Skip to main content
x
ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ የወጣባቸው የፅዳት ሽፍን ተሽከርካሪዎች ለማኅበራት ተላለፉ

ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ የወጣባቸው የፅዳት ሽፍን ተሽከርካሪዎች ለማኅበራት ተላለፉ

  • በከተማዋ የሚገኙትን 814 ጊዜያዊ ቆሻሻ ማስቀመጫዎች ወደ 80 ለማውረድ ታቅዷል

የቤት ለቤት ደረቅ ቆሻሻ ማሰባሰብ ሥርዓቱን ዘመናዊ ለማድረግ የሚያስችሉ 54 ሽፍን ተሽከርካሪዎች በ15 ሚሊዮን 768 ሺሕ ብር ተገዝተው 200 ለሚሆኑ የፅዳት ማኅበራት ተላለፉ፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ኋላቀር የሆነውን ከቤት ደረቅ ቆሻሻ የማጓጓዝ ሥርዓት ይቀይራሉ የተባሉት 54 ተሽከርካሪዎች የተላለፉት 20 በመቶ መቆጠብ ለቻሉ ማኅበራት ሲሆን፣ 80 በመቶ ብድሩን የሸፈነው መንግሥት ነው፡፡

ሽፍን የቆሻሻ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎቹ እያንዳንዳቸው ከቀረጥ ነፃ 292 ሺሕ ብር መገዛታቸውንና የአንዱ የመያዝ አቅምም 35 ኩንታል መሆኑን የአዲስ አበባ ፅዳት አስተዳደር ኤጀንሲ ከፍተኛ የሕዝብ ግንኙነት ኤክስፐርት አቶ በረኸኛው ሱልጣን ገልጸዋል፡፡

አቶ በረኸኛው እንደሚሉት፣ በአዲስ አበባ 6,400 አባላት ያሏቸው 578 ማኅበራት ሲኖሩ፣ በቀጣይ ማኅበራቱን ወደ ሽርክናና ዩኒየን ለማሳደግ እየተሠራ ነው፡፡ ቅድሚያ 20 በመቶ ለሚቆጥቡም መንግሥት 80 በመቶ አበድሮ ቆሻሻን በጋሪ የመግፋት ሥርዓቱን ለመለወጥ ሥራዎች ተጀምረዋል፡፡

ሐሙስ ሐምሌ 27 ቀን 2009 ዓ.ም. የቆሻሻ ማንሻ ሽፍን ተሽከርካሪዎቹ ለማኅበራቱ በተላለፉበት ወቅት እንደተነገረው፣ ተሽከርካሪዎቹ የከተማዋ ነዋሪ ቆሻሻ በየወቅቱ እንደማይነሳ የሚያቀርበውን ቅሬታ ለመፍታት ያስችላሉ፡፡

ተሽከርካሪዎቹ በየአካባቢው እየገቡ ቆሻሻን ከቤት ለቤት ለመሰብሰብ የሚያስችሉ ሲሆን፣ ይህም ኋላቀሩን የቆሻሻ አሰባሰብ ሥርዓት ዘመናዊና ቀልጣፋ ለማድረግ እንደሚያስችል አቶ በረኸኛው ተናግረዋል፡፡

በአሥሩም ክፍለ ከተሞች ለሚገኙና ቅድሚያ 20 በመቶ ለቆጠቡ የፅዳት ማኅበራት የተሰጡት መኪኖች፣ የገንዳ ቆሻሻ የማንሳትና የማጓጓዝ ሥርዓቱን በመቀነስ የተቀናጀ የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ስልትን ለመዘርጋት ያግዛሉም ተብሏል፡፡

በከተማዋ 814 ጊዜያዊ የቆሻሻ ማስቀመጫዎች ያሉ ሲሆን፣ በተደጋጋሚም ቅሬታ ይነሳባቸዋል፡፡ በአንዳንድ ሥፍራዎች ደግሞ ጊዜያዊ ማስቀመጫ ብቻ ሳይሆኑ ቆሻሻ መጣያም ሆነው ይታያሉ፡፡ አቶ በረኸኛው እንደገለጹት፣ ከጊዜያዊ ቆሻሻ ማስቀመጫ ጋር የነበሩትን ችግሮች ለመቅረፍና አሰባሰቡንና አወጋገዱን ሥርዓት ለማስያዝ 814 ጊዜያዊ የቆሻሻ ማስቀመጫዎቹን ወደ 80 ለማውረድ ታቅዷል፡፡

ለፅዳት ማኅበራት የተሰጡ መኪኖች ከየቤቱ የሚሰበሰቡትን ደረቅ ቆሻሻ የሚያደርሱትም፣ ጊዜያዊ ቆሻሻ ማስቀመጫ ሥፍራዎች መሆኑን አክለዋል፡፡