Skip to main content
x
ክቡር ሚኒስትሩ ለመሥሪያ ቤቱ በቅርብ ከተቀጠረ ታዋቂ ኤክስፐርት ጋር እየተነጋገሩ ነው

ክቡር ሚኒስትሩ ለመሥሪያ ቤቱ በቅርብ ከተቀጠረ ታዋቂ ኤክስፐርት ጋር እየተነጋገሩ ነው

[ክቡር ሚኒስትሩ ለመሥሪያ ቤቱ በቅርብ ከተቀጠረ ታዋቂ ኤክስፐርት ጋር እየተነጋገሩ ነው]

 • እንዴት ነው ለመድክ?
 • ክቡር ሚኒስትር. . .
 • ምነው?
 • ኧረ መልመድ አቅቶኛል፡፡
 • ምኑ ነው ያቃተህ?
 • ሰው እኮ እየሠራ አይደለም፡፡
 • እንዴት ነው የማይሠራው?
 • አፍ ለአፍ ገጥሞ ወሬ ነው የያዘው፡፡
 • የምን ወሬ?
 • በተለይ ጠዋት ጠዋት ሥራ የለም ማለት ይቻላል፡፡
 • ከሰዓት በኋላስ?
 • ቁጭ ብሎ ማዛጋት ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ሌላ ምን አጋጠመህ?
 • የአነጋገር ዘይቤው ሊገባኝ አልቻለም፡፡
 • የምን አነጋገር?
 • ክቡር ሚኒስትር የአንዳንዶቹ ንግግር በኮድ የተቆለፈ ይመስላል፡፡
 • ምን እያልክ ነው?
 • አንዱ ይነሳና እንደ አቅጣጫ ይላል፡፡
 • ምን?
 • ሌላው ይመጣና ‹ያለበት ሁኔታ ነው ያለው› ይላል፡፡
 • ምን እያልክ ነው?
 • አንዳንዱ ደግሞ. . .
 • አንዳንዱ ምን?
 • አንዳንዱማ የሚናገረው ምን እንደሆነ አይታወቅም፡፡
 • ለምሳሌ?
 • አንዱን ሪፖርት አቅርብልኝ አልኩት፡፡
 • እሺ?
 • ብጠብቀው ብጠብቀው አያመጣም፡፡
 • ከዚያስ?
 • ለምን አታቀርብም ስለው. . .
 • ምናለ እባክህ?
 • በሒደት ላይ ነው ብሎ ገላመጠኝ፡፡
 • የምን ሒደት ነው?
 • ክቡር ሚኒስትር የእኔም ጥያቄ ይኼው ነበር፡፡
 • ታዲያ ምን ዓይነት መልስ አገኘህ?
 • ‹እየተሳለጠ› ነው የሚል ክቡር ሚኒስትር?
 • መጨረሻው ምን ሆነ ታዲያ?
 • ያልተጀመረ ነገር ምን መጨረሻ አለው ክቡር ሚኒስትር?
 • ታዲያ ምን አሰብክ?
 • ወስኛለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምን ለማድረግ?
 • ሥራዬን ለመልቀቅ ነዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ለምን ብለህ?
 • በገዛ ቋንቋዬ ለምን ባይተዋር እሆናለሁ?
 • ምን አልከኝ?
 • ቻው ክቡር ሚኒስትር!

[ክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸውን ጠሩትና መጣ]

