Skip to main content
x

የጋራ መግባቢያ የቸገረው የኢትዮጵያ ታሪክ

በበቀለ ሹሜ

ሰላም፣ ነፃነት፣ ፍትሕ፣ ዴሞክራሲ፣ ብልፅግና የመልካም ሕይወት መሠረቶች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የተሻለ ሕይወትን ሲሹ ለዚህም በተለያየ ደረጃና መልክ ሲታገሉ ኖረዋል፡፡ የተሳሰሩና በአንድ ቀንበር ሥር የኖሩ እንደ መሆናቸው የትግላቸው መፍጠንና ስኬታማነት የተባበረ ክንድን፣ ይህ ደግሞ አካባቢያዊ ውስንነትን ጥሶ ከሁሉም በላይ በጋራ ዓላማ ላይ ማተኮርን ሲጠይቃቸው ኖሯል፡፡

ልማት ሊሳካልን ቀርቶ ከረሃብ የማምለጥ ጥያቄ ዋና እስከመሆን ገዝፎና ከብዶ የነበረው ለምንድነው? የዕድገት፣ የሰላም፣ የነፃነት፣ የፍትሕና የዴሞክራሲ ችግራችን የት ቦታ ነው?

ገዢዎቻችን የዕድገት እንቅፋቶችንና የመራባችንን ምክንያት ተፈጥሮ በምታደርሰው በደልና በሕዝብ ቁጥር መጨመር ሲያሳብቡ ኖረዋል፡፡ ሲከፋም በውስጥና በውጭ ጠላቶች አላሠራም ባይነት ሲብራራና ሲመካኝ ማየትም ያልተለመደ አይደለም፡፡

ይበልጥ የሚያዋጣን ግን ከእዚህ ሁሉ ሰበቦች ተላቅቀን የችግሮቻችንን ጓዳ ጎድጓዳ በታሪክ ጎዳና ብንመረምር ነው፡፡ ታሪክ ‹‹እህ›› ብሎ ላደመጣትና ልብ ብሎ ለተረዳት ብዙ ትሰጣለች፡፡

አሳዛኙ ችግር ግን ታሪካችንም ራሱ በኢትዮጵያ ሕዝቦች ላይ የወደቀው ቀንበር ሰለባ ነው፡፡ ዛሬም አብሮን ያለ የተጠናወተን ችግራችን ነው፡፡ ሲወርድ ሲዋረድ የመጡ፣ በፀረ ጭቆና ትግሉ ውስጥ የተቋቋሙ፣ ትምክህትንና እብሪትን ሙያ አድርገው የሚያስይዙ፣ እንዲሁም ለቁርሾና ለፀብ አራጋቢዎች የሚመቹ ታሪክ መሳይ አስተሳሰቦች በየዋልታው አሉ፡፡

በአንድ በኩል ሰሎሞናዊ ነገሥታት ከአምላክ ጋር በዝምድና የመተሳሰርና እስራኤላዊ የዘር ሐረግ የማግኘት ሕልማቸውን ያሟሉበት፣ የንግሥተ ሳባ ከንጉሥ ሰለሞን የፀነሸችበት አፈ ታሪክ፣ ነገሥታት ሰማያዊ ተልዕኮ የፈጸሙበት ቅድስናና ገናናነት ያገኙበት ገድል አሁንም አዲስ ጉልበት አግኝቶ አስተሳሰብን ሲያጣብብ እናያለን፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የነፍጠኛውን ሥርዓት በደል በማጋለጥና በመታገል እንቅስቃሴ ውስጥ ከብሶትና ከጊዜያት ብዛት ሴማዊነትን ጠላት ያደረገ አሳሳች መስመር በቅሏል፡፡

እነዚህና መሰል አስተሳሰቦች ኅብረተሰቡ ውስጥ መርዝ የማበጀት አቅም የማይኖራቸው ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ አስተዳደር እየተሟላ መምጣት ከቻለና አብሮም የሚያጋልጣቸው የታሪክ ማረሚያ ከኖረ ነው፡፡ ታሪካችን በነፃነት መጠናት፣ በነፃነት መነገርና ማነጋገር ያለበትም ለዚህ ነው፡፡   

