አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!
አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!

ክቡር ሚንስተር

 

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚስታቸው ጋር እያወሩ ነው]

 • ምነው ተከዝሽ?
 • ብዙ ነገር ያሳስበኛል፡፡
 • ምን ያሳስብሻል?
 • የወደፊት ሕይወታችን፡፡
 • የወደፊት ሕይወታችን ምን ሆነ?
 • መቼ ይገባሃል አንተ?
 • ማለት?
 • ቤት እንኳን መቼ አለን?
 • ይኼኛው ቤትስ?
 • አይ አንተ?
 • ምነው?
 • ቤቱ እኮ የመንግሥት ነው፡፡
 • ቢሆንስ እየኖርንበት አይደለ እንዴ?
 • ዕድሜ ልክህን ሥልጣን ላይ የምትቆይ ይመስልሃል?
 • የሰማሽው ነገር አለ እንዴ?
 • ምን?
 • ከሥልጣን ልነሳ ነው እንዴ?
 • ኧረ የሰይጣን ጆሮ ይደፈን፡፡
 • ታዲያ ምንድን ነው የምታወሪው?
 • ስለወደፊቱ ዕጣ ፈንታ ከአሁኑ ማሰብ አለብህ፡፡
 • እና ምን ይደረግ እያልሽ ነው?
 • ከአንድ ሰው ጋር ሳወራ ነበር፡፡
 • እሺ፡፡
 • እነዚህ የ40/60 ቤቶች በጣም አሪፍ ናቸው አሉ፡፡
 • እሱማ እኔም ሰምቻለሁ፡፡
 • ታዲያ እነሱ ቤቶች እንዴት ናቸው?
 • ምን እያልሽ ነው?
 • የምለውማ ገብቶሃል፡፡
 • ሴትዮ ጤነኛ ነሽ ግን?
 • በሚገባ እንጂ፡፡
 • እነሱ እኮ የሕዝብ ናቸው፡፡
 • አይ አንተ?
 • ስሚ ሕዝብ ቆጥቦ እኮ ነው የተሠሩት፡፡
 • ቢሆንም እኔ ወሬ ሰምቻለሁ፡፡
 • የምን ወሬ?
 • የተዘጋጁት ለማን እንደሆነ፡፡
 • ለማን ነው?
 • ለባለሥልጣናት!

[ክቡር ሚኒስትሩ አንድ ወዳጃቸው ሚኒስትር ጋ ደወሉ] 

 • ሄሎ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንዴት ነህ ወዳጄ?
 • ሰላም ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ቢዚ እንደሆንክ አውቃለሁ፣ አንድ ነገር ልጠይቅህ ነበር፡፡
 • ምን ክቡር ሚኒስትር?
 • እነዚህ 40/60 ቤቶች እንዴት ናቸው?
 • ያው በጥሩ ሁኔታ እየተሠሩ ነው፡፡
 • እሱማ አውቃለሁ ግን…
 • ግን ምን ክቡር ሚኒስትር?
 • ቤቶቹን እንዴት ማግኘት ይቻላል?
 • ተመዝግበዋል እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
 • ኧረ በፍጹም፡፡
 • እና ቤቶቹን ወደዷቸው?
 • በጣም ነው የወደድኳቸው፡፡
 • ዋናው እንኳን እርስዎ ወደዷቸው፡፡
 • ማግኘት እችላለሁ እንዴ?
 • እንዴታ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • የተሠሩት ለሕዝቡ መስሎኝ?
 • የተሠሩትማ…
 • እ…
 • ለእኛው ነው!

