Skip to main content
x
የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በለንደን

የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በለንደን

ከሳምንት ያነሰ ዕድሜ የቀረው 16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በለንደን ከተማ ይካሄዳል፡፡ የኦሊምፒክና የዓለም ሻምፒዮኖቹን ባለወርቆች ጨምሮ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ አትሌቶች ከፍተኛ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ኢትዮጵያ በተለይ በሴቶች የኦሊምፒክና የዓለም ሻምፒዮና ባለወርቆች አልማዝ አያና፣ ገንዘቤ ዲባባና ጥሩነሽ ዲባባን ጨምሮ ወጣትና ነባር አትሌቶችን መርጣ ዝግጅቷን አጠናቃለች፡፡

በሌላ በኩል ለንደን በበጋዋ (ለኢትዮጵያ ክረምቷ) ከምታስተናግዳቸው የዓለም ድንቅ አትሌቶች መካከል ጃማይካዊው ዩሴን ቦልት አንዱ ነው፡፡ ያለፉትን ሁለት የዓለም ሻምፒዮናዎች በ100ሜ - 200ሜ ሩጫ ድርብ ድል፣ እንዲሁም በለንደንና ሪዮ ኦሊምፒክ ድርብርብ ድሎች ያስመዘገበው ቦልት ዘንድሮ የሚያደርገው የ100ሜ ውድድር የመጨረሻውና የስንብት እንደሚሆን ተዘግቧል፡፡

እንዲሁም ሞ ፋራህ የምንጊዜም የ5 ሺሕና 10 ሺሕ ሜትር ሩጫ የዓለም ቁንጮ ለመሆን፣ በለንደን በሁለቱም ርቀቶች በማሸነፍና ለአምስተኛ ጊዜ ለመንገሥ ፍላጎት አለው፡፡ ፋራህ በለንደንና ሪዮ ኦሊምፒክ አራት ወርቆች፣ እ.ኤ.አ. በ2013 እና 2015 የዓለም ሻምፒዮና እንደዚሁ አራት ወርቆች በድል አድራጊነት ማጥለቁ ይታወሳል፡፡

ፕሮግራሙ

የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በኢንተርናሽናል አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር አማካይነት በ1975 ዓ.ም. (1983) ሲጀመር በየአራት ዓመቱ ለማካሄድ ነበር፡፡ የመጀመሪያዎቹ ሻምፒዮናዎች በ1975 እና 1979 ዓ.ም. ከተካሄዱ በኋላ ከሦስተኛው ሻምፒዮና ጀምሮ በየሁለት ዓመቱ እየተካሄደ ዘንድሮ 16ኛው ላይ ደርሷል፡፡

ዓርብ ሐምሌ 28 ቀን 2009 ዓ.ም. በሚጀመረው 16ኛው የዓለም ሻምፒዮና የወንዶች የ10 ሺሕ ሜትር ፍጻሜ ይካሄድበታል፡፡ በዚሁም ኢትዮጵያውያኑ አባዲ ሐዲስ፣ ጀማል ይመርና አንዱዓለም በልሁ በተፎካካሪነት ይጠበቃሉ፡፡ በመጪው ጥቅምት 20ኛ ዓመቱን የሚይዘው አባዲ በሪዮ ኦሊምፒክ 10 ሺሕ ሜትር ፍጻሜ በ27፡36.34 ደቂቃ 15ኛ ሆኖ ማጠናቀቁ ይታወሳል፡፡ አባዲ ከ3,000 እስከ 10,000 ሜትር የሚሮጥ ሲሆን፣ የ10,000 ሜትር ምርጥ ጊዜው አምና ሄንግሎ ላይ ያስመዘገበው 26፡57.88 ነው፡፡

ጀማል ይመር ከ10 ሺሕ ሜትር ሌላ በ10 ኪ.ሜና ኪ.ሜ የጎዳና ሩጫ ተወዳዳሪነቱ የሚታወቅ ሲሆን፣ ባለፈው ወር በሄንግሎ በ10 ሺሕ ሜትር ያስመዘገበው 27፡08.08 ምርጡ ጊዜው ነው፡፡ በዘንድሮው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ10 ሺሕ ሜትር ሙክታር እድሪስና አባዲ ሐዲስን አስከትሎ አንደኛ የወጣው አንዱዓለም በልሁ ሦስተኛው ተወዳዳሪ ነው፡፡

