Skip to main content
x
የኢሕአዴግና የመድረክ ውዝግብና የፓርቲዎቹ ድርድር

የኢሕአዴግና የመድረክ ውዝግብና የፓርቲዎቹ ድርድር

ኢሕአዴግ ለአገር አቀፍ ፓርቲዎች ባደረገው የእንወያይ ግብዣ መሠረት ከጥር 10 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግና 21 አገር አቀፍ ፓርቲዎች በውይይቱ እየተሳተፉ ነበር፡፡ ኢሕአዴግ ከ21 አገር አቀፍ ፓርቲዎች ጋር ሰባት ዙር ውይይቶችን አድርጓል፡፡ ስምንተኛውን ዙር ውይይትም ሚያዚያ 2 ቀን 2009 ዓ.ም. ለማካሄድ ቀጠሮ ተይዟል፡፡ የእስካሁኖቹ ውይይቶች የውይይትና የድርድር ማድረጊያ ደንብ ላይ የተገደቡ ነበሩ፡፡ ከሚፈለገው ጊዜ በላይ ዘግይቷል እየተባለ በሚተቸው ውይይት ፓርቲዎቹ በተወሰኑ ቁልፍ ጉዳዮች ላይ መስማማት ችለው ነበር፡፡

ውይይቶቹና ድርድሮቹ የሚካሄዱባቸውን ዝርዝር ሥነ ሥርዓቶች ለመወሰን በተደረገው ጥረትም፣ 22 አገር አቀፍ ፓርቲዎች በስምምነት ለመወሰን 12 ጉዳዮችን ለይተዋል፡፡ እነዚህም ጉዳዮች የድርድሩ ዓላማዎች፣ የድርድርና የክርክር ተሳታፊ ፓርቲዎች፣ የድርድርና የክርክር አባል ፓርቲዎችና የፓርቲ ተወካዮች ብዛት፣ ምልዓተ ጉባዔና ውሳኔ አሰጣጥ፣ የድርድር አጀንዳ ስለማቅረብና የማቅረቢያ ጊዜ ገደብ፣ እንዲሁም የድርድር አጀንዳ አወሳሰንና አጀማመር፣ የሚዲያ አጠቃቀም፣ የንግግርና የተናጋሪዎች አሰያየም፣ የድርድርና የክርክር አመራር፣ ታዛቢዎችና የሚኖራቸው ሚና፣ ሥነ ምግባርና ዲሲፕሊን፣ ውስጣዊ አደረጃጀት፣ አስተዳደር፣ የሎጂስቲክስ ድጋፍና የስብሰባ ቦታ ናቸው፡፡

ተሳታፊ ፓርቲዎች ሞቅ ያለ ውይይትና ክርክር ካደረጉ በኋላ የውይይቱ፣ የክርክሩ ወይም የድርድሩ ዓላማዎች ላይ ተስማምተዋል፡፡ በዚህም በአገሪቱ ሰላማዊና ሕጋዊ በሆነ መንገድ ሥልጣን በምርጫ ሥርዓት ብቻ ለአሸናፊ የፖለቲካ ፓርቲ የሚተላለፍበትን ሥርዓት ይበልጥ ለማስፋት፣ በድርድር ወቅት የሚነሱ የተለያዩ ሐሳቦችን እንደ ግብዓት በመጠቀም መሠረታዊ ማሻሻያ የሚያስፈልጋቸው ሕጎችን ለማሻሻልና የአፈጻጸም ጉድለቶችን ለማስተካከል፣ የፓርቲዎችን የዴሞክራሲያዊ የእርስ በርስ ግንኙነት ለማጠናከርና ለአገሪቱ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ዕድገት የሚኖራቸውን አስተዋጽኦ ለማጎልበት፣ ሕዝቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያቀርቡትን አማራጭ ሐሳብ፣ ያላቸውን ሐሳብ ተገንዝቦ በዕውቀትና በመረጃ ላይ ተመሥርቶ እንዲንቀሳቀስ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር፣ ለብሔራዊ መግባባት አስተዋጽኦ ለማድረግ፣ እንዲሁም የአገሪቱን የፖለቲካ ምኅዳር ችግሮች ነቅሶ በማውጣት ለመድበለ ፓርቲ ሥርዓቱ ችግሮች መፍትሔ ለመስጠት ድርድሩን እንደ መልካም አጋጣሚ ለመጠቀም ተስማምተዋል፡፡

ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግና መድረክ ያነሷቸው ሁለት አጀንዳዎች ግን አጀማመሩ መልካም የነበረውን ውይይት ዘላቂነት አጠራጣሪ አድርጎታል፡፡ ለድርድር፣ ለክርክርና ለውይይት ዝርዝር ሥነ ሥርዓቶችንና ደንቦችን ለመቅረፅ ሰባት ዙር ውይይት ያደረጉት ፓርቲዎች፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ውይይቱ በተናጠል ወይም በተወካይ አልያም አንድ ለአንድ ይደረግና ማን ያደራድር በሚሉ ሁለት ጉዳዮች ላይ መስማማት ተስኗቸዋል፡፡

በዋና አደራዳሪነት አልያም ለብቻው በጎንዮሽ ከኢሕአዴግ ጋር ለመደራደር ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት ባለማግኘቱ መድረክ ከውይይቱ ራሱን ማግለሉን በቅርቡ አስታውቋል፡፡ ኢሕአዴግ ከ21 አገር አቀፍ ፓርቲዎች ጋር እያደረገ ባለው ውይይት ላይ በስድስት ዙሮች ከተሳተፈ በኋላ፣ በሰባተኛው ራሱን ያገለለው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) መጋቢት 22 ቀን 2009 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ በጽሕፈት ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንደገለጸው፣ ኢሕአዴግ ይህን የሐሳብ ልውውጥ ማዕቀፍ ያዘጋጀው በጫና ምክንያት ነው፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምኅዳር በእጅጉ ተቀይሯል፡፡ ሕዝብ ሞት ሳይፈራ እምቢኝ ብሎ ድምፁን ሊያሰማ የደፈረበት፣ በሚሊዮኖች ወጥቶ ያንን ተዓምር የሠራበትና መንግሥት ላይ ጫና የፈጠረበት ጊዜ ነው፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንድታወጅና ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ገዥው ፓርቲ እንዲነጋገር ጫና የፈጠረው ይኼው ነው፡፡ እኛ ደግሞ ያንን ሆ ብሎ የወጣውን ሕዝብ ጥያቄ የምንወግን ነን፡፡ ከሕዝብ እየሰማን ተግባራዊ ለማድረግ የምንታገል ነን፤›› በማለት የመድረክ የወቅቱ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ የጫናውን መንስዔ አስረድተዋል፡፡

መድረክ ይህንኑ አቋም በውይይቱ መድረክም ሲያንፀባርቀው ነበር፡፡ የኢሕአዴግ ተወካዮች አቶ ሽፈራው ሽጉጤ፣ አቶ አስመላሽ ወልደ ሥላሴና አቶ አብዱላዚዝ መሐመድን ባላስደሰተ ሁኔታ ይህን ስሜት ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ተጋርተውታል፡፡

አቶ አስመላሽ፣ ‹‹ኢሕአዴግ የሚፈራ ድርጅት አይደለም፡፡ በተፅዕኖ አይደለም ወደ ድርድር እየገባ ያለው፡፡ የምንወያየውና የምንደራደረው የዚህን አገር ሕዝብ ይጠቅማል ብለን ስለምናምን ነው፤›› ብለዋል፡፡ አቶ ሽፈራውም በተመሳሳይ፣ ‹‹አገሪቱ አጣብቂኝ ውስጥ አይደለችም፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡ ‹‹የመድበለ ፓርቲ ሥርዓቱን በምንፈትሽበት ጊዜ መጠናከር በሚገባው ደረጃ ያልተጠናከረ እንደሆነ ገምግመናል፡፡ ‹‹የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት መጠናከር የተረጋጋ አገርና የበለፀገ ኅብረተሰብ ለመፍጠር ወሳኝ ነው ብለን እናምናለን፡፡ አሁን በአገራችን በሕጋዊ መንገድ ተመዝግበው የፖለቲካ ትግል ለማድረግና እንወክላለን የሚሉትን የኅብረተሰብ ክፍል ጥቅሞችና መብቶች ለማስከበር፣ በአገሪቱም የፖለቲካ ምኅዳር እንዲሰፋ ከሚፈልጉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ድርድር በማድረግ ለእነሱ ትግል የማይመች ሁኔታን ለመፍታት ነው ወደ ድርድሩ የገባነው፤›› በማለት አቶ ሽፈራው አብራርተዋል፡፡

