Skip to main content
x
ያልሠለጠነ ከተሜነት

ያልሠለጠነ ከተሜነት

በከተሞች አካባቢ ያለው የተሻለ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ብዙዎችን እንደሚስብ ይታመናል፡፡ ያለው የተሻለ የመሠረተ ልማት አውታርም ከተሞችን ከገጠር በተሻለ ለኑሮ ምቹ ያደርጋቸዋል፡፡  

የከተሞች መስፋፋት በአግባቡ ማስተዳደር ካልተቻለ ከጥቅሙ ጉዳቱ ሊያመዝን ይችላል፡፡ የአንድ ከተማ ዕድገት ከከተማው ሕዝብ ቁጥር ጋር ተመጣጣኝ በማይሆንበት ጊዜ በቀላሉ የማይፈቱ ቀውሶችን ይፈጥራል፡፡ መጠለያ የማግኘት ችግር፣ የሥራ አጥነት መሥፋፋት፣ የጤና አገልግሎት ተደራሽ አለመሆን፣ ሌሎችም የመሠረተ ልማት ተደራሽነት ችግሮች ከከተሞች መስፋፋት ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ  ቀውሶች ናቸው፡፡

ከተሞችን ለኑሮ ምቹ እናድርግ በሚል መርህ መጋቢት 25 ቀን 2009 ዓ.ም. በሒልተን ሆቴል በተዘጋጀው የሁለት ቀናት ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ የዚህ ችግር ሰለባ መሆኗ ተንፀባርቋል፡፡

በዕለቱ የተገኙ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ከበደ ወርቁ ከከተሞች መስፋፋት ጋር ተያይዞ በአገሪቱ ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች እንዲሁም ከአደጋ ጋር ተያያዥነት ያላቸው የጤና ችግሮች እየተስፋፉ መምጣታቸውን ገልጸዋል፡፡

ጤናማ ባልሆነ የአመጋገብ ሥርዓት፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ባለማድረግ፣ ክብደት በመጨመርና በመሳሰሉት በሚከሰቱ በሽታዎች በርካታ ከተሜዎች እየተጠቁ ይገኛሉ፡፡ ለስኳር፣ ለልብ፣ ለካንሰር፣ ለደም ግፊት፣ ለአዕምሮ ጤና ችግር የሚጋለጡ ሰዎች ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፡፡ ከኢንዱስትሪዎች መስፋፋት እንዲሁም ከዘመናዊ የትራንስፖርት አገልግሎት ዓይነቶች መጨመር ጋር ተያይዞ አደጋዎች በእጅጉ እየጨመሩ እንደሚገኙም ለማወቅ ተችሏል፡፡ የግንባታዎችና የትልልቅ ፋብሪካዎች መስፋፋትን ተከትሎም የሥራ ላይ አደጋዎች እየበዙም መጥተዋል፡፡ በከተሞች ሥራ እናገኛለን በሚል ከየሥፍራው ወደ ከተሞች በሚፈልሱት ምክንያት በከተሞች ድህነት እየተስፋፋ እንደሚገኝም በዕለቱ ይፋ የተደረጉ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡

የከተሞች መስፋፋትን ተከትሎ የሚከሰተው ድህነት

ከጥቂት ዓመታት በፊት በአገሪቱ በተለያዩ ከተሞች በድህነት የሚኖሩ ሰዎች ቁጥር 11 በመቶ ነበር፡፡ ይኼ ቁጥር እ.ኤ.አ በ2011 ወደ 14 በመቶ አድጓል፡፡  በአገሪቱ ያለው የከተሞች መስፋፋት ከአገሪቱ የሕዝብ ቁጥር ዕድገት ምጣኔ በላይ ሆኗል፡፡ ይኼ ድህነት የበለጠ እንዳይስፋፋ፣ የከተሞች የማስተናገድ አቅምና የነዋሪዎቹ ምጣኔ የተራራቀ እንዳይሆን ከባድ ሥራ መሠራት እንዳለበት የሚጠቁም ነው፡፡

  በአሁኑ ወቅት ሥራ አጥነት፣ ድህነት፣ ድርቅና ሌሎችም መሠል ጉዳዮች ብዙዎች የሚኖሩበትን  ቀዬ ትተው ወደ ከተሞች እንዲፈልሱና ከተሞች አለ ልክ በሰው እንዲጨናነቁ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

ከ10 እስከ 19 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች ወደ ከተሞች የሚፈልሱት የመማር ዕድል ለማግኘት ሲሆን፣ 28.6 በመቶ የሚሆኑት ወንዶችና 32.4 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች ለሥራ ፍለጋ ነው፡፡ በሌሎች የተለያዩ ግፊቶች ቀያቸውን ትተው ወደ ከተሞች የሚኮበልሉም ብዙ ናቸው፡፡ ይሁንና ለምን ያህሉ ይሳካላቸዋል? የሚለው ጉዳይ አጠያያቂ ነው፡፡