የግዛት ጥቅለላው ተከናውኖ አገር “ማዘመን” የተጀማመረበት የ20ኛው ክፍለ ዘመን ምዕራፍ ከሃይማኖታዊና ከዜና መዋዕል ግዳጆች የተላቀቀ ታሪክ መጻፍ የተጀመረበትም ጊዜ ነው፡፡ ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ አዘንባይነቱ እንዳለ ሆኖ ኢትዮጵያን የተመለከቱ ታሪኮች በአማርኛ ሊጻፉ ችለዋል፡፡ እነ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ የዘመኑ የነባርነትና የመዘመን ድርብ ገጽታ መገለጫ እንደ ነበሩ ሁሉ፣ ሕክምና የተማረው ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ ዘመኑን ርቆ ያለፈ ሰው ነበር፡፡ የጻፋቸው መንግሥትና የሕዝብ አስተዳደር፣ አፄ ምኒልክና ኢትዮጵያ በብስለታቸው ዛሬም ተጠቃሽ እየሆኑ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በተለያየ አቅጣጫ አሻራቸውን ያሳረፉ ግለሰቦች ጥቂት አይደሉም፡፡ ለናሙና ያህል ጣሊያን የተማረው በዚያም ምክንያት ከአድሏዊነት ከተቆጠበ የአጻጻፍ ሥነ ምግባር ጋር ለመተዋወቅ ዕድል የነበረው አፈወርቅ ገብረ እየሱስ የሚያስጎበድድ የእንጀራ ገመድ ሳይኖርበት፣ በዳግማዊ አፄ ምኒልክ ሥራው ታሪክን እንደ እጅ መንሻ በመጠቀም ጀምሮ፣ ለፋሽስት ጣሊያን ፕሮፓጋንዳ ግንባር ቀደም ተዋናይ እስከ መሆን የአድርባይነት ስም ተክሏል፡፡ ተመስገን ገብሬ የራስ ኃይሉ ፀሐፊ ሆኖ ጉቦ እንዴት ከአቤት ባዮች ይግጥ እንደነበር እየተረከ፣ ሥርዓቱ ምን ያህል የጉቦ ደም ሥር እንደነበረው ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ የግል ታሪክ በበለፀገ ቋንቋ ትቶልናል፡፡ በስተኋላ ከመጡትም ውስጥ ማኅተመ ሥላሴ ወልደ መስቀል ያጠናቀረው የአሮጌውን ሥርዓት ጓዳ ጎድጓዳ አጭቆ የያዘው ዝክረ ነገር የዝርዝር ሥራዎች በር ከፋች የሆኑትን ሁሉ ልቆ የሚቆም ዕንቁ ነው፡፡ ትምህርት ቤቶችንና አጠቃላይ አንባቢን በማገልገል ረገድ ከበደ ሚካኤል በአማርኛ ሥነ ጽሑፍ፣ ተክለ ፃዲቅ መኩሪያ በኢትዮጵያ ታሪክ ሥራዎች ተጋፊ ያልነበረው ሚና ተጫውተዋል፡፡ ሙያዊ የታሪክ ጥናት በ1950ዎቹ ውስጥ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዮኒቨርሲቲ የታሪክ ክፍል መከፈትና ከኢትዮጵያ ጥናት ተቋም መመሥረት ጋር ቢጀመርም፣ የውጭ ቋንቋን አጥር ዘሎ የተሰናዳ ነገር ለሕዝብ ማቅረብ አልቻለም ነበር፡፡  

ቲዎሎጂ፣ የሴም ቋንቋዎች፣ ፍልስፍናና ታሪክ የተማረው ፕሮፌሰር ታምራት አማኑኤልም፣ በቀዳማዊ ምኒልክ አማካይነት ሰለሞናዊ የነጋሢ ዘር በኋላም ፅላተ ሙሴና ብሉያት መጻሕፍት ወደ ኢትዮጵያ የመጣበትን አፈታሪክ የሞገተ ጽሑፍ በመጻፉ ከዘመኑ የተለየ ሰው ነበር፡፡ ጽሑፉ ወደ እንግሊዝኛ ተተርጉሞ ወደ ውጭ ከመላክ ባለፈ በጊዜው በአገር ውስጥ አደባባይ የወጣ ባይሆንም፣ ከጸሐፊው እጅ ወጥቶ ሳይጠፋ ለመቆየቱ ብስለቱ፣ የሐሳብና የቋንቋ አደራደሩ ማራኪነት ድርሻ ሳያዋጣ አልቀረም፡፡ አማኑኤል የአባት ስም ሳይሆን የተወለደበት ዕለተ በዓል ነው፡፡ አባቱ አዛዥ ገብረ ማርያም ፋንታ ይባላል፡፡ (Maison Des Etudes Ethiopienes Bulletin 11 A.A. 1997)፡፡

