Skip to main content
x

የሰው ልጅ እንደ ዕቃ በገበያ ላይ . . .

በዳዊት ከበደ አርአያ

በዚች ዕለትና ሰዓት ሚሊዮኖች እየተጓዙ ነው፡፡ ብዙዎች ከሰሃራ በታች የሚገኙ የአፍሪካ አገሮች ወጣቶች በሕገወጥ መንገድ የመሰደድ ምክንያታቸው የተለያየ ቢሆንም፣ በዋናነት ግን የተሻለ የገቢ ምንጭና ኑሮ በመሻት ነው፡፡ እዚህ ላይ ሕገወጥ ደላሎችና በሰው ንግድ የተሰማሩ አዘዋዋሪዎች የማይጨበጥ ተስፋ በመስጠት የሚጫወቱት ሚናም ቀላል አይደለም፡፡ እነዚህ ሕገወጥ ደላሎችና አዘዋዋሪዎች የፋይናንስ አቅማቸው እጅግ የፈረጠመ፣ ከአገር አገር የተዘረጋ ሰንሰለታቸውና መዋቅራቸው የተወሳሰበና የረቀቀ ነው፡፡ ከዚህ በመነሳትም በየአገሩ ካሉ የመንግሥት መዋቅሮች ጋር የተሳሰረና ተፅዕኖውም በዚያው ልክ የገዘፈ መሆኑን፣ የተለያዩ በሕገወጥ ስደት ላይ ጥናት ያደረጉ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና የመገናኛ ብዙኃን ይገልጻሉ፡፡

በቅርቡ ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (IOM) ይፋ ያደርገው ጥናት እንደሚያመለክተው ከሆነ፣ እነዚህ ከተለያዩ አገሮች በሕገወጥ መንገድ በደላሎች ተፅዕኖ የሚሰደዱ ሰዎች ተስፋ ወደ ሚያደርጉት አውሮፓ ለመድረስ፣ እያንዳንዳቸው በአማካይ ከ35 እስከ 40 ሺሕ ዶላር ለእነዚህ ሕገወጥ አዘዋዋሪዎች ይከፍላሉ፡፡ ይኼ ኢትዮጵያውያንን የሚጨምር ሲሆን፣ አሁን ባለው የምንዛሪ ዋጋ እንኳን ብናሰላው ከ800 ሺሕ እስከ አንድ ሚሊዮን ብር እንደ ማለት ነው፡፡ ብዙዎች በዚህ አስቸጋሪ ጉዞ ለከባድ ድብደባና አስገድዶ መደፈር፣ እንዲሁም በቃላት ለመግለጽ ለሚከብድና ለሚዘገንን ኢሰብዓዊ አያያዝ ተጋልጠዋል፡፡ የተጠየቁት ገንዘብ መክፈል ያልቻሉ በተለይም አፍሪካውያን ስደተኞች በአሁኑ ጊዜ በሊቢያ ምድር ያሉበት ሁኔታ በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ይፈጸማል ብሎ መገመት አስቸጋሪ ነው፡፡

ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት በቅርቡ ይፋ ባደረገው መረጃ እነዚህ በሕገወጥ መንገድ ወደ አውሮፓ ለመሻገር ሊቢያ ውስጥ በአዘዋዋሪዎች እጅ የሚገኙ አፍሪካውያን ስደተኞች፣ በዚህ በሠለጠነ ዘመን ገበያ ላይ እንደ ዕቃ ይሸጣሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ብዙ አፍሪካውያን ስደተኞች ሜድትራንያን ባህር አቋርጠው ለመድረስ በተለያዩ ማጎሪያዎችና እስር ቤቶች ያለ ምግብና መፀዳጃ ታሽገው በእነዚህ አዘዋዋሪዎች እጅ እንደሚገኙ የገለጸው ድርጅቱ፣ ሜድትራንያን ባህር ለማቋረጥ በቂ ገንዘብ መክፈል ያልቻሉና ከትውልድ አገራቸው ተነስተው አስቸጋሪውን የሰሃራ በረሃ ሲያቋርጡ ገንዘባቸውን አሟጠው ለደላሎቹ የከፈሉ ናቸው፡፡ ታዲያ የሚጠብቃቸው ዕጣ ፈንታ ገበያ ላይ እንደ ዕቃ መሸጥ ነው፡፡ እንደ ድርጅቱ መረጃ ከሆነ እነዚህ ስደተኞች ገበያ ላይ ከአንድ ደላላ ወደ ሌላው እያንዳንዳቸው ከ200 እስከ 500 ዶላር ይሸጣሉ፣ አልያም ይገዛሉ፡፡

