Skip to main content
x
የምግብ ዋስትና ላይ የተጋረጠው ፈተና

የምግብ ዋስትና ላይ የተጋረጠው ፈተና

ኩታ ገጠም ከሆነውና ከአምስት ሔክታር በላይ ከሚሸፍነው መሬት ላይ በመስመር የተዘራው በቆሎ፣ ቡቃያ ሆኗል፡፡ ለም ከሆነው አፈር ላይ ብቅ ብቅ ያሉትን በቆሎዎች ማጭድና መኮትኮቻ በመያዝ እግር በእግር የሚኮተኩቱ፣ አንዳንዱን ቡቃያ መሃሉን ፈልቀቅ እያደረጉ የሚያዩ አርሶ አደሮችም አሉ፡፡ በገረረው የተሲያት ፀሐይ አርሶ አደሮች ብቻ ሳይሆኑ በወረዳው የተመደቡ የግብርና ባለሙያዎችም በማሳው ውስጥ እየተዘዋወሩ ይቃኛሉ፡፡ ባለሙያዎቹ የአንዱን እግር ቡቃያ በቆሎ ገለጥ በማድረግ ሰሞኑን በቆሎን እያጠቃ ነው የተባለውን ‹‹የአሜሪካ ተምች›› ሲያገኙ ‹‹ይህ ነገር እያዳረሰው ነው›› በማለት የሌላውን የበቆሎ ቡቃያ ቅጠል ያያሉ፡፡ አንዳንዱ ላይ ሁለት አንዳንዱ ላይ አንድ የአሜሪካ ተምች ያገኛሉ፡፡ ቡቃያው ውስጥ በመጠናቸው አነስ ያሉ ተምቾች ሲገኙ፣ ከአፈሩ ውስጥ የሚወጣው ደግሞ ተለቅ ያለ ነው፡፡

በደቡብ ክልል በጉራጌ ዞን ከሚገኘው ሆሌ ቀበሌ አበሽጌ ወረዳ የሚያደርሰው አብዛኛው በጠጠር የተሸፈነ መንገድ ግራና ቀኙ በለመለመና ለዓይን በሚማርክ የበቆሎ ቡቃያ ተሸፍኗል፡፡ በአካባቢው ካሉት ማሳዎች በአበሽጌ ወረዳ ፊቴ ጀጁ ቀበሌ ያለው ‹‹በአሜሪካ ተምች›› (Fall Armyworm) ከተመቱ የደቡብ ክልል ወረዳዎች አንዱ ነው፡፡ በመሆኑም አርሶ አደሩ እረፍት የለውም፡፡ ከጧት እስከ ማታ በቆሎውን እግር በእግር እየተከታተለ ማየት ይጠበቅበታል፡፡ ተምቹን ሲያገኝ ደግሞ እዚያው በቆሎው ውስጥ እንዳለ በቅጠልና ቅጠሉ ጨፍልቆ መግደል አለበት፡፡ ይህ ሥራ አድካሚና ብዙ የሰው ኃይል የሚፈልግ ቢሆንም ተምቹን ለመከላከል ተመራጩ ዘዴ ነው፡፡

በቀበሌው ባላቸው አንድ ሔክታር መሬት ላይ የዘሩትን በቆሎ ከተምቹ ለማዳንና እንዲፋፋ ማጭዳቸውን ይዘው እያንዳንዱን በቆሎ እግር በእግር የሚኮተኩቱት አርሶ አደር ታዬ ደምሴ እንደሚሉት፣ የግብርና ሥራ ከዚህ ቀደምም ቢሆን ከሥር ከሥሩ መገኘትን የሚጠይቅ ቢሆንም፣ የዘንድሮው ለየት ይላል፡፡

ያማረው የበቆሎ ቡቃያ መልክ ብቻ አሳይቶ ያለምርት እንዳይቀር በየዕለቱ የበቆሎውን ቅጠል ከሙሽራው ፈልቀቅ እያደረጉ ማየት፣ መሬቱንም ቆፈር ቆፈር እያደረጉ ለፀሐይ ማጋለጥ ይፈልጋል፡፡ ይህ የሚደረገውም አፈሩን ኮትኮት በማድረግ ተምቹን ለፀሐይ  ለማጋለጥ አሊያም የተሸበለለ ቡቃያ ውስጥ ገብቶ የተደበቀውን እዛው ጨፍልቆ ለመግደል ነው፡፡