ይህ ሁኔታ ሳይለወጥ የ1966 ዓ.ም. አብዮት ፈነዳ፡፡ ከአብዮቱ ጋር ተያይዞ የመጣው ማርክሳዊ አስተሳሰብ ከአዲስ ዓይነት የታሪክ አመለካከትና አተናተን ጋር አስተዋወቀ፡፡ ነባሮቹ በነገሥታት ጀብዱዎች ላይ የሚያተኩሩና (የየሠራዊታቸውን ተጋድሎዎች ሁሉ የእነሱ መገለጫ ያደረጉ) ከተረት ያልተራገፉ ታሪኮች በአዲሱ አመለካከት እርባና አጡ፡፡ አዲስ መጡ አመለካከት ከተወሰኑ ጅምሮችና ከቀመራዊ ኩረጃዎች ያለፈ ጥልቀት አግኝቶ፣ ሁሉን ገጽ አገላብጦ በሚያሳይ እውነታዊ ትንታኔ የ“ተናቁት”ን የእነ ተክለ ፃድቅ መኩሪያ መጻሕፍት የተኩ ሥራዎች ማፍራት ግን አልቻለም፡፡

የተራማጆቹ ትግል ተሸንፎ ማርክሲዝም የደርግ መታወቂያ ካርድ ብቻ ሲሆን፣ ሜዳ ላይ የተገኙ ከማርክሲዝም የተራረፉ የታሪክ እሳቤዎችና ባዶነት፣ ከተናቁ ቀደምት ሥራዎች ጋር ሆነው አረፉ፡፡ በሰሜን ከነበሩ የጠመንጃ ታጋዮች መጎልበት ጋር ደርግ እየተዳከመ ሲሄድና የአገሪቱ አንድነት እያሳሰበ ሲመጣ የተናቁትን የተክለ ፃዲቅ መኩሪያ መጻሕፍት በመብራት መፈለግና ድጋሚ ማሳተም መጣ፡፡ ከእነዚህ ጋር የዶ/ር ላጵሶ ጌ ድሌቦ መጻሕፍት፣ የኢትዮጵያ ረዥም የሕዝብና የመንግሥት ታሪክና የኢትዮጵያ የገባር ሥርዓትና ጅምር ካፒታሊዝም ተቀዳድመው ደረሱ፡፡

ደርግ ወድቆ ሕወሓት/ኢሕአዴግ፣ ሻዕቢያና ኦነግ በኢትዮጵያ የፖለቲካ አደባባይ ላይ ሲታዩም ዳግመኛ ግራ መጋባት ነገሠ፡፡ “ከመቶ ዓመታት ወዲህ የተፈጠረች ኢትዮጵያ” ባዩና “ባለረዥም ታሪኳ ኢትዮጵያ” መተካተክ ጀመሩ፡፡ የሻዕቢያን አመለካከት ለመመከት የጳውሎስ ኞኞ  ምኒልክ ተከተለ፡፡ ይኼ ሁሉ ሲሆን የታሪክ ሙያተኞቹ ሠፈር ከእንግዝሊኛ ድንበር ያለፈና ግራ መጋባቱን የሚያቀል ሥራ ወደ ሕዝብ መወርወር አልቻለም፡፡ በተበታተነ ደረጃ (በመጽሔት) ከተደረጉ አስተዋጽኦዎችና ወደ አማርኛ ተተርጉሞ በ1989 ዓ.ም ከታተመው የባህሩ ዘውዴ (ከ19ኛው አጋማሽ የሚነሳ) የኢትዮጵያ ታሪክ ሌላ አልነበረም፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክ ጥያቄዎች በርካታ እንደመሆናቸው የኤርትራ ጉዳይን ዳበስ ያደረገው ይኼ ትንሽ መጽሐፍ (ከነበረው የተሟላ የታሪክ መጽሐፍ ጥማት አኳያ) ከቅምሻ  የሚያልፍ አልነበረም፡፡ በእንግሊዝኛ በ1984 ዓ.ም. አደባባይ በወጣ ጊዜ ተሻሚ በዝቶ በተደጋጋሚ መታተሙም ይኼንኑ የሰውን ጥማት የሚገልጽ ነበር፡፡ የኤርትራን ጉዳይ እንቆቅልሽ በቅጡ ለማጤን የዘውዴ ረታ ሥራ የኤርትራ ጉዳይ እስኪወጣ መጠበቅ ግድ ነበር፡፡

