Skip to main content
x
የአገሪቱ ሰላምና ደኅንነት ባለቤት ሕዝብ ነው!

የአገሪቱ ሰላምና ደኅንነት ባለቤት ሕዝብ ነው!

የኢትዮጵያ ሕዝብ እጅግ በጣም ሰላማዊና ጨዋ በመሆኑ፣ ለአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔም ሆነ ለተለያዩ ጉዳዮች ወደ አገሪቱ የሚመጡ የውጭ ሰዎች በአግባቡ ተስተናግደው በሰላም ወደ መጡበት ይመለሳሉ፡፡ ሕዝቡ ለረዥም ዘመናት ያካበተውና ሁሌም በመልካም ስሙ የሚነሳበት እንግዳ ተቀብሎ የማስተናገድ አኩሪ ባህል፣ አሁንም በስፋት እየቀጠለ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከኒውዮርክና ከብራሰልስ ቀጥላ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የዲፕሎማቲክና የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ መናኸሪያ እንደ መሆኗ መጠን፣ በውጭ ዜጎች ላይ የሚደርሱ አነስተኛ ክስተቶች ቢያጋጥሙ እንኳ ከድንገተኛነት የዘለሉ አይደሉም፡፡ ይህንን ይመሰለ ጨዋና ኩሩ ሕዝብ በአግባቡ ማስተዳደርና መብቶቹን በሚገባ የመጠበቅ ኃላፊነት የመንግሥት ነው፡፡ ሕዝብ የአገሩ ባለቤት እንደሆነ መታመን አለበት፡፡

የውጭ ዜጎች በኢትዮጵያ የሚያደርጉት ቆይታ ከሚያስገኘው ጥቅም በላይ፣ ሕዝቡ በጨዋነት የሚያሳያቸው አቀራረቦችና መስተንግዶዎች የአገሪቱ ትልቅ እሴት ናቸው፡፡ በአፍሪካም ሆነ በዓለም ከሚገኙ አገሮች ለፀጥታና ለደኅንነት አስተማማኝ ሆኖ መገኘት ብርቅ በሆነበት በዚህ ጊዜ፣ ኢትዮጵያ ለእንግዶቿ ፍፁም ሰላምና ደኅንነት ዋስትና መስጠት መቻሏ ትልቅ ነገር ነው፡፡ የዚህ ሰላምና ደኅንነት ባለቤት የሆነው ይህ ኩሩ ሕዝብ ደግሞ ተገቢው እንክብካቤና ጥበቃ ሊደረግለት ይገባል፡፡ ሕዝቡ ለአገሩ ካለው ፍቅርና ብሔራዊ ስሜት የተነሳ የውጭ ዜጎች ደኅንነታቸው አስተማማኝ ሲሆን፣ የአገሪቱ ተፈላጊነትም የበለጠ እየጨመረ ይሄዳል፡፡ ይህንን የመሰለ ኩሩና ጨዋ ሕዝብ ሲከበርና መሠረታዊ መብቶቹ በአግባቡ ሲከበሩለት ከዚህ የበለጠ ውጤት ይገኛል፡፡ የአገሪቱ ሰላምና ደኅንነትም አስተማማኝ ይሆናል፡፡

ሕዝብና መንግሥትን ከሚያጋጩና አገርን ችግር ውስጥ ከሚከቱ ዋነኛ ጉዳዮች መካል አንዱ በአገር ጉዳይ ላይ ያለ ግንዛቤ ነው፡፡ ሕዝብ አገሬ መመራት ያለባት በዴሞክራሲያዊ መንገድ በተመረጠ መንግሥት ነው ሲል፣ ራሱ በነፃነት የተሳተፈበት ምርጫ እንዲኖር ይፈልጋል፡፡ በሕግ የበላይነት ሥር የምትመራ ዴሞክራሲያዊት አገር እንድትኖረው አጥብቆ ይሻል፡፡ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ጥያቄውን በአግባቡ የሚመልስለት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት መኖር አለበት ይላል፡፡ ሕገወጥነትና በጉልበት ላይ የተመረኮዙ ድርጊቶች እንዲወገዱለት ይፈልጋል፡፡ በገዛ አገሩ ጉዳይ ዋነኛ ተዋናይ በመሆን በልማቱም ሆነ በዴሞክራሲው መስክ ተሳትፎው እንዲያድግ ይጠይቃል፡፡ የሥልጣንም ሆነ የሀብት ፍትሐዊ ክፍፍል ያለበትና ሁሉንም ዜጎች በእኩልነት የምታስተናግድ አንድነቷ የተጠናከረ አገር እንድትኖረው ይመኛል፡፡ በዚህም መሠረት አገሩን ከመቼውም ጊዜ በላይ መጠበቅና መንከባከብ፣ ለዕድገቷም መስዕዋትነት መክፈል ተቀዳሚ ዓላማው ይሆናል፡፡ የሰላምና የመረጋጋት ምንጭ እሱ ነውና፡፡