አቶ ታዬ እንደሚሉት፣ ተምቹ ከዚህ ቀደም በበርበሬ ተክል ላይ ቢያጋጥማቸውም በበቆሎ ላይ ሲያዩት ይህ የመጀመሪያ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም እንዲህ ዓይነት ‹‹ትል›› በቆሎ ላይ ገጥሟቸው እንደማያውቅ በመናገር፣ የግብርና ባለሙያዎች በሰጧቸው ምክር መሠረት በየዕለቱ የበቆሎውን ቡቃያ በመፈተሽና በመኮትኮት ተምቹን እየለቀሙ መሆኑን ነግረውናል፡፡

‹‹በቃ ብዙ ነገር ይሰማናል፡፡ የዓመት አዝመራችን ነው፡፡ ምርቱን የምናገኘውም በዓመት ነው፡፡ ስሜታችን ተጎድቷል፡፡ እንናደዳለን፡፡ ተምቹን እግር በግር በመልቀም በኩል አብዛኛው ልፋት የኔ ቢሆንም፣ ልጆቼ ከትምህርት ቤት ሲመጡ ያግዙኛል፤›› ያሉትም ተስፋ በቆረጠ አነጋገር ነበር፡፡

በዓል ካልሆነ በስተቀር ከማሳቸው እንደማይቦዝኑ የሚናገሩ አቶ ታዬ፣ በአንድ ሔክታር መሬት ላይ የዘሩትን በቆሎ ሲቃኙ ያዩት ተምች እንዳያያዙ፣ ማሳውን ያስተርፈዋል ብለው እንደማያስቡ፣ የዘሩበት ሥፍራ ‹‹ቀይት›› ቀይና ለም አፈር በመሆኑ ኩትኮታ ቢጨርሱም ቡቃያው ሙሽራ ውስጥ አነስ አነስ ያሉትን፣ ከመሬት ደግሞ ትላልቁን ተምች በማግኘታቸው ምርት አገኛለሁ የሚል ተስፋ እንደሌላቸው ነግረውናል፡፡ ተምቹ ሌት እንጂ ቀን ላይ እንደሚደበቅ፣ እሳቸውም በቡቃያው ላይ ለውጥ የሚያዩት ጠዋት ጠዋት ወደ ማሳቸው ሲመጡ እንደሆነም አክለዋል፡፡

በሥፍራው መረጃ የሰጡን የጉራጌ ዞን የእርሻ የተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ሰብል ጥበቃ ባለሙያ አቶ ዘመተ አይፎክሩ፣ የአበሽጌ ወረዳ የአዝዕርት ልማት ባለሙያ አቶ ሲሳይ ወልደማርያም እና የፊቴ ጀጁ ቀበሌ የግብርና ሰብል ባለሙያ አቶ ዮሴፍ ጴጥሮስ፣ ምንም እንኳን  አርሶ አደሩ አቶ ታዬ በማሳቸው ላይ ተስፋ ቢቆርጡም፣ በቀን በቀን የለቀማ ሥራው ከተከናወነና መድኃኒት ከተረጨ አዝመራው ሊተርፍ ይችላል ብለዋል፡፡

ቡቃያውን ከነሥሩ በመንቀል ብሎም እዛው መሬት እንዳለ ወገቡን በመስበር ተምቹ መኖሩን በማረጋገጥም አርሶ አደሩ መድኃኒት ርጭት ማድረግ እንዳለባቸው ሲመክሩ ሰምተናል፡፡

ባለሙያዎቹ እንደነገሩን አንድ ሔክተር መሬት እስከ 58 ሺሕ እግር በቆሎ የሚይዝ ሲሆን፣ በአበሽጌ ወረዳ ብቻ ከ6,300 ሔክታር መሬት በላይ በበቆሎ ተሸፍኗል፡፡ ተምቹ በወረዳው በሚገኙ የበቆሎ ማሳዎች በሙሉ ባይገኝም፣ ምልክቱ ግን ለባለሙያዎቹም ሆነ ለአርሶ አደሩ ሥጋት ሆኗል፡፡

