Skip to main content
x

የኦሮሚያ “የኢኮኖሚ አብዮት” የወለዳቸው ተስፋዎችና ሥጋቶች

አወዳይ ከጥቂት ዓመታት በፊት በሐሮማያ ወረዳ ሥር ያለች አንዲት ትንሽ ቀበሌ ነበረች፡፡ አሁን ከተማዋ ከሐረርጌ ከተሞች ምናልባት ከጭሮ (አሰበ) ቀጥሎ ሁለተኛዋ ትልቅ ከተማ ነች፡፡ ከተማዋ ለአገሪቱ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ዓመታዊ ገቢ የሚያስገኝላት የጫት ንግድ (ቢዝነስ) ማዕከል ነች፡፡ የጫት ንግድ (ቢዝነስ) ተዋናዮቹን የአውሮፕላን ባለቤት እስከ ማድረግ የሚደርስ ትልቅ ንግድ ነው፡፡ ሌሎቹ የንግዱ ተዋናዮችም እንደየደረጃቸውና ሚናቸው ተጠቃሚ ናቸው፡፡ አሁን የአወዳይ ከተማ በእሷ ደረጃ ካሉ ሌሎች የአገራችን ከተሞች ሁሉ የበለጠ በርካታ ሚሊዮነሮች የሚኖሩባት ከተማ ነች፡፡ የአወዳይ ሚሊዮነሮችና ሌሎችም የመካከለኛ ገቢ ባለቤቶች በእነሱ ደረጃ እንዳለ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የኢንተርፕረነርሺፕ ክህሎታቸው ውስን ስለሆነ፣ ገንዘባቸውን ቅንጡ መኖሪያ ቤት በመገንባት፣ መኪና  በመግዛት፣ ወይም ባለሦስት ወይም አራት ፎቅ ሕንፃ በመገንባትና በመሳሰሉት የተለመዱ ዘርፎች ላይ ነው የሚያውሉት፡፡

በነገራችን ላይ ከአወዳይ ባሻገር እስከ ምዕራብ ሐረርጌ ድረስ ያሉ በርካታ ወረዳዎች በጫት ወጪ ንግድ ተሳታፊ ናቸው፡፡ የአዲስ አበባና የአካባቢዋን የጫት ገበያም ቀላል በማይባል ደረጃ የተቆጣጠረው ሐረርጌ ነው፡፡ ሐረርጌ ከጫት ባሻገር የአገሪቱ ምርጥ የሚባለው ቡና አምራች አካባቢም ነው፡፡

ግን ሌላ ተቃራኒ ሀቅም አለ፡፡ ሐረርጌ ከሌሎቹ የኦሮሚያ አካባቢዎች በላይ የምግብ ዋስትና ችግር ያለበት አካባቢ ነው፡፡ ከፍተኛ የመሬት ጥበት ያለበት አካባቢ ነው፡፡ በዚህም መሬትም ሥራም የሌላቸው ወጣቶች የሞሉበት አካባቢ ነው፡፡ እነኚህን ተቃራኒ እውነታዎች ማስታረቅ የመንግሥት ኃላፊነት ነበር፡፡ በተለይ ‹‹ግራ ዘመም›› የሆነው ኢሕአዴግ በዚህ ጉዳይ ላይ “ቀኝ ዘመሞች ቢሆኑ የማያደርጉትን” ዕርምጃ መውሰድ ነበረበት፣ ግን አልወሰደም፡፡ አወዳይ ላይ በተወሰኑ ሰዎች እጅ ብዙ ሚሊዮን ብር አለ፡፡ ይኼ ብር ግን ለብዙኃኑ የሐረርጌ ምንዱባን የሥራ ዕድልን ሊፈጥር በሚችልበት ሁኔታ አይደለም ኢንቨስት እየተደረገ ያለው፡፡

