Skip to main content
x
የአሜሪካና የሰሜን ኮሪያ ፍጥጫ

የአሜሪካና የሰሜን ኮሪያ ፍጥጫ

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከዚህ ቀደም ከነበሩት የአሜሪካ መሪዎች ለየት ከሚያደርጓቸው ባህሪያት አንዱ፣ የማንንም ምክር ሳይጠይቁና ምን ያስከትላል ብለው ሳይገምቱ አዕምሯቸው የነገራቸውን በትዊተር ገጻቸው ላይ ማስፈራቸው ነው፡፡ የፈለጉትን መልዕክት ለማስተላለፍ የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይም ሆነ ጋዜጣዊ መግለጫ አያስፈልጋቸውም፡፡ የዋይት ሐውስን የተለመደ ሥነ ምግባር ጥሰውም በትዊተራቸው የፈለጉትን መልዕክት ያስተላልፋሉ፡፡

የጦርነት መናኸሪያ በሆነችውና አሜሪካና ሩሲያ በሰው ይፋለሙበታል በምትባለው ሶሪያ፣ የሶሪያ ፕሬዚዳንት በሽር አል አሳድ በንፁኃን ዜጎች ላይ የኬሚካል ጦር መሣሪያ ተጠቅመዋል በማለት የቀረበውን ሪፖርት ተከትሎ አሜሪካ በሶሪያ ድብደባ አካሂዳለች፣ በአፍጋኒስታንም እንዲሁ፡፡

በዚህ ድብደባ አሜሪካ የተጠቀመችው ቦምብ ‹የቦምቦች ሁሉ እናት› የተባለውን ነው፡፡ በሶሪያ የጦር አውሮፕላን ማኮብኮቢያንም በሚሳይል መትታለች፡፡ አሜሪካ ድብደባውን ስትፈጽም የሶሪያ መንግሥት በንፁኃን ላይ ፈጽሟል የተባለውን የኬሚካል ጦር መሣሪያ ድብደባ ለማስቆም ቢሆንም፣ ነገሩ ግን ሰሜን ኮሪያን ጭምር ለማስደንበር እንደነበር ተነግሯል፡፡ ሶሪያም ሆነች ሩሲያ ሶሪያ ውስጥ በኬሚካል ጦር መሣሪያ የተፈጸመ ጥቃት እንዳልነበረ በተደጋጋሚ ቢገልጹም፣ ተቀባይነትን አጥተው ሶሪያ በአሜሪካ ቶምሀውክ ክሩዝ ሚሳይሎች ድብደባ ተፈጽሞባታል፡፡

በሶሪያ ላይ ወታደራዊ ዕርምጃ መውሰዳቸውን የተናገሩት ትራምፕ አያይዘውም በትዊተር ገጻቸው፣ ‹‹አላውቅም፣ ምናልባት ‘የቦምቦች ሁሉ እናት’ ለሰሜን ኮሪያ መልዕክት ልኮ እንደሆነ?›› ሲሉም አስፍረዋል፡፡ የትራምፕ ትዊተር ቀድሞውንም በውጥረት ውስጥ ላሉት አሜሪካና ሰሜን ኮሪያ ላይ ቤንዚን እንደማርከፍከፍ ነው ሲሉም፣ የሰሜን ኮሪያ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ተናግረዋል፡፡ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሃን ሶንግ ሪኦል ከአሶሺየትድ ፕሬስ ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ አሜሪካ በግዴለሽነት ለምታደርገው ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ፒዮንግያንግ ምላሹን ለመስጠት ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል፡፡

የትራምፕ አስተዳደር ሌሎችን የማያቀርብና ውጥረት የሞላበት፣ በተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ዘመን ከነበረውም የከፋ መሆኑን በመግለጽ ሰሜን ኮሪያ የኑክሌር ማብላያዋን በጥራትም ሆነ በቁጥር እንደምታጠናክር አክለዋል፡፡ የትራምፕ አስተዳደር ጦርነት የሚፈልግ ከሆነም ጦርነት ለመግጠም አገራቸው ዝግጁ መሆኗን አሳውቀዋል፡፡

በዋሽንግተንና በፒዮንግያንግ መሀል ውጥረት የጀመረው በአሜሪካ 33ኛ ፕሬዚዳንት ሃሪ ትሩማን ዘመንና እ.ኤ.አ. ከ1950-1953 በዘለቀው የኮሪያ ጦርነት ወቅት ነው፡፡ በወቅቱ ጦርነቱ በሰላም ስምምነትም አልተቋጨም ነበር፡፡ በሰሜን ኮሪያና በአሜሪካ መካከልም ውጥረቱ ለዓመታት ሰፍኖ ቢቆይም፣ ሁኔታዎች የከረሩት ፕሬዚዳንት ትራምፕ ሥልጣን ከመያዛቸው ነው፡፡