ፎል አርሚዎር የሚባለው የአሜሪካ ተምች ከ80 በላይ አዝዕርቶችን እንደሚበላ በውጭ የተሠሩ ጥናቶች ቢያሳዩም፣ እስካሁን በኢትዮጵያ በስድስት ክልሎች የታየው በበቆሎ ላይ ነው፡፡ እንደ ጉራጌ ዞን ጌሾንና የጫካ ደን የሚበላ ትል የታየ ሲሆን፣ ይህ ለግብርና ባለሙያዎቹ አዲስ ነው፡፡ አርሶ አደሮቹ ግን ጌሾ ላይ የታየውን ከዚህ ቀደም ያውቁት እንደነበር እንደነገሯቸው ባለሙያዎቹ ነግረውናል፡፡

በዞን በሦስት ወረዳዎች ላይ የታየውን ተምች ለመቆጣጠር አርሶ አደሩም ሆነ የግብርና ባለሙያው በየማሳው ቅኝት የሚያደርጉ ሲሆን፣ ቅኝት ከሚያደርጉባቸውና ኩታ ገጠም ከሆኑ እርሻዎች አንዱ በተምቹ የተጠቃው የአቶ ታዬ እርሻ ነው፡፡   

አቶ ታዬ ማሳቸው ከቡቃያነቱ በአሜሪካ ተምች ተመትቶ ተስፋ ቢያስቆርጣቸውም፣ በመስኖ የተዘራውና ከቡቃያነቱ ጀምሮ ተምቹ የታየበት በቆሎ፣ የግብርና ባለሙያዎች ዕገዛ ታክሎበት አርሶ አደሩ ባደረገው የተምች ለቀማና የኬሜካል ርጭት ዛሬ ላይ በቆሎው ለመሸጎጥ (እሸት) ደርሷል፡፡

በጉራጌ ዞን የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ትብብር ከዛው ከአበሽጌ ወረዳ ሳንወጣ ከፊቴ ጀጁ ቀበሌ እስከ አሥር ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኘው ናቻ ጉሊት ቀበሌ ላይ አንድ አርሶ አደር በአንድ ሔክታር መሬት ላይ በመስኖ ያለማውን በቆሎ ለማየት ችለን ነበር፡፡

በሥፍራው በተገኘንበት ረቡዕ ሰኔ 7 ቀን 2009 ዓ.ም. የበቆሎውን ባለቤት ባናገኝም፣ እርሻውን የሚያግዝና በወረዳው የተመደበ ባለሙያ አግኝተን ነበር፡፡ ይህ ማሳ፣ የዞኑ ግብርና ባለሙዎች ከሁለት ወር በፊት በአሜሪካው ተምች ዙሪያ ሥልጠና ወስደው እንደተመለሱ ለመጀመሪያ ጊዜ ተምቹን ያዩበት ነው፡፡

በናቻ ጉሊት ቀበሌ የተፈጥሮ ሀብት ባለሙያ አቶ መለስ ገለቶ እንደሚሉት፣ ለመጀመርያ ጊዜ በወረዳው የተጠቃው ማሳ ባለቤት ኬሚካል እንዲጠቀምና በእጅ ለቀማ እግር በእግር እንዲከታተል መክረውታል፡፡ አርሶ አደሩ ይህንን በማድረጉም በመስኖ በአንድ ሔክታር መሬት ላይ የዘራው በቀሎ ለፍሬ ሊበቃ ትንሽ ቀርቶታል፡፡ ግን ተምቹ ምርቱ እስከሚነሳ የሚያወድም በመሆኑ ይህ ተስፋ የተጣለበት ማሳ እንዳይጠፋ ከዕለት ዕለት ክትትል ይደረግለታል፡፡

