Skip to main content
x

ከኢንተርኔት መዝጋት የተሻለ አሠራር ይፈጠር

የኢንተርኔት አገልግሎት ተቋርጦ ሰነበተ፡፡ ከ40 ሚሊዮን በላይ የሞባይል ደንበኞችን ያፈራው ኢትዮቴሌኮም፣ ለሞባይል ኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሳይሰጥ ወይም ምንም መረጃውን ሳያስተላልፍ አገልግሎቱን አቋርጧል፡፡ ከሞባይል ውጭ ያለው የኢንተርኔት አገልግሎትም ቢሆን ሲደነቃቀፍ ነበር፡፡

ኩባንያው ስለ አገልግሎቱ መቋረጥ ድምፁን አጥፍቶ ቢቆይም፣ ረፋዱ ላይ ከመንግሥት ኮሙዩኒኬሽንስ ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር በተሰጠ መግለጫ እርግጥም የኢንተርኔት አገልግሎቱ መቋረጡን፣ የተቋረጠውም ከአገር አቀፍ ብሔራዊ ፈተናዎች ጋር በተያያዘ እንደሆነ ሰምተናል፡፡

የአገልግሎቱ መቋረጥ ችግር ፈጥሯል፡፡ ከመረጃ መረቦች ጋር የተሳሰረው ይህ ትውልድ፣ በተስተጓጎለው አገልግሎት ሳቢያ ብዙ እንደሚያጣ መገመት ይችላል፡፡ መደበኛው የኢንተርኔት አገልግሎትም ቢሆን በሁሉም ቦታ እንደሚፈለገውና እንደተለመደው አገልግሎት የሚሰጥበት ስላልነበር፣ ከግለሰብ ጀምሮ የዕለት ሥራቸውን ከኢንተርኔት ጋር ያስተሳሰሩ ተቋማት ላይም ጫና አሳድሯል፡፡ የፋይናንስ ተቋማት የኢንተርኔት ባንክ አገልግሎት ቀጥ ብሏል፡፡ ገንዘብ ከአንዱ ወደ ሌላው ማሸጋገር ተገቶ ሰንብቷል፡፡ በሕጋዊ መንገድ ከውጭ የሚላክ የሐዋላ ገንዘብ መቀበል አዳጋች ሆኖ ቆይቷል፡፡

ገንዘብ የተላከላቸው ደንበኞች የባንኮችን ደጅ ቢጠኑም ‹‹የኮኔክሽን ችግር ስላለ ልናስተናግዳችሁ አንችልም፤›› ተብለዋል፡፡ በመሆኑም የአገልግሎቱ መስተጓጎል ብዙ ክፍተት መፍጠሩ ግልጽ ነው፡፡ ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ደንበኞች ወቅታዊ መረጃ ኖሯቸው እንዲዘጋጁበት ማድረግ ተገቢ ቢሆንም መንግሥት ኢንተርኔት መዝጋቱን እንዲናገር መጎትጎት አስፈልጎት ሲታይ ግን ያስተዛዝባል፡፡

የአገልግሎቱ መቋረጥ ከዚህ ቀደም የተከሰተው ዓይነት ተግባር እንዳይፈጸም ቅድመ ጥንቃቄ ለማድረግ ሆነም አልሆነ ሕዝብ እንዲያውቀው ማድረግ ምን ክፋት ይኖረው ይሆን? መፍትሔው ኢንተርኔት ማቋረጥ ሳይሆን፣ የፈተና ስርቆት ምንጮችን ማድረቅ ቀዳሚው ዕርምጃ ሊሆን በተገባ ነበር፡፡ ድረገጾች የፈተና ውጤት መለዋወጫ ሰሌዳ እንዳይሆኑ ሲባል ኢንተርኔት መጠርቀም መፍትሔ አይሆንም፡፡ እንከመቼስ እንዲህ ያለ ዕርምጃ እየተወሰደ ይዘለቃል?