እነዚህ ገበያ ላይ እንደ ዕቃ የሚሸጡት ስደተኞች ለቀጣይና መቋሚያ የሌለው የገንዘብ ክፍያና አስገዳጅ የጉልበት ሥራ የሚዳረጉ ሲሆን፣ ሴቶቹ ደግሞ በተለያዩ የጎሳ መሪዎችና ሕገወጥ አዘዋዋሪዎች ተገደው ይደፈራሉ፡፡

አትማን በልቤሲ የተባሉ በሊቢያ የድርጅቱ ተወካይ አብዛኛዎቹ ገበያ ላይ እንደ ዕቃ የሚሸጡት የምሥራቅና የምዕራብ አፍሪካ ስደተኞች ናቸው ይላሉ፡፡ በተለይም ሳብሃ በተባለች የሊቢያ የሕገወጥ ዝውውር ማዕከል የሆነች ከተማ በገንዘብ ለገዙዋቸው ግለሰቦች በጋራዥ ሥራና ከባድ የጉልበት ሥራ እንደ ባርያ ማገልገል ይጠበቅባቸዋል ሲሉም አክለዋል፡፡ በሊቢያ የሕገወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች ሰንሰለት እጅግ እየተጠናከረ በመምጣቱ ሰዎችን ገበያ ላይ እንደ ዕቃ መሸጥና መግዛት ልማድ እንደሆነ ድርጅቱ በተጨባጭ ማረጋገጡን ይናገራል፡፡ ድርጅቱ በርካታ ስደተኞች ማነጋገሩን የሚገልጹት ተወካዩ፣ በተለይም ሴቶች ዘግናኝ በሆነ ኢሰብዓዊ አያያዝ በእያንዳንዱ ግለሰብ ይደፈራሉ፣ ይደበደባሉ፣ በመጨረሻም እንዲከፍሉ የተጠየቁት ገንዘብ መክፈል ካልቻሉ ወዲያው ይገደላሉ፡፡ ወይም ከሞት ያልተናነሰ ዘግናኝ ድብደባ ተፈጽሞባቸው በአሰቃቂ ሁኔታ ይሞታሉ ብለዋል፡፡

ሞሐመድ አብዲከር የተባሉ የዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት የኦፕሬሽንና የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ ዳይሬክተር ለዘጋርድያን ጋዜጣ እንደገለጹት ከሆነ፣ እነዚህ ሕገወጥ አዘዋዋሪዎች ሴቶችን ለሾፌሮቻቸው ሳይቀር አስገድደው እንዲደፍሩዋቸው በደመወዝ መልክ እንደሚሰጥዋቸው ተናግረው፣ ‹‹ሁኔታው እጅግ በጣም ዘግናኝና አሳዛኝ ነው፡፡ ሊቢያ ውስጥ በቆየን ቁጥር በየቀኑ አዳዲስ ከዚህ በፊት ሰምተናቸው የማናውቅ ኢሰብዓዊ ተግባራትና ጭካኔ ነው የምንሰማውና የምናየው፣ እነዚህ ስደተኞች ሲናገሩ እንባቸው እንደ ጎርፍ ነው ከዓይናቸው የሚፈሰው፣ በጣም አስፈሪ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ብቻ ብዙዎቹ ዓለም አቀፍ ተቋማትና የመገናኛ ብዙኃን እንደሚገልጹት ከሆነ፣ እነዚህ በሊቢያ ውስጥ በሕገወጥ አዘዋዋሪዎች እጅ የሚገኙ ስደተኞች ችግርና ስቃይ ያንገላታቸው፣ በተስፋ መቁረጥና ጭንቀት ሰብዓዊ አካሎቻቸው እጅግ የተጎሳቆሉ ናቸው፡፡ ሞት በአካል ቆሞ የሚታይበት ምድር ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ 

 ይህም ሆኖ በአሁኑ ወቅት ብዙዎቹ ወጣቶች ያላቸውን ጥሪትና ገንዘብ ከፍለው ወደዚህ የገሃነም ምድር እየተጓዙ ነው፡፡ በዚህ የተነሳም ብዙዎቹ በንዴትና በፀፀት ስሜት ራሳቸውን ያጠፋሉ፡፡ የተቀሩት ደግሞ በከባድ የሥነ አዕምሮ ጭንቀት ለዕብደት ይዳረጋሉ፡፡