ወጣም ወረደ እስከ ዛሬ ድረስ እውነተኛው የኢትዮጵያ ታሪክ የቱ ነው የሚል ጥያቄ እንደ ሐውልት ቆሞ ይገኛል፡፡ ከንግሥተ ሳባ ጀምሮ ሲቆጠር የኖረው ታሪክ ነኩቷል፡፡ ፖለቲካ ታሪክን ሲወልድም ታይቷል፡፡ የረዥም ዘመናት የኢትዮጵያ ባለታሪክነት ከመቶ ዓመታት የታሪክ አመለካከት ጋር የፈጠረው ልትሚያ ጋብ ቢልም ፍጥጫው አለ፡፡ ከፖለቲካ ሙሌት ውጪ የኢትዮጵያን ትክክለኛ ታሪክ የማወቅ ጉጉት ዛሬም ትኩስ ነው፡፡ ጉጉቱ ብቻውን አይደለም፡፡ የታሪክ ባዶነትን ለመሙላት የሚጠቅሙ ነገሮችን የማዋጣት መፍጨርጨርም አብሮት አለ፡፡ የኢትዮጵያን ታሪክ በአዲስ ዓይን የመሰደር ሙከራዎች፣ የታሪክ ፋይዳ ያላቸው የግል ትዝታዎችና ማስታወሻዎች ለሕዝብ ማጋራት፣ በውጭ ጸሐፊዎች የቀረቡ ትንታኔዎችንና ትረካዎችን መተርጎም፣ ለታሪክ ምንጭ የሆኑ የግዕዝ ሰነዶችን ወደ አማርኛ መመለስ፣ ቀደምት የታሪክ ሥራዎችን እንደገና አሳትሞ ማቅረብ፣ የብሔረሰብ ታሪኮች (የአገው፣ የከፋ፣ የሲዳማ፣ የጉራጌ፣ የስልጤ፣ ወዘተ) መጻፍና ማጻፍ ቀጥሏል፡፡

እነዚህ ጥረቶች ብዙ እየጠቀሙ ነውና ምሥጋና ይገባቸዋል፡፡ ግዕዝ ባለማወቅ ሳንገደብ መነታረኪያ የነበሩ ሰነዶችን ዓይተን እንድንፈርድ አስችለውናል፡፡ የመዋዕለ ዜናና የገድል አጻጻፍን እንድናውቅ፣ ምን ያህል መተመመኛ መሆን እንደሚችሉና እንደማይችሉ እንድናጤን ረድተውናል፡፡ በፊት በቅጡ ያልታወቁ መረጃዎችንና አዳዲስ የዕይታና የትንታኔ ፍካቶችን አጋርተውናል፡፡ ወደ ፊትም ገና በግዕዝ ያሉ፣ በዓረብም ሆነ በአውሮፓ ቀደምት ጸሐፊዎች የተከተቡ የታሪክ ምንጮች ወደ አማርኛ እንዲተረጎሙ እንጠብቃለን፡፡ ከግዕዝ ወደ አማርኛ በሚደረግ ትርጎማ ውስጥ ምንጩን ከነትርጉሙ ማስቀመጥ ለማመሳከር ቢመችም ዋጋ ስለሚያበዛ እንደ ስንክሳር ያሉትን ወፍራም መጻሕፍት ገዝቶ ለመጠቀም እንቅፋት ይሆናል፡፡

ሁሉም ጥረቶች ተጋግዘው የሚረጩት ያልተጻፈ የጋራ መልዕክትም ነበራቸው፡፡ በዕድሜያችን ያየነውንና የሰማነውን፣ በግዕዝም በፈረንጅም ተጽፎ ጥቂቶች ብቻ ያገኟቸው የነበሩ የታሪክ ሰነዶችን ያደረሰንን ያህል እያቀረብንላችሁ ነው፣ ፍልፈላውንም፣ ብጠራውንም እንደሚሆን አድርጋችሁ የምትሉትን በሉን የሚል፣ ውዝግቦችን አምሸክሽኮ የረታ ውጤት ገና እንዳለመታየቱ የአደራ መልዕክቱ እስካሁንም እየተንቀዋለለ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክን ማወቅ የጠማው አንባቢ ቢቸግረው፣ ተመራማሪም (ለሚያጉላሉ ጥያቄዎች መልስ ፈላጊም) እየሆነ ነው፡፡

