Skip to main content
x
content/መንግሥት-ሙስናን-ለመታገል-ቁርጠኝነት-ካለው-የራሱን-ጓዳ-ይፈትሽ

content/መንግሥት-ሙስናን-ለመታገል-ቁርጠኝነት-ካለው-የራሱን-ጓዳ-ይፈትሽ

የዓረብ ባህረ ሰላጤ አገሮች የገቡበት ቀውስ ወደ አፍሪካ ቀንድ እየተዛመተ ነው፡፡ ከቀድሞ ወዳጆቿ ጋር ችግር ውስጥ የገባችው ኳታር ፊታቸውን በነሷት ኤርትራና ጂቡቲ ሳቢያ አኩርፋ፣ በሁለቱ ባላንጣዎች ድንበር አካባቢ ያሠፈረችውን ጦር ስታነሳ የቀውሱ አንድ አንጓ ወደ አካባቢያችን አምርቷል፡፡ ወትሮም ከጂቡቲ ጋር በድንበር ጉዳይ የምትወዛገበው ኤርትራ፣ አጋጣሚውን ተጠቅማ የራስ ዱሜራ ኮረብታዎችንና ደሴቶችን መቆጣጠሯ ሌላ ዙር ውዝግብ ቀስቅሷል፡፡ የአፍሪካ ቀንድ ባብኤል መንደብ በተባለው የኤደን ሰላጤን ከቀይ ባህር ጋር በሚያገናኘው ሰርጥ ምክንያት፣ በዓለም ላይ ካሉ ታዋቂ ስትራቴጂካዊ ሥፍራዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ ይህ አካባቢ አውሮፓን ከደቡብ፣ ከደቡብ ምሥራቅና ከምሥራቅ እስያ ጋር የሚያገናኝ ሁነኛ ጠባብ መተላለፊያ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በአካባቢው የባህር የበላይነት ለማግኘትና ጥቅሞቻቸውን ለማስከበር ሲሉ አገሮች የባህር ኃይሎቻቸውን አስፍረዋል፡፡ የባህር ላይ ውንብድና አስቸጋሪ በነበረበት ወቅት ደግሞ ቻይና ሳትቀር እዚህ አካባቢ ሠፍራለች፡፡ የባህረ ሰላጤው አገሮችም ለተለያዩ ዓላማዎች ሲያንዣብቡ ነበር፡፡ የተሳካላቸውም የጦር ሠፈር መሥርተዋል፡፡ አሁን ደግሞ የሳዑዲ ዓረቢያ መራሹ ኃይል ኳታርን በሽብርተኝነት ወንጅሎ ግንኙነቱን ሲያቋርጥ፣ ችግሩ ወደ አፍሪካ ቀንድ ጎራ ብሏል፡፡ ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ብልኃትና ንቃት ያስፈልጋል፡፡

