Skip to main content
x

የሳምንቱ ገጠመኝ

ሰውየው በጠዋት ተነስተው ወደ ሥራ ሊሄዱ ሲነሱ ባለቤታቸው ቤት ውስጥ የሉም፡፡ መፀዳጃ ቤት ደርሰው ከተጣጠቡ በኋላ ለባብሰው ቁርስ ፍለጋ ወጥ ቤት ቢገቡ ምንም ነገር የለም፡፡ የሻይ ፔርሙዙም ባዶ ነው፡፡ የባለቤታቸው ቤት ውስጥ አለመኖርና ቁርስ አለመዘጋጀቱ ከንክኖአቸው ስለነበር፣ ሞባይል ስልካቸውን ከኪሳቸው አውጥተው ወደ ባለቤታቸው ይደውላሉ፡፡ ባለቤታቸውም በፍጥነት መስመር ውስጥ ይገባሉ፡፡ ሰውየው፣ ‹‹ለመሆኑ በጠዋት የት ነው የሄድሽው?›› በማለት ይጠይቃሉ፡፡ ሴትዮዋም የዕድር ጥሩንባ ሰምተው ለቅሶ ለመድረስ መሄዳቸውን ይናገራሉ፡፡ ሰውየውም፣ ‹‹ታዲያ ሥራ እንደምገባ እያወቅሽ ለምን ቁስ አልሠራሽልኝም?›› ብለው ሲጠይቁ፣ ‹‹በጣም የሚጣፍጥ ቁርስ ሠርቼ ነበር፡፡ ነገር ግን በጣም ስለቸኮልኩ የአንተንም የእኔንም በልቼው ሄድኩ፤›› ብለው ሚስት ሲመልሱ፣ ‹‹ብትቸኩይማ እንኳን የእኔን የራስሽንም አትበይውም ነበር፤›› ብለው ወደ ሥራቸው ሄዱ በማለት ይህንን ቀልድ መሰል ነገር የነገረኝ ጓደኛዬ ነው፡፡

ሰውየው እንዳሉት ሴትዮዋ እጅ የሚያስቆረጥም ቁርስ ቢሠሩም ቢቸኩሉ ኖሮ በእርግጥም አይበሉትም ነበር፡፡ ነገር ግን እንዲያው ስንጠራጠር ያንን ተከሽኖ የተሠራ ቁርስ ሁለት ቦታ ካካፈሉ በኋላ የራሳቸውን በልተው ጨርሰው ሲጥማቸው፣ ከባላቸው ላይ መቆነጣጠር ሲጀምሩ ነው ሳያስቡት ሙልጩን ያወጡት፡፡ ‹‹የበሰበሰ ዝናብ አይፈራም›› እንደሚባለው መሆኑ ነው፡፡ የችኮላ ነገር ሲነሳ በዚህ ዘመን በጣም የሚያሳስቡ ነገሮች አሉ፡፡ እስኪ መንገዱን ልብ በሉና እዩት፡፡ ከከባድ የጭነት መኪና እስከ ትንሿ ቪትዝ ድረስ መክነፍ ነው፡፡ ከአፍ እስከ ገደፍ ጢም አድርጎ ሰዎችን ያሳፈረ የከተማ አውቶብስ ‹‹ፎርሙላ ዋን›› ውድድር ላይ ያለ ይመስል ይፈተለካል፡፡ አሸዋ፣ ጠጠር ወይም ብረት ዘጭ አድርጎ የጫነ ሲኖትራክ ወደ ላይ ለመብረር ይቃጣዋል፡፡ ከወጣት እስከ አዛውንት (በሁለቱም ፆታዎች) የሚነዱዋቸውን አውቶሞቢሎች ክንፍ ያስገጠሙላቸው ይመስላሉ፡፡ ይህ ሁሉ አስፈሪ ትዕይንት በሚታይበት አዲስ አበባ የመንገድ ላይ የትራፊክ ምልክቶችም ሆኑ እነሱን ተክተው የሚሠሩ የመንገድ ላይ መስመሮች አይከበሩም፡፡ የዜብራ ማቋረጫ ተንቆ በየቀኑ ሰው ይገጭበታል፡፡ የዚህ ሁሉ መንስዔ ግን ከመጠን ያለፈ ጥድፊያና ችኮላ ነው፡፡