ተምቹ በባህሪው ከቡቃያ ምርት እስከሚነሳ የሚያወድም በመሆኑ በበቆሎው የዕድገት ጊዜያት በሙሉ ክትትል ይፈልጋል፡፡ ከቡቃያነቱ ተጠቅቶ ለመትረፍ የቻለው ማሳም ዕለት ከዕለት ክትትክ ተደርጎለታል፡፡ ይህም ተስፋ የሚሰጥ መሆኑን አቶ መለስ ይናገራሉ፡፡   

በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጥላሁን ከበደ እንደሚሉት፣ በሸካ ዞን የሚገኙ አርሶ አደሮች ‹ምን መጣብን› በማለት የአሜሪካ ተምች የተባለውን ትል ማየታቸውን ያሳወቁት ከየካቲት 25 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ነው፡፡

በደቡብ ክልል ተምቹ ቀድሞ የታየባቸው የበቆሎ ማሳዎች በበልግ ቀድመው በሚዘሩት በቤንች ማጂ ዞን፣ በሸካና በከፋ ዞኖች ነው፡፡ ተምቹ ከተከሰተ ወዲህ ክልሉ ለእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር አሳውቆ፣ የዘመቻ ሥራ ጀምረዋል፡፡ ሆኖም አስቀድሞ መከላከሉንና የዘመቻ ሥራውን ከጀመሩ በኋላ የታዘቡት የተምቹ ባህሪና የመዛመት አቅሙ አደገኛ መሆኑን ነው፡፡

በንፋስ የምትበረው፣ በቀን እስከ 200 እንቁላል ወይም በምትቆይበት የሕይወት ዘመኗ (21 ቀናት) 2000 ያህል እንቁላል የምትፈለፍለውና እስከ 500 ኪሎ ሜትር በንፋስ የምትበረው ‹‹የእሳት ራቷ›› በቆሎውን ለማዳን የሚደረገውን ርብርብ ፈታኝ አድርጋዋለች፡፡

አቶ ጥላሁን እንደሚሉት፣ ባለሙያዎችና አርሶ አደሩ በአንድ ማሳ ላይ ርብርብ ሲያደርጉ፣ በቀጣዩ ማሳ ላይ ታየ ይባላል፡፡ ዛሬ አንድ ዞን ላይ በሚገኝ እርሻ የአሜሪካ ተምቹ ታየ ሲባል፣ ነገ ከሌላ ዞን መረጃ ይመጣል፡፡ በክልሉ ካሉት 18 መዋቅሮችም ከየም ልዩ ወረዳ በስተቀር በ17 መዋቅሮች በሦስት ልዩ ወረዳዎችና በ14ቱም ዞኖች ተከስቷል፡፡ ሆኖም ክስተቱ በሁሉም ማሳዎች ላይ ሳይሆን በአንዳንዱቹ ከእነዚህ ማሳዎችም በሁሉም የበቆሎ እግር ላይ ሳይሆን በተወሰኑት ላይ ነው፡፡  

በክልሉ በበቆሎ የተሸፈነው ማሳ 330 ሺሕ 400 ሔክታር ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ተምች መኖሩ የተረጋገጠው በ57 ሺሕ 300 ሔክታር በተዘራው በቆሎ ላይ ነው፡፡ ይህንን ለመቆጣጠርና በቀሪዎቹ ባልተከሰተባቸው ማሳዎች እንዳይከሰት አስቀድሞ ለመከላከል ግብረ ኃይልም በየሥፍራው ተሰማርቷል፡፡

እንደ ክልሉ የበቆሎውን ማሳ የመታደጉን ሥራ ውጤታማ ያደረገው፣ በእጅ እየለቀሙ መግደሉና በዘመቻ መሥራቱ ነው፡፡ በሰው ኃይል መለቀሙም የኬሚካል ርጭቱን ለመቀነስ ከመርዳቱ በተጨማሪ ተምቹ የበቆሎው ሙሽራ ውስጥ ስለሚደበቅ ኬሚካል የማደርስባቸውን ተምቾች ለማግኘት ነው፡፡ 