እነዚህ ሕገወጥ ደላሎች አሁንም ኢትዮጵያ ውስጥ ኤርትራውያን ስደተኞች በሚኖሩባቸው ካምፕ ሳይቀር በመግባት የወንጀል ድርጊታቸው ያከናውናሉ፡፡ በቅርቡ ከእነዚህ የስደተኞች ካምፕ በሕገወጥ ደላሎች ተታለው ወደ አውሮፓ ለመሻገር በከባድ የጭነት መኪና ተሳፍረው ሱዳን ውስጥ ሲጓዙ የነበሩ ከ60 በላይ ኤርትራውያንና ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ባጋጠማቸው የመኪና አደጋ አንድ የወሬ ነጋሪ እንኳን ሳይቀር አልቀዋል፡፡

ይህ ዘግናኝና አስከፊ አደጋ ማጋጠሙ እንደተነገረ ከቀናት በኋላ ደግሞ 26 ሕገወጥ ስደተኞችን ጭኖ ወደ ሱዳን በሌሊት ሲጓዝ የነበረ የጭነት መኪና ሁመራ አካባቢ እንደደረሰ ገደል ውስጥ ገብቶ አንድ ሰው ወዲያውኑ ሲሞት፣ የተቀሩት በከባድ ቆስለው ወደ ሽሬና መቀሌ ዓይደር ሆስፒታል ተወስደዋል፡፡ ይህ የሚነግረን ሀቅ ቢኖር ብዙዎች ጥረውና ግረው መለወጥ እየቻሉ በማይጨበጥ የደላሎች ተስፋ ተታለው ለከፋ አደጋ ችግር እየተጋለጡ መሆናቸው ነው፡፡

በእርግጥ በዚህ የሕገወጥ ደላሎች የሰንሰለት ሰዎችን የማዘዋወር ድርጊት ምክንያት እያለቀ ያለው ወጣት እጅግ ከመብዛቱ የተነሳ፣ ድርጊቱ የተወሳሰበ በመሆኑ በቀላሉ መከላከል የሚቻል አይደለም፡፡ የመንግሥት፣  የቤተሰብ፣ የሕዝብ የተለያየ በዚህ ጉዳይ የተሰማሩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትና የመገናኛ ብዙኃን የተቀናጀና ቀጣይነት ያለው ሥራ ይጠይቃል፡፡ በአንድ ወቅት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ሊቢያ ውስጥ በጽንፈኛው አይኤስ በአሰቃቂ ሁኔታ ሲገደሉ ጊዚያዊ አጀንዳና ቁጣ ፈጥሮ ተወራበት፡፡ የመንግሥትም ሆነ የግል መገናኛ ብዙኃን ሳይቀሩ ቢያንስ የሳምንት መነጋገሪያ አጀንዳቸው ሆኖ ስለሕገወጥ ስደትና ደላሎች ብዙ ተባለ፡፡ ሕገወጥ ስደት የሚያስከትለው አደጋና ችግር በየመንገዱ ሳይቀር የአገር ወሬ ሆነ ይህ ግን የሳምንት ረዘም ቢልም የአንድ ወር አጀንዳ ሆኖ አለፈ፡፡

የዜጎች በሕገወጥ መንገድ መሰደድና የደላሎች ወንጀል ግን በሳምንት የወሬ ጋጋታና ቁጣ የሚቆም አልሆነም፡፡ አደጋውና ውስብስብነቱ ገዝፎ የብዙ ቤተሰቦችን ሕይወትና ኑሮ እያናጋ፣ የብዙ ወጣቶች ሕይወት መቅጠፉን ቀጥሎበታል፡፡ ብዙዎች አሁንም ከላይ ወደ ገለጽኩት የገሃነም ምድር ገንዘብን ከፍለው ሰለባ ለመሆን በአሁኑ ወቅት እየተጓዙ ነው፡፡ እስኪ በዚህ ጉዳይ ላይ ሐሳብ ያላችሁ ወይም የችግሩ ሰለባ የሆናችሁ ካላችሁ በግልጽ እንነጋገርበት፡፡ ስለዚህ ጉዳይ እንጻፍ፣ የምናውቀውን እውነተኛ ታሪክ ለሌሎች እናካፍል፡፡ ለዛሬ በዚህ ይበቃኛል! በቀጣይ በሌሎች የሕገወጥ ስደተኞች እውነተኛ ታሪክ ያገናኘን፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