ሰፊው ሕዝብ የሚመገብባቸው ምግብ ቤቶች ጎራ በሉ፡፡ ምግብ የሚበላ ሳይሆን ጦርነት የሚካሄድ ነው የሚመስለው፡፡ በተለይ አፍላ ጎረምሶች የተለያዩ ምግቦችን በጋራ ማዕድ አስቀርበው ሲመገቡ ከአመጋገብ ወግና ልማድ ያፈነገጡ ድርጊቶችን እየፈጸሙ ነው፡፡ ምግብ ሲበላ ለአፍ የሚመጥን ጉርሻ ይዘጋጅና በሥርዓቱ ወደ ውስጥ ይላካል፡፡ ከዚያም በምላስ አጋዥነት መንጋጋ በሚገባ እያላመጠ ወደ ጉሮሮ ሲወርድ ማጣጣም የሚባል የተፈጥሮ ፀጋ ያጅበዋል፡፡ በዚህ መሠረት መመገብ ዕርካታን ከመፍጠሩም በላይ የመፍጨት ሒደቱን ዘና ያደርገዋል፡፡ ካላስፈላጊ መጨናነቅና ያልታሰበ ትንታም ይከላከላል፡፡ ይህ ተፈጥሯዊና ሳይንሳዊ አመጋገብ ለዓይን በሚዘገንኑ ጉርሻዎችና ትንፋሽ በሚያሳጥሩ የአፍ ውስጥ መወጠሮች ተተክቶ፣ አመጋገብ የውጊያ ቀጣና መስሏል፡፡ በሽሚያ ተጀምሮ በሽሚያ የሚያልቀው አጓጉል አመጋገብ ለዛው ጠፍቶና የማዕድ ሥርዓት ብልሽትሽቱ ወጥቶ ማየት ደስ አይልም፡፡ በገበታው ዙሪያ የሚታየው መጣደፍና ሳያጣጥሙ መመገብ የዘመናችን መገለጫ ሆኗል፡፡ ሁሉም በጥድፊያና በችኮላ  የድርሻውን አንስቶ ወደሚሄድበት ይነጉዳል፡፡

እነዚህን ከላይ የተጠቀሱትን ምሳሌዎች ያነሳሁት ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ በቀደም ዕለት አመሻሽ ላይ ሒልተን ሆቴል ቢራ ለመጠጣት እሄዳለሁ፡፡ አንዳንዴ እዚያ ሄጄ የቀዘቀዘ ቢራ መጠጣትና ከጓደኞቼ ጋር መጫወት ደስ ይለኛል፡፡ የዚያን ዕለት ከአንድ ጓደኛዬ ጋር ተቀጣጥረን የምንነጋገርበት ጉዳይ ስለነበረ፣ እንደተለመደው ቀዝቃዛውን ቢራ እየተጎነጨን ስናወራ አንድ በርቀት የምናውቀው ሰው ይመጣል፡፡ እኔ ይህንን ሰው ከሁለት ዓመታት ወዲህ ዓይቼው አላውቅም፡፡ ቅርበት ስለሌለንም ትዝ አይለኝም፡፡ የዚያን ቀን ግን እየሳቀ መጥቶ ሰላምታ ሲያቀርብልን ጥድፊያው ለየት ያለ ነበረ፡፡ ለሳምንት ያህል የተለያየን እስከማይመስል ድረስ እንደ ነገሩ ሰላም ብሎን ወንበር ስቦ ተቀመጠ፡፡ ወዲያው ከተለያዩ ኪሶቹ ውስጥ አምስት የሞባይል ቀፎዎች አውጥቶ ጠረጴዛው ላይ ደረደራቸው፡፡ ልክ ለገበያ እንደሚቀርቡ አስመስሎ፡፡ በየተራ ስልኮቹን እያነሳ እየደወለ ከተለያዩ ሰዎች ጋር ሲነጋገር ከመጣደፉ የተነሳ ምን እንደሚናገር ለመስማት አዳጋች ነበር፡፡ ከሞላ ጎደል ያወቅነው ግን ተባራሪ ሥራ ላይ መሆኑን ነው፡፡