13 በመቶ የሚሆኑት ሴቶችና 21 በመቶ የሚሆኑት ወንዶች አስበው የመጡለትን የትምህርት ዕድል አያገኙም፡፡ የሥራ ዕድል ለማግኘት ወደ ከተማ የሚፈልሱት ሴቶችም በቤት ሠራተኝነት፣ በካፍቴሪያ አስተናጋጅነት አሊያም በቡና ቤት ሠራተኝነት ተቀጥሮ ከመሥራት ባለፈ የተሻለ ሥራ የማግኘት ዕድላቸው የጠበበ ነው፡፡ 19 ከመቶ የሚሆኑት ሥራ ፈላጊ ሴቶች የተባሉትን የሥራ ዓይነቶች እንደማያገኙ በከተማ ጤና ማጠናከሪያ ፕሮግራም የተሠራው ጥናት ያመለክታል፡፡

መሰል አጋጣሚዎችና ሌሎችም በከተሞች ያለው የሥራ አጦች ቁጥር በተለይም ወጣት ሥራ አጦች 15 በመቶ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ በቀን በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በሚፈልሱበት አዲስ አበባ ያለው የሥራ አጦች ቁጥር ደግሞ 32.5 በመቶ ነው፡፡ ሁኔታው በአገር አቀፍ ደረጃ በድህነት የሚኖሩ ሰዎች ቁጥርን 29.6 በመቶ አድርጓል፡፡ በአገራችን ከፍተኛ የድሆች ቁጥር ካላቸው ከተሞች መካከል አዲስ አበባና ድሬደዋ ግንባር ቀደም ናቸው፡፡ 28.1 በመቶ የሚሆኑት አዲስ አበቤዎችም በድህነት የሚኖሩ ናቸው፡፡

 ለዚህም ቁጥራቸው በየዕለቱ እያሻቀበ የሚገኘውን የጎዳና ልጆች፣ የኔ ቢጤዎች መመልከት በቂ ነው፡፡ ለኑሮ በማይመቹ በተጨናነቁ አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎችም በከተሞች እየተስፋፋ ያለውን ድህነት ያንፀባርቃሉ፡፡

ከ70 እስከ 80 በመቶ የሚሆኑት ከተሜዎች የሚኖሩት በተጨናነቁና ለኑሮ በማይመቹ አካባቢዎች ነው፡፡ ሁኔታው ለተለያዩ ችግሮች እንዲጋለጡ እያደረጋቸውም ይገኛል፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች የንፁሕ ውኃ ተደራሽነት፣ የግልና የአካባቢ ንፅህና ጉዳይም አደጋ ውስጥ ነው፡፡ 

በከተሞች ከፅዳት ጋር ተያይዘው የሚታዩ ችግሮች

ከገጠሩ በተለየ በአገሪቱ በሚገኙ ትልልቅ ከተሞች በተለይም በአዲስ አበባ በቀላሉ ሊቀረፍ የማይችል የፅዳት ችግር አለ፡፡ ከመኖሪያ ቤቶች አካባቢ ጀምሮ በከተማዋ በተለያዩ ጎዳናዎች ላይ የሚታዩ የቆሻሻ ክምሮች፣ ብስባሾች፣ በአንዳንድ አካባቢዎች አስፋልት ላይ የሚተኙ መጥፎ ጠረን ያላቸው ፍሳሾች፣ በማዳበሪያ ታስረው የተከመሩ እንዲሁም ከገንዳ ላይ የሚያነሳቸው ያጡ ቆሻሻዎች በአካባቢያቸው የሚኖሩትንና የሚያልፉትን ሲያማርሩ ማየት ተለምዷል፡፡ በከተማዋ የሚገኙ ወንዞች ሳይቀሩ ከየቤቱ፣ ከየፋብሪካውና ከተለያዩ ተቋማት በሚወጡ ቆሻሻዎች እየተመረዙ ነው፡፡  

በጄኤስ አይ የከተማ ጤና ማጠናከሪያ ፕሮጀክት ኃላፊ አቶ ኅብረት ዓለሙ በቅርቡ ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በአዲስ አበባ ከፅዳትና ከቆሻሻ አወጋገድ ጋር ተያይዞ ያለው ችግር በቀላሉ የማይፈታ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ከወራት በፊት ተከስቶ የነበረው አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከትም ከፅዳት ጉድለት ጋር የተገናኘ እንደሆነ በመግለጽ በከተማዋ ያለው የፅዳት ጉዳይ ብዙዎች ለተለያዩ በሽታዎች የሚዳርግ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የመፀዳጃ ቤት ችግርም በከተማዋ ፅዳት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እየፈጠሩ ከሚገኙ ችግሮች መካከል አንዱ ነው፡፡

በከተሞች ያለው የመፀዳጃ ቤቶች ሁኔታ ምን ይመስላል?