እንደሚታወቀው የአፍሪካ ቀንድ ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ጂቡቲ፣ ሶማሊያ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ደቡብ ሱዳንና ሱዳንን የሚያቅፍ ነው፡፡ እነዚህ አገሮች ደግሞ ከዓረብ ባህረ ሰላጤ አገሮች ጋር በታሪክ፣ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በባህል፣ በሃይማኖትና በተለያዩ ጉዳዮች ስለሚተሳሰሩ እዚያ አካባቢ ችግር ሲፈጠር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ያገኛቸዋል፡፡ በመካከለኛው ምሥራቅ በተለያዩ ጊዜያት የተፈጠሩ የፖለቲካ ሽኩቻዎች በአፍሪካ ቀንድ ላይ ተፅዕኖአቸው ይታወቃል፡፡ ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት ደረጃ የአፍሪካ ቀንድ ማዕከል እንደ መሆኗ መጠን፣ ከኤርትራ ጋር ለዓመታት በገባችበት ውዝግብ ምክንያት፣ ወደብ አልባ ስለሆነች የጂቡቲና የአካባቢው ወደቦች ጥገኛ ከመሆኗ አንፃርና ከሌሎች ጂኦ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ትልቅ የቤት ሥራ አለባት፡፡ በእርግጥ ሳዑዲ መራሹ ኃይልና ኳታር የገቡበትን ውዝግብ ተከትሎ ጎራዎችን ከመቀላቀል ይልቅ፣ በገለልተኝነት ችግሩ በውይይት እንዲፈታ አቋም መያዙ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ይህም አቋም ከአገሪቱ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ የሚመነጭ መሆኑ በይፋ ተገልጿል፡፡ አንድ አገር በመርህ ላይ ተመሥርቶ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለው አቋም ሲያራምድ ይመሰገናል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንን አቋሙን አጠናክሮ የመቀጠሉና ያለመቀጠሉ ጉዳይ የሚወሰነው ወደፊት በሚፈጠሩ ክስተቶች ላይ ሊመሠረት እንደሚችልም መገንዘብ ይገባል፡፡ ይህ ደግሞ ማንም አገር ብሔራዊ ጥቅሙን ከሚያሠላበት ማዕዘን አንፃር የሚቃኝ ነው፡፡ የሆኖ ሆኖ ግን አሁን እየታየ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የዲፕሎማሲ ሥራው እጅግ በጣም ፈጣን፣ ከተለዋዋጭ ሁኔታዎች ጋር የሚገናዘብና ብልኃትና ንቃት የታከለበት መሆን ይኖርበታል፡፡

ኢትዮጵያ በአካባቢው ካሉት አገሮች አንፃር ስትታይ የራሷ ልዩ መገለጫዎች አሉዋት፡፡ የእንግሊዝ፣ የፈረንሣይና የጣሊያን ቅኝ ገዥዎች አካባቢውን እንደ ቅርጫ በተቀራመቱበት ወቅት ኢትዮጵያ ከእነሱ ጋር በመፋለም ነፃነቷን ያስረከበች ልዩ አገር ናት፡፡ በጀግኖች ልጆቿ መስዕዋትነት፡፡ ምንም እንኳ ኤርትራ ቀደም ሲል በቅኝ ገዥዎች መዳፍ ውስጥ ያሳለፈችና ካለፉት 26 ዓመታት ወዲህ ደግሞ ከኢትዮጵያ የተለየች ብትሆንም፣ በአካባቢው ሰፊ የባህር ተጋሪ አገር በመሆኗ አሁንም ልዩ ትኩረት ያስፈልጋል፡፡ የኤርትራ መንግሥት በሚያሳየው የጀብደኝነት ባህሪ ምክንያት አቋሙን እየቀያየረ ያዋጣኛል የሚለውን ጎራ ሲደባለቅ፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ኢትዮጵያን የሚጎዳ ማናቸውንም ድርጊት ከመፈጸም ወደ ኋላ አይልም፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በተደጋጋሚ ማዕቀብ የተጣለበት የኤርትራ መንግሥት በየመን ዘመቻ የሳዑዲ መራሹን ኃይል ደግፎ ጦር ሲያዘምት፣ አሁን ደግሞ የኳታር ወታደሮች የለቀቁትንና ጂቡቲ ጥያቄ የምታነሳበትን ሥፍራ መልሶ ወሮ ሲይዝና ነገ ከነገ ወዲያ አካባቢውን ለማተራመስ ሲሯሯጥ፣ ዓለም አቀፍ ሕግ እንዴት እንደሚሠራ ማወቅ ተገቢ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል ሆና የዲፕሎማሲው ሥራ ይጠፋታል ለማለት ሳይሆን፣ በዚህ ፈጣንና ተለዋዋጭ ዓለም ውስጥ ነቃ ማለትና ብልኃትን መዘንጋት ተገቢ አይደለም ለማለት ነው፡፡ ለአጉል ጀብደኛ የዲፕሎማሲ ጡንቻ ማሳየት ስለሚገባ፡፡

