Skip to main content
x

የውኃ ፍርኃትና ሥጋት (ኢትዮጵያና ግብፅ)

ጆርጅ ፍሬድማን የተባሉ የጂኦፖለቲክስ ምሁር ቦታና ፍራቻ በጂኦፖለቲክስ ጥናት ውስጥ ሁነኛ ሥፍራ አላቸው ይላሉ፡፡ ቦታና ፍራቻ የአንድን አገር የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ባህሪ በመወሰን ረገድም ወሳኞች ናቸው፡፡ ይኸው እውነታ ኢትዮጵያንና ግብፅን ለይቶ አልተዋቸውም፡፡ ኢትዮጵያ የዓባይ ወንዝ ዋነኛ መገኛ በመሆኗ ወንዙ በተመጣጠነና ምክንታዊ በሆነ መንገድ ጥቅም ላይ መዋል አለበት የሚል አቋም ሲኖራት፣ ግብፅ ደግሞ በወንዙ መጥለቂያ አካባቢ በመኖሯና ሥልጣኔዋና እስትንፋሷ የተገነባው በዚሁ ዳርቻ በመሆኑ አንድም ጠብታ ሳይጎድል ድንበሯ ውስጥ ,ልö እንዲገባ ትፈልጋለች፡፡ በመሆኑም ግብፅ ኢትዮጵያ፣ ግድብና መስኖ የሚባሉት ቃላት ፈጽሞ አይመቿትም፡፡

በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው የውኃና ጂኦፖለቲካዊ እሰጥ አገባ መነሻው ጥንት ነው፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርና በኃይድሮፖለቲክስ ጥናታቸው የሚታወቁት ዶ/ር ተስፋዬ ታፈሰ፣ እ.ኤ.አ. በ2001 ባሳተሙት THE NILE QUESTION: Hydropolitics, Legal Wrangling, Modus Vivendi and Perspectives” በተባለው መጽሐፍ ውስጥ ግብፆች በፍርኃት፣ በጥርጣሬና በሥጋት ተሸክመው ዕድሜ ልካቸውን አሳልፈዋል ይሉናል፡፡ የዚህ ሁሉ ምንጭ ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ሊከናወን ይችል ይሆናል ብለው የሚያስቡት ዓባይን የመገደብ ሥራ ነው፡፡ የጥንትም ሆነ የቅርቦቹ የግብፅ መሪዎች ለሕዝባቸው ሲነግሩት የኖሩት አንድ ነገር ብቻ ነው፡፡ የኢትዮጵያን የዓባይን ፍሰት የመቆጣጠርና የግብፅን ሕዝብ በረሃብ የመጨረስ ዕNድ፡፡

በመሆኑም ግብፃውያን ኢትዮጵያን በፍራቻና በጥርጣሬ ሲመለከቷት ኖረዋል፡፡ ዶ/ር ተስፋዬ በመጽሐፋቸው እንደጠቀሱት ይህንን በሚገባ የተገነዘቡት የኢትዮጵያ መሪዎች ምንም እንኳን አቅሙ ባይኖራቸውም፣ ዓባይን የመገደቡን ጉዳይ በማስፈራሪÃነት ሲጠቀሙበት የተስተዋሉባቸው ጊዜዎች ነበሩ፡፡ ግብፅ ውስጥ የሚገኙ የኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን ተከታዮች ጥቃት እንዳይደርስባቸውና ግብፅ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ እንድትልክ የዓባይን ወንዝ በ«ስፈራሪያነት ተጠቅመውበታል፡፡

ከ1066 እስከ 1072 ባሉት ሰባት ዓመታት ግብፆች በረሃብ በመጠቃታቸው፣ በወቅቱ የነበረው የግብፅ ካሊፍ መልዕክተኞችን ወደ ኢትዮጵያ በመላክ የተገደበው የዓባይ ወንዝ እንዲለቀቅላቸው የኢትዮጵያን ንጉሥ ለማሳመን ጥረዋል፡፡ በወቅቱ የረሃቡ መነሻ ኢትዮጵያ የዓባይን ወንዝ መገደቧ ነው ብለው ያምኑ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ የወንዙ መነሻ መሆኗና የግብፃውያን የግድብ ፍራቻ የኃይድሮና የጂኦፖለቲካዊ ንትርክ መነሻ ከሆነ እጅግ የቆየ መሆኑ ማመላከቻው ይህ ታሪክ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን መሪዎችም ግብፅ አንዳች ተንኮል ብታስብ ወንዙን መገደባቸው እንደማይቀር ሲዝቱ ቆይተዋል፡፡ ግብፅም መፍትሔው ኢትዮጵያን መቆጣጠር ወይም ማተራመስ መሆኑን ማሰብ ከጀመረች እጅግ ቆይታለች፡፡

