አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!
አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!

የትራፊክ ደኅንነት ዘመቻ ተጀመረ

 

በሁለተኛው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን በጀት ዓመት 10,000 ተሽከርካሪዎች በ61 ሰዎች ላይ የሚያደርሱትን የትራፊክ አደጋ ወደ 21 ዝቅ ለማድረግ ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ፡፡ አብዛኛው የትራፊክ አደጋ እየተከሰተ ያለው በአሽከርካሪዎች የሥነምግባር ችግር እንደሆነ፣ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠትም በሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ መሠራት እንዳለበት፣ የትራንስፖርት ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ ሰኞ ጥር 29 ቀን 2009 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

የትራፊክ አደጋ በገዳይነታቸው ከሚታወቁ በሽታዎች በላይ ብዙዎችን ለሞት እየዳረገ እንደሚገኝ፣ የአሽከርካሪዎች ሥነ ምግባር ችግር፣ የብቃት ማነስ ለአብዛኛዎቹ አደጋዎች መንስዔ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት ‹‹የኤችአይቪ ወረርሽኝን ለመቆጣጠር የተደረገውን ዓይነት ዘመቻ የትራፊክ አደጋን ለመከላከል መደረግ አለበት፡፡ ትውልዱን ለመቅረፅም ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር የትራፊክ ደኅንነት በሥርዓተ ትምህርቱ ተካቶ እንዲሰጥ ለማድረግም ታስቧል፤›› በማለት ማኅበራዊ ለውጥ ማምጣት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

ምንም እንኳን የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥና የመንገድ መሠረተ ልማቶች በየጊዜው እየተሻሻሉ ቢመጡም፣ የመንገድ ደኅንነት አደጋዎች በከፍተኛ መጠን እየጨመረ በመሆኑ ትኩረት ተደርጎበት ሊሠራ እንደሚገባ፣ ማኅበረሰቡም በባለቤትነት ስሜት የድርሻውን ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

በአገሪቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ የትራፊክ ፍሰት እየጨመረ ይገኛል፡፡ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ተሽከርካሪዎች ቁጥርም በከፍተኛ መጠን እየጨመረ ነው፡፡ ይህ ጉዳዩን አሳሳቢና አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጠው የሚያስገድድ ሲሆን፣ በአገሪቱ እየደረሰ ያለውን የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ ከጥር 18 እስከ ግንቦት 7 ቀን 2009 ዓ.ም. የሚቆይ አገር አቀፍ የትራፊክ ደኅንነት ንቅናቄ መጀመሩን ሚኒስትሩ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

በንቅናቄው የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን እንደሚሰሩ፣ በተደጋጋሚ ጊዜ አደጋ የሚከሰትባቸው ቦታዎች ላይ ፍተሻ በማድረግ ደንብ ተላልፈው የሚያሽከረክሩን በመያዝ ዕርምጃ እንደሚወስድ፣ የፍጥነት መቀነሻ ስልቶችን በመጠቀም በፍጥነት ምክንያት የሚከሰቱ አደጋዎችን ለመቀነስ ጥረት እንደሚደረግ እንዲሁም ሕዝቡን የጉዳዩ ባለቤት ለማድረግ እንደሚሠራ ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡   

አፍሪካ ከሌላው ዓለም በተለየ ለትራፊክ አደጋ 24 በመቶ ተጋላጭ ነች፡፡ በዓለም ላይ ከሚከሰተው የትራፊክ አደጋ 90 በመቶው የሚሆነው የሚከሰተውም በአፍሪካ ነው፡፡ ነገር ግን በአህጉሪቱ የሚገኘው የተሽከርካሪ ብዛት ከሌላው ዓለም አንፃር ከአንድ በመቶ ያነሰ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ያለው  የተሽከርካሪ ንፅፅር ደግሞ ለ100,000 ሰዎች ያለው የተሽከርካሪ ድርሻ 5.6 በመቶ ነው፡፡ ይህንን ያህል ውስን የሆነ የተሽከርካሪ ቁጥር ባለበት ሁኔታ እየደረሰ ያለው የትራፊክ አደጋ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት በ2006 ዓ.ም. ባወጣው መረጃ መሠረት፣ በእንግሊዝ በ100,000 ተሽከርካሪዎች የሚደርሰው አደጋ ሁለት ብቻ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ግን በ10,000 ተሽከርካሪዎች እስከ 120 የትራፊክ አደጋዎች ይከሰቱ ነበር፡፡  