በተጨማሪም እንደ መድረክ እምነት ውይይቱ፣ ክርክሩ ወይም ድርድሩ አሁን እየተካሄደ ባለበት መንገድ ከቀጠለ ውጤት አያመጣም፡፡ ‹‹እዚህ መድረክ ላይ የተገኘነው ድርድር የሚኖር መስሎን ነው፤›› ያሉት ፕሮፌሰር በየነ፣ የኢሕአዴግን ባህሪ ፓርቲያቸው ጠንቅቆ ቢያውቅም ፖለቲካ እስከሆነ ድረስ የተገኘውን አጋጣሚ ለመጠቀም የገዥውን ፓርቲ ጥያቄ እንደተቀበለ አስገንዝበዋል፡፡ ‹‹ውጤት በማያስገኝ ጉዳይ ውስጥ ብዙ መቆየት ሕዝባችንን ማሳሳት ነው፤›› ሲሉም ውይይቱ ሕዝቡ በሚፈልገው መንገድ እየተካሄደ እንዳልሆነ አመልክተዋል፡፡

መድረክ፣ ‹‹ድርድሩ ተጨባጭ ውጤት ሊያስገኝ በሚችልበት ሁኔታ የሁለትዮሽ እንዲሆንና በገለልተኛ አደራዳሪዎች እንዲመራ ያቀረብነው ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ አላገኘም፤›› ሲል በጋዜጣዊ መግለጫው ገልጿል፡፡

መድረክ 22 የፖለቲካ ፓርቲዎች ልዑካን የየፓርቲያቸውን አጀንዳዎችና አቋሞች ይዘው ተራ በተራ በሚጨቃጨቁበት ስብሰባ ወይም ጉባዔ ውጤት ይገኛል ብሎ እንደማያምን አስረድቷል፡፡ በዚህ ትክክለኛ የድርድር ባህሪ በሌለውና ውጤታማ ሊሆን በማይችል የ22 ፓርቲዎች ውይይት ሒደት ውስጥ መቀጠል ተገቢ ሆኖ ስላላገኘው ራሱን እንዳገለለም አስታውቋል፡፡

‹‹የሁለትዮሽ የድርድር አማራጭ ለኢሕአዴግ አቅርበን ምላሽ በመጠባበቅ ላይ እንገኛለን፤›› ያሉት የመድረክ አመራሮች፣ ኢሕአዴግ ፈቃደኝነቱን በአስቸኳይ እንዲገልጽ አጥብቀው ጠይቀዋል፡፡

መድረክ በዚህ ሁኔታ ከሒደቱ ራሱን ማግለሉ ያለው ጠቀሜታና ጉዳት ላይ ጋዜጣዊ መግለጫውን የተከታተሉ ጋዜጠኞች የተለያዩ ጥያቄዎችን አቅርበዋል፡፡ ከእነዚህ ጥያቄዎች አንዱ መድረክ ብቻዬን መደራደር እፈልጋለሁ ማለቱ እንደ ቅድመ-ሁኔታ አይወሰድም ወይ ተብሎ የቀረበው ነው፡፡