የእጅ ለቀማው በነፍስ ወከፍ እያንዳንዱን በቆሎ በመፈተሽ የሚከናወን መሆኑ ግን ሌላ ፈተና ነው፡፡ በአማካይ በአንድ ሔክታር ማሳ ላይ ከ50 ሺሕ እስከ 60 ሺሕ የበቆሎ እግር ስለሚኖር ፣ እያንዳንዱ አርሶ አደር ይህንን አንድ በአንድ ፈትሾ ይችላል ወይ? የሚለው ጥያቄ ያስነሳል፡፡ በክልሉ ከተዘራው አንፃር የተከሰተበት ማሳ አነስተኛ መሆኑን አቶ ጥላሁን ተናግረው፣ በቀሪዎቹ ላይ እንዳይስፋፋ በወፍ በረር ቅኝት፣ በልማት ቡድንና በአንድ ለአንድ የልማት ቁርኝት ዕለት በዕለት ማሳዎች እንዲጎበኙ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

ከአንድ ሔክታር የበቆሎ ማሳ በአማካይ ከ40 እስከ 50 ኩንታል የሚገኝ ሲሆን ሞዴሎች ከዚህ በላይ ይሄዳሉ፡፡ አነስተኛ አርሶ አደሮች ደግሞ ከ20 እስከ 30 ኩንታል በሔክታር ያገኛሉ፡፡

በጉራጌ ዞን ያገኘናቸው ባለሙያዎች እንደነገሩን ደግሞ በአንድ ሔክታር መሬት የሚዘራ በቆሎ ከዘሩ ምርት እስከሚነሳበት ድረስ የአርሶ አደሩን ጉልበት ጨምሮ እስከ 15 ሺሕ ብር ያስወጣል፡፡

የአሜሪካ ተምቹ በቆሎ ማሳ ላይ ቢታይም፣ ከሥር ከሥር የመከላከሉ ሥራ እየተከናወነ በመሆኑ በክልሉ ሙሉ ለሙሉ የወደመ ማሳ የለም፡፡ ሆኖም የካቲት 2009 ዓ.ም. ላይ የተከሰተባቸውና መጋቢት ላይ የተዘሩት፣ ቅጠላቸውና ሙሽራው በትሉ ከተነካ በቆሎው አገግሞ ስለሚነሳ ይቀጭጫል፣ ይህም እስከ አራት በመቶ ያህል የምርት ቅናሽ ያስከትላል፡፡ 

በተወሰኑ አካባቢዎች ላይ በቆሎ የደረሰ ሲሆን፣ ትልቁን የምርት ሽፋን የሚይዘው ግን ግንቦት ላይ የተዘራውና አሁን በቡቃያነት ደረጃ የሚገኘው ነው፡፡

‹‹አጠቃላይ አንደ አገር አደገኛ ሁኔታ ውስጥ ስላለን የተከሰተውን ተምችና ሌሎችም በሰብል ላይ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ ተባይና ነፍሳትን ለመከታተል፣ ለመቋቋምና ምላሽ ለመስጠት በብሔራዊ ደረጃ ሊሠራ እንደሚገባ በቅርቡ በሐዋሳ ተካሄዶ በነበረ ብሔራዊ ስብሰባ ላይ ተወያይተናል›› ያሉት አቶ ጥላሁን፣ ሚኒስትሮች ዩኒቨርሲቲዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተገኙበት፣ በምግብ ዋስትና ላይ የተጋረጠው ፈተና አጠቃላይ ዓመታዊ ምርት ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖ ከባድ ስለሆነ እንደ አገር መረባረብ እንደሚያስፈልግ መነጋገራቸውን አስታውሰዋል፡፡ ዝግጅቱም ሲከሰት እሳት የማጥፋት ሳይሆን፣ ቀድሞ መከላከሉና መቆጣጠሩ ላይ ማተኮር እንዳለበት አክለዋል፡፡

በደቡብ ክልል የካቲት መጀመርያ ላይ የተከሰተው የአሜሪካ ተምች አሁን ላይ በስድስት ክልሎች ታይቷል፡፡ ይህ ተምች ከጎበኛቸው ክልሎች ሌላኛው የአማራ ክልል ነው፡፡ በክልሉ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ተስፋሁን መንግሥቴ እንደነገሩን፣ በክልሉ በዋናነት ምዕራብ ጎጃም አዊ፣ ምሥራቅ ጎጃምና ደቡብ ጎንደር ላይ ተከስቷል፡፡ ቃለ መጠይቅ ባደረግንላቸው ባለፈው ሳምንት በክልሉ በአራት ዞኖችና በ16 ወረዳዎች፣ በ35 ቀበሌዎች ባሉ የበቆሎ ማሳዎች ላይ ችግሩ ታይቷል፡፡ ወደ ሌሎች ሥፍራዎች ይዛመታል የሚል ሥጋትም አለ፡፡

