Skip to main content
x
ክቡር ሚኒስትር ከአንድ ባለጉዳይ ጋር ቢሮአቸው ውስጥ እየተነጋገሩ ነው

ክቡር ሚኒስትር ከአንድ ባለጉዳይ ጋር ቢሮአቸው ውስጥ እየተነጋገሩ ነው

[ክቡር ሚኒስትር ከአንድ ባለጉዳይ ጋር ቢሮአቸው ውስጥ እየተነጋገሩ ነው]

  • ለምን ነበር የመጣኸው ወዳጄ?
  • አሳሳቢ ጉዳይ ገጥሞኝ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • እስቲ ንገረኝ፡፡
  • ክቡር ሚኒስትር እርስዎን ለማግኘት እኮ አንድ ዓመት ነው የፈጀብኝ፡፡
  • ለምን እባክህ?
  • ማን አስቀርቦ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ይኼን ያህል?
  • እርስዎን ከማግኘት ኤቨረስት ተራራ መውጣት ይቀላል፡፡
  • ኧረ አታጋን እባክህ?
  • ባጋንን ኖሮ ዓመት ሙሉ እለፋ ነበር ክቡር ሚኒስትር?
  • እሺ ለምን ፈለግከኝ?
  • ክቡር ሚኒስትር ለአገር የሚጠቅም ነገር ነው፡፡
  • ምንድነው እሱ?
  • የውጭ ባለሀብቶች ኢንቨስት ለማድረግ ይፈልጉ ነበር፡፡
  • ታዲያ ማን ከለከላቸው?
  • ማን ያስቀርባቸው ክቡር ሚኒስትር?
  • እንዴት እባክህ?
  • ደላሎች ጣልቃ እየገቡ አስቸገሩ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • የምን ደላላ ነው የምትለው?
  • እንደ እርጎ ዝንብ ጥልቅ እያሉ የሚያስቸግሩ ናቸዋ፡፡
  • ስለምንድነው የምታወራው?
  • የውጭ ኢንቨስተሮች በመከራ ስናመጣ ማስተናገድ አልተቻለም ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • እንዴት ሆኖ?
  • አንዱ ወገን ለኮሚሽን እየተሯሯጠ ጉቦ ይቀባበላል፡፡
  • ሌላውስ?
  • ሌላው ደግሞ ድርሻውን ካላገኘ እንቅፋት ይሆናል፡፡
  • እሺ?
  • አገር በሕጉ መሠረት ማስተናገድ ሲገባት ቢሮክራሲው አላሠራ ይላል፡፡
  • ለዚህ ነው የፈለግከኝ?
  • ሌላም አለ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ምን?
  • ኤሌክትሪክ እየጠፋ ሥራ መሥራት አልተቻለም፡፡
  • እሺ?
  • በዚህ ላይ ለኢንቨስትመንት የማይመች ተግባር ይፈጸማል፡፡
  • ለምሳሌ?
  • ኢንቨስተሮችን ማበሳጨት አንዱ ችግር ነው፡፡
  • አቤቱታ ማቅረብ ይቻላል እኮ?
  • የት ነው የሚቀርበው ክቡር ሚኒስትር?
  • ቅሬታ የሚሰማ አካል ዘንድ፡፡
  • ችግር ሲፈጠር የሚያዳምጥ የለም፡፡
  • ቀጥል፡፡
  • ኢንቨስተሮች እየተማረሩ ነው ሲባል ግድ የማይሰጣቸው ሞልተዋል፡፡
  • ለምን ይሆን?
  • ወይ አለማወቅ ወይ ንቀት እየበዛ ነዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • እኔ ምን ላድርግ ታዲያ?
  • ኃላፊነትዎን ይወጡ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • እንዴት አድርጌ እባክህ?
  • ስብሰባችሁ ላይ ተነጋገሩበት ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • አንተ የምትለውን እንዴት ላምን እችላለሁ?
  • ክቡር ሚኒስትር ዓለም አቀፍ ሚዲያው እያናፈሰው እኮ ነው፡፡
  • ምኑን?
  • የታዋቂውን አፍሪካዊ ኢንቨስተር ኩርፊያ ነዋ?
  • ማነው እሱ?
  • አሊኮ ዳንጎቴ፡፡
  • ምናለ እባክህ?
  • የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንቴን አቆማለሁ ብሏል፡፡
  • አትቀልድ በለው፡፡
  • አይ ክቡር ሚኒስትር?
  • ምነው?
  • ኢንቨስተር ቀልድ እንደማያውቅ አያውቁም እንዴ?
  • ምንድነው የሚያውቀው ታዲያ?
  • መወሰን!

[ክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸውን አስጠርተው እየተነጋገሩ ነው]

  • የሰሞኑን ወሬ ለምን አልነገርከኝም?
  • የቱን?
  • የቢሊየነሩን የሲሚንቶ ፋብሪካ ባለቤት ጉዳይ ነዋ፡፡
  • ክቡር ሚኒስትር አልሰሙም እንዴ?
  • አንተ ካልነገርከኝ እንዴት እሰማለሁ?
  • ሰውየው አምርሯል አሉ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • እኛ በገዛ ሀብታችን ማዘዝ አንችልም ማለት ነው?
  • እንችላለን ክቡር ሚኒስትር፣ ግን. . .
  • ግን ምን?
  • ዙሩን አከረርነው መሰል?
  • የምኑን ዙር?
  • ኢንቨስተር እሽሩሩ ይፈልጋል እኮ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ይኼን የት ነው የተማርከው?
  • አገሮች ለኢንቨስትመንት ምቹ መሆን አለባቸው ይባል የለ እንዴ?
  • እኛ ምን አጠፋን ታዲያ?
  • ሥራቸው እንቅፋት ሲያጋጥመው መደገፍ አቅቶናል ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • እኛ መቼ እንቢ አልን?
  • እንቢ ብላችኋል ተባልን እኮ ክቡር ሚኒስትር?
  • ማን ነው ያለን እባክህ?
  • የውጭ ሚዲያ ላይ እንደዚያ ነው የተባለው ክቡር ሚኒስትር?
  • አንዳንዴ ቆፍጠን ማለት አለብን፡፡
  • በእኛ ጥፋት ኢንቨስተሮች ሲሸሹ ሌሎች አገሮች ይፈነድቃሉ፡፡
  • ምን ለመሆን?
  • ኢንቨስተሮቹን እያግባቡ ጠራርገው ይወስዱብናል ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • እኛም አንድ ነገር ማድረግ አለብን፡፡
  • ምን ክቡር ሚኒስትር?
  • የጥፋት ኃይሎችን ማጋለጥ ነዋ፡፡
  • ክቡር ሚኒስትር?
  • አቤት?
  • ከዚህ በፊት ሌላ ነገር ቢቀድም ይሻላል ክቡር ሚኒስትር፡፡
  •  ምን ይቅደም?
  • የተበላሸውን ማስተካከል ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ምንድነው የተበላሸው አንተ?
  • የአገሪቱ ስም ጎደፈ እኮ ክቡር ሚኒስትር?
  • ምን ተብሎ?
  • ለኢንቨስትመንት የማትመች፡፡
  • ማን ነው ያለው?
  • መቼም እኔ እንዳልሆንኩ ያውቃሉ!

[ክቡር ሚኒስትሩ ተበሳጭተው ጸሐፊያቸውን አስጠሯት]

  • የታለ ያ የማስተባበሪያ ዳይሬክተር ተብዬው?
  • የለም ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • የት ሄደ?
  • ፈቃድ ሞልቶ እረፍት ወጥቷል እኮ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ካለበት በአስቸኳይ አስጠሪው፡፡
  • አገር ውስጥ የለም ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ምን?
  • አሜሪካ ሄዷል ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ምን ሊሠራ ነው የሄደው?
  • ሚስቱ እዚያ ልትወልድ ነው መሰል ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • እሱም ለዚህ በቃ?
  • አይ ክቡር ሚኒስትር?
  • ምነው?
  • እሱ እኮ ንጉሥ ማለት ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • እንዴት እባክሽ?
  • ወዳጀ ብዙ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ማለት?
  • በዚህ በኩል የአገር ውስጥ ባለሀብቶች. . .
  • ምን?
  • በዚያ በኩል የውጭ ኢንቨስተሮች. . .
  • ምንድነው የምትይው?
  • ይወዱታል ማለቴ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • እሱ ምን ስለሆነ?
  • አሪፍ ጉዳይ ገዳይ ነዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ይኼ ደግሞ ምን ማለት ነው?
  • ጉዳያቸውን ያስፈጽምላቸዋል ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • እሱ ተላላኪ የሆነው ከያዘው ኃላፊነት በልጦበት ነው?
  • እንደ ጉድ ብር ያፍስበታል ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • እንዴት ተደርጎ እባክሽ?
  • ስማርት ስለሆነ ነዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ሀብት በሀብት ሆኗል እያልሽኝ ነው?
  • ቢጠሩት የማይሰማ ነዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • እንዴት ሊሆን ቻለ?
  • ሁሉንም ነገር ተቆጣጠረው ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ይኼ ሁሉ ሲደረግ አንቺ የት ነበርሽ?
  • እዚችው ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • እንዴት አልነገርሽኝም?
  • የእሱ ምላስ ጥሬ እየቆላ እኔን ማን ሰምቶኝ ክቡር ሚኒስትር?
  • ከአሜሪካ መቼ ነው የሚመለሰው?
  • አሜሪካ የሄደ ሰው ስለመመለሱ ምን ማረጋገጫ አለ?
  • ማለት?
  • አይመጡም ያልናቸው ከች ይላሉ፡፡
  • ይመጣሉ ያልናቸውስ?
  • መግለጫ ሲሰጡ ይሰማሉ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • የምን መግለጫ?
  • ፀሐዩ መንግሥታችንን እያወገዙ ነዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ልማታዊ መንግሥታችንን ምን ብለው ያወግዛሉ?
  • አገሪቱን ገሃነም አደረጋት እያሉ ነዋ!

