሪያ ሳይቀር ጥቅም ላይ በማዋል ጠላቶቼ ያላቸውን ማሳደድ ተያያዘ፡፡ በዚህም ሕፃናት፣ አዛውንቶችና አቅመ ደካሞች በኬሚካል የተበከለ አየር በመተንፈስ አለቁ የንፁኃን ዜጎች አስከሬን በነጫጭ ፎጣዎች ተጠቅልሎ ለሶሪያውያንና ለዓለም ሕዝብ ይፋ ሆነ፡፡ ድርጊቱ ከዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ ከፍተኛ ውግዘት አስከተለ፡፡ ዓለም በአንድ አቋም የበሽር አል አሳድን አስተዳደር አወገዘ፡፡ ሰውየውና መንግሥታቸው አለቀላቸው ተባለ፡፡ የሶሪያን ጦርነት  ለመከታተል የሶሪያውያንን የሕዝብ ሁኔታ ከግንዛቤ ማስገባት ተገቢ ይሆናል፡፡

የሶሪያውያንን አጠቃላይ ሕዝብ ወስደን ካየን ሰማኒያ በመቶ ዓረቦች፣ ዘጠኝ በመቶ ኩርዶች፣ ዜሮ ነጥብ ስምንት (0.8) በመቶ አርሜኒያዎችና ዘጠኝ በመቶ ክርስቲያኖች ናቸው፡፡ ከአጠቃላዩ እስልምና ተከታይ ሰባ በመቶ የሱኒ፣ ሦስት በመቶ የሺዓና የተቀረው የአለቪስ ተከታይ ነው፡፡ አለቪስ የተሰኘው ክፍል በዋናነት ከሱኒና ከሺዓ የተለየ ሲሆን፣ በሁለቱም ተከታዮች የሚሰጠው ሥፍራ አነስተኛ ነው፡፡ ፕሬዚዳንት በሽር አል አሳድና ቤተሰቦቻቸው እንዲሁም አብዛኞቹ ደጋፊዎቻቸው በዚሁ ጎራ የሚገኙ ናቸው፡፡ የተጠቀሱ ክፍፍሎችና ክፍፍሎቹን የተከተሉ የአጋርነት ድጋፎች ሶሪውያኑን፣ እንዲሁም የውጭውን ኃይል ከዚህ ቀደም የነበሩ ልዩነቶች በማስፋት ከድጡ ወደ ማጡ በመክተት የጠላትና የወዳጅ ጎራ እንዲፈጠር አደረገ፡፡ የዓለማችን ኃያላን አገሮችም የሚወግኑትን ወይም በጠላትነት ፈርጀው የሚያጠቁትን ወገን ለመለየት ይኼንኑ ክፍፍል ታሳቢ ማድረጋቸው አልቀሩም ፡፡

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የሶሪያ አስተዳደር በንፁኃን ዜጎች ላይ የፈጸመው የኬሚካል ጥቃት የአሜሪካ የብሔራዊ ደኅንነት ጉዳይ እንደሆነ ድርጊቱ በተፈጸመ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ አስታወቁ፡፡ በዚህም አሜሪካ እጇን በሶሪያ በሚካሄደው ጦርነት እንደምታስገባ በመግለጽ የመንግሥትን አማፅያን በሲአይኤ በኩል ማሠልጠንና ማስታጠቁን ተያያዘችው፡፡ በሌላ በኩል ከአሜሪካ ጋር የቀዝቃዛው ጦርነት ተፋላሚ የነበረችዋና በፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ አባል የሆነችዋ ሩሲያም ድርጊቱን በማውገዝ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጉዳዩን እንዲያጣራ፣ የበሽር አል አሳድ መንግሥት በሩን ክፍት በማድረግ ሒደቱን እንዲደግፍ አሳሰበች፡፡

 የሩሲያ መሪዎች በወቅቱ አሜሪካ ሶሪያን እንደ ኢራቅ ልትደበድብ ትችላለች ከሚል ሥጋት የመነጨ እንደነበር ብዙዎች በወቅቱ ሐሳባቸውን ገልጸዋል፡፡ ሆኖም የአሜሪካ መንግሥት ቀጥተኛ በሆነ ድብደባ ከመሳተፍ ይልቅ ተዘዋዋሪ ተሳትፎን መረጠ፡፡ በዚህም አማፅያኑን ማሠልጠንና ማስታጠቁን ተያያዙት፡፡

