Skip to main content
x

ያልተደራጀ ሕዝብ ምን ቢያወራ ምን ቢሠራ የፖለቲካ ውጤት የለውም

ስለአገር ነፃነትና ሰላም ስናነሳ ያለፈውን ጊዜ ትዝታ፣ የአሁኑን ሁኔታና የወደፊቱን ተስፋ በቅደም ተከተል መርምረን መሆን አለበት፡፡ ያለፈው ተሞክሯችን የአሁኑን ተጨባጭ ሁኔታ ለማስተካከል፣ የአሁኑ ይዘታችን ደግሞ የወደፊት ዕጣ ፈንታችንን በአግባቡ ለመተለም ይረዳናል፡፡ እነዚህን ሁኔታዎች በብስለት፣ በመረጋጋትና ከስሜት ነፃ ሆነን በማስተሳሰር አገራችንን ጠንካራ መሠረት ላይ ለማቆም መትጋት አለብን፡፡

በአገራችን ውስጥ ያለው የፖለቲካ ውጥንቅጥ አንድም ጊዜ ማሠሪያ ሳይበጅለት ከአርባ ዓመታት ላላነሰ ጊዜ አገሪቱ በመሪዎችና በተማሪዎች ፍጥጫ አበሳዋን እያየች ነው፡፡ ፍጥጫዎቹ የማይቆሙትና ወደ አንድ ውል ያለው ነገር ተሰብስበው ሕዝቡን ማረጋጋት ያልቻሉት ከአያት ቅድመ አያቶቻችን ጀምሮ መሪና ተመሪ፣ ሕዝብና መንግሥት፣ ትክክለኛውን የሕዝብ ፍላጎት በእኩልነትና በነፃነት በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ የተመሠረተ ውይይት ማድረግና ለተግባራዊነቱ በጋራ መቆመ የማይሞከርና የማይታሰብ ስለሆነ ነው፡፡

በዚህ ዘመን ግን ይኼን የአንድ ወገን አዛዥና ታዛዥነት ጊዜ ያለፈበት አሠራርና አስተሳሰብም ጭምር ነው፡፡ በእኛ አገር ግን ይኼ ሐሳብ መሠረቱ ጥልቅ ስለሆነ በቀላሉ ከሰዎቻችን አዕምሮ ሊወጣ ባለመቻሉ፣ የእሱ ውልድ የሆነው ፀረ ዴሞክራሲያዊ አሠራር በሕዝባችን ላይ በቀላሉ የማይገመት መከራ እያስከተለ ነው፡፡ በመሆኑም መንግሥት ለሕዝብ እሱ ማድረግ የሚፈልገውን ብቻ እያደረገ፣ ለሌሎች ፍላጎትና ሐሳብ ቦታ ሳይሰጥ በመቅረቱ የመከራ ዘመናችን እየረዘመ የመጠፋፊያ ጊዜያችንን እያቀረብን ነው፡፡

ባለፉት ዓመታት አገራችን ለከፋ የፖለቲካ ውጥንቅጥ ተዳርጋ ነበር፡፡ ይኼ ውጥንቅጥ የበርካቶችን ሕይወት የበላ፣ ንብረት ያወደመና የሕዝብን ሰላማዊ ኑሮ ያናጋ ሥጋት ፈጥሮ ነበር፡፡ ይኼ ሁኔታ በአሁን ጊዜ ተለውጧል ለማለት ጊዜው ገና ነው፡፡ አሁን አገሪቱ በጊዜያዊ ሁኔታ አዋጅ ሥር የምትተዳደር በመሆኑ ይኼ ጊዜ ሲያበቃ ምን እንደሚከተል ለማወቅ ይከብዳል፡፡ ነገር ግን አገሪቱ የብልሆችና የእውነተኛ ምሁራን አገር ከሆነች የአዋጁ ጊዜ ከማለቁ በፊት መፍትሔዎቹ መቅደም አለባቸው፡፡ ትክክለኛው የሕዝብ ፍላጎት መለየት አለበት፡፡

እነዚህ የሕዝብ ፍላጎቶች በሰላማዊ መንገድም ሆነ በአዋጅ ይፋ ሆነዋል፡፡ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ መንግሥት ከተቃዋሚዎች ጋር ለመደራደር መፈለጉን፣ ተቃዋሚዎችም ለረዥም ጊዜ ሲጠይቁት የነበረ ጥያቄ በመሆኑ ተቀብለውት ነበር፡፡ ይኼ አስተሳሰብ በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት ያለው የዘመኑ የችግር መፍቻ ዘዴ በመሆኑ አበሳችንን ለመጨረስ ትክክለኛ ጅምር ነው ብለን ነበር፡፡ ነገር ግን የእኛ ነገር ሳንካ ስለማያጣው ጉዞው ገና ሳይጀመር ባቡሩ ተንገራግጮ ሊቆም ነው፡፡

