Skip to main content
x
የፋሲካ እንቁላል

የፋሲካ እንቁላል

የፋሲካ እንቁላል ይሉታል፡፡ በፋሲካ ወቅት በቀለም ተውቦ፤ ተጋጊጦና ተነቅሶም ለወዳጅ ዘመድ እንደ ስጦታ የሚቀርብ ነው፡፡ በምእራባውያኑ በዕድሜ ጠገቡ ባህል የዶሮን እንቁላል በቀለማት አስውቦ ለወዳጅ የሚበረከትበት አካሄድ ቢኖርም በዘመናዊው ባህል ደግሞ ከቸኮሌት የተሠራ እንቁላልን በባለቀለማት መጠቅለያ በመጠቅለል ወይም ከላስቲክ የተሠራ እንቁላልን በቸኮሌት በመሙላት ስጦታ ሲለዋወጡም እየተስተዋለ ነው፡፡

በክርስትና እምነት ባህል እንቁላል የሚገለጸው ከመልሶ መወለድና ለምነት ጋር ቢሆንም ከፋሲካ ጋር በተያያዘ ግን እንቁላል የሚገለጸው የኢየሱስ ክርስቶስ መቃብር ባዶ ሆኖ መገኘትን ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም እንቁላሉ በቀይ ቀለም የሚዋበውም ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ለማዳን ሲል ያፈሰሰውን ደም ለማስታወስ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ባህል በሜሶፖታሚያ ክርስትና ከገባበት ጊዜ አንስቶ እንደተጀመረ ይነገራል፡፡ በኋላም ወደ ሩሲያና ሰርቢያ በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አማካይነት ገብቷል፡፡ በመቀጠልም በካቶሊክና በፕሮቴስታንት ቤተ ክርስቲያናት አማካይነት ወደ አውሮፓ ዘልቋል፡፡

 በኢትዮጵያ ለፋሲካ በዓል በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ዘንድ ዶሮ ማረድና አክፍሎት ማድረግ የተለመደ ሲሆን፣ የእንቁላል ሚናም ዶሮ ወጥ ውስጥ መግባት ነው፡፡ ከዚህ በዘለለ እንቁላልን አስጊጦ ስጦታ መለዋወጥም ሆነ በእንቁላል ቅርፅ የተሠራ ግዑዝ ነገር በቀለም አሸብርቆ በጎዳና ላይ ማቆም የተለመደ አይደለም፡፡ የ2009 ዓ.ም. የፋሲካ በዓልን አስቀድሞ ግን ቦሌ መድኃኔዓለም አካባቢ በሚገኘው ኤድና ሞል ደጃፍ ሁለት በቀለም የተዋቡና በእንቁላል ቅርፅ የተሠሩ፣ ሰው ሠራሽ እንቁላሎች ግራና ቀኝ ቆመው ታይተዋል፡፡ በዚሁ ዓመት የገና በዓል ሲከበር እስከ አሥር ሜትር የሚረዝሙና ብዙዎቹ በፊልም የሚያውቋቸው የምዕራባውያኑ የገና ዛፎች በመብራት ተውበው ታይተዋል፡፡ እንቁላል ቀስ በቀስ በእግሩ ይሄዳል እንዲሉ!

የሥጋ ዶሮ

የትኛውም ሆቴል፣ ሬስቶራንት ወይም ምግብ ቤት ብትገቡ ዶሮ የማይጠቀስበት የምግብ ዝርዝር አታገኙም ለማለት ይቻላል። እንዲያውም ቶሎ የሚደርሱ ምግቦችን የሚያዘጋጁ ሬስቶራንቶች የዶሮን ሥጋ በማዘጋጀት ረገድ የተዋጣላቸው ሆነዋል። ልዩ ዝግጅት ሲኖራቸው ዶሮ መሥራት የሚመርጡ ማኅበረሰቦች አሁንም አሉ። እንዲሁም እንደ ሕንድ ያሉ አንዳንድ አገሮች አስደናቂ የሆነ የተለያየ ዓይነት የዶሮ አሠራር ዘዴ አላቸው። ለምሳሌ ያህል በበርበሬ የተሠራ ዶሮ ወይም ላል መርጊ፤ ዶሮ ዝልዝል ወይም ከርጊ መርጊ፤ በዝንጅብል የታሸ ዶሮ ወይም አድራክ መርጊ የመሳሰሉ የዶሮ አሠራሮች እጅ የሚያስቆረጥሙ ናቸው!

ከዶሮ የተዘጋጀ ምግብ ይህን ያህል ተወዳጅ የሆነው ለምንድን ነው? አንዱ ምክንያት የዶሮን ያህል በተለያዩ ቅመማ ቅመሞች ጣፍጦ ሊሠራ የሚችል ምግብ የለም። አንተ የምትወደው በምን መልክ ተሠርቶ ሲቀርብ ነው? ጥብስ፣ አሮስቶ ወይስ ወጥ? ማንኛውንም የምግብ አዘገጃጀት መጽሐፍ ብትመለከት እያንዳንዱን ምግብ እንዲጥም ለማድረግ ታስቦ የተዘጋጀ በደርዘን የሚቆጠር የዶሮ አሠራር ዓይነት ልታገኝ ትችላለህ።

ዶሮ በብዙ አገሮች በብዛት ስለሚገኝ በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ርካሽ ነው ማለት ይቻላል። በተጨማሪም ዶሮ ለሰውነት እጅግ አስፈላጊ የሆኑትን ፕሮቲን፣ ቫይታሚንና ማዕድኖችን ስለያዘ በምግብ ጥናት ጠበብት ዘንድ ተመራጭ ነው። ሆኖም በዶሮ ሥጋ ውስጥ ያለው የካሎሪ፣ የጠጣር ቅባት (saturated fats) እና የሌሎች ቅባቶች መጠን አነስተኛ ነው።

  • ‹‹ንቁ!›› (2001)

***

ሊቅና ልቅ !!

እኒያው አፈ ሊቆች 
ጣዝማ አንደበታቸው - ምድር ስር ተቀብሮ
ምስጥ እያነጎደው - ሰርስሮ ቦርቡሮ፤

እኒያው አፈ ልቆች
መንታ ልሳናቸው - በአየሩ ተናኝቶ
ዙሪያ ገባው ሁሉ - ገምቶና ተግማምቶ፤

ዳሩ የአገሬ ሰው
የምስጥ ኩይሳ - ባነቀፈው ቁጥር
ጣዝማ አለ ብሎ ነው - ሊያወጣው የሚጥር፡፡

ከአፈ ሊቆች ልቆ - አፈ ልቅ እንደ አሸን - በፈላበት አገር
ቅል ዱባ ነው ተብሎ - ይሰማል ሲነገር፡፡
ቅል በቅልነቱ - ከዱባ ከላቀ
ያኔ ሰው አለቀ - ያኔ አገር አለቀ፡፡

ከአፈ ሊቅ አፈ ልቅ - ከአሁኑ የባሰ - ሳይደባለቁ
ግርዱንና ምርቱን - ማጥሪያ፣ ማንጓለያ - አውድማ ለቅልቁ!!

  • ደመቀ ከበደ - መሀል ሸገር