እንደ ሠራዊት የመጣውን ተምች እንደ ሠራዊት ለመመከት በተዋረድ ኮሚቴ መቋቋሙን፣ በዋናነት አርሶ አደሩ ከማሳው አጠገብ ስላለም እንዴት መከላከል እንደሚችል ሥልጠና ተሰጥቷልም ብለዋል፡፡ አዊ ውስጥ በአንድ አርሶ አደር ማሳ ማለትም 0.25 ሔክታር መሬት ላይ የተደረገ ለቀማም ውጤታማ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

‹‹አርሶ አደሩ አረም እንደሚያርመው ትሉንም ያርማል›› ሲሉ የገለጹት ምክትል ኃላፊው ከድሮው ተምች የአሁኑ ልዩነቱ በፍጥነት ቅጠሉን መብላቱና ከቡቃያ በቆሎው እስከሚነሳበት ማውደሙ ነው ብለዋል፡፡ የቀደመው ዝናብ ሲጥል ወፍሮ የሚፈርጥ ሲሆን፣ አዲሱ ራሱን ደብቆ የመቆየትና የማውደም ባህሪ አለው፡፡

አቶ ተስፋሁን እንደሚሉት፣ አደገኛ ስለመሆኑ ምልክት ያሳየውን ተምች ማጥፋት ካልተቻለ በመኸር ምርት ላይ ጉዳቱ ያይላል፡፡

በአማራ ክልል ተምቹ በተከሰተባቸው አካባቢዎች በቆሎ ደህና ምርት ከመስጠትና የምግብ ዋስትና ከመሆን አኳያ ትልቁ ሰብል ስለሆነ፣ ምርቱን ማጣት ለጎላ ጉዳት ይዳርጋልም ብለዋል፡፡

በእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር የዕፅዋት ጥበቃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዘብዴዎስ ሰለቶ እንደሚሉት፣ አሥር ሔክታር የሚሸፍን ማሳ ቢኖር በዚህ ላይ የተዘሩት በቆሎዎች በሙሉ በትሉ ተጠቅተዋል ማለት አይደለም፡፡ በየመሀሉ አልፎ አልፎ ቢከሰትም እንደ አጠቃላይ አሥር ሔክታር መሬት ላይ የተዘራው በቆሎ ላይ ተምቹ ታይቷል የሚባለው መጀመሪያ የታዩትን ተምቾች መቆጣጠር ካልተቻለ ቀሪውን ስለሚያዳርሱት ነው፡፡

ተባዩ በባህሪው ለኢትዮጵያ እንግዳ በመሆኑ መጠናት ያለባቸው ጉዳዮች መኖራቸውን በማስታወስ፣ በሚኒስቴሩ የተዛማች ተባዮች አሰናና መከላከል ክፍል ከክልሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ቀድሞ የመተንበይ፣ የማስጠንቀቅና አቅጣጫ ሰጥቶ የመከላከል ሥራ እየሠራ መሆኑን አክለዋል፡፡ ተምቹ ኢትዮጵያ ሳይገባም በፊት፣ ሊገባ ይችላል በሚል መለየት እንዲቻል በራሪ ወረቀት መበተኑን፣ ክልሎችም የሥልጠና ማኑዋል አዘጋጅተው ሥልጠና መስጠታቸውን ተናግረዋል፡፡