 • ምን እየተደረገ እንዳለ ትነግረኛለህ?
 • ስለምኑ ክቡር ሚኒስትር?
 • በስንት መከራ ያመጣነው ኤክስፐርት ሊለቅ ነው እኮ?
 • ምን ሆንኩኝ አለ ደግሞ?
 • የምንነጋገረው አልገባህም መሰል?
 • ክቡር ሚኒስትር ይንገሩኛ?
 • ከአስፈጻሚዎች ጋር መግባባት አቅቶኛል ነው ያለኝ፡፡
 • ለምን ክቡር ሚኒስትር?
 • የንግግራችን ዘይቤ እንዳልገባው ነው የነገረኝ፡፡
 • እንግዲያው ቁጭ አድርጌ አቅጣጫ እሰጠዋለሁ፡፡
 • አንዱ ባዕድ የሆነበት አቅጣጫ የሚባለው ቃል ነው፡፡
 • በቃ መሥሪያ ቤቱ ያለበትን ሁኔታ በሚገባ አስረዳዋለሁ፡፡
 • ያለበት ሁኔታ ነው ያለው የሚባለው አነጋገር ጠንዝቶበታል፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ታዲያ ለምን አናሳልጥለትም?
 • ምኑን ነው የምናሳልጥለት?
 • በግምገማ መወጠር ነዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምን ልንለው?
 • የነበረበት የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት. . .
 • ምን?
 • እዚህ ሲመጣ እጅና እግሩን እንዳሰረው ነዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እሺ?
 • የፀረ ሰላም ኃይሎች ፕሮፓጋንዳ ተፅዕኖ. . .
 • እሱ ደግሞ ምን ይሆን?
 • ከልማታዊ አስተሳሰብ ጋር እየተጋጨበት ነዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ሌላስ?
 • ሌላው ተሃድሶ ያስፈልገዋል ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • አይ የእኛ አማካሪ?
 • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • እሱ እኮ በቃኝ ብሏል፡፡
 • በቃ ሄደ ማለት ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • አዎን አልኩህ፡፡
 • በቃ ግልግል ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እሱን የመሰለ ኤክስፐርት ከየት ልታመጣልኝ ነው?
 • እናሠለጥናለን ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንዴት አድርገህ እባክህ?
 • እንኳን አንድ ተራ ኤክስፐርት. . .
 • እህ?
 • አልበርት አንስታይንን የሚያስንቁትን እናሠለጥናለን!

[ክቡር ሚኒስትር ለበላይ አካል የሚያቀርቡት ሪፖርት ግራ አጋብቷቸው ከጸሐፊያቸው ጋር እየተነጋገሩ ነው]

 • ይኼንን ሪፖርት ማን ነው የሠራው?
 • ክቡር ሚኒስትር አማካሪዎ ነው፡፡
 • ብፈልገው አጣሁት የት ነው ያለው?
 • የዘመድ ቀብር ብሎ ከከተማ ወጥቷል፡፡
 • ይኼንን ሪፖርት ምን ብዬ ነው የማቀርበው?
 • ምን ሆነ ክቡር ሚኒስትር?
 • ተጫውቶበታል እኮ?
 • ይኼን ያህል ክቡር ሚኒስትር?
 • ከውሸቱ ብዛት መንግሥት የመደበልንን በጀት በእጥፍ አሳድጎታል፡፡
 • ኧረ ክቡር ሚኒስትር?
 • በዘጠኝ ወራት ሠራነው ያለው በዘጠኝ ዓመት እንኳ የሚሞከር አይመስልም፡፡
 • እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
 • በእያንዳንዱ ክንውን ሥር የሰጠው መግለጫማ ያሳፍራል፡፡
 • ምን ብሎ ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • የበላይ አካል በሰጠው አቅጣጫ መሠረት ብሎ ሰምቼው የማላውቀውን ያወራል፡፡
 • ሌላስ ክቡር ሚኒስትር?
 • ልማቱን ለማሳለጥ ስንል ዘጠኝ ወራት ሙሉ ተኝተን አናውቅም የሚለው ነገር ደግሞ ግራ ያጋባል፡፡
 • ወይ ክቡር ሚኒስትር?
 • ምነው?
 • ይኼ ማጋነን አቻ የለውም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምን ይኼ ብቻ?
 • ምን አለ ደግሞ ክቡር ሚኒስትር?
 • በሒደት ላይ ያሉ በማለት የዘረዘራቸውን እንኳን መንግሥት እኔም አላውቃቸውም፡፡
 • ምንድናቸው ክቡር ሚኒስትር?
 • መያዣ መጨበጫ የላቸውም፡፡
 • ምን ይሻላል ክቡር ሚኒስትር?
 • እኔ ምን አውቄ?
 • ኧረ መላ ይበሉ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • መላ ባውቅማ ይጫወትብኝ ነበር?
 • በእርግጥ ልክ ነዎት ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንዴት?
 • እዚህ ቤት የቃላት ጨዋታ እንጂ መቼ ይሠራል?
 • ለምን እንዲህ አልሽ?
 • የአፍ ኮማንዶ ያለው ብቻ አይደል እንዴ የተሰባሰበው?
 • ይኼ ደግሞ ምን ማለት ነው?
 • ለመፈክር ቀድሞ ደራሽ የሆኑ ማለት ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንዲህ ለምን አልሽ?
 • ክቡር ሚኒስትር ያ ኤክስፐርት ምን እንዳለኝ ያውቃሉ?
 • ምናለ እባክሽ?
 • ወሬ ብቻ!

