ክቡር ሚንስተር

[ክቡር ሚኒስትሩ በጠዋት ከቤት ሊወጡ ሲሉ ሚስታቸው ቁርስ እየበሉ አገኟቸው]

 • ቁርስ አትበላም እንዴ?
 • ኧረ እበላለሁ፡፡
 • በል ቤት ያፈራውን አፍህ ላይ ጣል አድርግ፡፡
 • ቁርስ ይኼ ነው እንዴ?
 • ምነው?
 • ደረቅ ዳቦና የገበታ ቅቤ?
 • እና ምን ጠብቀህ ነበር?
 • እኔማ ስምንት ዘጠኝ ዓይነት ነዋ፡፡
 • ያደለውማ ይጾማል፡፡
 • ከሃይማኖት ጋር አታነካኪኝ፡፡
 • እና ስምንት ዘጠኝ ዓይነት ነበር የጠበቅከው?
 • እህሳ?
 • አንተ ግን ትንሽ አታፍርም?
 • ለምንድን ነው የማፍረው?
 • አገሪቷ ውስጥ ምን እንዳለ ራሱ ረስተኸዋል አይደል?
 • አገሪቷ ውስጥማ ከፍተኛ ዕድገት እንዳለ አውቃለሁ፡፡
 • እ…
 • ለዚህ እኮ የእኛም የቁርስ ዓይነት በከፍተኛ ደረጃ ማደግ አለበት የምለው?
 • እና እንቁላል አማረህ?
 • ምን እሱ ብቻ?
 • ከጎኑ ቅንጬም ይደረግበት?
 • በትክክል፡፡
 • ጥብስ ነገርም ይኑረው?
 • የፈረንጅም ቢኖር አሪፍ ነው፡፡
 • ስለዚህ ፓንኬክም ይደረግበታ?
 • ፍሬንች ቶስትም ቢኖር አይከፋም፡፡
 • እኔ የምልህ አገሪቷ ውስጥ ከአምስት ሚሊዮን በላይ ሕዝብ መራቡን ዘነጋኸው እንዴ?
 • ረሃቡ ከእኔ ቁርስ ጋር ምን አገናኘው?
 • የአንተ ቁርስ ከአገሪቷ ዕድገት ጋር ነው የሚገናኘው?
 • ስሚ ቀኑን ሙሉ ከስንት ባለሀብት ጋር መሰለሽ የምገናኘው፡፡
 • ብትገናኝስ ታዲያ?
 • በቃ ሲያገሱ ራሱ የጠጡት ጁስ ይሸተኛል፡፡
 • እና ጁስም አማረህ?
 • ምን አለበት?
 • የኑሮ ውድነቱን ረሳኸው እንዴ?
 • ማለት?
 • ኑሮ በጣም ተወዷል፡፡
 • ቢወደድስ?
 • ይኸው የልጆች ትምህርት ቤት ራሱ ሊጨመር ነው፡፡
 • ባለፈው ዓመት አይደል እንዴ 30 ፐርሰንት የጨመሩት?
 • ይኸው ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮም ስለሚጨምሩ ስብሰባ ጠርተውኛል፡፡
 • እነሱ ምነው አበዙት?
 • እና ሰውዬ ከየት መጥቶ ነው የጠየቅከው ነገር የሚደረገው?
 • ለነገሩ እኔም እጨምራለሁ፡፡
 • ደመወዝተኛ መሆንህን ረሳኸው?
 • ደመወዜን አይደለም የምጨምረው፡፡
 • ታዲያ ሌላ ምን ልትጨምር ነው?
 • ኮሚሽኔን፡፡
 • ገቢህን ከጨመርክ ለእኔ ችግር የለውም፡፡
 • ስሚ እኔ ልክ እንደ መንግሥት ጥልቅ ተሃድሶው ውስጥ ነኝ፡፡
 • የምን ጥልቅ ተሃድስ ነው?
 • በቃ በራሴ ላይ አብዮት ላስነሶ ነው፡፡
 • የምን አብዮት?
 • የኢኮኖሚ!