የዓረብ ባህረ ሰላጤ አገሮችና ግብፅ ጭምር በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ሲርመሰመሱ ለምን መጣችሁ ተብሎ ግስላ መሆን ተገቢ ባይሆንም፣ ሁሉንም እንዳመጣጡ በጥበብ አስተናግዶ ጥቅምንና ብሔራዊ ደኅንነትን ማስከበር የመንግሥት ወግ ነው፡፡ ሁለት ተቀናቃኝ ኃይሎች ድንገት ተነስተው ጠብ ሲፈጥሩና አንዱ ሌላውን አሸባሪ እያለ ሲወነጅል፣ በተቻለ መጠን ገለልተኛ ሆኖ ሰላማዊ መፍትሔ እንዲገኝ ጥረት ማድረግም ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን እዚህ በውስብስብ ግንኙነት የተለወሰ እሰጥ አገባ ውስጥ ያለውን ድብቅ አጀንዳ ደግሞ በብልጠት ተከታትሎ ማወቅ የግድ ይላል፡፡ በነዳጅ ሀብት የከበሩ ኃይሎች አንዲት ደሃ አገር (የመን) ላይ ያደረሱን ፍጅትና ውድመት እያጤኑም ጉዳዩን በጥልቀት መገምገም ብልህነት ነው፡፡ ዛሬ ወዳጅ ያደረጉት ነገ ጠላት፣ ትናንት ጠላት የነበረው ዛሬ ወዳጅ መሆኑ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ከዘላቂ ወዳጅነት ይልቅ ዘላቂ ጥቅም የሚቀድመውም ለዚህ ነው፡፡ ትናንት በድንበር ጉዳይ ሲወዛገቡ የነበሩት ኤርትራና ጂቡቲ በድርድር አማካይነት ተለሳልሰው የሚወዛገቡበትን አካባቢ ለኳታር ጦር አስረክበው ነበር፡፡ በሳዑዲ መራሹ የየመን ጦርነት ውስጥም ከኳታር ጋር ተሳታፊ ነበሩ፡፡ አሁን ደግሞ ከሳዑዲ ጋር በመወገናቸው ምክንያት የትናንት ወዳጃቸው ኳታር ድንበሩን ትታ ስትወጣ የአንድ ጎራ ደጋፊ ቢሆኑም፣ ሁለቱም ተመልሰው ወደ ነበረው ጠላትነታቸው ገብተዋል፡፡ ጊዜያዊው ዓላማ እንኳ ትዕግሥት አልሰጣቸውም፡፡ ኢትዮጵያ ግን መርህ አልባ መሆን የለባትም፡፡

በዓረብ ባህረ ሰላጤ አገሮች ቀውስ ምክንያት የአካባቢው ግለት ጨምሯል፡፡ ወትሮም በተለያዩ ችግሮች ቋፍ ውስጥ ያለው የአፍሪካ ቀንድ ከሁለቱ አገሮች በተጨማሪ፣ ሶማሊያ ባራመደችው አቋም ምክንያት ገጽታው ሊቀየር ይችላል፡፡ ሶማሊያ የሁለቱን ጎራ አልቀላቀልም በማለቷና ገለልተኛ አቋም በመያዟ ምክንያት ዳዴ በማለት ላይ የሚገኘው አዲሱ መንግሥቷ ፈተና ውስጥ ገብቷል፡፡ በሌሎች አገር የበረራ ፈቃድ የተከለከለው የኳታር አየር መንገድ፣ በሶማሊያ ሰማይ ላይ በርካታ በረራዎችን እንዲያደርግ መፈቀዱ እነ ሳዑዲን አስቀይሟል፡፡ ሶማሊያ ከእነ ሳዑዲ ዳጎስ ያለ የገንዘብ ስጦታ ቢቀርብላትም፣ ለሁለቱ ወገኖች ወዳጅ መሆን እንጂ ጎራ መቀላቀል እንደማትፈልግ አስታውቃ አልቀበልም ብላለች፡፡ ይህ ውሳኔዋ የቅጣት በትር እንዲዘጋጅላት ሰበብ ሆኗል፡፡ አዲሱን የሶማሊያ መንግሥት እያቋቋሙ ያሉት የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስና የሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥታት በርካታ የተቃዱ ፕሮጀክቶቻቸውን መሰረዛቸው ተሰምቷል፡፡ በጦርነት የወደመችው ሶማሊያ በዓረብ ባህረ ሰላጤ አገሮች የታሰቡላት የመልሶ ግንባታ ፕሮጀክቶች እየተጠፉባት ያለው ገለልተኛ አቋም አራምዳለሁ በማለቷ ነው፡፡ ሶማሊያ ሁለቱን ወገኖች በወዳጅነትና በገለልተኛነት ለማየት የመረጠችበት ምክንያት አልተወደደም፡፡ ኢትዮጵያ ምንም እንኳ እስካሁን በገለልተኝነቷ ሳቢያ የደረሰባት ችግር ባይኖርም፣ በአሁኑ ጊዜ በአካባቢው ፈርጠም ያለችና ተደማጭ በመሆኗ ምንም ባትባልም፣ ነገ ተነገ ወዲያ ምን ሊፈጠር ይችላል ለሚለው ግን በብቃት መልስ ማግኘት አለባት፡፡ ንቃት የታከለበት ብልኃት መኖር የግድ ነው፡፡ ብልጠት የተካነ ዲፕሎማሲ ያስፈልጋል፡፡