ይኼን ሒደት ድርድር በሉት ክርክር፣ ውይይት በሉት ጭውውት ሕዝቡ በተለያዩ ምክንያቶች ይፈልገዋል፡፡ በዋናነት ሕዝቡ የሚፈልገው ያለምንም መሪ ድርጅት ባለፈው ዓመት ሕዝብ በተለይ ወጣቱ ያነሳቸውንና የተዋደቀላቸውን መብቶችና ጥቅሞች መንግሥት ከራሱ ግምገማ በመነሳት የሚሰጠውን ተግባራዊ ምላሽ ለማወቅ ነው፡፡ በተጨማሪ መታወቅ ያለበት ያልተደራጀ ሕዝብ ምን ቢያወራ ምን ቢሠራ ለድል የሚያበቃ ፖለቲካዊ አቅም የለውም፡፡ ስለዚህ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሕዝብን አጀንዳ አንስተው እግረ መንገዳቸውንም የሕዝቡን ትግል ቢያንስ ቢያንስ ለዚህ መድረክ በባለቤትነት ተቀብለውና ተገቢው ሕዝባዊ አጀንዳ አስይዘው በመደራደር፣ የአንድን የፖለቲካ ድርጅት እውነተኛ ተግባር ይወጣሉ ከሚል መነሻ ነው፡፡

ነገር ግን ይኼን መድረክ ኢሕአዴግ ጊዜ ለመግዛት ሲል የቀየሰው ሥልት ነው፡፡ የሚሉና የተቃዋሚዎችን የመደራደር ብቃትና ፍላጎትንም የሚጠራጠሩ አልጠፉም፡፡ እነዚህ ጥርጣሬዎች ዝም ብለው ያለምክንያት የሚነሱ አይደሉም፡፡ ካለፈው ታሪካችን ተሞክሮ ነው፡፡ በተለይ ድርድሮቹ የሚካሄዱት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ነው፡፡ ስለተባለም በኢትዮጵያ ውስጥ አዲስ ተራማጅ ባህል ሊጀመር ነው የሚል ሐሳብ አጭሯል፡፡

ሆኖም ግን ገና ወደ ዋናው አጀንዳ ድርድር ሳይገባ የስብሰባውን ሥነ ሥርዓት በሚመለከተው ውይይት ላይ፣ በድርድሩ ጊዜ አጀንዳ ሊሆኑ የሚችሉ ጉዳዮች ያለቦታቸው መጥተው ተደነቀሩና ቅድመ ሁኔታ ሁነው ተነገሩን፡፡ እንግዲህ ሲወራ የነበረው ሁሉ ለእንቧይ ካብነት እንኳ ሳይበቃ የልጆች ጨዋታ ዓይነት ሆኖ ተገኘ፡፡ ላለመስማማት ምክንያት ተብለው የሰማናቸው በኢሕአዴግ በኩል መድረኩን የምንመራው በተራ ሁላችን ተቀያይረን እንጂ በሌላ ገለልተኛ ወገን መመራት የለበትም የሚል ነው፡፡

በመድረክ በኩል ደግሞ ሁሉንም ተቃዋሚ ድርጅቶች እኔና እኔ የምመርጣቸው ድርጅቶች ውክልና ወስደን እንደራደር፣ ያለበለዚያ ለእኔ ሌላ ለብቻ የውይይት መድረክ ይዘጋጅ የሚል የነበረ ሲሆን፣ በስተመጨረሻ ደግሞ የታሰሩት አባሎቼ ካልተፈቱ አልደራደርም የሚል ነው፡፡ እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ቅድመ ሁኔታዎች የታሰበውን ትልቅ የችግር መፍቻ ይሆናል የተባለውን መድረክ የሚያሰናክሉ ከሆነ፣ ሁሉቱም ወገኖች ቆም ብለው ራሳቸውን መመርመር ይገባቸዋል፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ቅድመ ሁኔታ አያስፈልግም ከተባለና ከተስማሙበት በመንግሥትም ሆነ በተቃዋሚዎች በኩል ቅድመ ሁኔታ ማምጣት ለምን አስፈለገ?  በመጀመሪያው ቀን ውይይት ቅድመ ሁኔታ የለም ሲባል ራስን ማግለል ይቻል ነበር፡፡ ሌላው አስገራሚ ጉዳይ ደግሞ በቅድመ ሁኔታው ውስጥ የተቀመጡት ነጥቦች ከአጠቃላዩ የውይይት ጭብጦች ጋር ስንመዝነው፣ የሚኖራቸው ሥፍራ እዚህ ግባ የማይባል መሆኑ ነው፡፡

