ክቡር ሚኒስትሩ የኮክቴል ግብዣ ላይ አንድ የምዕራብ አገር ዲፕሎማት እያነጋራቸው ነው
[ክቡር ሚኒስትሩ የኮክቴል ግብዣ ላይ አንድ የምዕራብ አገር ዲፕሎማት እያነጋራቸው ነው]
- ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እንደምን አለህ ሚስተር ዲፕሎማት፡፡
- ክቡር ሚኒስትር አዲሱ ሹመት ተስማማዎት?
- አገሬን ለማገልገል ሁሌም ዝግጁ ስለሆንኩ ችግር የለም፡፡
- አገር ሲሉ አንድ ነገር ትዝ አለኝ፡፡
- ምን ይሆን?
- ለመሆኑ የአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት እንዴት ነው?
- እንደምታየው ነዋ፡፡
- የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በዚሁ መቀጠሉ ነው?
- በእሱ እኮ ነው ሰላምና መረጋጋት የተፈጠረው፡፡
- በአዋጁ ብቻ መቀጠል አለባችሁ እንዴ?
- እንግዲህ ሁኔታው ይወስነዋል፡፡
- ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ከመፍጠር አኳያስ?
- መጀመሪያ እሳት ይጠፋል፣ ከዚያ ለቀሪው ይታሰባል፡፡
- በነገራችን ላይ ክቡር ሚኒስትር. . .
- አቤት?
- የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሪፖርትን እንዴት አገኙት?
- አንተን ልጠይቅህ እንጂ?
- እኔማ በገለልተኛ አካል ተጣርቶ ቢቀርብ ተመራጭ ነበር እላለሁ፡፡
- ኮሚሽኑም እኮ በነፃነት ነው የሠራው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ከመንግሥት በጀት እየተመደበለት እንዴት ነፃ ይሆናል?
- የእናተን አናውቅም እንዴ?
- ምኑን?
- ሪፖርት የሚያቀርቡ እነ ምናምን ዎች ማን ነው ጃስ የሚላቸው?
- ቢያንስ እኛ ሲስተም ዘርግተናል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ሲስተማቲክ ብትለው ይሻላል እባክህ፡፡
- ምን ለማለት ነው ክቡር ሚኒስትር?
- የዘረጋችሁት ሲስተም መሰሪና ሴረኛ መሆኑን ስለማውቅ ነዋ፡፡
- ተጠያቂነትና ኃላፊነት አለብን እኮ?
- አትቀልድ እባክህ፡፡
- እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
- እናንተ እኮ የምትናገሩትና የምትሠሩት የተለያየ ነው፡፡
- አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር?
- ዴሞክራሲ ትላላችሁ፣ ከለየላቸው አምባገነኖች ጋር ዋንጫ ታነሳላችሁ፡፡
- እንዴ?
- እኛን በሰብዓዊ መብት ጥሰትና በዴሞክራሲ ዕጦት እየከሰሳችሁ የለየላቸውን ታሞካሻላችሁ፡፡
- ለምሳሌ?
- ስም አልጠራም ታውቃለህ ክቡር ዲፕሎማት፡፡
- ኢትዮጵያ እኮ በሰላምና በፀጥታ ጉዳዮች የምዕራባውያን ስትራቴጂካዊ አጋር ናት፡፡
- ይኼማ ግልጽ ነው፡፡
- በሰላም ማስከበርም ትልቅ ተሳትፎ አላት፡፡
- ዓለም ያውቀዋል፡፡
- በአገር ውስጥ ግን ተቃዋሚዎችን አትታገሱም፡፡
- ልዩነታችን እኮ እዚህ ላይ ነው፡፡
- ችግሩን ማሻሻል ለምን ያቅታል ክቡር ሚኒስትር?
- የዕይታ ችግር አለባችሁ፡፡
- እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
- ማየትና መስማት የምትወዱት ኔጌቲቭ ነገሮችን ነው፡፡
- ኧረ ፖዘቲቭ ነገሮችን እናያለን ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ታዲያ ለምን ትነዘንዘኛለህ?
- የሚያሳዝኑ ነገሮች ስለሚበዙ ነዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ዕይታህን አስተካክል፡፡
- በምን ላስተካክል?
- አሪፍ መነጽር ያስፈልግሃል ክቡር ዲፕሎማት፡፡
- ምን ዓይነት መነጽር?
- ካስፈለገህ ሜድ ኢን ቻይና!
[ክቡር ሚኒስትሩ ቢሮአቸው ውስጥ ከአማካሪያቸው ጋር እየተነጋገሩ ነው]
- የዓለም ወቅታዊ ሁኔታ ምን ይመስላል?
- ክቡር ሚኒስትር በጣም ያሳስባል፡፡
- ምኑ ነው የሚያሳስበው?
- ይኼው አሜሪካና ሰሜን ኮሪያ ተፋጠዋል፡፡
- ምን እንሁን ነው የሚሉት?
- አሜሪካ ሶሪያን በክሩዝ ሚሳይል ከደበደበች በኋላ ነዋ ክቡር ሚኒስትር?