ለቀረበው ጥያቄ ፕሮፌሰር በየነ ሲመልሱ፣ ‹‹አንገብጋቢ የሆኑ ጉዳዮች አሉ፡፡ የድርድር ምኅዳሩን ተዓማኒ የሚያደርጉ ዕርምጃዎች እንዲወሰዱ ጠይቀን ነበር፡፡ መሪዎችን አስሮ ተደራደር አይባልም፡፡ ከፍተኛ አመራራችንን ሲያስር ምክንያት እንዳገኘ ሁሉ ሲፈታም አንድ ምክንያት አያጣም፤›› ብለዋል፡፡

ፕሮፌሰሩ መድረክ ‘ብቻዬን ልደራደር’ እንዳላለም ተከራክረዋል፡፡ ‹‹የቀራችሁት ፓርቲዎች ዋጋ የላችሁም፡፡ ቁጭ ብላችሁ እኛ የምናገኘውን ብቻ ጠብቁ አላልንም፤›› ብለዋል፡፡ መድረክ ከሚመስሉት ፓርቲዎች ማለትም የፓለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባል ያልሆኑ፣ በኢሕአዴግ ላይ ጥገኛ ያልሆኑና የጥቅም ግንኙነት የሌላቸው ፓርቲዎች ጋር አብሮ የመደራደር ፍላጎት አሁንም እንዳለው አመልክተዋል፡፡

ፕሮፌሰር በየነ በ2001 ዓ.ም. ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከኢሕአዴግ ጋር በሥነ ምግባር ደንቡ ላይ ሲወያዩ ከነበራቸው ልምድ ብዙ መማራቸውንም ተናግረዋል፡፡ ‹‹በደንቡ ላይ ከኢሕአዴግ ጋር ለመደራደር ሄድን፡፡ ኢሕአዴግ ወደ አሥር የሚሆኑ በባለሟልነት የያዛቸውን ፓርቲዎች ይዞ መጣ፡፡ በኋላ ወደ ጉዳዩ ሲገባ እነዚህ ፓርቲዎች እኛ የምናነሳውን ሁሉ ይኼ የእኛ ጉዳይ አይደለም ማለት ጀመሩ፡፡ የምርጫ ቦርድ ተዓማኒ በሆነ መልኩ እንደገና ይዋቀር የሚለው አጀንዳ ጉዳዬ አይደለም ከሚል ፓርቲ ጋር እንዴት መደራደር ይቻላል?›› ብለዋል፡፡  

በዘንድሮው ውይይትም ተመሳሳይ ነገር ማስተዋላቸውን አውስተዋል፡፡ ‹‹በነበርንባቸው ስድስት ዙሮች በርካታ ሐሳቦችንና አካሄዶችን አንስተናል፡፡ ከዚህ ውስጥ አንዱንም ሐሳብ ማንሳት አይፈልጉም፡፡ እኛ እኮ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ልንደራደር አልሄድንም፡፡ የሚሰጥም የሚነሳም ኢሕአዴግ ነው፡፡ ዋናው ነገር ኢሕአዴግ አለመቀበሉ ነው፡፡ የሌሎቹ አይቸግረንም፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

መድረክ ‘በቂ መግባባት’ የተሰኘ ጽንሰ ሐሳብን በመጠቀም አቋሙን ለማስገንዘብ ሞክሯል፡፡ ፕሮፌሰር በየነ፣ ‹‹ኢሕአዴግ ከዋነኛ ወይም ከቀዳሚ ተደራዳሪው ጋር ከተስማማና የቀሩት ከተስማሙ መልካም፣ ካልሆነም ልዩነታቸውን አስመዝግበው መቀጠል ይችላሉ፡፡ በአገራችን የፖለቲካ ሕይወት ውስጥ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ ፓርቲዎች ከተስማሙ መቀጠል ይቻላል፡፡ መድረክ ዋነኛ ተቃዋሚ ፓርቲ የሆነው በላቡ ነው፡፡ አባሎቻችን በነፍሳቸው መስዋዕትነት ከፍለው የተመዘገበ ውጤት ነው፡፡ ያለፈውን ምርጫ ብንወስድ ከኢሕአዴግ ቀጥሎ ብዙ ዕጩ ያቀረበው መድረክ ነው፡፡ ምን ያህል ድምፅ አግኝተን እንደተሸነፍን እስካሁን ምርጫ ቦርድ አልገለጸልንም፤›› ሲሉ ጽንሰ ሐሳባቸውን አብራርተዋል፡፡