ይህም ሆኖ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በሲአይኤ በኩል ለመንግሥት አማፅያን የሚደረገው ድጋፍ ከአማፅያኑ ጎን ተሠልፈው የበሽርን መንግሥት ለመጣል ፍልሚያ ከሚያካሂዱ ቡድኖች በተጨማሪ፣ የጂሀድ ፍልሚያ የሚያካሂዱ በሶሪያ የሚገኙ ጽንፈኛና አሸባሪ ቡድኖችን እየጠቀመና መሣሪያም በቀላሉ እያገኙና እየተጠናከሩ እንዲሄዱ በር እንደከፈተላቸው ተገነዘቡ፡፡ አይኤስን ጨምሮ ሌሎች ጽንፈኛ ቡድኖች የአሜሪካን ትጥቅ በአማፅያኑ ካባ ሥር ተጠልለው እስከ አፍንጫቸው ታጠቁ፡፡ ይህ አሜሪካ የምትወስዳቸውን ዕርምጃዎች በድጋሚ እንድታጤን አስገደዳት፡፡ የሶሪያን አማፅያን መደገፉን መቀጠል በሽርን ከሥልጣን ለማባረር ወሳኝ እንደሆነ ቢታመንም፣ ይኼንኑ ለማሳካት ለአማፅያኑ የምታስታጥቀው መሣሪያ ግን ወደ አሸባሪዎች እጅ እንዲገባ አሜሪካ አልፈለገችም፡፡ አይኤስ ምንም እንኳን ከአል አሳድ መንግሥት ጋር ፍልሚያ ውስጥ በመሆን አሜሪካ ከምታስታጥቃቸው አማፂያን ጎን ተሠልፎ የሚዋጋ ቢሆንም፣ የጠላቴ ጠላት… የሚለው ብሂል በዚህ ወቅት አይሠራም አለች፡፡  በዚህም አሜሪካ ድጋፏን በተዘዋዋሪ ለሌላ ወገን ማድረግ መረጠች፡፡

ከአሜሪካ በተጨማሪ በሶሪያ ምድር ከበሽር ከአል አሳድ አስተዳደር ጋር ለሚፋለሙ አማፅያን ድጋፋቸውን የሚሰጡ የውጭ ኃይሎች ከአስተዳደሩ ባሻገር፣ የአል አሳድን አጋሮች የድጋፍ እንቅስቃሴ በዓይነ ቁራኛ የሚከታተሉ ይገኛሉ፡፡ በመካከለኛው ምሥራቅ የሶሪያ መንግሥት ጠንካራ አጋር የሆነችዋና በሺዓ እስልምና ተከታዮች ብዛት የምትታወቀዋ ኢራን በየቀኑ አውሮፕላኖችዋን በቁሳቁስና በሰው ኃይል እየሞላች ወደ ደማስቆ የምታደርገው እንቅስቃሴ ያላማራቸው፣ በሱኒ አማኞች ብዛት የሚታወቁት ቱጃሮቹ ሳዑዲ ዓረቢያና ኳታር በቱርክና ዮርዳኖስ በኩል የበሽርን መንግሥት ለሚፋለሙ አማፅያን ድጋፋቸውን ሲለግሱ ሰነባብተዋል፡፡

ቱርኮች በሶሪያ በሚካሄደው ጦርነት በአል አሳድ ላይ ከተከፈተው ዘመቻ ይልቅ የኩርዶችን እንቅስቃሴ በዓይነ ቁራኛ በመከታተል፣ በሥፍራው ኩርዶችን ከሚፋለመው አይኤስ ጋርም አልፎ አልፎ ከመፋለም ይልቅ እንዳላዩ በማለፍ  ጭምር ይንቀሳቀሱ እንደነበር ይነገራል፡፡ በሌላ ወገን  እ.ኤ.አ በ2012 የዓመቱ አጋማሽ አካባቢ የሊባኖሱ የሺዓ ቡድን ሒዝቦላ በኢራን ድጋፍ ከአል አሳድ ጎን ተሠልፎ ውጊያውን ተቀላቅሏል፡፡ በዚህም ሳዑዲ ቀደም ሲል ታደርግ የነበረውን ድጋፍ ዮርዳኖስን በመጠቀም አጠናክራ ቀጠለች፡፡