[የክቡር ሚኒስትሩ የቅርብ ዘመድ ደወለላቸው] 

 • ሄሎ ጋሼ፡፡
 • እሺ እንዴት ነህ?
 • ኧረ ችግር ውስጥ ነኝ ጋሼ፡፡
 • የምን ችግር ደግሞ?
 • ትንሽ ከመንግሥት ጋር እየተጋጨሁ ነው፡፡
 • ተቃዋሚ ሆንኩ እንዳትለኝ?
 • እንደሱ አይደለም ጋሼ፡፡
 • ታዲያ ምን ተፈጠረ?
 • በታክስ ጉዳይ ነው፡፡
 • ታክስ አትከፍልም እንዴ?
 • ኧረ እኔ እከፍላለሁ፡፡
 • በታክስ እኔ ቀልድ እንደማላውቅ ታውቃለህ?
 • አውቃለሁ ጋሼ፡፡
 • ታዲያ ምንድን ነው?
 • አንድ ከገጠር ያመጣሁት ዘመዳችን ነበር፡፡
 • እሺ ምን ሆነ?
 • ለእሱ የከፈትኩለት ሱቅ ነበር፡፡
 • እሺ፡፡
 • እኔ ሳላውቅ ለካ ለዓመታት ታክስ ከፍሎ አያውቅም፡፡
 • ታዲያ አንተ ምን አገባህ?
 • ሱቁ በእኔ ስም ነው ያለው፡፡
 • ወይ ጣጣ፡፡
 • አሁን ዓቃቤ ሕግ ነገሩን እያከረረው ነው፡፡
 • እና ምን አድርግ ነው የምትለኝ?
 • አንተ ሚኒስትር አይደለህ እንዴ ጋሼ?
 • ታዲያ ብሆንስ?
 • ክሱን አስቋርጠው፡፡
 • እስቲ ለማንኛውም የዳኛውን ስምና ቁጥር ቴክስት አድርግልኝ፡፡
 • እሺ ጋሼ፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ ዳኛው ጋ ደወሉ] 

 • ሄሎ፡፡
 • እንዴት ነህ ክቡር ዳኛ?
 • ማን ልበል?
 • ክቡር ሚኒስትር ነኝ፡፡
 • እንዴት ነዎት ክቡር ሚኒስትር?
 • ሰላም ነኝ፡፡
 • ምን ልርዳዎት?
 • አንድ ዘመዴ አንተ ጋ ኬዝ ነበረው፡፡
 • የምን ኬዝ?
 • ትናንትና በታክስ ጉዳይ ፍርድ ቤት የነበረው ኬዝ፡፡
 • እ… አወቅኩት ሰውዬውን፡፡
 • ስለእሱ ጉዳይ ለማውራት ነበር፡፡
 • ያውሩኛ ምን ችግር አለው?
 • በስልክ ጥሩ ስላልሆነ በአካል ተገናኝተን ብናወራስ?
 • ክቡር ሚኒስትር ሥራ ስለሚበዛብኝ ከቻሉ የሚፈልጉትን በስልክ ይንገሩኝ፡፡
 • ሰውዬው ጥፋተኛ አይደለም፡፡
 • እሱማ በፍርድ ቤት የሚታይ ጉዳይ ነው፡፡
 • አይገባህም እንዴ አንተ?
 • ስልኩን ልዘጋው ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • በጣም ተናንቀናል ማለት ነው፡፡
 • ምን አሉኝ?
 • የምነግርህን አትሰማም እንዴ?
 • ክቡር ሚኒስትር ፍርድ ቤቱ በትዕዛዝ አይደለም የሚሠራው፡፡
 • እና በምንድን ነው የሚሠራው?
 • እንዴት እንደሚሠራ ለማወቅ ሕገ መንግሥቱን ቢያነቡት ጥሩ ነው፡፡
 • እና ትዕዛዙን አትቀበልም?
 • ለመሆኑ ሰሞኑን ሚዲያ ተከታትለዋል?
 • በምን ጉዳይ ላይ?
 • አሜሪካ ስለተፈጸመው ጉዳይ፡፡
 • ምን ተፈጸመ?
 • ፕሬዚዳንቱ አንድ ትዕዛዝ አውጥተው ነበር፡፡
 • እሺ፡፡
 • ከዛ በኋላ ግን የፕሬዚዳንቱን ትዕዛዝ ፍርድ ቤት ሻረው፡፡
 • ምን እያልከኝ ነው?
 • ልልዎት የፈለኩትማ ፍርድ ቤትን ማንም አያዘውም ነው፡፡
 • ማሞ ሌላ መታወቂያው ሌላ አሉ፡፡
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • አሜሪካ ሌላ…
 • እ…
 • ኢትዮጵያ ሌላ!

