አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!
አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!

የኢትዮጵያና የኬንያ አትሌቶች ዜግነት ቀይረው እንዳይሮጡ ታገዱ

የዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር (አይኤኤኤፍ) የኢትዮጵያና የኬንያ አትሌቶች ዜግነት ቀይረው ለማንኛውም አገር  እንዳይሮጡ ማገዱ ታወቀ፡፡

አይኤኤኤፍ ባለፈው ማክሰኞ ጥር 30 ቀን 2009 ዓ.ም. ለአባል ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች እንዳስታወቀው፣ ውሳኔው የተላለፈው በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያውያንና ኬንያውያንና ለሌሎች አገሮች ዜግነት ቀይረው የሚሮጡ አትሌቶች ቁጥር ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በመጨመሩ ነው፡፡

ከዚህ በፊት የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ማኅበርን ጨምሮ ታላላቅ ውድድሮችን የሚያዘጋጁ አገሮች የኢትዮጵያና የኬንያ አትሌቶች በበላይነት የሚያጠናቅቋቸው ርቀቶችን የኦሊምፒክና የዓለም ሻምፒዮናዎችን ጨምሮ እንዲቀሩ ጫና ሲያደርጉ መቆየታቸው አይዘነጋም፡፡

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ በበኩሉ፣ አይኤኤኤፍ በሁለቱ አገሮች ላይ ያስተላለፈው ውሳኔ ሐሳቡ የመነጨው ከአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌዴሬሽን (ሲኤኤ) መሆኑን ለሪፖርተር ገልጿል፡፡ እንደ ኃይሌ የአይኤኤኤፍ ውሳኔ ከሰዎች ሰብአዊ መብት አኳያ ሲታይ አከራካሪ ቢመስልም፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ዜግነት እየቀየሩ የሚሮጡ ኬንያውያን አትሌቶች ቁጥር መጠን እያለፈ መምጣቱ ለውሳኔው ተገቢነት ማረጋገጫ እንደሆነ ይስማማል፡፡

በቅርቡ በተከናወነው የአውሮፓ አገሮች አገር አቋራጭ ውድድር ቱርክን ወክለው የተወዳደሩ ኬንያውያን የሜዳሊያ ሰንጠረዡን ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር መቻላቸው ለዚህ ውሳኔ እንደማሳያ ሊሆን እንደሚችልም ጠቁሟል፡፡ የአፍሪካም ሆነ የዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ለዚህ ውሳኔ የበቁት ከዚህ የአውሮፓውያኑ አገር አቋራጭ ሻምፒዮና በኋላ መሆኑንም ሳይናገር አላለፈም፡፡

ዕገዳው ምንም እንኳ ኢትዮጵያውያን አትሌቶችን የሚመለከት ቢሆንም፣ ከዚህ በፊት ለተለያዩ አገሮች ሲሮጡ ከነበሩ ብዙ ኬንያውያን ጋር ሲደረግ የቆየው ፉክክር ተቀንሶ ከኬንያውያን ጋር ብቻ መሆኑ ለኢትዮጵያውያን አትሌቶች ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለውም ተናግሯል፡፡

እንደ አገር ውሳኔውን እንዴት ታየዋለህ? ለሚለው ኃይሌ፣ ‹‹እውነቱን ለመናገር ኬንያውንም ሆኑ ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ተፎካክረው ዕድል ለማያገኙ አትሌቶች ዜግነት ቀይረው ሲሮጡ የሚያገኙት ጥቅም ይኖራል፡፡ ጉዳዩን በዚህ መንገድ ከተመለከትነው ጉዳት አለው፡፡ ግን ደግሞ ሲበዛና የሰው ልጅ እንደ ሸቀጥ የሚታይበት ሁኔታና በዜግነት ስም የሚከናወነው ዝውውር መጠኑን እያለፈ መምጣቱ ተገቢ እንዳልሆነ ነው የሚገባኝ፤›› ብሏል፡፡