በዓለም ሻምፒዮና መክፈቻ ዕለት የሴቶች 1,500 ሜትር ማጣሪያ የዓለም ሪከርድ ባለቤቷ ገንዘቤ ዲባባ፣ ጉደፋይ ፀጋዬ፣ ፋንታዬ ወርቁና በሶ ሳዶ ይወዳደራሉ፡፡

ቅዳሜ ሐምሌ 29፣ አራት የፍጻሜ ውድድሮች በወንዶች 100 ሜ፣ በሴቶች 10 ሺሕ ሜትርና በወንዶች በከፍታ ዝላይና ዲስከስ ውርወራ ሲካሄድ፣ እኩለ ቀን ላይ ከአራት ዓመት በፊት የዓለም ሻምፒዮን የነበረው መሐመድ አማን የሚሳተፍበት የወንዶች 800 ሜትር የመጀመሪያ ማጣሪያ ይካሄዳል፡፡

በ10ሺ የኦሊምፒክ ሻምፒዮኖቹ አልማዝ አያናና ጥሩነሽ ዲባባ፣ ደራ ዲዳን ይዘው በፍጻሜው ይፎካከራሉ፡፡ አንጋፋዋ ጥሩነሽ በዚሁ ርቀት ከ12 ዓመት በፊት ጀምሮ ባደረገቻቸው የዓለም ሻምፒዮናዎች አራት ወርቅ ማግኘቷ ይታወሳል፡፡  

በሦስተኛው ቀን ውድድር ሐምሌ 30 ቀን ኢትዮጵያውያን የሚጠበቁበት የወንዶችና የሴቶች ማራቶን ይካሄዳል፡፡ ማለዳ ላይ ቀድሞ በሚካሄደው የወንዶች ማራቶን ታምራት ቶላ፣ ፀጋዬ መኰንንና የማነ ፀጋዬ የሚወዳደሩ ሲሆን፣ ከሦስት ሰዓት በኋላ በሚከናወነው የሴቶች ማራቶን ሻምፒዮኗ ማሬ ዲባባ፣ ብርሃኔ ዲባባ፣ ሹሬ ደምሴና አሰለፈች መርጊያ ተፎካካሪ ናቸው፡፡

ከኢትዮጵያ ወርቆች

የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀው ከ34 ዓመት በፊት በ1975 ዓ.ም. በሔልሲንኪ ከተማ (ፊንላንድ) ሲሆን፣ ኢትዮጵያ በነበራት ተሳትፎ ያገኘችው ውጤት ከበደ ባልቻ በማራቶን ያስመዘገበው የብር ሜዳሊያ ነበር፡፡ ከ81 ተወዳዳሪዎች 18ቱ ያቋረጡ ሲሆን፣ አንዱ ደረጃ ነዲ ነበር፡፡ ውድድሩን የአውስትራሊያው ሮቤርቶ ዲ ካስቴላ (2፡10.03) ሲያሸንፍ፣ ከበደ ባልቻ (2፡10.27) ሁለተኛ፣ የሞንትሪያልና ሞስኮ ኦሊምፒክ ባለድሉ የምሥራቅ ጀርመኑ ዋልዴማር ሲርፒኒስክ (2፡10.37) ሦስተኛ ሆኗል፡፡ ኢትዮጵያ በከበደ ብር ሜዳሊያ 15ኛ ሆና ማጠናቀቋ ይታወሳል፡፡