[ክቡር ሚኒስትሩ ኤምባሲ ውስጥ የተዘጋጀ ኮክቴል ላይ ከአንድ የታዋቂ ፓርቲ አመራር ጋር እያወሩ ነው]

 • ሰሞኑን ምነው ድምፅህ ጠፋ?
 • የእኔ ድምፅ የሚሰማው ከወቅታዊ ጉዳይ ጋር ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • አንተ በማኅበራዊ ሚዲያ እንጂ ብዙም እኮ አትሰማም፡፡
 • ዕድሜ ለኢሕአዴግ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • የኢሕአዴግን ስም ካልጠራህ ያቃዥሃል አይደል?
 • እንቅልፍም እኮ በእሱ ፈቃድ መስሎኝ ክቡር ሚኒስትር?
 • ትንሽ ቆይተህ በማንኪያ አጉርሰኝ ልትል ነው መሰል?
 • ‹ወጉ ቀርቶብኝ በቅጡ በኮነነኝ› ሲባል አልሰሙም?
 • ምን ማለት ይሆን?
 • መጉረሱና ማጉረሱ ቀርቶ በሥርዓቱ ማውራት ብንችል ጥሩ ነበር፡፡
 • ማን ከለከላችሁ ታዲያ?
 • ኢሕአዴግ ነዋ ክቡር ሚኒስትር?
 • ምን አድርጎ ክቡር ተቃዋሚ?
 • እስትንፋሳችንን ዘግቶት ነዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንዴት አድርጎ ነው የዘጋው እባክህ?
 • እጃችንን አስሮ፣ አፋችንን ግጥም አድርጎ ዘግቶ ነዋ፡፡
 • ከዚህ ሁሉ ለቅሶ እንደ ሠለጠነ ፓርቲ ለውይይትና ለድርድር መቅረብ አይሻላችሁም?
 • እሱንማ ሞክረን አቃተን እኮ?
 • ከኢሕአዴግ ጋር መነጋገር ነው ያቃታችሁ?
 • በምን ቋንቋ እንግባባ?
 • እንዴት?
 • የእናንተ ንግግር እኮ የተመሰጠረ ነው ክቡርነትዎ፡፡
 • እንዴት ሆኖ ነው የተመሰጠረው?
 • የቃላት ድሪቶዎች ይበዛሉ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • በግልጽ ተናገረው እባክህ?
 • የእናንተን ቃላት ለመረዳት ኮድ ሰባሪ ያስፈልጋል ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ይኼን ያህል አልገባናችሁም እንዴ?
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • የቋንቋ እጥረት አለባችሁ እንዴ?
 • በዚህ እንኳ አንታማም፡፡
 • ችግራችሁ ምንድነው ታዲያ?
 • ችግሩ የእኛ ሳይሆን የእናንተ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምን የሚባል ችግር?
 • ግራ ማጋባት ይባላል!