አቶ ሽፈራው፣ ‹‹በዚህ መድረክ እነማን ይሳተፉ የሚለውን በተመለከተ፣ በእኛ በኩል ለ21 የፖለቲካ ፓርቲዎች እኩል ዕውቅና እንሰጣለን፡፡ እነዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከኢሕአዴግ ጋር ለመደራደር ቢፈልጉ የመጀመሪያው አማራጭ ፓርቲዎቹ በዙር ይምሩ የሚል ነው፡፡ ሁለተኛ የምትተማመኑባቸውን ፓርቲዎችንም ሆነ ግለሰቦች መርጠን እንደራደራለን ካላችሁ የሁለትዮሽ ድርድር ለማድረግ ኢሕአዴግ ዝግጁ ነው፡፡ ሦስተኛ በእነዚህ አጀንዳዎች ላይ የተለየ አቋም አለኝ የሚል ፓርቲ ካለ፣ የሌሎችን የጋራ አጀንዳዎች ስንጨርስ ከዚያ ፓርቲ ጋር አንድ ለአንድ ለመደራደር ኢሕአዴግ ዝግጁ ነው፤›› ብለዋል፡፡ 

ፕሮፌሰር በየነ፣ ‹‹የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል፤›› በማለት የኢሕአዴግ ተወካዮች መድረክ ወይም ሕዝቡ የሚፈልገውን ለመስጠት ትንሽ ፍንጭ እንኳን እንዳላሳዩ ተችተዋል፡፡ የመድረክ ውጭ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጥላሁን እንደሻው፣ ‹‹ፓርቲዎችን ሊያስማማ የሚችለው አጀንዳ ብቻ አይደለም፡፡ አጀንዳ ላይ መስማማት ይቻላል፡፡ ነገር ግን አጀንዳ ላይ አንድ ሆኖ የተስማማ ሁሉ አንድ ሆኖ ይደራደራል ማለት አይደለም፡፡ በምርጫ ወይም በፖለቲካ ምኅዳር ላይ ለመደራደር ሊስማሙ ይችላሉ፡፡ ፓርቲዎችን አንድ የሚያደርጋቸው ነገር ከድርድሩ ሊያገኙ የሚፈልጉት ነገር ነው፡፡ ፓርቲዎቹ በአጀንዳው ተስማምተው ይመጡና የመድረክን አቋም ይቃወማሉ፡፡ ከዚያ ከኢሕአዴግ የምንጠብቀው መልስ ቀርቶ መድረክ ያቀረበውን ሐሳብ ሌሎቹ ፓርቲዎች ራሱ አልተቀበሉትም ብሎ ለማድበስበስ ይውላል፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡      

ሪፖርተር ያነጋገራቸውና ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የፖለቲካ ተንታኝ የመድረክ አቋም እንዳሳዘናቸው ይናገራሉ፡፡ ‹‹ሁሉንም ተቃዋሚ ፓርቲዎች በደምሳሳው መፈረጅ ትክክል አይደለም፡፡ የተወሰኑ ፓርቲዎች በትክክለኛው መንገድ ለመሥራት ይሞክራሉ፡፡ የራሳቸው የድጋፍ መሠረትም አላቸው፡፡ ያለተጨባጭ መሥፈርት ሌሎችን ውድቅ ማድረግ በየትኛውም መሥፈርት የማያሳምንና ጤነኛ ያልሆነ ዕርምጃ ነው፡፡ መድረክ ከሌሎች ፓርቲዎች ገዝፎ ሊታይ ይችል ይሆናል፡፡ ነገር ግን በሥርዓቱ ደስተኛ ያልሆኑ ዜጎች ብቸኛ ተወካይ አድርጎ ራሱን ለመቁጠሩ የነባራዊና የሞራል መሠረት የለውም፡፡ መድረክ የሐሳብ ልዩነት ቢኖረው እንኳን በዚህ ቀውጢ ጊዜ የተገኘን መልካም አጋጣሚ አቋርጦ ከመውጣት ይልቅ፣ ትንሽ ውጤትም ብትሆን ለማግኘት ቢቀጥሉበት ይሻል ነበር፤›› ሲሉ የቅያሜያቸውን መሠረት አስገንዝበዋል፡፡  