- ሁለቱን ምን አፋጠጣቸው ታዲያ?
- ክሩዝ ሚሳይሎቹን የተኮሱት የአሜሪካ የጦር መርከቦች ወደ ኮሪያ ልሳነ ምድር እንዲያመሩ በመደረጉ ነው፡፡
- ማን ነው ይኼንን የሚያደርገው?
- ፕሬዚዳንቱ ናቸው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ትራምፕ?
- አዎ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እነዚህ ሰዎች በእሳት እንደሚጫወቱ አይገባቸውም?
- ይኼ የተለመደ የመንግሥታት ችግር ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምን ማለት ነው?
- አይሰሙም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምንድነው የማይሰሙት?
- ሲመከሩ ነዋ፡፡
- ምንድነው የሚመከሩት?
- አሁን እኔ የእርስዎ አማካሪ ነኝ፡፡
- እሺ እባክህ?
- ብዙ ነገሮችን ሳማክርዎት መቼ ይሰሙኛል?
- ለምሳሌ?
- ሲወስኑ በተጨባጭ ሁኔታዎች ላይ ይመሥረቱ ስል አይሰሙኝም፡፡
- ሌላስ?
- ፍሌክሰብል ይሁኑ ስል አይሰሙኝም፡፡
- ምን ማለት ነው?
- ግትርነት ያበዛሉ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ግትር ለምን እንደምሆን ታውቃለህ?
- አላውቅም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምክሮችህ ልፍስፍስ ስለሆኑ፡፡
- እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
- መለሳለስ ትወዳለህ፡፡
- የሚጠቅም ከሆነ መለሳለስ እኮ ጥሩ ነው፡፡
- እኔ ደግሞ ኮስተር ያለ ውሳኔ ያስደስተኛል፡፡
- ሕዝብ እኮ ኮስተር ሲባልበት አይወድም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምግቡ በርበሬ መጠጡ አረቄ በሆነበት አገር ውስጥ?
- ኧረ የማይገናኝ ነገር አይናገሩ ክቡር ሚኒስትር?
- ችግርህ ምን እንደሆነ ታውቃለህ?
- ምንድነው ክቡር ሚኒስትር?
- ትፈራለህ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ሕዝብ እኮ እንዲህ ዓይነቱን ዘራፍ አይወድም፡፡
- አንተ አልክ፡፡
- እስቲ ወጣ ብለው ሕዝብን ያዳምጡ?
- አንተ ችግር አለብህ ፡፡
- እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
- የእኔ ኃላፊነት እኮ እየዞሩ ወሬ መቃረም አይደለም፡፡
- ታዲያ ምንድነው ክቡር ሚኒስትር?
- ሠርቶ ማሠራት ነው ይግባህ፡፡
- ግልጽ አልሆነልኝም ክቡር ሚኒስትር?
- በቃ ሥራህን መቀየር አለብህ፡፡
- ምን ለመሆን?
- በደብዳቤ ይገለጽልሃል፡፡
- የት ሊመድቡኝ ነው ክቡር ሚኒስትር?
- መዝገብ ቤት!
[ክቡር ሚኒስትሩ ለቅሶ ለመድረስ ሄደው ከአንድ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር ጋር ወሬ ይዘዋል]
- ከፓርቲዎች ድርድር ዘላችሁ ወጣችሁ አይደል?
- እናንተም የምትፈልጉት ይህንን ነው፡፡
- እኛ ደግሞ ምን አደረግን?
- ኢሕአዴግ መደራደር ያለበት እኮ ከታዋቂ ተቃዋሚ ጋር ነው፡፡
- ማን ነው ደግሞ ደረጃ የሚያወጣው?
- እኛ ባለን ተደማጭነት፣ በደጋፊ ብዛትና በሪከርዳችን የተሻልን ነን፡፡
- ‹የአይጥ ምስክሯ ድንቢጥ› እንዳትባሉ ብቻ፡፡
- እናንተ ደግሞ ከአነስተኛና ጥቃቅን ጋር መቀጠል ትችላላችሁ የተከበሩ ሚኒስትር፡፡
- እኔ እኮ የማይገባኝ . . .
- ምንድነው የተከበሩ?
- እናንተ ዕድሜ ልካችሁን እንዳጭበረበራችሁ ልትኖሩ ነው?
- በማጭበርበርማ አንታማም፡፡
- ማን ይታማላችሁ ታዲያ?
- መቼም የምርጫ ኮሮጆ ስንገለብጥ አንታወቅም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እናንተ?
- አዎ እኛ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እናንተ እኮ. . .
- እኛ ምን?
- ምን ይተርፋችኋል?
- እስቲ ይናገሩ?
- በዳያስፖራ የመዋጮ ገንዘብ ትባሉ የለ?
- ይህቺ የጅምላ ፍረጃ ትባላለች የተከበሩ፡፡
- አንዴ ግንባር፣ ውህደት፣ ጥምረት. . . እያላችሁ የምትባሉት በምንድነው ታዲያ?
- ይህቺ ይህቺማ የማን ሥራ እንደሆነች ይታወቃል፡፡
- እንዴት እባክህ?
