Skip to main content
x
የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን በአፍሪካ ዘላቂ ልማት ላይ የሚመክረውን ጉባዔ በአዲስ አበባ ሊያካሂድ ነው

የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን በአፍሪካ ዘላቂ ልማት ላይ የሚመክረውን ጉባዔ በአዲስ አበባ ሊያካሂድ ነው

  • የመጀመሪያዋ የኮሚሽኑ ዋና ኃላፊ ካሜሩናዊቷ ኢኮኖሚስት ሥራቸውን ጀምረዋል

በአፍሪካ የዘላቂ ልማት አጀንዳዎች ላይ የሚመከር ከፍተኛ የፖለቲካ ፎረም በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አስተናጋጅነት በመጪው ወር በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ተገለጸ፡፡

በተባበሩት መንግሥታት ሥር የሚተዳደረው የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ከግንቦት 8 እስከ ግንቦት 11 ቀን 2009 ዓ.ም. በአዲስ አበባ የሚካሄደው አኅጉር አቀፍ ከፍተኛ ጉባዔ፣ 17ቱ ዘላቂ የልማት ግቦች ሲተገበሩ የቆዩበትን ሒደትና የተመዘገቡ ለውጦችን የሚቃኝ እንደሚሆን ኮሚሽኑ ይፋ አድርጓል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2015 እስከ 2030 ባለው ጊዜ ውስጥ እንደሚተገበሩ የሚጠበቁት የዘላቂ ልማት ግቦች በአብዛኛው ድህነትን በማስወገድ ብልፅግናን በማዳረስ ሥራዎች ላይ ያጠነጠኑ ናቸው፡፡

ከዚህ አኳያ ጉባዔው እነዚህን ዘላቂ የልማት ግቦች ከአፍሪካ የልማት አጀንዳ 2063 የመጀመሪዎቹ አሥርታት ጋር በማዛመድ የልማት ግቦቹን የአተገባበር ሒደት የሚቃኝ እንደሚሆን ኮሚሽኑ ካወጣው መግለጫ ለመረዳት ተችሏል፡፡ በመሆኑም ኮሚሽኑ ከአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን፣ ከአፍሪካ ልማት ባንክና ከሌሎችም አጋዥ ተቋማት ጋር በመተባበር በሚያሰናዳው ጉባዔ ላይ የሚታደሙት የአፍሪካ ባለሥልጣናት፣ ከጉባዔው በመነሳት፣ በአሜሪካ ኒውዮርክ በሚካሄደው የዘላቂ ልማት ከፍተኛ ጉባዔ ላይ በሚካሄዱት ዓለም አቀፍ ክርክሮች ላይ የሚቀርቡ የመፍትሔ ሐሳቦችና ግብዓቶች ከአፍሪካ ወገን ለማቅረብ እንደሚያስችል ታምኖበታል፡፡

በሌላ በኩል የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ እስካሁን በወንዶች የተያዘውን አመራርነት በመጋራት፣ ካሜሩናዊቷ የኢኮኖሚክ ምሁርና የባንክ ባለሙያ ቬራ ሶንግዌ የኮሚሽኑ ዋና ኃላፊ በመሆን መሾማቸው ታውቋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ዋና ጸሐፊነት ከቀድሞው ባን ኪ ሙን የተረከቡት አንቶኒዮ ጉቴሬስ፣ አዲሲቷን የአፍሪካ ኢኮኖሚክስ ኮሚሽን ሶንግዌን በሥራ አስፈጻሚነት መሾማቸው ታውቋል፡፡ አዲሲቷ ተሿሚ በትልልቅ ተቋማት ውስጥ ሲያገለግሉ መቆየታቸው የተገለጸ ሲሆን፣ እስከ ቅርብ ጊዜም በዓለም ባንክ ሥር የሴኔጋል፣ የኬፕ ቬርዴ፣ የጋምቢያ፣ የጊኒ ቢሳው እንዲሁም የማውሪታንያ ዋና ዳይሬክተር በመሆን እ.ኤ.አ. ከ2012 እስከ 2015 ድረስ ማገልገላቸው ተጠቅሷል፡፡