Skip to main content
x
ወጋገን ባንክ በአዲስ ዓርማ በ800 ሚሊዮን ብር ወዳስገነባው ሕንፃ ሊገባ ነው

ወጋገን ባንክ በአዲስ ዓርማ በ800 ሚሊዮን ብር ወዳስገነባው ሕንፃ ሊገባ ነው

ወጋገን ባንክ ላለፉት 20 ዓመታት ሲገለገልበት የቆየውን የንግድ ዓርማ በመቀየር በአዲሱ ዓመት ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ ያወጣበትንና ግንባታው የተጠናቀቀውን የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ መገልገል እንደሚጀምር ይፋ አደረገ፡፡  

ባንኩ እስካሁን ሲገለገልበት የቆውን ዓርማ በአዲስ መተካቱን በማስመልከት ሐሙስ ሐምሌ 6 ቀን 2009 ዓ.ም. አዲሱን ዓርማ በይፋ ባስተዋወቀበት ሥነ ሥርዓት ወቅት እንደተገለጸው፣ ባንኩ አዲሱን ዓርማ ይዞ ወደ አዲሱ ሕንፃ በቅርቡ ይገባል፡፡ ባንኩ 20ኛ ዓመቱንም በአዲስ ሕንፃና በአዲስ ዓርማ ታጅቦ ያከብራል ተብሏል፡፡

የወጋገን ባንክ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ተፈሪ ዘውዱ እንደገለጹት፣ አዲስ ዓርማ የባንኩን እሴቶች፣ እ.ኤ.አ. በ2025 በአፍሪካ ከሚገኙት አሥር ስመ ጥርና ተፎካካሪ ባንኮች መካከል አንዱ ለመሆን ያስቀመጠውን ራዕይ በሚያንፀባርቅ መልኩ የተነደፈ ነው፡፡

‹‹ለ20 ዓመታት ያገለገለውን የልዩ ምልክት ዓርማ በአዲስ ለመተካት ስንወስን ያለፉት ዓመታት ስኬት፣ የወደፊቱ ብሩኅ ተስፋና ዛሬ የደረስንበትን ጽኑ መሠረት እንዲያንፀባርቅ እንዲሁም የመጪውን ስሜትና ዝንባሌ ከግምት ያስገባ ለውጥ ነው፤›› በማለት አቶ ተፈሪ ገልጸዋል፡፡

የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ዓርአያ ገብረ እግዚአብሔርም፣ ‹‹አዲሱ የባንኩ መግለጫ ዓርማ ለደንበኞችና ለሌሎች ባለድርሻ አካላት የባንኩ ራዕይ፣ ተልዕኮ፣ እሴቶች፣ ያለፈውን ስኬትና የወደፊቱን ግብ በሚወክል ከሌሎች ተወዳዳሪዎች በቀላሉ ለይተው እንዲያውቁትና እንዲያስታውሱት ያደርጋል፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም የባንኩን ገጽታም በወጥነት ለማስተዋወቅና ትኩረት በመሳብ ባንኩን ለማስተዋወቅ የሚደረገውን ጥረት እንደሚደግፍ ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡

አዲሱ ዓርማ ሁለት ዋና ዋና መገለጫዎች እንዳሉት ሲገለጽ፣ ‹‹ወጋገን›› ከሚለው ስያሜ አማርኛ ፊደላት ውስጥ ‹‹››ን በመውሰድና ከእንግሊዝኛው ‹‹Wegagen›› ከሚለው ቃል ደግሞ ‹‹W››ን በመሳብ፣ ሁለቱን በአንድ አቀናጅቶ በመያዝ የተቀረጸው አዲሱ ዓርማ፣ በክብ ቅርፅ ውስጥ ፀሐይን የሚወክል ሲሆን፣ በክቡ ውስጥ ወደ ጎን የተሰመረው ቀስት ደግሞ በማለዳ የሚታየውን የሰማይና የምድር መጋጠሚያ አድማስ እንደሚያመላክት ተብራርቷል፡፡ የዓርማው ትርጉም አሸናፊነትን፣ መስፋፋትን እንዲሁም የአገልግሎት ተደራሽነትና የባንኩን ስኬት እንደሚገልጽ የባንኩ ኃላፊዎች ተናግረዋል፡፡

አዲሱን ዓርማ ወደ ገበያ ይዘው ከመውጣታቸው በፊት ሁሉም የባንኩ ባለድርሻ አካላት የመከሩበት እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ባለአክሲዮኖች፣ የተመረጡ ደንበኞች፣ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላትና ሠራተኞች ተወያይተውበት አስተያየታቸው እንዲካተት ተደርጎ አሁን ይፋ ሊሆን መቻሉ ታውቋል፡፡ ይህ ሎጎ ላለፉት 12 ወራት ሲዘጋጅ ቆይቶ መጨረሻ ላይ የተመረጠው ዓርማ በአዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት ተመዝግቧል፡፡