[ክቡር ሚኒስትሩ ቢሮ ሲገቡ አማካሪያቸው ገባ]

 • ደህና አደሩ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እሺ ምን አለ?
 • በጣም ብዙ ነገር አለ፡፡
 • እኮ ምን?
 • ያው በዚህ ዓመት የምንጀምረው ፕሮጀክት አለ፡፡
 • አውቃለሁ፡፡
 • ስለዚህ ፕሮጀክቱን በአስቸኳይ መጀመር አለብን፡፡
 • ይጀመራ፡፡
 • አዎ ግን የፕሮጀክቱን ፕላን ማፅደቅ ይጠበቅብዎታል፡፡
 • ይፅደቃ፡፡
 • እኮ እንዲያነቡት ሰጥቼዎት ነበር፡፡
 • ለእኔ?
 • አዎን ሁለት ሳምንት አለፈው እኮ፡፡
 • በቃ አፅድቄዋለሁ፡፡
 • ሳያነቡት?
 • እሱን ማንበቢያ ጊዜ የለኝም፡፡
 • ይኼማ እንዴት ይሆናል ክቡር ሚኒስትር?
 • እያዘዝከኝ ነው እንዴ?
 • ኧረ በፍጹም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እና ምን እያልክ ነው?
 • በኋላ ላይ ተጠያቂነት ስለሚያስከትል፣ ቢያነቡት መልካም ነው፡፡
 • ማን ነው የሚጠይቀኝ?
 • ሌላው ቢቀር ህሊና መጠየቁ አይቀርም ብዬ ነው?
 • እሱንማ እያደነዘዝኩት ነው፡፡
 • በምን?
 • በገንዘብ ነዋ፡፡
 • ከድንዛዜው የነቃ ቀን ግን ጉድዎት ነው፡፡
 • ያልተጠየከውን አታውራ፡፡
 • ለማንኛውም ዛሬ እንግዶች ይመጣሉ፡፡
 • የምን እንግዳ?
 • ባለጉዳዮች ናቸው፡፡
 • ያለቀጠሮ?
 • ኧረ ቀጠሮ ከያዙ ወር ሆኗቸዋል፡፡
 • ስማ እኔ በስብሰባ ጊዜዬን አላጠፋም፡፡
 • ባለጉዳዮች እኮ ናቸው፡፡
 • እኔ ሌላ ጉዳይ አለኝ፡፡
 • የምን ጉዳይ?
 • በራሴ ላይ ጥልቅ ተሃድሶ እያካሄድኩ ነው፡፡
 • እንደዚያማ ከሆነ ባለጉዳዮቹን ማናገር እኮ የተሃድሶ አካል መሆን አለበት፡፡
 • በእኔ ተሃድሶ ውስጥ ባለጉዳይን ማናገር አልተካተተም፡፡
 • ታዲያ ምንድን ነው የተካተተው?
 • ባለሀብትን ማናገር፡፡
 • ምን?
 • ለመሆኑ ደመወዝህ ይበቃሃል?
 • ከየት መጥቶ ክቡር ሚኒስትር?
 • የኑሮ ውድነቱ ምንም አይሰማህም ታዲያ?
 • እሱማ ከአቅሜ በላይ ሆኗል፡፡
 • ስለዚህ ጊዜው አሁን ነው፡፡
 • የምኑ?
 • ራሳችን ላይ አብዮት የማስነሳቱ፡፡
 • የምን አብዮት?
 • የኢኮኖሚ!

[ክቡር ሚኒስትሩ አንድ ዳያስፖራ ወዳጃቸው ጋ ደወሉ]