[ክቡር ሚኒስትር ለምሣ ቤት ሲደርሱ ባለቤታቸው እየጠበቋቸው ነበር]

  • ዛሬ አሪፍ ምሣ አለ ማለት ነው፡፡
  • ሌላ ጊዜስ?
  • አንቺ ከሌለሽ እኮ አይጣፍጠኝም፡፡
  • እባክህ አትፎግረኝ፡፡
  • ፉገራ ባውቅ መጫወቻ እሆን ነበር?
  • ልክ ነህ የተከበርከው ሚኒስትር፡፡
  • ለምን እንዲህ አልሽ?
  • አንተ በሌላ ነገር ሰው ስታደርቅ ትውላለህ. . .
  • እሺ?
  • ሌሎች በአንተ ከለላ የራሳቸውን ኢምፓየር ይገነባሉ፡፡
  • ለምን እንዲህ አልሽ?
  • የማላውቅ መሰለህ?
  • ምኑን?
  • አንተ ነጋ ጠባ ቴሌቪዥን ላይ ልማት. . . ልማት. . . ትላለህ፡፡
  • ምን ለማለት ፈልገሽ ነው?
  • የምለውማ የሌሎቹን ጥፋት ለመሸፈን ትሯሯጣለህ ነው፡፡
  • ለምሳሌ?
  • ኢንቨስተሮች ተከፍተዋል ሲባል አንተ ታስተባብላለህ፡፡
  • እሺ እባክሽ?
  • አንተ እንደ ቋንጣ የደረቀ ወሬ ስታወራ ሌላው. . .
  • ሌላው ምን?
  • ሌላውማ በቪላ ላይ ቪላ. . .
  • ምን?
  • በቢዝነስ ላይ ቢዝነስ. . .
  • እንዴ?
  • በብር ላይ ብር ይከምራል፡፡
  • ያለ መረጃ አታውሪ እባክሽ?
  • በማስረጃም አስደግፍልሃለሁ፡፡
  • ምኑን?
  • የሀብት ተራራ ስለሠሩት ነዋ፡፡
  • ይኼንን ወሬ ከየት ነው የምትለቃቅሚው?
  • ዓይንህን ከፈት ብታደርግ ታየው ነበር፡፡
  • ዓይኔ ተጨፍኗል ማለት ነው?
  • ተጨፈነ ከማለት ይልቅ. . .
  • እህ?
  • ተደፍኗል ቢባል ይሻላል፡፡
  • አልገባኝም?
  • እስኪ የበታቾችህንና ዙሪያህ ያሉትን እያቸው፡፡
  • ምን ሆኑ?
  • ሠሩት፡፡
  • ምኑን ነው የሠሩት?
  • ሲስተሙን በሚመቻቸው መንገድ ተጠቀሙበት፡፡
  • እንዴት አድርገው?
  • እየፐወዙት ነዋ፡፡
  • ኧረ እባክሽ አልገባኝም?
  • ይቀጠርልሃል፡፡
  • ምንድነው የሚቀጠርልኝ?
  • አስተርጓሚ!