የባንኩን አዲስ ዓርማ የሠራው በመስኩ ልምድ ያካበተው ስቱዲዮኔት የተባለው አገር በቀል አማካሪ ድርጅት እንደሆነም ታውቋል፡፡

እንደ አቶ ተፈሪ ገለጻ ባንኩ ያካበታቸውን ነባር እሴቶች ጠብቆ የዘመኑን የባንክ አገልግሎት ተጠቃሚዎች ፍላጎት ለማርካት አልሞ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ላይ መሠረት ያደረገውን አዲስ የአገልግሎት አሰጣጥ ብራንድ ስትራቴጂ በሚያንፀባርቅ መልኩ የተሠራ ነው፡፡ አዲሱ የብራንድ ስትራቴጂና ዓርማ ባንኩ አሁን የደረሰበትን የዕድገት ደረጃና ገጽታ በማጉላት ተጠቃሚዎች በአገልግሎቱ ፍላጎታቸውን የሚያረካ ዘመናዊ ባንክ መሆኑን የበለጠ እንዲገነዘቡ ያደርጋል የሚል እምነትም አላቸው፡፡ የደንበኞችን ትኩረት በመሳብ የባንኩን ገጽታ በወጥነት ለማስተዋወቅ የሚደረገውን ጥረት ውጤታማነት ከፍ በመድረጉ ረገድም አዲሱ ዓርማ ይጠቅማል ተብሏል፡፡

ባንኩ የሚጠቀምበትን የአዲሱን ዓርማ ቀለም መረጣ ላይ ብዙ ስለመደከሙ የባንኩ መግለጫ ያመለክታል፡፡ ኮርፖሬት ቀለም፣ የአንድ ተቋም ብራንድ በሰዎች አዕምሮ ውስጥ እንዲሰርጽና እንዲታወስ ለማድረግ የብራንዱ መገለጫ በመሆኑ ከሚያገለግሉ የተለያዩ ነገሮች ውስጥ አንዱና ትልቅ ተፅዕኖ መፍጠር የሚችል እንደሆነ መጥቀስ በዚሁ ግንዛቤ የቀለም መረጣው ተከናውኗል፡፡ የቀለም ምርጫው የአንድን ተቋም መንፈስ ወይም መልዕክት ከቀለም በተሻለ መንገድ የሚገልጽ ነገር ባለመኖሩ አዲሱ ዓርማ በሚቀረፅበት ወቅትም ለቀለም ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ተገቢውን ወካይ ቀለም ሊመረጥ እንደተቻለ ተገልጿል፡፡ ይህም በቀለም መረጣ ላይ የዓርማ ዋነኛ ቀለም ብርቱካናማ እንዲሆን ተወስኗል፡፡ ብርቱካናማው ቀለም ተፈጥሯዊ ክስተት ከሆነው ጎህ ሲቀድ በሰማይ አድማስ ላይ ከሚታየው የጠዋት ፀሐይ ደማቅ ብርሃን የተቀዳ ሲሆን፣ የሚያመለክተውም በተስፋና በመልካም ምኞች የተሞላ ብሩህ ጊዜን እንደሆነ የቀለም ምርጫውን በተመለከተ በተሰጠው ማብራሪያ ላይ ተገልጿል፡፡

‹‹በንግዱ ዓለም፣ ብርቱካናማ ቀለም ታላቅነትን፣ አዳዲስ ነገሮችን የመፍጠር ተነሳሽነትን፣ የካበተ ዕውቀት፣ ልምድ፣ ሀብትና ጥራትን ይወክላል፤›› የባንኩ መግለጫ አዲሱን ዓርማ በተለያየ መንገድ ማስተዋወቅ መጀመሩን አስታውቋል፡፡

አዲሱ ዓርማ የባንኩን 20ኛ ዓመት በሚከበርበትና የከተማችን አዲስ ፈርጥ ያሉትን የባንኩን ሕንፃ ለማስመረቅ በዝግጅት ላይ ባለበት ወቅት መተዋወቁ ባንኩ ወደ አዲስ ምዕራፍ መሸጋገሩን እንደሚያሳይ የገለጹት አቶ ተፈሪ፣ እ.ኤ.አ. በ2025 ስለአሥሩ የአፍሪካ ባንኮች አንዱ ለመሆን የተነደፈን ዕቅድ ከግብ ለማድረስ አጋዥ ይሆናልም ብለውታል፡፡

ወጋገን ባንክ ከ20 ዓመታት በፊት የተቋቋመ ሲሆን፣ ከ3,000 በላይ ባለአክሲዮኖችን ይዞ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኝ የግል ባንክ ከመሆኑም በተጨማሪ ካፒታሉን ከ2.1 ቢሊዮን ብር በላይ ለማድረስ የተቻለው የፋይናንስ ተቋም ነው፡፡