 • ሄሎ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንዴት ነህ ወዳጄ?
 • አለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ስማ ምርር ብሎኝ እኮ ነው የምደውልልህ?
 • ምነው? ምነው?
 • ኧረ ኑሮ ውድነቱን አልቻልነውም፡፡
 • እ…
 • ይኸው ሁሉ ነገር ይጨምራል፡፡
 • መንግሥት ግን ምንድን ነው የሚያደርገው?
 • እኔንም ግርም የሚለኝ እርሱ ነው፡፡
 • እ…
 • በቃ አንድ ነገር ከወጣ ተመልሶ አይወርድም፡፡
 • እሱማ ከእናንተ ተምሮ ነው፡፡
 • ማለት?
 • ያው እናንተም ሥልጣን ላይ ወጥታችሁ አልወርድ ብላችኋል እኮ?
 • እኛንም ያስተማሩን እነሱ ናቸው፡፡
 • እነማን?
 • ነጋዴዎቹ፡፡
 • እ…
 • አንዴ የዕቃውን ዋጋ ይሰቅሉታል፣ ከዚያ አያወርዱትም፡፡
 • በቃ አንዱ አንዱ ላይ እያላከከ ግን እስከ መቼ እንዘልቀዋለን?
 • ስማ እሱን ተወውና የደወልኩበትን ጉዳይ ልንገርህ፡፡
 • እሺ ይንገሩኝ፡፡
 • እኔ ለኑሮ ውድነቱ መፍትሔ አግኝቻለሁ፡፡
 • ምን ዓይነት?
 • ወጪያችን ስለጨመረ፣ ገቢያችንንም መጨመር አለብን፡፡
 • እንዴት አድርገን?
 • ለምን ሐዋላ አንጀምርም?
 • ሐዋላ ሲሉኝ?
 • ይኸውልህ ነጋዴው በኤልሲ ችግር ተሰቃይቷል፡፡
 • እሺ፡፡
 • ስለዚህ አንተ እዚያ በዶላር ገንዘብ ትሰጣቸዋለህ፣ እኔ እዚህ በብር እቀበላለሁ፡፡
 • ይኼ ምን ይጠቅመኛል?
 • ምንዛሪው በብላክ ነዋ፡፡
 • የጥቁር ገበያ እንጀምር እያሉኝ ነው?
 • ስማ ራሴ ላይ ከፍተኛ አብዮት አስነስቻለሁ፡፡
 • የምን አብዮት?
 • የኢኮኖሚ!

[ክቡር ሚኒስትሩ አንድ ባለሀብት ጋር ደወሉ]

 • ከየት ተገኙ ዛሬ ክቡር ማኒስትር?
 • እኔ እኮ ሁሌም እፈልግሃለሁ፡፡
 • ኧረ በተደጋጋሚ ደውዬ ነበር ግን አያነሱም?
 • ምን የእኔ ነገር ስብሰባ ሆኜ ይሆናላ?
 • እሱን እንኳን አውቃለሁ፡፡
 • ዛሬ ግን አንድ ሐሳብ ይዤ ነው የመጣሁት፡፡
 • ምን ዓይነት ሐሳብ?
 • አንድ ላይ እንድንሠራ፡፡
 • ምን ክቡር ሚኒስትር?
 • ቢዝነስ ነዋ፡፡
 • ይኼማ ስጠብቀው የነበረው አጋጣሚ ነው፡፡
 • እንዴት?
 • ያው እኔ ሪል ስቴት እንዳለኝ ያውቃሉ?
 • በሚገባ፡፡
 • አሁን በርካታ መሬት እፈልጋለሁ፡፡
 • እሱንማ እኔ አቀርብልሃለሁ፡፡
 • ኪኪኪ…
 • ምን ያስቅሃል?
 • መሬት አቀርብልሃለሁ ሲሉኝ ነዋ፡፡
 • እውነቴን ነው፡፡
 • በቃ መሬት ካሰጡኝ እኔ ለግንባታው አሽዋ፣ ጠጠር፣ ሲሚንቶና ሌሎችም ግብዓቶች ስለሚያስፈልጉኝ እርስዎ ሊያቀርቡልኝ ይችላሉ፡፡
 • እሱን ነው የምልህ እኮ፡፡
 • ያሉዎትን ማሽነሪዎችም ልከራያቸው እችላለሁ፡፡
 • በቃ እንጠቃቀማለን ስልህ?
 • ለጀመርኩት ሆቴልም የፊኒሺንግ ዕቃ ለማስገባት ኤልሲ ያስፈቅዱልኝ?
 • ምንም ችግር የለም፡፡
 • ያው ዕቃዎቹ ከቀረጥ ነፃ ስለሚገቡ እዚህ በደንብ ያዋጡናል፡፡
 • አንተ በቃ የገባህ ሰው ነህ፡፡
 • እኔ የምልዎት ክቡር ሚኒስትር…
 • እ…
 • ከእኔ ጋር ለመሥራት ምን አነሳሳዎት?
 • በቃ በራሴ ላይ አብዮት ማቀጣጠል እንዳለብኝ ወስኛለሁ፡፡
 • የምን አብዮት ነው?
 • የኢኮኖሚ አብዮት!