Skip to main content
x
የኤልኒኖ ጠባሳ

የኤልኒኖ ጠባሳ

መነሻው በደቡብ አሜሪካ ከፓስፊክ ውቅያኖስ ላይ የሆነውና በአካባቢው በሚፈጠር የውኃ ሙቀት መጨመር የሚከሰተው ኤልኒኖ ከሁለት እስከ ሰባት ዓመታት እየቆጠረ ይመጣል፡፡ እንደየአካባቢው የተለያየ ቢሆንም ክስተቱ በዓለም ላይ የሚያስከትለው የአየር ንብረት ለውጥ ቀላል አይደለም፡፡ በደቡብ አፍሪካ፣ በካሪቢያን፣ በህንድና በኢንዶኔዥያ ድርቅን ሲያስከትል፤ በደቡብና በሰሜን አሜሪካ ደግሞ ጎርፍ ያስከትላል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2014 የጀመረውና በ2016 አጋማሽ ላይ ያበቃው የኤልኒኖ ክስተት፣ ምድር እስካሁን ካስተናገደችው ጠንካራ የተባለ ሲሆን፣ ካለፉት 130 ዓመታት ወዲህም ከባድ የሙቀት መጠን የተመዘገበበትም ነው፡፡

በ2015 የኢንዶኔዥያ ጫካዎችን በእሳት ለማጋየት የበቃና በተዘዋዋሪም በተፈጠረ የአየር ብክለት ከ100 ሺዎች በላይ ሕይወት የቀጠፈም ነው፡፡  ከሰሃራ በታች የሚገኙ የአፍሪካ አገሮችም ከ35 ዓመታት ወዲህ ተመዝግቦ በማያውቅ የድርቅ መጠን ተመትተዋል፡፡

ኤልኒኖ በግብርናው ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ከሁሉም የከፋ ነው፡፡ ከ40 ሚሊዮን በላይ አፍሪካውያንም ለከፋ የምግብ እጥረት ተጋልጠዋል፡፡ ኤልኒኖ በ2014 ጀምሮ በ2016 አጋማሽ ላይ ቢያበቃም፣ በአፍሪካ አገሮች ላይ ያሳረፈው ጠባሳ አልሻረም፡፡

በተለይ በአፍሪካ ቀንድ፣ ኢትዮጵያና ሶማሊያ ቀጥሎም ቦትስዋና፣ ማላዊ፣ ሞዛምቢክ፣ ሌሴቶ፣ ናሚቢያ፣ ዛምቢያ፣ ዚምባብዌ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ኬንያና ማዳጋስካር ስፋቱ ይለያይ እንጂ ግብርናቸው የኤልኒኖ ሰለባ ሆኗል፡፡ በዚምባብዌ ባለፈው በነሐሴ 2016 የምግብ ዕርዳታ የሚፈልጉት ቁጥር 2.2 ሚሊዮን የነበረ ሲሆን፣ ጥር ላይ ደግሞ ወደ 4.1 ሚሊዮን አሻቅቧል፡፡ ከእነዚህም 42 በመቶ ያህሉ በገጠር የሚኖሩ ናቸው፡፡

በሐምሌ 2008 ዓ.ም. ባስከተለው ድርቅም የተጎዱ ሰዎችን ለመርዳት ዓለም አቀፍ የምግብና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት አራት ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንደሚያስፈልግ አሳውቀው ነበር፡፡ ከዚህ ውስጥ 80 በመቶ ያህሉ ለምግብ ብቻ የሚውል ነበር፡፡ በአፍሪካ የድርቁ ሁኔታ እየቀነሰ ቢሆንም፣ በቀጣይ ለሚኖረው እርሻም ሥጋት አለ፡፡ ብዙዎቹ በድርቁ የተመቱ አገሮች አላገገሙም፡፡ ዘር፣ ማዳበሪያና የግብርና ግብዓቶች አልተዳረሳቸውም፡፡ ይህም ቀጣዩን የእርሻ ወቅት ያከሽፈዋል የሚል ሥጋት አሳድሯል፡፡

በአፍሪካ ካሪቢያንና ፓስፊክ አገሮች ግብርናና ትብብር ላይ አተኩሮ በየሦስት ወሩ በኔዘርላንድስ የሚታተመው ስፖር መጽሔት በ2017 የመጀመሪያ ዕትሙ እንዳሰፈረው፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት በግብርናው ላይ የተከሰተውን አደጋ ለመቀነስ በበልግ ወቅት ካልተሠራ 23 ሚሊዮን አፍሪካውያን እስከ ሰኔ 2010 ዓ.ም. ድረስ የዕርዳታ ምግብ ተመጽዋች ይሆናሉ፡፡