እዚህ ጋ ነው የኦሮሚያ የኢኮኖሚ አብዮት የዘገየ ቢሆንም አስፈላጊነቱ የሚታየን፡፡ ብዙም የኢንተርፕሩነርሺፕ ክህሎት የሌላቸው ሚሊዮነር አርሶ አደሮችና ከተማ ቀመሶች ከለመዱት ዘርፍ ውጪ ለብዙ ሺዎች የሥራ ዕድልን ሊፈጥሩ በሚችሉና ዘመን ተሻጋሪ በሆኑ ግዙፍ ኢንቨስትመንቶች መሰማራት የሚችሉት፣ ሐሳብ የሚያመነጭላቸውና የሚያስተባብራቸው ካለ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ኦሮሚያ እየሄደበት ያለው አቅጣጫ ሌሎች ክልሎችም ሊማሩበት የሚገባ ይመስለኛል፡፡

የኦሮሚያ የኢኮኖሚ አብዮት መቀጣጠልን ተከትሎ ብዙ ድምፆች እየተሰሙ ነው፡፡ አብዛኞቹ ድምፆች የተስፋና የማበረታቻ ናቸው፡፡ ጥቂት የሥጋትና የትችት ድምፆችም አሉ፡፡ ከሥጋት አንፃር እየተነሱ ያሉ ድምፆች የኢኮኖሚ አብዮቱ ሲጀመር ምንም እሴት የማይጨምሩ፣ የማዕድን ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች መሬት ነጠቃና የሲሚንቶ ፋብሪካዎች የፑሚስ ግብዓት በፋብሪካው በራሳቸው መሆኑ ቀርቶ በተደራጁ የኦሮሚያ ወጣቶች እንዲቀርብ መደረጉ ላይ የተመሠረቱ ናቸው (የታሰሩት ሳይፈቱ፣ የዴሞክራሲ ጥያቄዎች እንደዚህ ሳይሆኑ፣ እንደዚያ ሳይሆኑ፣ . . . የሚሉና ከኢኮኖሚ አብዮቱ ጋር ተያያዥነት የሌላቸውን አጀንዳዎች እዚህ ጋ አናይም)፡፡

 መሬት የተነጠቁ ሰዎች ‹‹ሕገ መንግሥታዊ መብታችን ተጣሰ!›› እያሉ ሲሆን፣ አቅም ያላቸው ባለሀብቶች አቅምና ቴክኖሎጂው በሌላቸው ወጣቶች ሊሠሩ የሚችሉ ሥራዎችን ሲሠሩ መቆየታቸውን መንግሥት እንዲያበረታታላቸው መጠበቃቸው ትክክል አይመስለኝም፡፡ ባይሆን ውሳኔው ድንገተኛ ነውና የመዘጋጃ ጊዜ እንዲሰጣቸው፣ ወይም የሥራ ዘርፍ ሲቀይሩ አስፈላጊው ማበረታቻና እንደ ሁኔታው ካሳም እንዲታሰብላቸው ቢጠይቁ ተገቢ ነው እላለሁ፡፡ 

በዚህ ረገድ ኢሕአዴግ ‹‹ማኅበራዊ መሠረቶቼ ናቸው›› የሚላቸውን አርሶ አደሮችን፣ የከተማ ንዑስ አምራቾችንና ላብ አደሮችን የረሳ በሚያስመስል ሁኔታ በ‹‹ማኅበራዊ መሠረቶቹ ላይ›› አንዳንዴ የቀኝ ኃይሎች እንኳ የማያደርጉትን ጫና ሲፈጥርባቸው ይስተዋላል፡፡ እዚህ ግባ በማይባል ካሳ አርሶ አደሮችና የከተማ ነዋሪዎች ከይዞታቸው እየተፈናቀሉ መሬታቸው ለባለሀብቶች ይሰጥባቸዋል፡፡ 30 ወይም 100 የከተማ ወይም የገጠር ነዋሪዎች ተፈናቅለው መሬቱን ያገኘው ‹‹ኢንቨስተር›› ሕንፃ ገንብቶ ቢሮዎችን በማከራየት ወይም የሸክላ አፈር ቆፍሮ በመሸጥ የራሱን ኑሮ ሲቀይር፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ ወይም በኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን ግን የሚጫወተው ሚና ሳይኖር የቆየ ቢሆንም፣ ቡራኬውን ያገኘው ግን ከ‹‹ግራ ዘመሙ›› ኢሕአዴግ ነበር፡፡ ማኅበራዊ መሠረታቸውን መካከለኛና ከፍተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች ላይ ያደረጉ በርካታ ምዕራባውያንም ሆኑ ወደ ብልፅግና እየተንደረደሩ ያሉት ምሥራቃውያን ፓርቲዎች እንኳ፣ በዚህ ደረጃ አቅም የሌላቸው የመሬት/ቤት ባለይዞታዎችን ሲጫኑ አይታይም፡፡