እኔ ደግሞ ጥሎብኝ ሁካታና ጥድፊያ ስለማልወድ፣ ‹‹ስለሥራ እኮ ቀስ ተብሎና ዞር ተብሎ ነው በስልክ የሚወራው፡፡ እባክህ ሰው መሀል ሁነህ እየጮህክ አትነጋገር. . .›› ስለው፣ አሁንም በተጣደፈ ምላሽ፣ ‹‹ችግር የለውም. . . ደግሞ ለሐበሻ. . . ሁሉ በእጃችን ሁሉ በደጃችን. . .››እያለ መናገር ሲጀምር ውስጤ በንዴት ቦግ አለ፡፡ እንደምንም ራሴን በመቆጣጠር ዝም አልኩ፡፡ ጓደኛዬ ለካ የእኔ ንዴት ተጋብቶበት ኖሮ፣ ‹‹አንተ አትሳደብ እንጂ. . . ምን ብትጠግብ ሕዝብ ትሳደባለህ እንዴ. . . የማላውቅህ መሰለህ እንዴ. . .›› እያለ በኃይለ ቃል ሲናገረው ሰውየው ደንገጥ አለ፡፡ ይኼኔ ወደ ሰውዬው ዞሬ፣ ‹‹እባክህ ሁለታችን የግል ጉዳይ ስለያዝን ሌላ ጠረጴዛ ትቀይር?›› ስለው ስልኮቹን ሰብስቦ እየተቆናጠረ ጥሎን ሄደ፡፡ ኃፍረት ይዞት ወይም ተናዶ እንደሆነ አላውቅም ከአካባቢው እልም ብሎ ጠፋ፡፡ እኔና ጓደኛዬ ባጋጠመን ድንገተኛ ጉዳይ እየተገረምን ወደ ወሬያችን ተመለስን፡፡

እኔና ጓደኛዬ ወሬውንም ቢራውንም አጠናቀን ቢል እንዲመጣልን ለአስተናጋጁዋ ምልክት ስናሳይ አንድ የማናውቀው ሰው ሰላም ብሎን ወንበር ስቦ ተቀመጠ፡፡ እኔም ጓደኛዬም ከዚህ በፊት አላየነውም፡፡ ሰውየው የተረጋጋ ሲሆን፣ አኳኋኑ ደግሞ ጨዋነት የተላበሰ ነው፡፡ ‹‹ቅድም ያ ባለጌ ሰውዬ ሲያበሳጫችሁ እያየሁ ነበር፡፡ በእርግጥ በቅርበት ሳይሆን በሩቅ እንደምታውቁት ገምቻለሁ፡፡ ይህ ሰው ምን እንደሚሠራ ታውቃላችሁ?›› ሲለን ሁለታችንም አንገታችንን በአሉታ ነቀነቅን፡፡ ‹‹ይኼ ሰውዬ የከተማ አውደልዳይ ነው፡፡ ጉዳይ አስፈጽማለሁ እያለ ከበርካታ ሰዎች ገንዘብ ይቀበላል፡፡ ባለጉዳዮችን ከባለሥልጣናት ጋር ለማገናኘት፣ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ወጣ ገበያ እያለ ጉዳይ ለማስፈጸም፣ ግብርና ታክስ ለማስቀነስ ወይም ለማሰረዝ፣ መሬት ለማሰጠት. . . እያለ ብዙዎችን የሞለጨ ሌባ ነው፤›› ሲለን እኔና ጓደኛዬ ተገረምን፡፡ ‹‹ሌባ ከሆነ ሰዎች እንዴት ያምኑታል?›› ስለው፣ ‹‹ብዙዎቹ ችኩልና ከላይ ከላይ የሚሮጡ ናቸው፡፡ በሕገወጥ መንገድ የሚያገኙትን እያሰቡ ሲጣደፉ የሌባ ሲሳይ ይሆናሉ. . .›› ብሎ ሲነግረን ሁለታችንም ሳናስበው ሳቅን፡፡ ቸኩያለሁ ያሉ ሚስት የባላቸውን ቁርስ እንደጠረጉት ሁሉ፣ ምድረ ችኩል ደግሞ ራሱንም አገርንም ያስጨረግዳል፡፡

(መስፍን ደምሴ፣ ከሾላ)