ነገር ግን፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የአንባቢ (የትርፍ ጊዜ ተመራማሪ) መሆን መቼ እንዲህ ዋዛ! በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ እንኳ በአግባቡ የደረጀና ለምርምር የሚበቃ የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት የለም፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መጻሕፍትና ቤተ መዛግብት ውስጥ ያለው የኢትዮጵያ ጥናት ክፍል (የአማርኛ ክፍልም ይባላል) ቀድሞ የነበረውን የካርድ ማውጫ ሁሉ አጥቶ፣ እንዲህ የሚል መጽሐፍ ፈልጌ ነበር ሲባል አራት አምስት ጥራዝ ይሰጣል፡፡ እነዚያ ጥራዞች በአማርኛም በእንግሊዝኛም ያሉ መጻሕፍት የተደቀደቀባቸው፣ የሚደጋገሙና የፊደል ቅደም ተከተል የሚባል የሌለባቸው ናቸው፡፡

የአንድ መጽሐፍ መለያ ቁጥር ፍለጋ ሁሉንም ጥራዞች ዓይቶ የጥናት ዝርዝር የማዘጋጀት ያህል ሊያለፉ ይችላል፡፡ የቤተ መጻሕፍቱ ሠራተኞች ቅን መሆናቸው እንጂ ቁመና ዓይቶ “ለጥናት ተባበሩት የሚል ደብዳቤ አለህ ወይ?” የሚል ጥያቄም ገና አልቀረም፡፡ የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም በቀላሉ መግባት የማይቻልበት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ የታሰረ ነው፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ገብቶ መጻሕፍት ለመግዛት እንኳ በአንድ በር ብቻ የመግባት ግዴታ፣ እንደጊዜው የሚለዋወጥ መታወቂያ ማስያዝ/መታወቂያ፣ አስይዞም ስም ጽፎ መፈረም፣ ጭራሽ “ዛሬ አይቻልም” መባልም አለ፡፡ ይኼንን ጣጣ አልፎ መጻሕፍት መደብራቸው ውስጥ ሲገባ ለዘመናዊ አሠራር ምሳሌ መሆን የሚገባው ሥፍራ ውስጥ የሚገኘው አሠራር ጥንታዊ መጽሐፍት ሁሉ መስታወት ውስጥ ተከርችመው በዓይን ብቻ ማየት የተፈቀደበት፡፡ (ሳጥኖች ለተለያየ ሰው የተሰጡ ሆነው ያ ሰው ወጣ ካለ እሱን መጠበቅ ግዴታ የነበረበትም ጊዜ ነበር፡፡) ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ የሚያሳትማቸው መጻሕፍት ተራ የመጻሕፍት መደብር ውስጥ እንደ ልብ ስለማይገኙ፣ ከዩኒቨርሲቲ ግቢ ውጪ እነሱን ለማግኘት እንኳ በአዲስ አበባ ደረጃ፣ የአራት ኪሎ አካባቢን መጠጋት ያስፈልጋል፡፡

የፈለገ ችግር ቢኖርም ሰው በግዢም በተውሶም እያለ ጥሩና አዲስ የወጣ የተባለን መጽሐፍ ከማንበብ አልቦዘነም፡፡ ንባብ ውስጥ ሲገባ ደግሞ ሌሎች ችግሮች ይገጥማሉ እንጂ፡፡

በትርጉምም ሆነ እንደነበረ በማሳተም ለሕዝብ የቀረቡ ቀደምት ሥራዎች ባለሙያ አሰናጅ ከሌላቸው አንባቢው የግንዛቤ ክፍተቶች ይፈትኑታል፡፡ ጥንታዊ የሥፍራ ስሞችን ከዛሬ ጋር የማገናዘብ፣ አሮጌ አባባሎችን የመረዳት፣ በመጽሐፉ ውስጥ በድፍኑ ጠቆም የተደረጉ የጎንዮሽና የጀርባ ክንዋኔዎች ያለማወቅ ችግር እንደገና ለአባዛኝ ንባብ ይዳርጋሉ፡፡ ከዶ/ር ስርገው ገላው፣ ከዶ/ር ጌታቸው ኃይሌና ከዶ/ር ዮናስ አድማሱ አሰናጅነት ጋር የተገናኘ አንባቢ ግራ ቀኙን የሚያሳይ አሰናጅነት አገራችን ውስጥ ምን ያህል ብርቅ እንደሆነና የዚህ ዓይነት አሰናጂነት ምን ያህል ልፋት ችሎ (ተዛማጁን፣ ተነፃፃሪና ተፋራሹን ሁሉ) በማስዳሰስ እንደሚበጅ ይገነዘባል፡፡