አዕላፍ ምንዱባን ከመሀል ከተማ እየተፈናቀሉ በእነሱ ቦታ ላይ ‹‹ኢንቨስተሮች›› ሕንፃ ገንብተው እንዲያከራዩ ከመፍቀድ፣ የመሬት ባለቤቶች በማኅበር ተደራጅተው ባንክም ብድር አመቻችቶላቸው ሕንፃውን እንዲገነቡ ቢደረግ እውነተኛ ሕዝባዊ ወይም ግራ ዘመም መንግሥት ያስብላል፡፡ በዚህ ረገድ ደኢሕዴን/ኢሕአዴግ በሐዋሳ ከተማ የመሬት ባለይዞታዎች ከባንክ ብድር እየተመቻቸላቸው የሚከራዩ ቤቶችን እንዲገነቡና የኢንዱስትሪ ፓርክ የጠራቸው አዳዲስ ነዋሪዎች በቤት እንዳይቸገሩ የጀመረውን አቅጣጫ ማጠናከር፣ ድጋፉ ለትልልቅ የንግድ ሕንፃዎችና ሪል ስቴቶች ግንባታ ጭምር ተፈጻሚ መሆን እንዲጀምር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

በገጠርም እሴት በማይጨምሩ የማዕድን ዘርፎች ተሰማርተው በርካታ ምንዱባን ሊሠሩ የሚችሉትን ብቻቸውን ሲሠሩ የነበሩ ‹‹ኢንቨስተሮች›› የእስከ ዛሬው ቡራኬ ኢሕአዴግ ማኅበራዊ መሠረቶቹን በመዘንጋት የተፈጠረ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋቸዋል፡፡ እንዲያውም ይኼው ዕርምጃ ወደ ከተሞችም ሊገባ እንደሚችል /እንደሚገባ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ 

የግዙፎቹ የሲሚንቶ ፋብሪካዎችን ግብዓት አቅርቦትን በተመለከተ ፋብሪካዎቹ በራሳቸው ለመሥራት ግሬደሮችን፣ ገልባጮችንና ሌሎችንም አስፈላጊ ግብዓቶች አሟልተው ሲሠሩ የነበሩ ከመሆናቸው አንፃር፣ ሠራተኞቻቸውም ሥራውን ለረዥም ጊዜ የለመዱትና የተካኑበት ከመሆናቸው አንፃር ብዙም ደስተኛ ባይሆኑ አይገርምም፡፡ እነሱ ላይ የሚፈጠር ቅሬታ ደግሞ በቀላሉ ሚዲያዎችና ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ አማካሪዎች ጆሮ ሊደርስ መቻሉን ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡ በንድፈ ሐሳብ ደረጃ የግብዓት አቅርቦቱን ወጣቶች ተደራጅተው መሥራታቸው ተገቢ ቢሆንና የግብዓት መሸጫ ዋጋውም ፋብሪካዎቹ በተስማሙበት መጠን ቢሆንም፣ አፈጻጸሙ ላይ መንጠባጠቦች ሊኖሩ እንደሚችሉ፣ ይኼ ደግሞ ከፍተኛ ፉክክር ባለበት የሲሚንቶ ገበያ ላይ በኦሮሚያ ያሉ ፋብሪካዎችን ተወዳዳሪነት አነሰም በዛ ሊጎዳ እንደሚችል ማሰብ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ይኼ ላለመሆኑ ዋስትና መስጠት ከተቻለ ኦሕዴድ/ኢሕአዴግ በነደፈው አቅጣጫ በሺሕ የሚቆጠሩ ወጣቶች የሥራ ዕድል ይፈጠርላቸዋል፡፡  ፋብሪካዎቹን የጎሪጥ የሚያይም አይኖርም፡፡ ሒደቱን ግን በጥንቃቄ መከታተልና ከፋብሪካዎቹ ማኔጅመንት ጋር ተቀራርቦ መሥራት ይጠይቃል፡፡