በአሁኑ ወቅት ይህንን ቁጥር ወደ 61 ዝቅ ለማድረግ የተቻለ ቢሆንም፣ የትራፊክ አደጋ እያደረሰ ካለው ጥፋት አኳያና የተያዘውን እቅድ ለማሳካት ገና ብዙ መሠራት እንዳለበት ግልጽ ነው፡፡

 የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ካሳሁን ኃይለማርያም ‹‹ተራ ብስክሌት፣ ጋሪ ሳይቀሩ በትራፊክ አደጋ ሰዎችን እየገደሉ ይገኛሉ፡፡ ሕጋዊ መንጃ ፈቃድ የሌላቸውም ብዙ አደጋ እያደረሱ ይገኛሉ፤›› በማለት አብዛኛው አደጋ በተመቹ መንገዶች ላይ፣ ረፋድ 4 ሰዓትና ከሰዓት አሥር ሰዓት ገደማ የሚደርስ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለዓመታት ያሽከረከሩ ልምድ ያላቸው አሽከርካሪዎችም በብዛት አደጋ እያደረሱ እንደሚገኝ፣ ይህም አብዛኛው አደጋ እየተከሰተ ያለው ከአሽከርካሪዎች ሥነ ምግባር ጉድለት መሆኑን፣ 85 በመቶ የሚሆነው አደጋ በአሽከርካሪዎች ችግር የሚከሰት መሆኑን በመግለፅ አደጋውን ለመቆጣጠር የባህሪ ለውጥ ማምጣት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ሥርዓቱ ላይም ክፍተት መኖሩን ‹‹መንጃ ፈቃድ በሕገ ወጥ መንገድ አውጥተው ለሌሎች የሚሰጡ ሕገወጥ ደላሎች አሉ፡፡ እነዚህን በማጋለጥ ፈንታ ጓደኛ ማድረግና ማድነቅ ተለምዷል፤›› ብለዋል፡፡ እንዲህ ያሉ ሕገ ወጦችን ለመከላከልም የፈተና አሰጣጥ ሥርዓቱን ለማሻሻል መታሰቡን ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም የእግረኛ መንገዶች ነፃ እንዲሆኑ ማድረግና በአሽከርካሪው ችግር አደጋ ሲከሰት ከአሽከርካሪዎቹ ጎን ለጎን የተሽከርካሪ ባለቤቶች ተጠያቂ የሚሆኑበትን አሠራር በመዘርጋት አደጋውን ለመከላከል መታሰቡን ዳይሬክተሩ ገልጿል፡፡  

ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፓርላማ አባላት ጥር 4 ቀን 2009 ዓ.ም. ለቀረበላቸው ጥያቄዎች መልስ በሰጡበት ወቅት በአገሪቱ የትራፊክ አደጋ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አስከፊ እየሆነ መምጣቱን፣ ችግሩን ለመቅረፍም በኤችአይቪ ላይ የተደረገው ዓይነት ጠንካራ ዘመቻ እንዲሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡ ችግሩን ለመቀነስ የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥን ጠበቅ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

 መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በ2007 ዓ.ም. በቀን አሥር ሰዎች በትራፊክ አደጋ ሕይወታቸውን ያጣሉ፡፡ 31 ሰዎች ደግሞ ጉዳት ይደርስባቸዋል፡፡ በአጠቃላይ በዚያው ዓመት 3,847 ሰዎች ሕይወታቸውን ሲያጡ፣ 5,918 ከባድና 6,508 ደግሞ ቀላል የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ 668 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረትም ወድሟል፡፡