[ክቡር ሚኒስትሩ ከአማካሪያቸው ጋር እያወሩ ነው] 

 • ስማ ይኼ ትራምፕ የሚባለውን ሰውዬ እየተከታተልከው ነው?
 • በሚገባ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ያወጣውን መመርያ ሰምተሃል አይደል?
 • ትራቭል ባኑን ነው?
 • ታዲያስ?
 • እሱ እኮ እኛን አይመለከትም፡፡
 • እንዴት አይመለከትም?
 • ለሰባት አገሮች ነው እኮ የወጣው፡፡
 • እኔ እሱን አይደለም የምልህ፡፡
 • ታዲያ ምን እያሉኝ ነው?
 • እዛ ያሉ ኢትዮጵያውያንን ጠራርጎ ሊልካቸው ነው፡፡
 • ማለት?
 • በቃ ይኼ ዶክመንት የሌለው ሁሉ መጠረዙ አይቀርም፡፡
 • ኧረ እንደዛ የሚባል ነገር የለም፡፡
 • ሰውዬው ሕገወጥ ስደተኛን አባርራለሁ ብሏል፡፡
 • ቢሆንም due process የሚባል ነገር አለ፡፡
 • ምንድን ነው እሱ?
 • አሜሪካ ምድር የረገጠ ሰው ዝም ብሎ አይባረርም፡፡
 • እንዴት አይባረርም?
 • ኬዙ በፍርድ ቤት ተይዞ እስከ አሥር ዓመት ሊቆይ ይችላል፡፡
 • ሰውዬው ለምን እንደተመረጠ ታውቃለህ?
 • ለምንድን ነው?
 • የማስፈጸም ብቃቱ ፈጣን በመሆኑ ነው፡፡
 • ምን እያሉ ነው ታዲያ?
 • አዲስ ስትራቴጂ ነው የሚጠቀመው፡፡
 • ምን ዓይነት ስትራቴጂ?
 • Fast due process የሚሉት፡፡
 • ስለ due process አላውቅም ብለውኝ አልነበር እንዴ?
 • የምትለውን ልስማ ብዬ ነው እንጂ በደንብ ነው ጠንቅቄ የማውቀው፡፡
 • እኔ ግን አሁን ስለሚሉት ነገር ሰምቼም አላውቅም፡፡
 • አታነብማ ችግሩ እሱ ነው፡፡
 • ብለው ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ለማንኛውም አሁን መዘጋጀት አለብን፡፡
 • ለምኑ ነው የምንዘጋጀው?
 • አሁን የመንግሥትን ልማት ሲያንቋሽሹ የነበሩ ጠላቶቻችን መምጫቸው ቀርቧል፡፡
 • እ…
 • በቃ በየጊዜው ባለሥልጣናትን ሲያዋርዱ የነበሩ ጉዳቸው ነው፡፡
 • አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር?
 • ስማ ያ ሰውዬ ጠርዞ ሲልካቸው እዚህ በሚገባ እንቀበላቸዋለን፡፡
 • ሰሞኑን ግን መንግሥት መግለጫ አውጥቷል፡፡
 • ምን የሚል?
 • እዛ ያሉ ኢትዮጵያውያን መንግሥትን የሚቃወሙት ለግሪን ካርድ ስለሆነ ወደ አገራቸው ተመልሰው በልማት ላይ መሳተፍ ይችላሉ ብሏል፡፡
 • እሱማ የሚሰማሩት ልማት ላይ ነው፡፡
 • ታዲያ እርስዎ ምን እያሉ ነው?
 • ጥያቄው የሚያለሙት ምንድን ነው የሚለው ነው?
 • ምንድን ነው የሚያለሙት ታዲያ?
 • ቂሊንጦን!