ሁኔታው እ.ኤ.አ. በ2013 የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮችን ለሁለት ከፈለ፡፡ የመጀመሪያ ክፋይ ከአማፅያኑ ጎን የተሠለፈው የሱኒ ኃይል ሲሆን ሁለተኛው በሽር አል አሳድን የሚደግፈውን የሺያዓ ወገን ነው፡፡ የዓረቡ ዓለም በሱኒና በሺዓ መከፋፈል የነበራቸው የከረመ ሹክቻ ተጋጋለ፡፡ አገሮቹ ሲደግፉም ሆነ ሲቃወሙ በዚሁ አሠላለፍ ሆነ፡፡

የአሜሪካ አቋም መቆሚያ አጣ፡፡ አሜሪካኖች የትኛውን ጠላት ብለው እንደሚዋጉ፣ ወዳጅ ብለው እንደሚደግፉ ግራ ተጋቡ፡፡ በሽር አል አሳድን ለመጣል የሚፋለመውን የኩርዶች ቡድን የሚዋጋው የጂሀድ አራማጁ አሸባሪው አይኤስ ውስብስብ ፈተና ፈጠረባቸው፡፡ ዋነኛ የአሜሪካ ጠላት የበሽር አል አሳድ መንግሥት ከመሆን ይልቅ የበሽርን መንግሥት የሚዋጋው አሸባሪው ቡድን መሆኑን በመገንዘብ የመሣሪያውን አፈሙዝ ወደ ቡድኑ አዞሩ፡፡ በዚህ ወቅት ቱርኮች በሶሪያ የሚገኙና በአይኤስ ጥቃት የተከፈተባቸውን የኩርድ ተዋጊዎችን ዋነኛ ጠላት በማድረግ ሲፋለሙ ሰንብተዋል፡፡ ቱርክና አሸባሪው ቡድን አይኤስ ወዳጆች ባይሆኑም፣ በሶሪያ የጋራ ጠላት አላቸው፡፡ የኩርድ አማፂዎች የጠላቴ ጠላት… ለቱርክ ይሠራል፡፡ ይህም ጉዳይ ለአሜሪካ ሌላ የቤት ሥራ ጨመረባት፡፡ ሆኖም በሽር አል አሳድ በዚህ ወቅት በርካታ ሥፍራዎችን እየተነጠቀ ነበር ፡፡

እ.ኤ.አ. መስከረም 2015 ከዚህ ቀደም በሶሪያ ምድር የነበሩ ጦርነቶችን ይዘት የሚቀያይር ክስተት ይዞ ብቅ አለ፡፡ የሩሲያ መንግሥት አይኤስን  ለመዋጋት በማለት የጦር አውሮፕላኖችን ወደ ሶሪያ አዘመተ፡፡ ከበሽር አላሳድ ጎን በመሠለፍ አይኤስን ለማጥቃት ሩሲያ  የምትወስዳቸው ዕርምጃዎች ግን በአሜሪካ የሚደገፉ አማፅያንን እየለቃቀመ የሚፈጅ ከመሆኑም ባሻገር፣ ንፁኃን ሶሪያውያንንም የጥቃቱ ዒላማ ማድረጉ ተረጋገጠ፡፡ ሁኔታው አሜሪካን ዳግም ብዥታ ውስጥ አስገባት፡፡ ሩሲያ ወደ ሶሪያ የገባሁት የዓለማችን አሸባሪ ቡድን አይኤስ ለማጥቃት ነው ስትል፣ አሜሪካ በአንፃሩ የሩሲያ አካሄድ አይኤስን ከማጥቃት ይልቅ ዋነኛ ዓላማዋ የበሽር አላሳድን አማፅያንና ተቀናቃኞች በሙሉ በመጨረስ የበሽርን መንግሥት ማጠናከር ነው ስትል ሩሲያ አካሄዷዋን እንድታስተካክል  በተደጋጋሚ አስጠነቀቀቻት፡፡