- እያሰረጋችሁ እያስገባችሁብን ስትጫወቱብን እንደነበር እናውቃለን እኮ?
- አኼኼ. . .
- ምነው ክቡር ሚኒስትር?
- በመዋጮ ገንዘብ ተባልታችሁ ስታበቁ ሰበብ አታጡም፡፡
- ለማንኛውም ክቡር ሚኒስትር?
- ምን?
- እኛ እናንተን አናምንም፡፡
- ስለዚህ?
- ውይይትም ይባል ድርድር በጅምላ ሳይሆን በተናጠል ይሁንና እንገናኝ፡፡
- ቅድመ ሁኔታ መሆኑ ነው?
- ለሕዝብ ስትሉ ብታደርጉት ይመረጣል፡፡
- በቁምህ ትቃዣለህ መሰል?
- እንዴት የተከበሩ?
- ሕዝብማ ፋይዳ እንደሌላችሁ ያውቃል፡፡
- ይህ አካሄድ ያዋጣል የተከበሩ?
- እናንተማ እንወያይ ስንላችሁ የተሸነፍን መስሏችሁ ነበር፡፡
- ሕዝብ ሰንጎ ሲይዛችሁ አይደለም አንዴ እንወያይ፣ አንዴ እንደራደር ስትሉ የነበረው?
- ተሳስተሃል፡፡
- እኔ ክቡር ሚኒስትር?
- እኔ ነኝ ታዲያ?
- ምንድነው ስህተቴ?
- ፖለቲካው አልገባህም፡፡
- እንዴት ሆኖ ክቡርነትዎ?
- የፓርቲ ፖለቲካ ጌም አልገባህም፡፡
- ጌም?
- አዎን ጌም፡፡
- ምንድነው እሱ?
- ካንዲ ክራሽ ልበልህ?
[ክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊያቸው የዕለቱን ፕሮግራማቸውን እንድትነግራቸው ጠርተዋት እየተነጋገሩ ነው]
- እስኪ የዕለቱን ውሎዬን ንገሪኝ፡፡
- ከረፋዱ አራት ሰዓት ላይ ከአማካሪዎት ጋር ቀጠሮ ተይዟል፡፡
- ሰርዢው፡፡
- አምስት ሰዓት ሲሆን ከጀርመን የመጣ ዳያስፖራ ቀጠሮ ይዟል፡፡
- ምንድነው የሚፈልገው?
- በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ለመወያየት ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ወቅታዊ ጉዳይ ከፈለገ ቴሌቪዥን ተመልከት በይው፡፡
- ለምን አያናግሩትም ክቡር ሚኒስትር?
- ወቅታዊ ጉዳይ የሚነገረው በሚዲያ እንጂ በእኔ አይደለም፡፡
- ስድስት ሰዓት ሲሆን ጉዳይ አለኝ ያሉ ኢንቨስተር ይመጣሉ፡፡
- ምድነው የሚፈልጉት?
- ቅሬታ ለማቅረብ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምንድነው ቅሬታቸው?
- የውጭ ምንዛሪ ማግኘት አልቻልኩም ነው የሚሉት፡፡
- እኔ ምን ላድርግላቸው ታዲያ?
- የት ይሂዱ ክብር ሚኒስትር?
- ወደ ላይ ሄደው ቅሬታቸውን ያቅርቡ፡፡
- የተባለውን አልሰሙም እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
- ምን ተባለ?
- ቅሬታዎች በየደረጃው መፈታት አለባቸው፡፡
- ማን ነው ያለው?
- ጠቅላይ ሚኒስትሩ ናቸው ያሉት፡፡
- መቼ ነው ያሉት?
- ሰሞኑን ለጋዜጠኞች መግለጫ ሲሰጡ ነዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ሌላስ ምን አሉ?
- እኔ ጠቅላይ ሚኒስትር እንጂ ቅሬታ ሰሚ አይደለሁም ብለዋል፡፡
- ወይ ጉድ?
- ምነው ክቡር ሚኒስትር?
- አይ ወዲህ ነው፡፡
- ምንድነው እሱ ክቡር ሚኒስትር?
- አሁንስ የመረረኝ ነገር. . .
- ምን መረረዎት?
- እኔም ቅሬታ መስማት ሰልችቶኛል፡፡
- ምን ይደረግ ታዲያ ክቡር ሚኒስትር?
- ቅሬታ የሚያስተናግድ ሚኒስቴር መቋቋም አለበት፡፡
- በቃ ካቢኔ ስብሰባ ላይ ያንሱት ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ቀልጂ አንቺ፡፡
- ቀልድ ብችል ኖሮ. . .
- ለነገሩ እንኳንም አልቻልሽ፡፡
- ለምን ክቡር ሚኒስትር?
- አጉል እቀልዳለሁ ስትይ ካገኘሽው ጋር ስትላተሚ ነበር የምትውይው፡፡
- መቀለድ ካልቻልኩ ምን ብሆን ይሻለኛል ክቡር ሚኒስትር?
- ወሬ አመላላሽ!
- እኔ ክቡር ሚኒስትር?
- እኔ ነኝ ታዲያ!