ማን ከማን ይደራደር ከሚለው አጀንዳ በተጨማሪ የአደራዳሪ ማንነት ሌላው የልዩነት ምንጭ ሆኗል፡፡ አደራዳሪ ማን ይሁን በሚለው ጉዳይ ላይ አንዳንድ ፓርቲዎች ነፃና ገለልተኛ አደራዳሪ ያስፈልጋል ሲሉ፣ ኢሕአዴግና ሌሎች ፓርቲዎች ግን ድርድሩን ተሳታፊ ፓርቲዎች በፈረቃ ሊያደርጉት እንደሚገባ አቋም ይዘዋል፡፡

መድረክና ኢሕአዴግ በሁለቱ አጀንዳዎች ላይ ያላቸውን አቋም ከሌሎች አመራሮች ጋር መክረው መልሳቸውን ለመጋቢት 20 ቀን 2009 ዓ.ም. ይዘው እንዲመጡ ቀጠሮም ተይዞ ነበር፡፡ በዚሁ ሰባተኛ ዙር ውይይት መድረክ አልተገኘም፡፡ ይሁንና አደራዳሪው ማን ይሁን በሚለው ላይ ኢሕአዴግ አቋም ቀይሮ ከሆነ ለመረዳት ለቀረበው ጥያቄ የተገኘው ምላሽ አስቀድሞ የቀረበው ከሌሎች ፓርቲዎች ነበር፡፡ በዚህም የተወሰኑ ፓርቲዎች ኢሕአዴግ ያቀረበው በፈረቃ የማደራደር ሚና ችግር እንደሌለበት መገንዘባቸውን በመግለጽ የአቋም ለውጥ አሳይተዋል፡፡

በእለቱ የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ፕሬዚዳንት ጫኔ ከበደ (ዶ/ር) ‹‹ድርድሩ መካሄድ ካለበት ገለልተኛና ነፃ ሆኖ አጀንዳዎቹንም ሊቀርፅና ሊያዋቅር የሚችል፣ ቃለ ጉባዔዎችን በአግባቡ ሊይዝ የሚችል አካል ማቋቋም አለብን፤›› ብለዋል፡፡ የኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሽፈራው ግን፣ ‹‹በሌላ አካል የእኛን ጥልቀት ለመለካት እጁን በሚያስገባው ኃይል ሳይሆን መተማመን ያለብን በራሳችን ኃይል ነው፡፡ እኛ ሦስተኛ ወገን የሚባል በሕዝብ ጉዳይ ላይ ድርሻና አቋም የለኝም ብሎ ለማደራደር የሚችል ሰው አለ ብለን አናምንም፡፡ ወይ ተቃዋሚን ይቃወማል፡፡ አልያም ተቃዋሚን ይደግፋል፡፡ እኛ ራሳችን በቂዎች ስለሆን ሦስተኛ ወገን አያስፈልገንም፡፡ ኢሕአዴግ በዚህ ጉዳይ ላይ የመጨረሻ አቋሙ ነው፤›› ሲሉ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡ በተመሳሳይ አቶ አስመላሽ፣ ‹‹ገለልተኛ የሚባል አካል የለም፡፡ በሚቀርበው አጀንዳ ላይ አቋም የሌለው ገለልተኛ አካል በምንም ተዓምር አይኖርም፡፡ ሲደግፉን ገለልተኛ ናቸው እንላለን፡፡ የማይደግፉን ከሆነ ደግሞ ገለልተኛ አይደሉም እንላለን፤›› ብለዋል፡፡   