የይዘት አሰናጅ መጀመሪያ እንዳመለጠ በዚያው መቅረት ግን ግድ የለበትም፡፡ ለሁለተኛ ለሦስተኛ ጊዜ እንደነበረ በማሳተም ፋንታ በአሰናጅ እያስነቀሱና እያበለፀጉ የማውጣት መፍትሔ በአገራችን ሊለመድ ይገባል፡፡

በተጨማሪ አሁን አሁን የአፍ መረጃዎች ከበፊቱ የበለጠ ትኩረት እንደማግኘታቸው አፈላልጎ ለትንታኔ ከመጠቀም ባለፈ፣ ጥሬ መረጃዎቹን ሌላ አጥኚ እንዲጠቀማቸው ለኅትመት እንደሚሆኑ አድርጎ አደባባይ ማውጣት አስፈላጊ ነው፡፡ መንግሥቱ ለማ የአባቱን ትውስታ ቀድቶ የተወሰነች ነገር ለመጻፍ በምንጭነት ተጠቅሞ ቢተወው (ባያሳትመው) ኖሮ ትዝታ ዘአለቃ ለማን የመሰለ ትረካ ሳናገኝ እንቀር ነበር፡፡ እንዲህ የበለፀገ ትውስታ ያላቸው አዛውንቶች ዛሬም በቅጡ ብንፈልግ አይታጡም፡፡ ከብዙ መረጃ ሰጪዎች የተገኙ የቃል መረጃዎች በጊዜና በሥፍራ ልዩነት ያሳዩዋቸውን ዥንጉርጉር ርቢዎች፣ የርቢዎች ድግግሞሽ ብዛትና ማነስ፣ ተቀናቃኝ (አፋራሽ) ትውፊት ያለባቸው መሆን አለመሆናቸውን የሚያሳዩ ምጥን ዝርዝራዊ ሥራዎችን አሰናድቶ ማቅረብም ጥቅሙ ከፍተኛ ነው፡፡

በተለይ ዛሬ በየክልል እየተቋቋሙ ያሉ ዩኒቨርሲቲዎች በየአካባቢው ከመጥፋት የተረፉት የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ሀገረሰባዊ ቅርሶች (የሕክምና፣ የሥነ ጥበብ፣ የቃል ትውፊቶችን) በማሰባሰብና በመጠበቅ/በማስጠበቅ ላይ በቶሎ መረባረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በተለይም የቃል መረጃዎችን በተመለከተ የአስተዳደር ፈቃድ ወረቀት አንቀርፍፎ መሄድ፣ የፖለቲካ ሰው መሆን፣ በቀላሉ ከተቃዋሚም ሆነ ከገዢ ፓርቲ ወገን ተደርጎ መፈረጅ፣ ለመታመን የሚያበቃ ቀረቤታ አለመፍጠር፣ የገንዘብ ክፍያን መጠቀም፣ ዋሸኝ (ቆርጠህ ቀጥል) የማለት ያህል ምሪት የሚሰጡ (ለምሳሌ “በዚህ አካባቢ ይህ ሕዝብ ከመቼ ጀምሮ መኖር እንደጀመረ ትውፊት የሚያቁ አዛውንቶች ፈልጌ”  የሚሉ ዓይነት የአቀራረብ ስህተቶች ከሚፈጥሯቸው ጉዳቶች (ጭመራዎች፣ ቅነሳቸውና ብረዛዎች) በተቻለ መጠን የፀዱና በንፅፅር ዘዴ የተጣሩ መረጃዎችን ለማሰባሰብ መቻል እጅግ ውድ የሆነ ታሪካዊ ኃላፊነትን መወጣት ነው፡፡

