Skip to main content
x
የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ነፀብራቆች

የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ነፀብራቆች

በለንደኑ 16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ5000 ሜትር ማጣርያ ባለድሉ ዮሚፍ ቀጀልቻና ዘና ብሎ ሦስተኛ የወጣው ሙክታር እድሪስ፣ ሁለተኛ ከወጣው ሞ ፋራህ ጋር፤ የባለወርቁ ሞ ፋራህ ገጽታ በ10000 ሜትር ፍጻሜ አጠገቡ አባዲ ሐዲስ ይታያል፡፡ በአሎሎ ውርወራ ሁለተኛ የወጣው የክሮሽያው አትሌት አንደኛ ለወጣው ፖላንዳዊ ደስታውን በመሸከም ነበር የገለጸው፡፡

የበጎች እረኛ

ሙሴ ባህር ከፍሎ ሕዝቡን አሻገረ፣

በታላቁ መጽሐፍ ይኼ ቃል ነበረ፤

የእኛ ሙሴ መርቶን፣

የአርነትን መንገድ በሩቅ አመላክቶን፣

በበረሃ ጉዞ ወንዙ ፊት አድርሶን፤

ይከፍለዋል ስንል ባህሩን በእጆቹ፣

መርከቡን ተሳፍሮ ከእነዘመዶቹ፣

በተስፋ ስናየው እንሳፈር ብለን፣

‹‹ዋና የምትችሉ ተከተሉኝ!›› አለን፡፡

ከነዓን ምድር ላይ ያሰበው ቢሞላም፣

ሙሴ ሕዝቡን መርቶ እሱ ግን አልገባም፤

እኛ መሪ ብለን ታምነነው ወጥተናል፣

እሱ እስራኤል ገብቶ እኛ ግን ቀርተናል፡፡

  • ሰሎሞን ሞገስ ‹‹የተገለጡ ዓይኖች›› (2009)

***

 

‹‹ላሙን ለኛ በረቱን ለእረኛ››

‹‹ተረት ተረት›› ሲል ተራቹ መላሹ ‹‹የላም በረት›› ‹‹የመሠረት›› እያለ መመለሱ፣ አድማጭ ተረቱን ለማዳመጥ መስማማቱን መግለጹ ነው፡፡ ተራቹ በዚህ ብቻ አይቆምም፣ ወደ ተረቱ የሚዘልቀው ‹‹ላሙን ለኛ በረቱን ለእረኛ›› በማለት ነው፡፡

ተረት በሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል ቢኖርም አካሔዱ ግን እንደየብሔረሰቡ ትውፊት ይለያል፡፡ ይህ የተረት መንደርደርያ የተገኘው ከአዲስ አበባ ሰሜን ምሥራቅ 140 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከሚገኘው አንኮበር ነው፡፡ አንኮበሮች ተረትን እንደ ቁም ነገር ማስተላለፊያ ማስተማሪያ /መማማሪያ፣ ይቅርታን ማስተማሪያ ብልሃት አድርገው ይጠቀሙበታል፡፡

‹‹ነገር በምሳሌ፣ ጠጅ በብርሌ፣ መዝሙር በሃሌ›› እንዲሉ አንኮበሮች ፍየልን በለፍላፊነት፣ ጦጣን በብልጠት፣ ዝንጀሮን በቂልነት፣ ኤሊን በአዝጋሚነት፣ በግን በየዋህነት፣ ጅብን በሆዳምነት፣ አንበሳን በጀግንነት፣ ዶሮን በረባሽነት በመጠቀም ቤተሰቦቻቸውን ልጆቻቸውን ያስተምሩበታል፡፡

***

ወንዶች ከሴቶች የበለጠ እንዲከፍሉ የሚጠየቁበት ካፌ

በአውስትራሊያ ሜልቦርን የሚገኝ የአትክልት ተመጋቢዎች ካፌ፣ ወንዶችና ሴቶች ለሚያገኙት ተመሳሳይ አገልገሎት፣ ወንዶች የሚከፍሉትን ከሴቶች 18 በመቶ ብለጫ እንዲከፍሉ አደረገ፡፡

ኤምኤስኤን እንደዘገበው፣ ክፍያው በፍላጎት የሚፈጸም ሲሆን፣ ገቢውም ትርፋማ ባልሆነ ዘርፍ የሚሠሩ የሴት ተቋማትን ለመደገፍ ነው፡፡ የካፌው ባለቤት አሌክስ ኦ ብራያን ለዴይሊ ሜል እንዳለው፣ ወንዶች ላገኙት አገልግሎት ሴቶች ከሚከፍሉት 18 በመቶ ጭማሪ መክፈል ካልፈለጉ አይገደዱም፡፡ ካፌው ወንዶችን ጭማሪ ገንዘብ ከማስከፈሉም በተጨማሪ ለሴት ተስተናጋጆች ቅድሚያ መቀመጫ ይሰጣል፡፡

***

ተመስጦ?

ባለፈው ሳምንት (ሐምሌ 26 ቀን 2009 ዓ.ም.) ኪነ ጥበበኛው ነፍስ ኄር ተስፋዬ ሳህሉ (1916-2009) ሥርዓተ ቀብር በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሲፈጸም፣ አንድ የውጭ ዜጋ በምሥራቅ አቅጣጫ በካህናት መግቢያ እጆቹን ዘርግቶ፣ እግሮቹን አጣጥፎ ጸሎቱን ያደርስ ነበር፡፡

ፎቶ በዳንኤል ጌታቸው

                              ***