Skip to main content
x

የሳምንቱ ገጠመኝ

ሆሌም ሠራተኞች ሜይ ዴይ ሲደርስ የተጠራቀሙ ብሶታቸው ይደመጣል፡፡ የፕሬስ ነፃነት ቀን ሲከበር የጋዜጠኞች ብሶት ይሰማል፡፡ እኛን በመሰሉ አገሮች ከመደራጀት እስከ ሰብዓዊ መብት ይዞታ ድረስ ያሉ ችግሮች ደግሞ ዘወትር እሮሮ ይደመጥባቸዋል፡፡ ለእኛ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት በወረቀት ላይ ቢሰፍርም ርቆ እንደተሰቀለ ዳቦ እንቁልልጭ ሆኖብናል፡፡ የሰብዓዊ መብት አያያዛችን የዓለም መነጋገሪያ ርዕስ ነው፡፡ እንኳን ተደራጅቶ ሰላማዊ ትግል ማድረግ የፈለጉትን መደገፍ ብርቅ ነው፡፡ ይህ ሁሉ እየሆነ ያለው ደግሞ መሠረታዊ የሚባሉት መብቶች በሕገ መንግሥት ሰፍረው ተግባራዊ የሚያደርጋቸው በመጥፋቱ ብቻ ሁልጊዜ ለቅሶ ነው፡፡ መንግሥት ደግሞ ከሁለት አሥርት በኋላም ‘የታዳጊ አገር ችግር ነው’ እያለ ያሾፋል፡፡ ማደግ እየተቻለ አለማደግን ማመካኛ ማድረግ ያናድዳል፡፡ እስቲ ነገር በምሳሌ እያልኩ አንዳንድ ጉዳዮችን ላንሳ፡፡ በቀልድ ሳይሻል አይቀርም፡፡ ቀለል ይበለና፡፡

አሜሪካ ውስጥ ነው አሉ ይህ ቀልድ ከዓመታት በፊት የተነገረው፡፡ ሰውዬው እኔ ነኝ ያለ የናጠጠ ከበርቴ ነው፡፡ ቢሊየነር፡፡ ዕድሜ ልኩን ለፍቶ በሀብት ባህር ውስጥ ቢዋኝም ሚስትም ልጆችም አልነበሩትም፡፡ ‘ዞሮ ዞሮ ከቤት፣ ኖሮ ኖሮ ከመሬት’ እንዲሉ፣ ሰውዬው ዕድሜው ተገባዶ የሞቱ ቀን ይቃረባል፡፡ ይኼኔ ከሀብቱ አብዛኛውን ለተለያዩ ፋውንዴሽኖችና የዕርዳታ ድርጅቶች አከፋፍሎ ካበቃ በኋላ 30 ሚሊዮን ዶላር ይቀረዋል፡፡ ይህ ገንዘብ ከራሱ ጋር እንዲቀበር ፈለገ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ከለፋበት ገንዘብ ትንሽም ቢሆን ከእሱ ጋር መሄድ እንዳለበት ነው፡፡ ይህ እንግዲህ የባለፀጋው ውሳኔ ነው፡፡ ውሳኔውንም ተግባራዊ ለማድረግ በሕይወቱ ውስጥ ወሳኝ ሥፍራ የሰጣቸውን ሦስት ሰዎች መጥራት ነበረበት፡፡

እነዚህ ሰዎች የንስሐ አባቱ፣ ሐኪሙና ጠበቃው ናቸው፡፡ ሦስቱንም ድል ያለ የምሳ ግብዣ አዘጋጅቶ ካበላቸውና ካጠጣቸው በኋላ በስጦታ መልክ ጠቀም ያለ ጉርሻ ሰጣቸው፡፡ ከዚያም ቡና እየጠጡ ሐሳቡን ገለጸላቸው፡፡ የበላ ሆድ አይጨክንምና በሐሳቡ ተስማሙ፡፡ በከበርቴው ውሳኔ መሠረት ሦስቱም በነፍስ ወከፍ አሥር ሚሊዮን ዶላር ወስደው እሱ ሲሞት የአስከሬን ሳጥኑ ውስጥ ለማስገባት አደራ ተቀበሉ፡፡ ከሳምንታት በኋላ ባለፀጋው ሞተ፡፡ የቀብር ሥርዓቱም በሚገባ ተፈጸመ፡፡ ሐዘኑም እየቆየ ተረሳ፡፡ ሰውየው ከዚህ ዓለም በሞት ከተለየ ዓመት ሆነው፡፡ አንድ ቀን ቄሱ የዚያ የከበርቴ ወዳጃቸው ሙት ዓመት መድረሱ ትዝ ሲላቸው አንድ ነገር ለማድረግ ወሰኑ፡፡