አሜሪካና ደቡብ ኮሪያ በጋራ የሚያካሂዱት ወታደራዊ ልምምድ ከመቼውም ጊዜ በላይ ነው፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ሰሜን ኮሪያ ምድር ለምድር ያምዘገዘገችውን የሚሳይል ሙከራ በማናቸውም ጊዜ ልትደግመው ትችላለች በሚል ነው፡፡ ፒዮንግያንግ በቅርቡ ለሙከራ ባለስቲክ ሚሳይል ያስወነጨፈች ሲሆን፣ የአሜሪካን ምድር ለመምታት የሚያስችላት ጥበብ ላይ መድረሷንም አሳውቃለች፡፡

ሚስተር ሃን ሰሜን ኮሪያ በቅርቡ ተጨማሪ የሚሳይል ሙከራ ማድረግ ስለመፈለጓ ፍንጭ ባይሰጡም፣ የፖለቲካ ተንታኞች ግን ሰሜን ኮሪያ የጦር የበላይነቱን አውድማ ሊቀይር የሚችል አቅም በጥቂት ዓመታት ውስጥ ይኖራታል ብለዋል፡፡
ሰሜን ኮሪያ ባለፈው ዓመት ብቻ የኃሃይድሮጅን ቦምብና በዓለም በጣም ጠንካራ የተባለ የዚሁ ዓይነት ቦምብ በመተኮስ ሙከራ አድርጋለች፡፡

አሜሪካና ደቡብ ኮሪያ በጋራ የሚያደርጉት ወታደራዊ ልምምድ ሰሜን ኮሪያ ወታደራዊ ንቃቷንና የመጠቁ የውትድርና ቴክኖሎጂዎቿን ያለምንም እረፍት እንድታጠናክር ምክንያት እንደሆነም ይነገራል፡፡ አሜሪካና ደቡብ ኮሪያ ባይቀበሉትም፣ በተለያየ ጊዜ የወጡ መረጃዎች የሁለቱ አገሮች ጣምራ ወታደራዊ ልምምድ የባላንጣቸው ሰሜን ኮሪያን መንግሥት ድንገተኛ ወረራ በማድረግ ከሥልጣን ለመገርሰስ መሆኑም ይነገራል፡፡ ይህን ደግሞ ሰሜን ኮሪያ ሁሌም ነቅታ እንድትጠብቅ አድርጓታል፡፡

ሰሜን ኮሪያ ብዙ ማዕቀቦች ቢጣሉባትም የኑክሌር ማበልፀጊያዋን እያጠናከረችና እያሳደገች ነው፡፡ ይህንንም ተከትሎ ፒዮንግያንግ በኢኮኖሚው እንድትሽመደመድና የኑክሌር ማበልፀጊያዋን እንድታመክን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ማዕቀቦችን ተፈጻሚ እንዲያደርግ ትራምፕ ሲወተውቱ፣ ሚስተር ሃን ደግሞ፣ ‹‹ትራምፕ ሁሌም ተንኳሽ ንግግሮችን በማድረግ ይታወቃል፤›› ብለዋል፡፡

ትራምፕ እንደሚሉት፣ ደቡብ ኮሪያ ሰሜኖችን ለማንበርከክ ወደኋላ የምትል ከሆነ አሜሪካ በራሷ እጅ ታደርገዋለች፡፡ ይህ ግን በፕሬዚዳንታዊ ቅስቀሳቸው ወቅት ከሰሜን ኮሪያው አቻቸው ኪም ጆን ኡን ጋር ለመነጋገር እንደሚፈልጉ ለገለጹት ትራምፕ ትችት አስከትሎባቸዋል፡፡ ሃን፣ ‹‹ይህ ጉንጭ ከማልፋት ያለፈ አልነበረም፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ማንኛውም የአሜሪካ ፖለቲከኛ የሰሜን ኮሪያን አስተዳደር ለመገርሰስ ጥረት የሚያደርግ ከሆነ አንቀበለውም፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

ሰሜን ኮሪያ የኑክሌር ጥቃትን ለመቋቋም የሚያስችል አቅም እንዳላትና ከአሜሪካ የሚመጣ ማንኛውንም ጥቃት ለመቋቋም መዘጋጀቷንም ሃን ተናግረዋል፡፡ የሰሜን ኮሪያና የአሜሪካ ፍጥጫ ወደ ጦርነት ሊያመራ ይችላል በሚል በየሚዲያዎች መነጋገሪያ መሆን ከጀመረ ቢሰነባብትም፣ እንደ አሁኑ ሥጋቱ ያየለበት ጊዜ የለም፡፡ ሁለቱ አገሮች ፍጥጫቸውን በሰላማዊ ንግግር ለመፍታትም ፍንጭ አላሳዩም፣ ይልቁንም ‹‹እስቲ እንሞካከር›› ዓይነት ፍጥጫ ውስጥ ናቸው፡፡