በመድረክ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ፕሮፌሰር በየነ፣ ‹‹የአደራዳሪ ጥያቄ በቀላሉ የሚጣጣል አይደለም፡፡ አደራዳሪ ለምን ያስፈልጋል የሚለውን ለማስረዳት ሞክረናል፡፡ ኢሕአዴግን ጨምሮ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሕዝቡን አላገለገሉም፣ አደራውን በልተዋል፡፡ አደራዳሪዎቹ አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች መሆን አለባቸው፡፡ መደማመጥ ያቃታቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች መሀል ገብተው ሃይ ማለት አለባቸው፡፡ ሀቁንና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የሚያሳዩ፣ አማራጭ ሐሳብና መፍትሔ የሚያመነጩ ምሁራን ሞልተውናል፡፡ ከዚህ ቀደም በነበረን ልምድ በመተማመን ተራ በተራ እየሰበሰብን ውጤት አስመዝግበን እናውቃለን፡፡ አሁን አደራዳሪ ያስፈልጋል ያልነው እምነት ጨርሶ ስለጠፋ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ለፖለቲካ ተንታኙ ማን አደራዳሪ ይሁን የሚለው አጀንዳ አገሪቱ አሁን ካለችበት ሁኔታ አንፃር ይህን ያህል አከራካሪ መሆኑ አልተዋጠላቸውም፡፡ ይሁንና የኢሕአዴግ ገለጻ ትዝብት ላይ የሚጥለው ነው ይላሉ፡፡ ‹‹በፍፁም ነፃና ገለልተኛ አካል ብሎ ነገር የለም የሚለው ገለጻ የተለመደ አይደለም፡፡ እንደ አገር ችግር ውስጥ መሆናችንን የሚያሳይ ነው፡፡ ባለሙያና በበቂ ደረጃ ገለልተኛ ተቋማትና ግለሰቦች የሉም እያልን ነው፣ ሲቪል ማኅበራትና ዴሞክራሲያዊ ተቋማት የሉም እያልን ነው፤›› ብለዋል፡፡

በዚሁ የአደራዳሪ ጉዳይ ላይ ስምምነት ባለመገኘቱ ነፃና ገለልተኛ አደራዳሪ ያስፈልጋል ያሉ ፓርቲዎች ድጋሚ ጉዳዩን አጢነውበት ምላሻቸውን ለሚያዝያ 2 ቀን 2009 ዓ.ም. እንዲያቀርቡ ተወስኗል፡፡

የሕግ ባለሙያና የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ሞላ ዘገዬ ለሪፖርተር እንደተናገሩት ደግሞ፣ ኢሕአዴግ የአገሪቱን ችግር ለመፍታት ከወሰነ ውይይት ማድረግ ያለበት ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር አይደለም፡፡ ‹‹በድርድሩ እየተሳተፉ ያሉት ፓርቲዎች ሕዝባዊ መሠረት ያላቸው አይደሉም፡፡ የሚወክሉት ሕዝብን ሳይሆን ራሳቸውን ነው፡፡ ድርድሩ መካሄድ ያለበት ሕዝብ ከሚያዳምጣቸውና ከሚያምናቸው የሲቪል ማኅበራት፣ የብዙኃን ድርጅቶች፣ የሙያ ማኅበራትና የሃይማኖት ተቋማት ጋር ነው፤›› ብለዋል፡፡

የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ጽንሰ ሐሳብ ከ1983 ዓ.ም. በኋላ ወደ ኢትዮጵያ የፖለቲካ ሕይወት የገባ ቢሆንም፣ የተደላደለና ቀጣይነት ያለው ዕድገት ማሳየት ተስኖት እየተንገዳገደ እንደሆነ በርካታ የፖለቲካ ተንታኞች ይገልጻሉ፡፡ በእርግጥም ኢሕአዴግ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ለመደራደር የተነሳሳው በውጤቱ ሕዝብ እንዲጠቀም ከሆነ፣ እንደ አቶ ሞላ ሁሉ የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማስፋት የመፍትሔ አካል መሆን ያለባቸው በርካታ አካላት እንደሆኑ የሚሰማቸው ዜጎች ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