ሰሞኑን አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በሶሪያ ላይ የመጀመሪያውን ቀጥተኛ ወታደራዊ ዕርምጃ ወስዷል፡፡ ለዕርምጃው መንስዔ የተባለው የሶሪያ መንግሥት ከዚህ ቀደም ጠላቶቹን ለመፍጀት በሚል ሰበብ እንደተጠቀመ የሚነገረውን የኬሚካል መሣሪያ፣ አሁንም በድጋሚ አማፂያን በያዙዋት ካሀን ሸክሆን በሚባለው የሰሜናዊ ሶሪያ አካባቢ በመጠቀም ሃያ ሕፃናትን  ጨምሮ 86 የሚጠጉ ንፁኃን ዜጎችን ፈጅቷል መባሉ ነው፡፡ ድርጊቱን የበሽር አል አሳድ መንግሥት እንዳልፈጸመ የተናገረ ሲሆን፣ የሩሲያ መንግሥትም ተመሳሳይ አቋም በመያዝ ድርጊቱ በአማፂያኑ የተፈጸመ እንደሆነ፣ የአሜሪካ መንግሥት የፈጸመው የቶምሐውክ ጥራዝ ሚሳይል ግን በሉዓላዊ አገር ላይ የተፈጸመ ወረራና ጥቃት መሆኑን ገልጸው አውግዘውታል፡፡ ሁኔታው አሜሪካንና ሩሲያን ወደ ከፍተኛ የፖለቲካና ወታደራዊ ውጥረት ውስጥ የከተተ ሲሆን፣ በፀጥታው ምክር ቤት አባላት ዘንድም ሩሲያ ሀይ ተብላለች፡፡ ውጥረቱ ግን እንደቀጠለ ነው፡፡ አሜሪካ ጥቃቱ ቀጣይ እንደሆነ ስትገልጽ ሩሲያ በበኩሏ በዚሁ ከቀጠለ የራሴ የምትለውን ዕርምጃ እንደምትወስድና የሶሪያን የመከላከያ አቅም እንደምታጠናክር አስታውቃለች፡፡

እ.ኤ.አ በ2011 የዓረብ ፀደይ ሕዝባዊ አመፅ የቱኒዚያ ፕሬዚዳንት ዚን ኤል አብዲን ቤን አሊንና የግብፁ ፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክን ከሥልጣን እንዲባረሩ ቢያደርግም፣ በሶሪያ ላይ ግን ጉልበት አጣ፡፡ ፕሬዚዳንት አል አሳድን ከሥልጣን ወንበራቸው ንቅንቅ የሚያደርጋቸውም ጠፋ፡፡ ይልቁንም የሶሪያውያን ሰቆቃ እጅግ ከፋ፡፡ ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ እስከ ወዲያኛው አሸለበ፡፡ አንድ ሚሊዮን የሚገመት ሕዝብ አካሉን አጣ፣ አሥራ ሁለት ሚሊዮን ሕዝብ ከአገሩ ተሰደደ፡፡

ከሶሪያ የመንግሥት ጦር እየኮበለሉ ሕዝባዊ አመፁን የደገፉና በኃላም የነፃይቱ ሶሪያ ጦር የአማፂ ቡድን ያቋቋሙት አማፂያን የበሽር አል አሳድን መንግሥት በጦርነት ቢፋለሙም፣ የውጭ ኃይሎች በሶሪያ ያለውን ሁኔታ አወሳሰቡት፡፡ ገሚሱ አማፂውያንን፣ ገሚሱ መንግሥትን እያስታጠቁ ጦርነቱን በማራዘም አገሪቱን ሰው አልባና አመድ አደረጉዋት፡፡ ሶሪያ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ፊት ከአገርነት ወደ አመድነት የተቀየረች ምድር ሆነች፡፡

የፖለቲካ ምሁራን ክስተቱን በመታዘብ የዓለም ፖለቲካ ወደ አዲስ ምዕራፍ እየተሸጋገረ ነው ሲሉ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ፖለቲካው የታሪክ ፍፃሜ ላይ መቃረቡን ይነግረናል እንዲሁም ሕዝባዊ መንግሥታት ጉልበታቸው እየቀነሰ መሆኑን፣ የሥልጣኔ ግጭት እየተከሰተ እንደሆነና ቀደም ሲል የነበረው ዓለም አቀፋዊ ባላንጣነት ዳግም እያንሰራራ አንደሆነ እየጻፉ፣ እየተናገሩና እያስተማሩ ይገኛሉ፡፡ ከሶሪያ ጋር በተያያዘ እየተከሰቱ የሚገኙ ጦርነቶችንና መዘዛቸውን በእነዚሁ ማዕቀፍ ማየቱ ጠቃሚ ይሆናል፡፡

ከአዘጋጁ፡ ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