በኦሮሞ የኢኮኖሚ አብዮት ላይ በይፋ እየተሰሙ ያሉ ሥጋቶች እነኚህ ብቻ ቢሆኑም፣ ትኩረትን የሚሹ ሌሎች ነጥቦችም ይኖራሉ፡፡

የመጀመሪያው አገሪቱ ወደ ኢኮኖሚያዊ ትራንስፎርሜሽን መሸጋገር ካለባት ከአንድ ኢንቨስተር እንዲመጣ የምንጠብቀውን ገንዘብ ከብዙ ሺሕ ነዋሪዎች በመሰብሰብ በራስ አቅም ግዙፍ ኢንቨስትመንቶችን መፍጠር ፋይዳው የሥራ ዕድል ከመፍጠር ያለፈ ነው፡፡ የነገዋ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በጥቂቶች እጅ ሥር አለመሆኑን ከወዲሁ የምናረጋግጥበትም ጭምር ነው፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃም ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ሆኖም በዚህ ረገድ ከዚህ በፊት ምንም አልተሠራም ማለት አይደለም፡፡

የዛሬ አሥር ዓመታት ገደማ የአክሲዮን ማኅበራትን ማቋቋም አጓጊና ብዙዎችን የሳበ ንግድ ሆኖ ነበር፡፡ አሁን የምናያቸው ስካይ ባስና አሊያንስ የከተማ አውቶብስ በዚህ መንገድ የተቋቋሙ ናቸው፡፡ የቅርብ ጊዜዎቹ ሦስት ቢራ ፋብሪካዎችም መሠረታቸው የአክሲዮን ቢዝነስ ነው፡፡ እስካሁን ከዳር ባይደርሱም የኅብር ስኳርና የሐበሻ ሲሚንቶም ሌሎቹ ተጠቃሽ አክሲዮን ወለድ ቢዝነሶች ናቸው፡፡

መንግሥት ይኼንን ዘርፍ በማጠናከር በርካታ ግዙፍ ኢንቨስትመንቶች እንዲፈጠሩ ማድረግ ሲገባው፣ ዜጎች በአክሲዮን በሚቋቋሙ ንግዶች ላይ አመኔታ እንዳይኖራቸው የሚያደርጉ ተደራራቢ መሰናክሎች ተፈጥረውባቸዋል፡፡ የፌዴራልም ሆነ የክልል ማኅበራት ማደራጃዎች በዚህ ረገድ ሲጫወቱ የነበረው ሚና ለብዙ ትችቶች የተጋለጠ ነው፡፡ መንግሥት በቅርቡ በዚህ ረገድ የነበሩ ክፍተቶችን ለመድፈን የሚያስችሉ ዕርምጃዎችን እወስዳለሁ እያለ ሲሆን፣ ዕርምጃው ማኅበራትን ከመደገፍ አልፎ የአገሪቱ ግዙፍ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሾች በጥቂት ግለሰቦች ሳይሆን በብዙኃን ዜጎች ባለቤትነት ሥር እንዲሆኑ የማድረግና ያለማድረግ ጉዳይ ጭምር መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት የምር ለውጥ ሊያመጣ ይገባል፡፡

 እስከ ዛሬ ኢሕአዴግ ሕዝባዊ መሠረቶቼ ለሚላቸው ከተሜዎች ያመቻቸላቸው በጥቃቅንና አነስተኛ መደራጀትና አሁን ደግሞ በከተማ ሴፍቲኔት መታቀፍን እንጂ፣ ትልልቆቹ ቢዝነሶች ላይ መሰማራትን ሳይሆን መቆየቱ ያሳዝናል፡፡ ይኼንን ግዙፍ ስህተቱን ሊያርም የሚችበት ዋነኛ መንገድ ነው የአክሲዮን ቢዝነስ እንዲያብብ ማድረግ፡፡

የኦሮሚያ ኢኮኖሚ አብዮት የወለዳቸው ግዙፍ ኩባንያዎችም በዚህ ረገድ ከተጋረጠባቸው ሥጋት ነፃ ማድረግ ከኦሕዴድ/ኢሕአዴግ ይጠበቃል፡፡ የመንግሥት ባለሥልጣናት አላስፈላጊ ጣልቃ ገብነት መቅረት፣ የአክሲዮን ማኅበራቱ ማኔጅመንቶች አቅምና ተዓማኒነት ደግሞ አስተማማኝ መሆን አለበት፡፡