ኤልኒኖ ያስከተለው ጉዳት ሳያገግም፣ ከሁለት እስከ አምስት ዓመታት እየጠበቀ የሚመጣውና ጎርፍ የሚያስከትለው ላሊና ሌላ ሥጋት ፈጥሯል፡፡ በኤልኒኖ ለተጎዱ አገሮች ላሊና የዝናብ ተስፋ ቢሆንም፣ ይህ መልካም ዜና አይደለም፡፡ ላሊና የሚያስከትለው ከባድ ዝናብ ለጎርፍ መንስዔ ነው፡፡ ሰብሎችን ያወድማል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ውኃ ወለድ የከብት በሽታዎችን ያስከትላል፡፡

የዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) በድርቁ የተጎዱ አካባቢዎች እንዲያገግሙ ማድረግ ካልተቻለ በዓለም አቀፍ ደረጃ 100 ሚሊዮን ሰዎች የኤልኒኖ ላሊና ተጎጂ ይሆናሉ ብሏል፡፡ ኢትዮጵያም ከአየር ንብረት ለውጡ ተፅዕኖ የተለየች አይደለችም፡፡

በኢትዮጵያ ከሁለት ዓመታት በፊት ከተከሰተው ድርቅ ዛሬም አላገገመችም፡፡ ከብቶች አልቀዋል፣ ሰዎች የምግብ ተረጂ ሆነዋል፡፡ በ2009 ዓ.ም. መጀመሪያ 5.6 ሚሊዮን የድርቅ ተጎጂዎች የምግብ ድጋፍ እየተደረገላቸው የነበረ ሲሆን፣ ይህ ቁጥር ከስድስት ወራት በኋላ ወደ 7.8 ሚሊዮን አሻቅቧል፡፡    

በኢትዮጵያ ድርቅን ተከትሎ የምግብ ተረጂዎች ቁጥር ከሰባት ሚሊዮን በላይ መድረሱን ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) አስታውቀዋል፡፡

ሚያዝያ 30 ቀን 2009 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ በተከበረው የዓለም ቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ቀን ላይ ፕሬዚዳንት ሙላቱ እንደገለጹት፣ ከተጠቀሱት ወገኖች መካከል ከ5.6 ሚሊዮን በላዩ ዘንድሮ በተከሰተው ድርቅ ዕርዳታ የሚፈልጉ ናቸው፡፡

መንግሥት የምግብ፣ የውኃና ሌሎችንም ዕርዳታዎች በማቅረብ ላይ መሆኑን ፕሬዚዳንቱ አመልክተው፣ በዚህ ሰብአዊ እንቅስቃሴ ላይ በአገር ውስጥና በውጭ አገር የሚገኙት አጋሮች ከመንግሥት ጎን መቆማቸውን አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ፕሬዚዳንት ዶ/ር አህመድ ረጃ፣ በኤልኒኖ ሳቢያ በተፈጠረው የአየር ንብረት መዛባት ጉዳት ለደረሰባቸው 800 ሺሕ ወገኖች ማኅበሩ አልሚ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ መሠረታዊ ቁሳቁሶችን እንዳቀረበ ተናግረዋል፡፡

ማኅበሩ በድርቅ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ዕርዳታ በማቅረብ ብቻ ሳይወሰን ኅብረተሰቡ አደጋን አስቀድሞ ለመከላከል የሚያስችሉትን የአቅም ግንባታ ሥራዎች በማከናወን ላይ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡

ለአደጋ የማይበገር ማኅበረሰብ ለመፍጠር የሚያስችል የአካባቢ ልማት ቢኖርም፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የራስን የገቢ ምንጭን ለማሳደግ የሚያስችሉ ሰብአዊ ተግባራትን እየሠራም ይገኛል ብለዋል፡፡

‹‹ለተጎጂዎች በያሉበት›› በሚል መሪ ቃል በተከናወነው ክብረ በዓል ላይ፣ የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ፌዴሬሽን ልዑክና በአፍሪካ ኅብረት ቋሚ ተወካይ ሚስተር ዮሱፍ ኢት ቼሎቼ፣ የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ልዑክ ሚስተር ጀምስ ፊኖልድ ተገኝተዋል፡፡ ሚስተር ዩሱፍ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ጎርፍና ድርቅ በኅብረተሰቡ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን ገልጸው፣ ይኼንን ጉዳት ለመከላከልና ለመቀነስ የሚያስችል ሥራ ለማከናወን ፌዴሬሽኑ ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑን አክለዋል፡፡ ሆኖም ዕርዳታው ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች በአግባቡ አለመድረሱን ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

በተፈጥሮ ሰው ሠራሽ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ፈጥኖ የሰብአዊ ዕርዳታ የሚያቀርበው የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የተቋቋመው በ1927 ዓ.ም. ነው፡፡