ለፀረ ተባይ መግዣ 45 ሚሊዮን ብር የተፈቀደ ሲሆን፣ ችግር ወዳለባቸው አካባቢዎች ኬሚካል የሚሠራጭም ይሆናል፡፡ ሆኖም ትሉ በኬሚካል ርጭት ብቻ የመጥፋቱ ጉዳይ አጠራጣሪ ስለሆነ፣ ሁሉም አርሶ አደር ማሳው ላይ ያሉትን በቆሎዎች እግር በእግር በየቀኑ እየፈተሸ እንዲለቅም የመፍትሔ ሐሳብ ተሰጥቷል፡፡ ይህም ከሌሎች አገሮች የተወሰደ ልምድ መሆኑን አቶ ዘብዴዎስ ተናግረዋል፡፡

በብሔራዊ ደረጃ ሲታይ በቆሎ በከተማ ደረጃ እንደ ጤፍ ምግብ ላይ ይውላል ባይባልም በገጠር ከጤፍ ቀጥሎ ዋና የምግብ ዋስትና ነው፡፡ ለኢንዱስትሪ ጥሬ ዕቃነትም ያገለግላል፡፡

ሚኒስቴሩ በአሜሪካ ተምች ዘሪያ መግለጫ በሰጡበት ሰኔ 7 ቀን 2009 ዓ.ም.  የሕዝብ ግንኙነት ቢሮ ኃላፊው አቶ ዓለማየሁ ብርሃኑ እንደገለጹት፣ በቆሎ ከፍተኛው የአገሪቱ የምግብ እህል ሲሆን፣ የበቆሎ ምርት በተምቹ ተጠቃ ማለት አጠቃላይ አገራዊ ምርት ላይ ትልቅ ጉዳት ከማድረሱም ባሻገር በምግብ እህል ራስን ችሎ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የሚደረገውን እንቅስቃሴ ወደኋላ ይጎትተዋል፡፡ ይህን መሰሉን ችግር የሚያስከትለውን የአሜሪካ መጤ ተምች ለመከላከል ሕዝባዊ ንቅናቄ መካሄድ ግድ ይላል፡፡ በዚህም ንቅናቄ ላይ ተማሪዎች፣ የፖሊስ ሠራዊት፣ የመከላከያ ኃይል፣ አርሶ አደሮችና ሌሎችም የኅብረተሰብ ክፍሎች በቡድን ተቀናጅተው ተምቹን ለመከላከል መንቀሳቀስ እንደሚገባቸው፣ የመከላከሉንም ሥራ ውጤታማ ለማድረግ 100,000 ሊትር ፀረ ተባይ ኬሚካል በየክልሎቹ እንደተሠራጨ አብራርተዋል፡፡

ተምቹ ለጊዜው በበቆሎ ሰብል ላይ ቢከሰትም፣ በሌሎች የሰብል ዓይነቶች ላይ ሊከሰት ስለሚችል በዘንድሮ የመኸር እርሻ ላይ ከፍተኛ የሆነ የቅድመ ጥንቃቄ ሥራ በመከናወን ላይ ነው፡፡ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣  በትግራይ፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎችም የእሳት ራት ማጥመጃ መረብ መዘርጋቱን አቶ ዘብዴዎስ ገልጸዋል፡፡

ለብዙዎቹ የአፍሪካ አገሮች ዋና ምግብ የሆነው በቆሎ፣ በኢትዮጵያም ቢሆን በተለያየ መልኩ ለምግብነት ይውላል፡፡ በከተማ በሚገኙ አብዛኞቹ ገበያዎች የበቆሎ ቅንጬና ከጤፍ ጋር አብሮ የሚፈጭ ሲሸጥ፣ የበቆሎ ምርት በብዛት በሚያመርቱ አካባቢዎች ያሉ የኅብረት ሥራ ማኅበራትም ከተፈጨ በቆሎ የተዘጋጀ የገንፎና የአብሲት ዱቄት ያቀርባሉ፡፡ እነዚህ ምርቶች ከውጭ ከሚገቡ ምርቶች ጎን ለጎን በሱፐር ማርኬቶችና በሱቆች የሚሸጡም ናቸው፡፡        

     ከዘንድሮ አጋማሽ ጀምሮ በአፍሪካ የምግብ ዋስትና ላይ ተጋረጠው የአሜሪካ ተምች መነሻው ደቡብ አሜሪካ መሆኑ በተለያዩ ጆርናሎች ላይ ሰፍሯል፡፡