[ክቡር ሚኒስትሩ ሾፌራቸው ወደ ቤት እየወሰዳቸው ነው]

 • አንተ ቀስ ብለህ ንዳ፡፡
 • ኧረ ቀስ እያልኩ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • መኪናው የፈጠነ መሰለኝ እኮ?
 • ጌጁን ይመልከቱት 30 ላይ ነን ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምነው መንገዱ ተጨናነቀ?
 • መንገዱ እኮ እንዲህ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ነው እንዴ?
 • ከፊታችን ያለውን መኪና ያዩታል ክቡር ሚኒስትር?
 • አዎ ይታየኛል፡፡
 • ዋጋው ስንት እንደሆነ ያውቃሉ ክቡር ሚኒስትር?
 • ስንት ነው እባክህ?
 • ሰባት ሚሊዮን ብር ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምን?
 • ሰባት ሚሊዮን ብር ነው የሚሸጠው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ለመሆኑ ማን ነው የሚሸጠው?
 • መኪና አስመጪዎች ናቸዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • የእዚህ መኪና ባለቤት ማን ነው?
 • ያውቁታል ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ማን ነው እሱ?
 • በአንድ ወቅት ቢሮዎ ሲመላለስ የነበረ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ለምን ነበረ የሚመላለሰው?
 • መሬት፣ የባንክ ብድርና የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ነው ሲመላለስ የነበረው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እስቲ በምልክት አስቁመው፡፡
 • እሺ ክቡር ሚኒስትር፡፡

[ሾፌሩ መኪናውን ካስቆመ በኋላ ጥግ ይዞ ሲቆም ክቡር ሚኒስትሩ ስልክ ደወሉ]

 • አንተ ብለህ ብለህ የሰባት ሚሊዮን ብር መኪና ትነዳለህ?
 • ክቡር ሚኒስትር የት ነው ያሉት?
 • ከኋላህ ቆሜያለሁ፡፡
 • ልምጣ እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
 • እዚያው አርፈህ ተቀመጥ፡፡
 • ምን ልታዘዝ ክቡር ሚኒስትር?
 • ልማታዊ መንግሥታችን ከየት እንዳነሳህ ታውቃለህ አይደል?
 • በሚገባ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እኔ እኮ የማውቅህ መርካቶ ስትቸረችር ነበር፡፡
 • ልክ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • መሬት፣ የባንክ ብድር፣ ከቀረጥ ነፃ፣ የውጭ ምንዛሪ. . . ለምነህ ያሰጠሁህ እኔ ነኝ፡፡
 • በትክክል ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • አንተ ግን ቀብረር ብለህ የሰባት ሚሊዮን ብር መኪና ትነዳለህ፡፡
 • የልማቱ ውጤት ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ይህንን ማመንህ ጥሩ ነው፡፡
 • በሚገባ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • አሁን አቅጣጫ እሰጥሃለሁ፡፡
 • ወዴት እንድሄድ ክቡር ሚኒስትር?
 • የትም አትሄድም፡፡
 • ካልሄድኩ የምን አቅጣጫ ነው ታዲያ?
 • አቅጣጫ ሲባል ኮምፓስ ነው እንዴት የሚታይህ?
 • የአቅጣጫ መጠቆሚያ እሱ አይደል እንዴ?
 • የእኔ አቅጣጫ ግን. . .
 • ምንድነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ትዕዛዝ ነው፡፡
 • ምን የሚባል ክቡር ሚኒስትር?
 • በፍጥነት ታስገባለህ፡፡
 • ምኑን ክቡር ሚኒስትር?
 • ድርሻዬን ነዋ፡፡
 • ታዲያ ዙሪያ ጥምጥም ለምን ሄዱ ክቡር ሚኒስትር?
 • ይልቁንስ ቶሎ አሳልጠው፡፡
 • ማሳለጥ ምንድነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ወደ አካውንቴ ክተተው!