Skip to main content
x

ያልተመዘገቡ መድኃኒቶች ገበያ ላይ መታየታቸው ቀንሷል ተባለ

ኢትዮጵያ ውስጥ በሕገወጥ መድኃኒቶች ላይ የቁጥጥርና ክትትል ሥራ በተጀመረበት በ1981 ዓ.ም. ጥራታቸው፣ ደኅንነታቸውና ፈዋሽነታቸው ያልተረጋገጡና ያልተመዘገቡ መድኃኒቶች ገበያ ላይ በስፋት ይገኙ እንደነበር፣ በአሁኑ ጊዜ ግን ገበያ መታየታቸው እየቀነሰ መምጣቱን የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን የላቦራቶሪ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አስታወቁ፡፡

የምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት አባል አገሮች ብሔራዊ የመድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ኃላፊዎች በአዲስ አበባ ሒልተን ከሐምሌ 25 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ለሦስት ቀናት የሚያካሂዱትን ስብሰባ አስመልክቶ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ቢቂላ ባይሳ እንደገለጹት፣ ከሚሰበሰቡት ናሙናዎች በተገኘው መረጃ መሠረት  ያልተመዘገቡ መድኃኒቶች ገበያ ላይ መታየታቸው ቀንሷል፡፡ 

ሕዝቡ በሕገወጥ መድኃኒቶች ዙሪያ የሚሰጠው ጥቆማ እየተሻሻለ መምጣቱም ለቁጥጥሩ መጠናከርና በዚህም የተነሳ ያልተመዘገበ መድኃኒት ገበያ ላይ ላለመታየቱ ሌላው ማስረጃ መሆኑን በመጠቆም ሥራው በየአምስት ዓመቱ በሚዘጋጀው ስትራቴጂክ ዕቅድ ውስጥ ልዩ ትኩረት እንደተሰጠው አስረድተዋል፡፡

‹‹የሀብት ውስንነት ባለበት አገር ትልቁ ሀብታችን ሕዝባችን ነው፡፡ ሕዝባችን ጥቆማውን ካጠናከረና ያልተመዘገቡ መድኃኒቶችን ከመግዛት ከተቆጠበ በሕገወጥ መድኃኒት ላይ የሚሰማሩ አካላት ከዚህ ድርጊታቸው ይታቀባሉ፡፡ እንደ ረዥም ጊዜ ስትራቴጂ ግን የጥቆማው ቁጥር እየጨመረ ሳይሆን እየቀነሰ መሄድ ይገባዋል፡፡ ምክንያቱም የችግሮች ጥቆማ እየጨመረ የሚሄድ ከሆነ መሠራት ያለባቸው በአግባቡ እንዳልተሠሩ ያሳያል፤›› ብለዋል፡፡

የቁጥጥሩ ሥራ በሚገባ ከተጠናከረ፣ አጎራባች አገሮችም በሚገባ ከተደራጁ፣ በሕገወጥ መንገድ የሚገቡና የሚወጡ መድኃኒቶች ከተገደቡ ሙሉ ለሙሉ ከችግሩ ነፃ ባይወጣም መጠኑን መቀነስ እንደሚቻልም ተናግረዋል፡፡

ለሕገወጥ መድኃኒት ዝውውር መስፋፋት መንስዔ ከሆኑት ምክንያቶች መካከል  አንዱና ዋንኛው ጥራታቸው፣ ደኅንነታቸውና ፈዋሽነታቸው የተረጋገጡ መድኃኒቶች በገበያ ላይ ሳይገኙ ሲቀሩ ነው፡፡ የተጠቀሱት መድኃኒቶች ገበያ ላይ እንዲገኙ ለማድረግ መንግሥት የተቻለውን ያህል ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡

ለዚህም የመድኃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ ተቋቁሞ እጥረት የሚታይባቸውና የተለየ በሽታ ለማከም የሚያገለግሉ መድኃኒቶች እንዲሟሉ ለማድረግ የሚያስችሉ በርካታ ሥራዎች በማከናወን ላይ መሆኑን ገልጸው፣ አቅርቦቶች ብቻ ሳይሆን የሚገቡ መድኃኒቶች ጥራታቸው፣ ደኅንነታቸውና ፈዋሽነታቸው የተረጋገጡ መሆኑን ለማረጋገጥ የሚያስችል ተግባር በኢትዮጵያ ምግብ፣ መድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ባለቤትነት አማካይነት እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

መድኃኒቶች እንዲገቡና እንዲመዘገቡ የሚፈቀድላቸውም ከአምራቾቹ ፋብሪካ ቁጥጥር ጀምሮ ስለመድኃኒቶቹ የሚገልጹ ሰነዶችን በመገምገምና በማረጋገጥ እንዲሁም ላቦራቶሪ ምርመራ ከተሠራላቸው በኋላ እንደሆነ፣ ይህም ለሕገወጥ መድኃኒቶች ቁጥጥር የመጀመርያ መሠረት ሊሆን እንደሚችል፣ በሕጋዊ መንገድ የገባውም በትክክል ለተፈለገው ዓላማ እየዋለ ነው ወይ? የሚለውን የቁጥጥር ሥራ የሚያከናውኑ አካላት ከፌዴራል እስከ ክልልና ወረዳ ድረስ እንደተደራጁ ምክትል ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡

በተቆጣጣሪ ብቻ የሚሠራው ሥራ በቂ እንዳልሆነ፣ ኅብረተሰቡ ራሱ የቁጥጥሩ ባለቤት እንዲሆንና ችግር ሲኖርም በአካባቢው ለሚገኙት የቁጥጥር አካላት ወይም ለፌዴራል ተቆጣጣሪ መሥሪያ ቤት ጥቆማ የሚሰጥበት ሥርዓት እንደተዘረጋም አክለዋል፡፡  

‹‹ይህ መሰሉ ሥራ እንደተጠበቀ ሆኖ ከአገር ውስጥ ባለድርሻ አካላት፣ ከክልል ተቆጣጣሪ ከዛም አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ካሉና በዘርፉ ከተሰማሩ አካላት ጋር አብሮ መሠራት ያለባቸው ተግባራት ተጠናክረው እየተከወኑ ነው፡፡ የዛሬውም ስብሰባ የዚሁ አንድ አካል ሲሆን ስብሰባውም ሊካሄድ የቻለው በኢትዮጵያ አነሳሽነት ነው፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያ የቁጥጥር ሥራ መጠናከር ብቻ በቂ ባለመሆኑና በአካባቢው ያሉ አጎራባች አገሮችም ካልተጠናከሩ እነሱ ዘንድ የደረሰ ችግር ወደ እኛ የሚይመጣበት ምክንያት የለም፤›› ብለዋል፡፡

በምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት አባል አገሮች ብሔራዊ የመድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ኃላፊዎችና ለጋሾች ተሳታፊ የሆኑበት ስብሰባ ዓላማ ጥራታቸው፣ ደኅንነታቸውና ፈዋሽነታቸው ያልተረጋገጡ መድኃኒቶች ላይ ጠበቅ ያለ ቁጥጥርና ክትትል ለማድረግ የተሰናዳውን ሪጅናል ስትራቴጂክ ፍሬምዎርክ ኤንድ ኢምፕሊመንቴሽን ፕላን ላይ ተወያይቶ ለማፅደቅ ነው፡፡