በውሳኔያቸው መሠረት ባለፀጋው በሞተበት ቀን ለሐኪሙና ለጠበቃው ጉዳዩን ገልጸው የምሳ ግብዣ አሰናዱ፡፡ ሦስቱም በቀጠሮአቸው መሠረት ተገናኝተው ከበርቴውን ወዳጃቸውን እያሰቡ ምሳ በሉ፡፡ ወይናቸውንም ጠጡ፡፡ በመጨረሻም ቡና ጠጥተው ሊለያዩ ሲሉ ቄሱ ንግግር ላድርግ አሉ፡፡ ሁለቱም ለማዳመጥ ተዘጋጁ፡፡ ‹‹ወንድሞቼ ያ ደግ ወዳጃችንን ፈጣሪ ነፍሱን ይማርልን፤›› ሲሉ ሁለቱም በፍጥነት ‹‹አሜን!›› አሉ፡፡ ቄሱ ቀጠሉ፡፡ ‹‹እንደምታስታውሱት ሦስታችንም አደራ ተጥሎብን ነበር፡፡ በእርግጥ አደራው ከባድ ነው፡፡ ግን እኔ ትንሽ ሥጋዬ አሳስቶኝ ከሰጠኝ አሥር ሚሊዮን ዶላር ውስጥ ሳጥኑ ውስጥ ያስገባሁት አንድ ሦስተኛውን ብቻ ነው…›› ሲሉ ሐኪሙ በመገረም እያያቸው፣ ‹‹አይ አባ ለካ እርስዎ ከእኛ የባሱ ነዎት፡፡ እኔ እንኳን ግማሹን ነው የከተትኩለት…›› አለ፡፡

ይህ ሁሉ ሲሆን ጠበቃው ቡናውን ፉት እያለ ሁለቱንም በትዝብት ያያቸው ነበር፡፡ ይኼን ጊዜ ሐኪሙ፣ ‹‹ወንድም ጠበቃ ተናገር እንጂ፡፡ ምነው ዝምታህና ትዝብትህ በረታ?›› ሲለው፣ ‹‹ከእናንተ ዓይነቶቹ አሳዛኝ ሰዎች ጋር የዚያ ደግ ሰው ወዳጅ መባሌ ያሳዝነኛል…›› ብሎ አሁንም ዝም አለ፡፡ ቄሱ ኃፍረት እየተሰማቸው፣ ‹‹እና አንተ ሁሉንም ገንዘብ ሳጥኑ ውስጥ ገለበጥኩት እያልክ ነው?›› ብለው መሬት መሬት ሲያዩ፣ ‹‹እኔ እኮ በሙያ ሥነ ምግባሬ የምኮራ፣ የሰው ሰባራ ሳንቲም የማልፈልግ፣ ለዚህም ማንም ሰው የሚመሰክርልኝ…›› እያለ በኃይለ ቃል ሲናገር ሐኪሙ ጣልቃ ገብቶ፣ ‹‹እውነት አንተ አሥር ሚሊዮን ዶላሩን ሳጥኑ ውስጥ ዓይንህ እያየ ከተትክ?›› ለማረጋገጥ ጥያቄ ሲያቀርብ፣ ‹‹ግጥም አድርጌ ነዋ!›› ብሎ መለሰለት፡፡ አሁን ቄሱ ተጠራጥረው፣ ‹‹ለመሆኑ ዶላር የያዘውን ከረጢት ሳጥኑ ውስጥ አራገፍክ?›› ሲሉት፣ ‹‹እናንተ ደግሞ በዚህ በሠለጠነ ዘመን ጥሬ ገንዘብ ሳጥን ውስጥ ይራገፋል እንዴ? በቼክ ነው ያስገባሁለት…›› ከማለቱ የሁለቱ ሳቅ ከአሜሪካ አልፎ ቻይና ድረስ ተሰማ አሉ፡፡ ወደው አይስቁ አሉ፡፡ እኛስ እንዲህ አይደል የምንሸወደው?

እኛም አገር አንድ ቀልድ አለ፡፡ ዶሮ አገር ሰላም ብላ እንቅልፏን ስትለጥጥ በሌሊት በሯ ተንኳኳ፡፡ በዚህ ደረቅ ሌሊት ማን ነው የሚያንኳኳው ብላ ከቆጧ ዘላ ወረደች አሉ፡፡ ከዚያም ተንደርድራ ሄዳ በሩን ስትከፍት ሦስት ዶሮዎች ቆመዋል፡፡ ‹‹ምን ሆናችሁ ነው ከጩኸታችን በፊት የምትቀሰቅሱኝ?›› ስትል አንዱ አውራ ዶሮ ጠጋ ብሎ፣ ‹‹መርዶ ልናረዳሽ ነው፤›› አላት፡፡ ደንገጥ ብላ፣ ‹‹የምን መርዶ?›› ስትለው አንዷ ቄብ ዶሮ ቀልቀል እያለች፣ ‹‹እናትሽ ሞታ ነዋ!›› ስትላት ሦስቱንም በቁጣና በመገረም አየቻቸው፡፡ ይኼኔ ሌላኛዋ ዶሮ፣ ‹‹እናትሽ ሞታ አታለቅሽም እንዴ?›› አለቻት፡፡ እሜቴ ዶሮ፣ ‹‹ትሙታ!›› አለች፡፡ ሦስቱም ደንግጠው በአንድነት ‹‹እንዴ?›› ሲሏት፣ ‹‹ኖረችም ጭሬ፣ ሞተችም ጭሬ ነው የምኖረው…›› ብላ በሯን ዘጋችባቸው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ‘ዶሮ ምን አለች?’ ሲባል፣ ‘ኖረችም ጭሬ፣ ሞተችም ጭሬ…’ እየተባለ ይተረታል፡፡ የእኛም ነገር እንዲህ ይመስለኛል፡፡ ሁሌ በነገር እንደተጫጫርን፡፡ (ወለላው አስረስ፣ ከአፍንጮ በር)