መንግሥት ሙሉ ጊዜውን በልማቱ ላይ አውሎ በመንገድ መሠረተ ልማት፣ በኢነርጂ፣ በባቡር፣ በስኳር፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ በመኖሪያ ቤቶችና በመሳሰሉት ሜጋ ፕሮጀክቶች ከፍተኛ የአገር ሀብት በማፍሰስ ትልልቅ ውጤቶች ታይተዋል፡፡ እነዚህ ግዙፍ ፕሮጀክቶች የአገሪቱን ኢኮኖሚ ትራንስፎርም ለማድረግና መዋቅራዊ ሽግግር ለማምጣት ትልቅ መንደርደሪያ ሆነዋል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃም ትልቅ ስም ለአገሪቱ አስገኝተዋል፡፡ ይሁንና ሕዝብ የልማቱ ባለቤት ሊሆን ይገባዋል፡፡ ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ትሩፋት ሕዝቡ በፍትሐዊነት እንደማያገኘው ካመነ፣ እሴት የማይጨምሩ ጥቂቶች ሚሊየነር እንደሚሆኑ ካሰበ፣ በገጠርም ሆነ በከተማ ለልማት ሲባል ተነስቶ ተመጣጣኝ ካሳና ጥቅም ካላገኘና በአጠቃላይ ዕድገቱን በባለቤትነት መንፈስ የማይመለከተው ከሆነ ችግር አለ፡፡ ችግሩ የሚመነጨው ደግሞ መንግሥትና ሕዝብ ባለመደማመጣቸው ነው፡፡ ይህም ችግር በአገሪቱ ላይ ከዚህ ቀደም ያስከተለው ቀውስ ይታወቃል፡፡ በዚህ መነሻ የጋራ ግንዛቤ ተፈጥሮ ለመሠረታዊ ለውጥ መነሳት ተገቢ ነው፡፡ የሕዝብ ተሳትፎ በሌለበት ሰላምም ሆነ መረጋጋት የለም፡፡

ይህ ኩሩ ሕዝብ ልዩነቱ እስከማይታወቅ ድረስ አንድነቱ ጎልቶ የሚታይ ነው፡፡ በጠባብነት አስተሳሰብ የተለከፉ የፖለቲካ ልሂቃን በማንነት ስም ሊከፋፍሉት ቢሞክሩ እንኳ አልተሳካላቸውም፡፡ ለዚህ ዋነኛ ምክንያት ደግሞ የአገር ፍቅር ብሔራዊ ስሜት ነው፡፡ ይህንን ጠንካራ የአንድነት መንፈስ ያለውን ሕዝብ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ማብቃት የፖለቲካ ልሂቃን ኃላፊነት ነው፡፡ ገዥው ፓርቲም ሆነ የተቃዋሚው ጎራ ከሥልጣን በላይ አገርና ሕዝብን ማሰብ አለባቸው፡፡ ሥልጣን ላይ ያለው ሥልጣኑን ሲያጠባብቅ በሚወስዳቸው አስከፊ ዕርምጃዎች ብዙ ነገሮች ተበላሽተዋል፡፡ በተቃውሞ ጎራ ያለው ደግሞ ብልጠት እየጎደለው የበለጠ ነገሮችን ሲያደፈርስ ከርሟል፡፡ የሁለቱ ወገኖች ጥፋት እኩል ነው ባይባልም፣ ኃላፊነት የጎደላቸው ድርጊቶች ግን አገሪቱንም ሆነ ሕዝቧን ጎድተዋል፡፡ ከእንዲህ ዓይነቱ አረንቋ ውስጥ በመውጣት ሥልጡን ለሆነው ዴሞክራሲያዊ ውይይትና ድርድር ራስን ማዘጋጀት የወቅቱ የማይታለፍ ጥያቄ ነው፡፡ ሕዝብ የሚፈልገውም በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መተዳደር ብቻ ነው፡፡ ሰላም ዘለቄታዊነት የሚያገኘው በዚህ መንገድ ብቻ ነው፡፡

በተደጋጋሚ ለማንሳት እንደፈለግነው ያለንበት ዓለም ተጨባጭ ሁኔታ አስተማማኝ አይደለም፡፡ ሌሎች ነገሮችን ገታ አድርገን አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በስደተኞች ላይ የጀመሩት ማዕቀብ፣ አገር አልባ ሆነው ለሚንከራተቱ ሰዎች ምን ያህል ፈተና እያመጣ እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ በገዛ አገር የባይተዋርነት ስሜት የተሰማቸው ወይም በተለያዩ ችግሮች ምክንያት የተሰደዱ ሰዎች መግቢያ ሲያጡ እየታየ፣ ለስደት ከሚዳርጉ አስከፊ ድርጊቶች መታቀብ ተገቢ ነው፡፡ በእኩልነትና በሰላም የሚኖሩባት ዴሞክራሲያዊት አገር ለመፍጠር በጋራ ከመረባበረብ ይልቅ፣ በረባ ባልረባው እየተናጀሱና ለክፉ እየተፈላለጉ መቀጠል የማይቻልበት ጊዜ ላይ ነን፡፡ ስለሆነም ሁሉም ወገኖች ለታፈረች፣ ለተከበረችና የሁሉም የጋራ እናት ለሆነች አገር መትጋት ይኖርባቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብም የሚፈልገው ይኼንን ነው፡፡ በመሆኑም መንግሥትና ሕዝብ በአገር የጋራ ጉዳይ ሊስማሙ ይገባል፡፡ ሕዝብም በአገሩ ጉዳይ የባለቤትነት ስሜት እንዲሰማው መደረግ አለበት፡፡ የሥልጣን ባለቤት የሆነው ሕዝብ በአገሩ ጉዳይ ባይተዋር መሆን የለበትም፡፡ ልማቱም ሆነ ዕድገቱ የሕዝብ ሊሆን የሚችለው፣ ሕዝብ በገዛ አገሩ የባለቤትነት ስሜት ሲኖረው ነው፡፡ በመሆኑም የአገሪቱ የሥልጣን ብቸኛ ባለቤት የኢትዮጵያ ሕዝብ መሆኑ ሊረጋገጥ ይገባል፡፡ የሰላምና የደኅንነት ባለቤትም እንዲሁ ሕዝብ ነው!