ቀድሞውንም አሜሪካ በሌሎች አገሮች ላይ የምታደርገውን ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት የማትደግፈው ቻይና፣ አሜሪካና ሰሜን ኮሪያ ታሪክ የማይዘነጋው ስህተት ውስጥ እንዳይገቡ አስጠንቅቃለች፡፡

ባሳለፍነው ሳምንት ማብቂያ ጋዜጣዊ ላይ መግለጫ የሰጡት የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ፣ ሁለቱም ወገኖች ጠብ አጫሪ የሆኑ ቅስቀሳዎችንና ዛቻቸውን ትተው ወደ ንግግር እንዲገቡ ጠይቀዋል፡፡ ቻይናም በአሜካሪና በሰሜን ኮሪያ መካከል የከረረውን ፍጥጫ በድርድር ለመፍታት ለሚደረግ ጥረት ማንኛውንም ድጋፍ እንደምታደርግ ተናግረዋል፡፡ ‹‹አንዴ ጦርነት ከተጀመረ ውጤቱ ዘርፈ ብዙ ጥፋት ነው፡፡ ማንም አያሸንፍም፡፡ ጦርነቱን ማንም ጀመረው ማን፣ በኮሪያ ልሳነ ምድር ግጭቱን የጀመረ ታሪካዊ ኃላፊነቱን ይወስዳል፣ ዋጋውንም ይከፍላል፤›› ብለዋል፡፡

የደቡብ ኮሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሚስተር ሃን ደግሞ ሰሜን ኮሪያ ማንኛውንም የኑክሌር ሙከራ ለማድረግ ዝግጁ ነች ማለታቸውንም፣ ‹‹የሰሜን ኮሪያ መንግሥት ዓለም አቀፍ ሕጎችን እንዴት እንደሚገረስስ የሚያሳይበት እውነተኛ ቀለሙ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የሰሜን ኮሪያ የሚሳይል ሙከራ ማድረግ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን የጣሰ ነው ተብለው አስተያየቶች ቢሰጡም፣ አሜሪካም ማን ከእኔ በቀር ብትልም፣ ቢቢሲ ማክሰኞ ዕለት ይዞት የወጣው ዘገባ ሰሜን ኮሪያ በሳምንት፣ በወር አሊያም በዓመት የሚሳይል ሙከራ ልታደርግ እንደምትችል አትቷል፡፡

አሜሪካ በሰሜን ኮሪያ ላይ ጥቃት ከሰነዘረች የጦርነት በሮች ይከፈታሉ ሲሉም የሰሜን ኮሪያው ሃን ተናግረዋል፡፡ የአሜሪካው ምክትል ፕሬዚዳንት ማይክ ፔንስ በደቡብ ኮሪያ ሲኦል በኋላም በጃፓን በነበራቸው ጉብኝት፣ ‹‹ለሰሜን ኮሪያ ያለን ትዕግሥት አብቅቷል፤›› ብለዋል፡፡ ሰሜን ኮሪያ አሜሪካን መሞከር የለባትም ያሉት ፔንስ፣ ትራምፕ በሶሪያና በአፍጋኒስታን ላይ ያሳለፉትን የጦር ድብደባ ውሳኔ ብቻ ማየት ይበቃል ሲሉም አክለዋል፡፡ ለደቡብ ኮሪያ መቶ በመቶ ድጋፍ በማድረግ አጋርነትን እናሳያለን በማለትም፣ ደቡብ ኮሪያ ሰሜን ኮሪያን እንድትተናኮል ድጋፍ ሰጥተዋል፡፡ ይህ ደግሞ የበለጠ ሥጋት ፈጥሯል፡፡

ከዚሁ ጎን ለጎን ደግሞ የሶሪያ ወዳጅ ለሆነችው ሰሜን ኮሪያ ዋና ወዳጅ ከሆነችው ቻይና ጋር የኑክሌርና የሚሳይል ሙከራዎች መቆም በሚችሉበት ሁኔታ ላይ አብረው እንደሚሠሩ ፔንስ ተናግረዋል፡፡ ትራምፕ ደግሞ አሜሪካ ሰሜን ኮሪያን ለመምታት ዝግጁ ናት ሲሉ ለቻይና ማስጠንቀቂያ አዘል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ የታይዋን ዕገዛ በመጠየቅ ጭምር፡፡

የሰሜን ኮሪያ የሚሳይል ሙከራ በቻይናም ሆነ በሩሲያ ድጋፍ አላገኘም፡፡ የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲንም ሰሜን ኮሪያ በተሳሳተ መንገድ ላይ እየሄደች ነው ብለዋል፡፡ ሰሜን ኮሪያ በበኩሏ ግን አሜሪካ ማንኛውንም የጦርነት ዕርምጃ ከወሰደች የኑክሌር ጦርነት ይጀመራል ስትል አስጠንቅቃለች፡፡