ሐቻምና በቤጂንግ በተካሄደው 15ኛው ሻምፒዮና ሦስት ወርቅ፣ ሦስት ብርና ሁለት ነሐስ ያገኘችው ኢትዮጵያ፣ ወርቁን በገንዘቤ ዲባባ በ1,500 ሜትር፣ በማሬ ዲባባ በማራቶን፣ በአልማዝ አያና በ5 ሺሕ ሜትር ሲሆን፣ ብሩን የማነ ፀጋዬ በማራቶን፣ ገለቴ ቡርቃ በ10 ሺሕ ሜትር፣ ሰንበሬ ተፈሪ በ5 ሺሕ ሜትር፤ ነሐሱን ሐጎስ ገብረሕይወት በ5 ሺሕ ሜትር፣ ገንዘቤ ዲባባ በ5 ሺሕ ሜትር አጥልቀዋል፡፡ ባጠቃላይ ውጤት ኢትዮጵያ 5ኛ ሆና አጠናቃለች፡፡

አውራዎቹ

ኢትዮጵያ በ15ቱ ሻምፒዮናዎች 25 ወርቅ ሜዳሊያዎች ያገኘች ሲሆን፣ አምስት ወርቅ በማግኘት ጥሩነሽ ዲባባና ቀነኒሳ በቀለ ቀዳሚዎች ናቸው፡፡ ጥሩነሽ በ10 ሺሕ ሜትር በሔልሲንኪ (2005)፣ በኦሳካ (2007)፣ በሞስኮ (2013)፣ በ5 ሺሕ ሜትር በፓሪስ (2003)፣ በሔልሲንኪ (2005) በማሸነፍ ነበር ወርቆቹን ያጠለቀችው፡፡

ቀነኒሳ በ10 ሺሕ ሜትር በፓሪስ (2003)፣ ሔልሲንኪ (2005)፣ ኦሳካ (2007)፣ በርሊን (2009)፤ በ5,000 ሜትር በበርሊን (2009) በማሸነፍ ወርቆቹን ተሸልሟል፡፡ ቀዳሚው ባለታሪክ ኃይሌ ገብረሥላሴ በ10 ሺሕ ሜትር በአራት ተከታታይ ሻምፒዮናዎች ስቱትጋርት (1993)፣ ጉተንበርግ (1995)፣ አቴንስ (1997)፣ ሲቪያ (1999) ማንንም ጣልቃ ሳያስገባ ወርቁን ጠቅሎታል፡፡

ሌሎቹ ባለወርቆች መሠረት ደፋር በ5 ሺሕ ሜትር ሔልሲንኪና ሞስኮ ሁለት ወርቅ፣ ገዛኸኝ አበራ በኤድመንተን በማራቶን፣ ደራርቱ ቱሉ በ10 ሺሕ፣ ጌጤ ዋሚ በሲቪያ በ10 ሺሕ፣ ብርሃኔ አደሬ በፓሪስ በ10 ሺሕ፣ ኢብራሂም ጀይላን በዴጉ 10 ሺሕ፣ መሐመድ አማን በሞስኮ 800 ሜትር፣ ማሬ ዲባባ በቤጂንግ ማራቶን፣ አልማዝ አያና በ5 ሺሕ ሜትር፣ ገንዘቤ ዲባባ በ1,500 ሜትር ወርቅ ያገኙ ናቸው፡፡

በሐቻምናው የዓለም ሻምፒዮና ማሬ ዲባባ፣ አልማዝ አያና፣ ገንዘቤ ዲባባ ባለድሎች ስለነበሩ በቀጥታ በተጋባዥነት በመግባታቸው፣ ኢትዮጵያ በየውድድሮቹ አራት አራት ሯጮች በማሳተፍ  ተጠቃሚ ሆናለች፡፡

ኢትዮጵያና የ34 ዓመቱ ምርጥ ደረጃ

ደረጃ

አገር

ወርቅ

ብር

ነሐስ

ድምር

1

አሜሪካ

143

96

84

323

2

ሩሲያ 

53

59

58

170

3

 ኬንያ

50

43

35

128

4

 ጀርመን

31

29

37

97

5

 ጃማይካ

31

44

35

110

6

 ብሪታንያ

26

29

36

91

7

ኢትዮጵያ

25

22

25

72

8

 ሶቭዬት ኅብረት

22

27

28

77

9

 ኩባ

21

23

12

56

10

ምሥራቅ ጀርመን

20

18

15

53