ከመፀዳጃ ቤት ጋር ተያይዘው የሚነሱ የተለያዩ ችግሮች አሉ፡፡ በተለይም ተጨናንቀው በተሠሩ መንደሮች አካባቢ ችግሩ ይበረታል፡፡ በየጊዜው እንዲመጠጡ አይደረግም፡፡ በአቅራቢያ ከሚገኙ ወንዞች ጋር እንዲቀላቀሉ የሚደረጉም አሉ፡፡ ካለው የመፀዳጃ ቤት ችግር ጋር ተያይዞ በላስቲክ ተፀዳድተው ሜዳ ላይ የሚወረውሩ እንዲሁም በየመንገዱ የሚፀዳዱ ያጋጥማሉ፡፡ እንዲህ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የሕዝብ መፀዳጃ ቤቶች ዓይነተኛ መፍትሔ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን እነሱም የተለያዩ ችግሮች እንዳሉባቸው ከቀናት በፊት ይፋ የተደረገው የኢትዮጵያ የከተሞች ጤና ማጠናከሪያ ፕሮግራም የዳሰሳ ጥናት ያመለክታል፡፡

ጥናቱ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በትግራይ፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል እንዲሁም በሐረር፣ በድሬደዋና በአዲስ አበባ ከተማ ያለውን የሕዝብ መፀዳጃ ቤቶች ሁኔታ በዝርዝር አስቀምጧል፡፡ 335 የሚሆኑ የሕዝብ መፀዳጃ ቤቶች በዳሰሳ ጥናቱ ተካተዋል፡፡ 25 በመቶ የሚሆኑት በደቡብ ክልል፣ 20.9 በመቶ በትግራይ፣ 20.6 በመቶ በኦሮሚያ፣ 17 በመቶ በአዲስ አበባ፣ 11 በመቶ በአማራ፣ 4 በመቶ ድሬደዋና 1 በመቶ በሐረር ክልል የሚገኙ ናቸው፡፡

በጥናቱ መሠረት አብዛኛዎቹ መፀዳጃ ቤቶች ዕድሜ ጠገብና ተገቢውን አገልግሎት መስጠት የማይችሉ ናቸው፡፡ ለምሳሌ በአዲስ አበባ 71 በመቶው የሚሆኑት የሕዝብ መፀዳጃ ቤቶች ከ20 ዓመታት በፊት የተገነቡ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ በጥናቱ የተካተቱት 22 በመቶ የሚሆኑት መፀዳጃ ቤቶች ጥቅም እየሰጡ አይደለም፡፡ የተቀሩትም ቢሆኑ ከፍተኛ የፅዳትና የአጠቃቀም ችግር ያለባቸው ናቸው፡፡       

የፍሳሽ አወጋገድ ችግር

የተቀናጀ የፍሳሽ ማስወገጃ ሥርዓት አለመኖር በአገሪቱ ለሚገኙ አብዛኛዎቹ ከተሞች ትልቅ ራስ ምታት ነው፡፡ የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎች ሞልተው ፍሳሽ በየመንገዱና በየሰው በረንዳ ተኝቶ ይታያል፡፡ ሲ/ር መሠረት ተስፋዬ ይባላሉ፡፡ በአዲስ አበባ ወረዳ 12 የካ ክፍለ ከተማ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያ ሆነው መሥራት ከጀመሩ ሰባት ዓመታትን አስቆጥረዋል፡፡ በሥራቸው በቀላሉ ሊፈቱት ያልቻሉት ነገር ቢኖር እንዳሻው የተባለውን የፍሳሽ አወጋገድ ችግር መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ከድርጅቶችና ከመኖሪያ ቤቶች የሚወጣ ፈሳሽ በተገቢው የሚወገድበት ሥርዓት ባለመኖሩ በሚሠሩበት አካባቢ የሚገኙ ነዋሪዎች በጣም ይቸገራሉ፡፡ ብዙዎችም በተደጋጋሚ ጊዜ በጉንፋንና በሌሎች የመተንፈሻ አካል በሽታ እንደሚጠቁ ይናገራሉ፡፡