ከኦሮሚያ ኩባንያዎች ጋር ተያይዞ ትኩረት የሚያሻው ሌላው ሥጋት ደግሞ የኢንቨስትመንት ዘርፎች መረጣ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ አንዳንድ ዘርፎች በገበያው ውስጥ አስቀድሞ በቂ ተዋናይ የተሰማራባቸው ናቸው፡፡ ለዚህም የሲሚንቶ ፋብሪካንና የትራንስፖርት ንግድን መጥቀስ ይቻላል፡፡ የንግድ ዘርፎቹ በክልሉ ተወላጆች፣ በጎ ፈቃደኛ ምሁራንና በክልሉ አመራሮች የሚደገፉ ከመሆናቸው አንፃር፣ እንዲሁም ዘርፎቹ የግዙፍ ካፒታል ባለቤቶች ከመሆናቸው አንፃር ብዙም ባልተደፈሩ፣ ግን አዋጪ በሆኑ ዘርፎች ላይ መሰማራት ቢታሰብበት መልካም ይመስለኛል፡፡

በሌላ በኩል በኦሮሚያ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የክልል ኢንዶውመንቶችም ሊነሳ የሚችለው ሥጋት የአገሪቱን አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበረሰብ የመፍጠር ራዕይን ሊሸረሽር በሚችል መንገድ ንግዶቹ ብሔር ተኮር እየሆኑ የመቋቋማቸው ጉዳይ ነው፡፡ ሥጋትነቱ ከአገሪቱ ራዕይ ባሻገር የተቋማቱንም በነፃ ፉክክር ላይ የተመሠረተ ገበያን የማስፋት ጥረትንም ሊጎዳ ይችላል፡፡ በዚህ ረገድ ነገ ምን ዓይነት የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመፍጠር ጥረት እያደረግን ነው? የሚለውን ማሰብ ከሁሉም ይጠበቃል፡፡ አንዱ ከጀመረ ግን ሌላውም መከተሉ አይቀሬ ነውና በዚህ ረገድ ኦሮሚያን መውቀስ አይቻልም፡፡ ምክንያቱም አሁን ከአማራ ክልል አካባቢ የግዙፍ ኩባንያ ምሥረታ እየተሰማ ነውና፡፡

በተረፈ አሁን በመላ አገሪቱ እየተቋቋሙ ካሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮች መካከል የ49 በመቶ ድርሻቸው ልምድ ባላቸው የውጭ ባለሀብቶች የሚያዙ ግዙፍ የኢንዱስትሪ አክሲዮኖች እየተቋቋሙ፣ በየእጃችን ያለውን ገንዘብ አክሲዮን እንድንገዛበት የማኅበራት ማደራጃም ይሁን ሌላ አካል ቢሠራ የአገሪቱ ቁጥር አንድ ባለውለታ ይሆናል፡፡ የባንግላዴሽ፣ የቻይናና ሌሎች የምሥራቅ እስያ ልምድ ያላቸው ኩባንያዎችን ሎቢ እያደረጉ በአገሪቱ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ላይ እንዲሰማሩና 51 በመቶ ድርሻቸውን ደግሞ በአክሲዮን እንዲሸጡ ማድረግ ከተቻለ፣ በአገራችን የጨርቃ ጨርቅ ንግድ ላይ እመርታዊ ለውጥ ማምጣት ያስችላል፡፡ በሌሎች ዘርፎችም ላይ ተመሳሳይ ሥራዎችን መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ኅብረተሰቡ አመኔታ እንዲያድርበት ማድረግ ከተቻለ ተዓምር መሥራት ይቻላል፡፡ የኦዳ አውቶብስ አክሲዮን ማኅበር በአንድ ቀን ብቻ ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ አክሲዮን መሸጡ የሚያሳየን ይኼንኑ ነው፡፡ ባለሀብቶችን እንጠብቅ ቢባል ኖሮ ይኼን ያህል ካፒታል ያለው ኢንቨስተር በቀላሉ የሚገኝ አልነበረም፡፡

 ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected]. ማግኘት ይቻላል፡፡