እዚህ ላይ ከሌሎች መካከል በነፃነት መጠናትና በነፃነት መነገር ያለበትን ኢትዮጵያን የአገነባብ ታሪክ በአጭሩ ማንሳት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ታሪክ ባለ ብዙ አቅጣጫ ነው፡፡ የንግድ እንቅስቃሴ መስመሮች አካሄድ፣ የልዩ ልዩ አካባቢ ገዢዎች የመስፋፋትና የመገዛዛት ትግል፣ የሕዝቦች እንቅስቃሴና የአሠፋፈር ለውጥ የሚያሳየውና የሚያስገነዝበውም ይኼንኑ ነው፡፡ ከአክሱም ተነስተን በአንድ አቅጣጫ ቁልቁል ከማየት መውጣት፣ ከገዢዎቹ ዘመቻ ውጪ ያሉትን ሌሎች የታሪክ አክርማዎች መለየት መቻልም አለብን:: ይኼን ጊዜ የማይገናኙ የሚመስሉ የታሪክ ኃይሎች ወደፊትና ወደኋላ በሚል አካሄድ እየተያያዙና ከአንዱ ጉድኝት ወደ ሌላ ጉድኝት እያለፉ ለሰፊ አገር ግንባታ የተጫወቱትን ሚና እናጤናለን፡፡

አንዳንድ ‹‹ታሪክ አዋቂዎች›› እና ‹‹አወቅን ባዮች›› በምኒልክ የተጠቃለለች ኢትዮጵያን መፈጠር የብሔር ብሔረሰቦችን የነፃ አገርነት ዕድገት በመቶ ዓመታት ያሳጣ ማለታቸው የቆየና ዛሬም የሚሰማ ቢሆንም፣ ከእውነትነት ይልቅ ምኞታዊነት የሚያጠቃው አስተሳሰብ ነው፡፡ በዚያን ጊዜ ‹‹ብሔሮች››ን በየበኩል፣ ነፃ አገር ወደ መሆን የሚወስድ ታሪካዊና ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ሥነ ልቦናዊ ሁኔታ ፈጽሞ አልነበረም፡፡ በፍፁማዊ የሥልጣን ይዞታዎች ውስጥ በካፒታሊዝምና በከበርቴዎች አዲስ ዕድገት ፊውዳላዊነትን ሲበጣጥስ ኖሮ ከአሮጌ ቀፎ የመውጣት ዓይነት ባህርይ የታየበትን የአውሮፓ ብሔራዊ መንግሥታትን አፈጣጠር ታሪክን ለኢትዮጵያ መመኘት ሰማይና ምድርን ከማገናኘት የማይሻል ነው፡፡

ታሪክ በሄደበት ጎዳና ላይ ወደኋላ እያዩ ምኒልክ እንዲህ ባያደርግ ኖሮ ብሎ ማሰብ የሰው ልጅ እሳትን ባያገኝ ኖሮ መዳብና ብረትን አቅልጦና ጦር ሠርቶ ባልተወጋ ነበር ብሎ የመቆጨትን ያህል ከንቱ ነው፡፡ መጀመሪያ ነገር ኢትዮጵያ ሕዝቦች ታሪክ ከላይ ወደ ታች ከሰሜን ወደ ደቡብ ቁልቁል እየተንደረደሩ የመስፋፋት ብቻ አይደለም፡፡

በአገረ - ኢትዮጵያ ውስጥ ታላቅ ሚና ያለውን የኦሮሞ ሕዝቦችን ሥርጭት እንውሰድ፡፡ የኦሮሞ ጎሳዎች በአንድ ጋብቻ መወሰንን ግድ ባላደረገ የትዳር ሁኔታ፣ ከተወላጅ እኩል ባለመብት በሚኮንበት ጉዲፈቻና ኦሮሞ ያልሆነን ወደ ራሳቸው በመቀላቀል ዘይቤያቸው ቁጥራቸው የሚባዛና የሚበራከት ነበር፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ እንቅስቃሴያቸውም በቁጥር መበራከት በሚቀሰቅስ ሰፊ የመሬት ፍላጎትና አንድ የገዳ ዘመን ካስገኘው መሬት አልፎ ይዞታን የማስፋፋት ውስጣዊ ግፊት ነበሩት፡፡ የሰሜንና የደቡባዊ ገዢዎች የበላይነት ትግል ላይ የሚደርሰውን የሁለት በኩል መዳከም እያስተዋሉና ራሳቸውም በየበኩላቸውን ምት እያሳረፉ አጥለቅላቂ እንቅስቃሴ ወደ ምዕራብ፣ ወደ መሀል፣ ወደ ምሥራቅና ወደ ሰሜን እስከ ትግራይ ድረስ አድርገዋል፡፡ የተራዘመ የማስቆም ትግል ባያጋጥማቸውና በራሳቸውም ላይ ማኅበራዊ ለውጦች ባይደርስ ኖሮ እንቅስቃሴያቸው ኤርትራንም የሚሸፍን በሆነ ነበር፡፡ 