በከተሞች ያለው የጤና ሁኔታ

በተፋፈጉ፣ በፍሳሽና በመጥፎ ጠረን በተበከሉ አካባቢዎች መኖር እንዲሁም በእነዚህ አካባቢዎች የበቀሉ አትክልቶችን መመገብ ብዙዎቹን ከተሜዎች ለተለያዩ የጤና ችግሮች እያጋለጡ ይገኛሉ፡፡ አሁን አሁን እየተለመደ የመጣው ጤናማ ያልሆነ የአመጋገብ ሥርዓት ማለትም ከፍተኛ የቅባት ክምችት ያለባቸውን ምግቦች መመገብ፣ ስኳርና ጨው ማብዛት፣ አልኮል አብዝቶ መጠጣት፣ ሲጋራ ማጨስና የመሳሰሉት በከተሞች የሚታዩና በርካቶችን ለተለያዩ የውስጥ ደዌ ችግሮች የሚዳርጉ ናቸው፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው ዶ/ር ከበደ እንደሚሉት፣ ጤናማ ያልሆነ የአመጋብ ሥርዓት፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ፣ ክብደት መጨመርና የመሳሰሉት ብዙዎችን ለስኳር፣ ለልብ፣ ለካንሰር ለደም ግፊት ለአዕምሮ ጤና ችግር እየዳረጉ ይገኛሉ፡፡ አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያመለክቱትም ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ሥርጭት በከተሞች አካባቢ ይበዛል፡፡ በአዲስ አበባ 24 በመቶ የሚሆነው ሞት እየተከሰተ የሚገኘው ከልብ ሕመም ጋር በተያያዘ ነው፡፡ በሁሉም ከተሞች ለሚፈጠረው አሥር በመቶ ሞትም ካንሰር ምክንያቱ ነው፡፡

ከተሞችን ለኑሮ ምቹና ተስማሚ ለማድረግ የተለየዩ ፖሊሲዎችና እስትራቴጂዎች ተቀርፀው ሲተገበሩ ቆይቷል፡፡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች፣ የመንገድ፣ የውኃ፣ የኤሌክትሪክ ማስፋፊያ ግንባታዎች ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ በጤናው ረገድ ያሉትን ችግሮች ለመቅረፍም ከባለፉት አሥርት ዓመታት ጀምሮ በመተግበር ላይ የሚገኘው የከተማ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ተጠቃሽ ነው፡፡

ይህ በገጠራማው የአገሪቱ ክፍሎች ተግባራዊ ተደርጎ መልካም የሚባል ውጤት የተገኘበት ፕሮግራም ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት 5,000 የሚሆኑ የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች በ400 ከተሞች ተመድበው አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡ በግል ንፅሕናና በአካባቢ ጥበቃ፣ በቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት፣ በበሽታ መከላከልና መቆጣጠር እንዲሁም በአደጋ መከላከልና መቆጣጠር ዙሪያ ለማኅበረሰቡ ሙያዊ ድጋፍ ይሰጣሉ፡፡ ነገር ግን በአገሪቱ ካለው ውስን የከተማ ጤና አተገባበር ልምድና ፈጣን የከተሞች ዕድገት አንፃር ሲታይ እዚህ ግባ የሚባል ለውጥ መፍጠር አልተቻለም፡፡

‹‹የከተሞች ዕድገትና የከተማ ነዋሪዎች ማኅበራዊ፣ የግል የኑሮ ደረጃና የአኗኗር ዘይቤ በእጅጉ የተለያየ መሆን የከተማ ነዋሪዎች ችግር የተወሳሰበ እንዲሆን አድርጓል፤›› ያሉት ዶ/ር ከበደ ችግሩን ለመቅረፍ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

በከተሞች ያለውን አስከፊ ድህነት ለመቀነስም የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ፡፡ አብዛኛዎቹ በከተማ የሚገኙ ድሆች በአነስተኛ የሥራ መስክ ወይም በጣም ዝቅተኛ ገቢ በሚያስገኝ ሥራ ላይ የተሰማሩ ናቸው፡፡ ጧሪና ደጋፊ የሌላቸው አረጋውያንና አካል ጉዳተኞች፣ ጎዳና ተዳዳሪዎች ዋነኛ የከተሞች የድህነት ገጽታ አመላካች ናቸው፡፡ እነዚህን የኅብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ የሚያደርግ የአሥር ዓመት የምግብ ዋስትና ፕሮግራምና ስትራቴጂ በከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር አማካይነት ተቀይሶ በተግባር ለማዋል እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ነው፡፡ በፕሮግራሙ በ927 ከተሞች የሚገኙ 4.7 ሚሊዮን በድህነት የሚኖሩ ዜጐችን ለመደገፍ ዕቅድ ተይዟል፡፡

የማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ ጥናት እንደሚያመለክተው፣ 19 በመቶ የሚሆነው የአገሪቱ ሕዝብ የሚኖረው በከተሞች ነው፡፡ በየዓመቱ ከ3.8 እስከ 5.4 በመቶ የሚደርስ የከተሞች ዕድገት እየተመዘገበ ይገኛል፡፡ ከ20 ዓመታት በኋላም የከተማ ነዋሪዎች ቁጥር 42.3 ሚሊዮን ይደርሳል፡፡