በ17ኛው ክፍል ዘመን መጠናቀቂያ አካባቢ ግብፅ በቱርክ በመደገፍ ኢትዮጵያን ለመውረርና ለማተራመስ ሞክራለች፡፡ ግብፃውያን የዓባይ ወንዝ የሚፈስባቸውን አካባቢዎች በመቆጣጠርና ከግዛታቸው ጋር በማዋሀድ ታላቋን ግብፅ ለመፍጠርም አስበው ያውቃሉ፡፡ ምዕራባውያን አማካሪዎቻቸውም ጭምር ኢትዮጵያን መቆጣጠር፣ ወይም በኢትዮጵያ ሥርዓት አልባነት እንዲሰፍን ማድረግ፣ ኢትዮጵያውያን ዓባይን ስለመገደብ እንዳያስቡ ማስቻያ መሣሪያ መሆኑን ይነግሯቸው ነበር፡፡ ታላቋን ግብፅ የመመሥረት ህልማቸውን ለማሳካትም ግብፃውያን አሜሪካውያንን ስዊሶችን፣ እንግሊዞችንና ዴንማርካውያን ቅጥረኞችን በማሰማራት ኢትዮጵያን ለመውረር የሚያደርጉትን ጥረት እንዲያግዟቸው ያደርጉ ነበር ሲሉ ዶ/ር ተስፋዬ በመጽሐፋቸው አካትተዋል፡፡

ግብፃውያን ኢትዮጵያ ዓባይን ለመገደብ የገንዘብ አቅም የላትም ብለው ያምኑ የነበረ ሲሆን፣ ዓለም አቀፍ ለጋሾችና አበዳሪዎችም ለኢትዮጵያ ገንዘብ እንዳያቀርቡ ሌት ተቀን ሠርተዋል፡፡ ኢትዮጵያን ለማተራመስም መቀነታቸውን ፈትተዋል፡፡ የትኛውም የግብፅ መሪ ወደ ሥልጣን የወጣ ቀን የመጀመርያ ሥራው “ነጠላዬን አቀብሉኝ” በማለት ºቱን ወደ ኢትዮጵያ መጠቆም ነው፡፡ ዋነኛ ሥራው ፍርኃትና ሥጋትን ማስቀጠል ነው፡፡ አሁን በእስር ላይ የሚገኙት መሐመድ ሙርሲና ሚኒስትሮቻቸው ዓለም በቴሌቪዥን መስኮት እየተመለከታቸው ኢትዮጵያን ማተራመስና  ግንድቡንም ማፍረስ እንዳለባቸው ተነጋግረዋል፡፡ በመሆኑም ግብፅ የኢትዮጵያንና ዓባይን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ ማጠንጠኛ አንደኛው ዘንጓ አድርጋዋለች፡፡

ግብፅ በአሁኑ ፕሬዚዳንቷ አብዱልፈታህ አልሲሲ አማካይነት የተለየ ነገር አሳይታናለች፡፡ አልሲሲ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርም ደሳለኝና ከፕሬዚዳንት አል በሽር ጋር በመሆን የመርሆዎች መግለጫና ለትብብር መነሻ የሆነውን ስምምነት ፈርመዋል፡፡ ስምምነቱ እርባና ቢስ ነው ብለው የሚያምኑ እንዳሉ ሁሉ፣ ታሪካዊና ጠቃሚ ነው ብለው የሚያምኑም በርካታ ናቸው፡፡ ዶ/ር ሳልማን የተባሉ የውኃ ፖለቲካ ምሁር ኢትዮጵያ አሸንፋለች ይላሉ፡፡ በእሳቸው እምነት ስምምነቱ የግብፅን የተዘጋ በር ከፍቷል፡፡ መነጋገርንና ትብብርን ይሰብካል፡፡ ልማትን፣ አካባቢያዊ ውህደትንና ዘላቂነትን ያበረታታል፡፡ በዚህ ስምምነት ግብፅ “ግድቡ ይገደብ፣ ነገር ግን ጉልህ የሆነ ጉዳት በማያደርስ ሁኔታ መሆን አለበት፤” ትላለች፡፡ ፍትሐዊ አጠቃቀምን ደግፋለች፡፡ አለመግባባት ቢፈጠር እንኳ የጠረጴዛ ውይይትን መርጣለች፡፡ ከግድቡ የሚመነጭ የኤሌክትሪክ ኃይልን ለመግዛትም ተስማምታለች፡፡