ከላይና ከታች የነበረው የሁለት በኩል የበላይነት ትግል፣ ዘረፋና ማስገበር ከሚያስገኘው የሲሳይ ጥቅም ጋር የተያያዘ ከመሆኑ ሌላ ከሞላ ጎደል የበላይነትን ይዘው የመጡት የሰሜኑ ገዢዎች እንደ ገዢነት መኳንንትነት ደረጃቸው የነበራቸው የጋሻ ጃግሬ ብዛት፣ የዘምቶ አስገባሪነትና የምርኮ አፋሽነት የአኗኗር ባህርያቸው በነበሩበት ተወስኖና ተቻችሎ ከመኖር ጋር የሚቃረን፣ መዋዋጥንና የሰፊ ግዛት መፈጠርን የሚጠይቅ ነበር፡፡ ምኒልክ መደምደሚያ ሆኑ እንጂ የመስፋፋቱ ትግል አዲስ አልነበረም፡፡ ምኒልክ ከሌሎች ነጋሢያን ሁሉ የተረገሙና የ‹‹ብሔሮች›› ፀር ሆነው ሳይሆን የኃይል ብልጫ አግኝተው የፈጸሙትና ሌላውም ነጋሢ ወይም አሚር ብልጫ አግኝቶ ቢሆን ኖሮ ወደ ኋላ የማይልበት ተግባር ነበር፡፡

ይህንን ሁኔታና የውጭ ወራሪዎች ቅኝ ገዢዎች ይፈጥሩት የነበረውን ተጨማሪ ጫና ሳናገናዝብ፣ በዘመነ መሳፍንት ተፈጥሮ የነበረውን ቁርጥራጭነት ከምዕራብ አውሮፓ የብሔራዊ መንግሥታት አፈጣጠር ጋር እያምታታንና እያንዳንዱ ቁራጭ ግዛት ነፃ ሆኖ ቢቀጥል ኖሮ ብለን የምንቆጭም አልታጣንም፡፡ በተለይም በዛሬው 21ኛው ክፍለ ዘመን ልዩ ዓላማዊ ሁኔታ ውስጥ ተቀምጠው ለኢትዮጵያ አሮጌ መፍትሔ የሚያስቡላት የኋሊት ተጓዦችም አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል እንደ ኦነግ ዓይነቶቹ የቅኝ/የመነጠል ጥያቄ ሲሉ ይኸው ግማሽ ምዕተ ዓመታት ሞሉዋቸው፡፡ ዛሬ በገዢነት ላይ ያለው ፓርቲም ችግሩን ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኛነት ብሎ ሾሞታል፡፡

ገዢው ርዕዮተ ዓለም ያባዛው ብሔርተኛ አስተሳሰብ፣ አደረጃጀትና የተዘረጋውም መንግሥታዊ አወቃቀር የብሔር ጥያቄን አልመለሰም፣ ዴሞክራሲንም ማስፈን አልተቻለም፡፡ የብሔር/ብሔረሰቦች መብትና ነፃነት የማክበር ጉዳይ በጭራሽ በጥያቄ የሚቀርብ አይደለም፡፡ አንዳንዶች እንዲያውም የብሔሮችን ጉዳይ የ‹‹አብዮታዊ ዴሞክራሲ›› አንዱ መለያና ማስረጃ ሊያደርጉ ይፈልጋሉ፡፡ እነዚህ ፖለቲካን ደህና ሰንብች ብለው ቢገላገሉ ይሻላቸዋል፡፡ ብሔር/ብሔረሰቦችን አውቆና አክብሮ የመያዝ ነገር ኢሕአዴግም ሆኑ ተቃዋሚዎች ሊያመልጡት የማይችሉት የኢትዮጵያ እውነት ነው፡፡ ዋናው ጉዳይ ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ አስተዳደር የማደራጀትና የትኛውም ዓይነት ፖለቲካዊ ጥያቄ (የብሔር/ብሔረሰቦችም ጭምር) በሰላማዊ፣ በዴሞክራሲያዊና በሕጋዊ መንገድ መፈታት አለበት የሚለው አመለካከትና እምነት መሠረት መያዙ ሥርዓት የተበጀለት መሆኑ ነው፡፡ 

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