በሌላ በኩል የዓረብ ባህረ ሰላጤ አገሮች ቀውስ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ወደ አፍሪካ ቀንድ እየተዛመተ ወትሮም እንደነገሩ የሆነውን ሰላም እንዳያናጋና አካባቢው ወደነበረበት አዘቅት እንዳይመለስ ብርቱ መሆን የግድ ይላል፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ለአገራችን ካለን ፍቅርና አክብሮት በመነሳት ልክ እንደ ጀግኖቹ አባቶቻችንና እናቶቻችን ለአገራችን ዘብ መቆም አለብን፡፡ ፖለቲካና መሰል ልዩነቶችን ወደ ጎን በማለት አገር ሊያፈራርስ የሚችል እንቅስቃሴን ማምከን አለብን፡፡ አንዳንድ አርቆ ማሰብ እንደ ጎደላቸው ጽንፈኞች ሳይሆን፣ አገሩን እንደሚያፈቅር ኩሩ ዜጋ ይህ ቀውስ እንዴት እንደሚመከት ሐሳብ ማዋጣት ተገቢ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ቀውሱንና ሊከተል የሚችለውን አደገኛ ውጤት እንደ መልካም አጋጣሚ የሚያዩ ራዕይ አልባዎች ወደ ልቦናቸው ሊመለሱ ይገባል፡፡ መንግሥትም በዚህ ወሳኝ ወቅት የአገሪቱ አንጋፋ ምሁራን፣ ዲፕሎማቶች፣ የዕውቀትና የልምድ ባለቤት የሆኑ ባለሙያዎች፣ ተመራማሪዎችና ሌሎች በጎ ፈቃደኛ ዜጎች የሚሳተፉበት መድረክ ማዘጋጀት ይገባዋል፡፡ በአባቶቻችንና በእናቶቻችን የጀግንነት ገድል ለትውልድ የተላለፈች እናት አገር የአሁን ዘመን ልጆቿን ሁለገብ ተሳትፎ ትፈልጋለች፡፡ ኢትዮጵያ የማንም ተላላኪና መርህ አልባ ያልሆነች ታሪካዊ አገር ናት፡፡ ለዓለም ጥቁር ሕዝቦች ተምሳሌት የሆነውን የዓድዋ ታላቁን ፀረ ኮሎኒያሊስት ጦርነት በድል የደመደመች የኩሩዎች አገር ናት፡፡ ኢትዮጵያነት ጀግንነት፣ አርቆ አሳቢነት፣ አስተዋይነትና ርህራሔ የተሞሉበት ታላቅ እሴት ነው፡፡ ይህንን ታላቅ እሴት መጠበቅ የሚቻለው በጠንካራ አንድነት ብቻ ነው፡፡ ይህች ታሪካዊት አገር አሁንም በንቃትና በብልኃት መጠበቅ አለባት!