ከዚህ አንፃር ሲታይ ዶ/ር ሳልማን በፍፁም ትክክል ናቸው፡፡ ዶክተሩ ስምምነቱ ውስጥ ባይጠቀስም እ.ኤ.አ. የ1929 እና 1959 ስምምነቶች ፈርሰዋል ብለው ያምናሉ፡፡ ግብፅ እነዚህን ስምምነቶች ሳትጨምሩና ሳትቀንሱ እንዲሁም ሳታንገራግሩ ተቀበሉኝ በማለት ተቸክላ መቆየቷ ይታወቃል፡፡ ለውጡን ያመጣው ምዕራባውያን በዚህ ጉዳይ ላይ ፊት ስላነሷትና ኢትዮጵም በበርካታ መንገዶች እየገነገነች መምጣቷ XምI ነው፡፡ ሆኖም ግን የጦር ሠፈር የመመሥረት ዕቅዷ በሶማሌላንድ ተቀባይነት ያጣው ግብፅ ትብብር በመመሥረትና በማጠናከር ሰበብ ኢትዮጵያን እየከበበች መሆኗ ደግሞ “ያደቆነ ሰይጣን ሳያቀስ አይቀርም፤” አሰኝቷል፡፡ በመሆኑም ግብፅ እርግጡን እስካልነገረችን ድረስ አንፃራዊ ዝግጅት ማድረግ የግድ ይለናል፡፡

ግድቡን እየገደብን መሆኑና የኃይል ሚዛኑን እየቀየርን ለመሆኑ የማያጠራጥር ሲሆን፣ ይህ ውጤት የተገኘው በመሪዎች የፖለቲካ ቁርጠኝነትና ሕዝብን እያሳተፈ ያለ አገራዊ ፕሮጀክት በመፍጠራችን መሆኑ ሌላው የማያጠራጥር ጉዳይ ነው፡፡ ሕዝቡን ማስተባበርና የባለቤትነት ስሜት እንዲሰማው ማድረግ የመንግሥት ኃላፊነት ነው፡፡ ጎን ለጎንም መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን ማድረግ የግብፅን ዓይነት የጠብ አጫሪነት ፍላጎት በማዳፈን የውስጥ ሰላምን ለመጠበቅ፣ እንዲሁም ልማትን ለማረጋገጥ የሚረዳ በመሆኑ ትጋታችን እጥፍ ድርብ መሆን አለበት፡፡

የዓባይ ተፋሰስ አገሮችን በማስተባበር ወደ አንድ አቅጣጫ በማምጣት ለፍትሐዊ ተጠቃሚነት አጥብቃ የሠራችው ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ እንዲካተቱበት መሥራት ይጠበቅባታል፡፡ የመርሆዎች መግለጫ ስምምነቱን መሠረት አድርጋ ጫና ማሳደር አለባት፡፡ የዓባይ ተፋሰስ አገሮች የጋራ ፕሮጀክት ቢኖራቸው ለአካባቢው ውህደት ጉልህ አስተዋጽኦ ስለሚኖረው ኢትዮጵያ የጀመረችውን መቀጠል አለባት፡፡ ለዴሞክራሲው መጎልበት አሁን ግድ እያለ ያለውን የተቃዋሚዎችንና የመንግሥትን/ኢሕአዴግን ውይይት ወደላቀ ደረጃ ማሸጋገር የቤት ሥራችን ነው፡፡ የጀመርነውን በጎ ነገር ሁሉ ለማስቀጠልና ደንቃራዎቻችንን አስወግደንና አልፈን ለመሄድ ወታደራዊ ኃይላችንን ማጎልበትም መርሳት የለብንም፡፡ ወታደራዊ ኃይላችን ጠብ አጫሪዎችን ለማቀዝቀዝና  “ተመጣጣኝ” ብቻ ሳይሆን ሥር የሚነቅል ዕርምጃ ለመውሰድም እንጠቀምበት፡፡ ለዓለም አቀፍ ሰላም መስፈን የበኩላችንን ለማበርከት የምናደርገው ጥረትም እጅግ በተሻለ መንገድ መቀጠል አለበት፡፡

ግብፃውያን በተለይም መሪዎቻቸው ለዘመናት ተጣብቷቸው የቆየው ፍርኃትና ሥጋት እንዲህ በቀላሉ ይላቀቃቸዋል ብሎ ማሰብ የዋህነት በመሆኑ፣ ሕዝብና መንግሥት እጅና ጓንት በመሆን አገርን ማልማትና ድንበሯንም መጠበቅ ይገባናል፡፡ ይህ ለኢሕአዴግ፣ ለተቃዋሚዎች፣ ለዚህኛው ወይም ለዚÃኛው ብሔረሰብ ወይም ደግሞ ለተወሰነ የኅብረተሰብ ክፍል ብቻ የሚተው ጉዳይ አይደለም፡፡ ሁላችንም ኃላፊዎች ነን፡፡ ለሚቀጥለው ትውልድ የምናስረክባት አገር ሁሌም የተሻለች መሆኗን ማረጋገጥ አለብን፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ያለንበት ጂኦፖለቲካዊና ኃይድሮፖለቲካዊ ሁኔታ ከምንጊዜውም በላይ እየተወጠረ መሄዱ ነው፡፡ ያለንበት ቦታና ሁኔታ ፍፁም የሚያስተኛ አይደለም፡፡

የውኃ ፍርኃትና ሥጋት (ኢትዮጵያና ግብፅ)

ልኡልሰገድ

  

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