የኢንተርኔት አገልግሎቱን ማቋረጡ አማራጭ የሌለው መፍትሔ ሆኖ ከተገኘም በሙሉም ሆነ በከፊል አገልግሎታቸው ከኢንተርኔት ጋር የተያያዙ ተቋማት ላይ ተፅዕኖ በማያሳድር አኳኋን ጉዳቱን መቀነስ ይችል ነበር፡፡ ነገር ግን አንዱን ለመከላከል ሲባል በሌላው ላይ ጉዳት ማድረስ እንዳይሆንም ቅድመ ጥንቃቄ መደረግ ነበረበት፡፡

ከተገልጋዩ ባሻገር ኢትዮ ቴሌም ቢሆን በሚሊዮን የሚገመት ገቢ አጥቷል፡፡ የተለያዩ መረጃዎችን በየዕለቱ በሞባይሉ መከታተል የለመደ ተጠቃሚ፣ የቅድመ ክፍያ ካርድ ግዥውን ሳይፈልግ ለመቀነስ ተገዶ ሰንብቷል፡፡

በመደበኛው መንገድ ገንዘብ ለመላክ ብዙ ፈተና በሚታይበት በዚህ ወቅት እንዲህ ያለው የግንኙነት ማቋረጥ ዕርምጃ፣ በግድ መደበኛ ወዳልሆነው መንገድ ሰዎችን የሚገፋ እንደሆነ መገመትም ይቻላል፡፡ ባንኮች ገንዘብ ከአንዱ ወደ አንዱ የሒሳብ መዝገብ ለማዘዋወር ሲያዩ ከከረሙት ችግር በላይ በገንዘብ ዝውውሩ አማካይነት ሊካሔዱ የታሰቡ ግብይቶች እንቅፋት እንዲገጥማቸው ማድረጉንም እንደረዳለን፡፡

ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ተሽከርካሪዎች ዓመታዊ የቴክኒክ ምርመራ ለማድረግና ቦሎ ለማስለጠፍ ፈልገው ኢንተርኔት የለም በመባሉ ሰበብ የተፈጠረውን ትርምስ ልብ ይሏል፡፡ በ‹‹ኮኔክሽን የለም›› ሰበብ በትራፊክ የተቀጡ አሽከርካሪዎች፣ ቅጣታቸውን ለመክፈል አለመቻላቸው ሳይበቃቸው በወቅቱ አልከፈልክም ተብለው በድጋሚ ለመከሰስ የበቁበት አጋጣሚ ጥቃቅን ምሳሌ ሊሆን ይችላል፡፡ በትላልቅ ተቋማት ላይ የደረሰውን ቤቱ ይቁጠረው፡፡

ከዚህ የሚከፋው ግን የኢትዮጵያ መንግሥት በየጊዜው የፈተና መሰረቅ ጉዳይ ወይም ሌላ ከኢንተርኔት ጋር የተያያዘ ሥጋት ባደረበት ጊዜ ሁሉ ኢንተርኔት የሚዘጋ ከሆነ እንኳንና ለገዛ ሕዝቡ ለሌላውስ የሚያተርፈው አመኔታ እንደምን ያለ ነው? የውጭ ኢንቨስትመንት አደገ ተመደገ፣ ኢኮኖሚው ገሰገሰ በሚባልበት አገር ውስጥ ያውም ከሳምንት በላይ ኢንተርኔት እየዘጉ መቀጠል፣ ለአንዳንድ ሹማምንት ‹‹ላይክ›› የማድረግና ያለማድረግ ስላቅ ብቻ ውጤት አይመስልም፡፡ እንደ መብት የሚታየው ይህ አገልግሎት፣ በአገሪቱ መንግሥት ላይ የሚያስነሳው የተዓማኒነትና የአቅም ብቃት ጥያቄ በጉልህ ሊጠቀስ የሚችል ነው፡፡

በከፊልም ሆነ በሙሉ የኢንተርኔት አገልግሎት እያቋረጡ መዝለቅ ስለማይቻል በእስካሁኑ ተምረን ሌሎች አማራጮች እንዲኖሩ ማድረግ ግድ ይላል፡፡ ካልሆነ አንዱን ስንከላከል በሌላ መንገድ የምናጣው ስለሚበዛ አተርፍ ባይ አጉዳይ እንዳንሆን ይታሰብበት፡፡