በኢሕአዴግ በኩል ገለልተኛ የሆነ አወያይ ለመቀበል የተቸገረበት ምክንያት ምንድነው? ይኼ ጉባዔ እኮ አስፈጻሚውን አካል የሚሾም ወይም የሚሽር ፓርላማ አይደለም፡፡ አወያይ (Moderator) የሚባለውም አፈ ጉባዔ እኮ አይደለም፡፡ ደግሞስ በእኛ በኩል ሌላ አማራጭ አንቀበልም ብሎ መደምደም ቅድመ ሁኔታ ካልሆነ ምን ሊሆን ይችላል? ጉባዔውን የሚመራው አካል እኮ በዘፈቀደ ሳይሆን በጋራ ፀድቆ በሚሰጠው የስብሰባ አመራር ደንብ ይኖራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ገለልተኛ ማለት ደግሞ ገለልተኛ ነው፡፡ ገለልተኛ የሚባል ሰው የለም ብሎ ለመከራከር የኢሕአዴግ የመነሻ ሐሳብ ጥርጣሬ እንጂ፣ በምንም ሁኔታ እውነት ሊሆን አይችልም፡፡ ኢሕአዴግ እኔ ያሰብኩት እንጂ የሌሎች ሐሳብ ተግባር ላይ የሚውለው በመቃብሬ ላይ ነው የሚለውን ነገር ወደ ድርድሩ ከመግባቱ በፊት ከጊዜው ሁኔታ ጋር ማስተካከል አለበት፡፡ እንግዲህ በዚህ ትንሽ ጉዳይ ላይ እንደ አስፈላጊነቱ አቋምን ማስተካከል (Flexibility) ካላሳየ፣ በድርድሩ ላይ ይነሳሉ ተብለው በሚታሰቡ ዋና ጉዳዮች ላይ ሕዝቡ ምንም እንዳይጠብቅ አመላካች ይሆናል፡፡

በመድረክ በኩል ከተሰሙት ሐሳቦች ውስጥ ተቃዋሚ ድርጅቶችን ወክለን እኔና እኔ የምፈልጋቸው ድርጅቶች ብቻ ለድርድር ይቅረቡ ማለት፣ በሌሎች ተቃዋሚዎች ላይ ያለውን አቋም ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ነው፡፡ ብናምንበትም ባናምንበትም ሁሉም ተቃዋሚ የሚባሉት ድርጅቶች እነሱ ያሟሉትን መሥፈርት አሟልተው ነው በሕጋዊነት የተመዘገቡት ተብሎ ይታመናል፡፡ ስለዚህ ራሱን አግዝፎ ሌላውን ማሳነስ ከዚያም አልፎ ዕውቅና እስከ መከልከል መሄድ በእጅጉ ያስተዛዝባል፡፡ ሲሆን ሲሆን ሌሎችም ተጨምረው እንዲጋበዙ ሐሳብ ማቅረብና መድረኩን ማስፋት ሲገባ ማጥበብ ትክክል አይሆንም፡፡ እናንተ የማትቀበሉዋቸው ሌሎች ድርጅቶች የእኔ የሚሏቸውን ሐሳባቸውን ማን ሊያቀርብላቸው ነው? ይኼ ከአንድ የዴሞክራሲ እርሾ በትንሹም ቢሆን ካለው ድርጅት የሚቀርብ ሐሳብ አይደለም፡፡ ለነገሩማ ሁሉም ተቃዋሚ ድርጅቶች በየአምስት ዓመቱ በምርጫ ወቅት ብልጭ ብለው ከሚጠፉ በስተቀር ይኼን ያህል የሚያኩራራ ድርጊት የፈጸሙ አላየንም፡፡

ሌላው የሕዝብን ቀልብ በመጠኑም ቢሆን ሊስብ የሚችል እንዲያውም በውጭም ሆነ በአገር ውስጥ ያሉ አንዳንድ ሰዎች የሚደግፉት የታሰሩት አባሎቻችንን ሳንስፈታ ወደ ድርድሩ እንገባም የሚለውን ነው፡፡ የታሰሩት የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅት አባላት የመፈታት ጥያቄ የበርካታ ሕዝብ ጥያቄ ሊሆን ይችላል፡፡ መጠየቁም ተገቢ ነው፡፡ ታዲያ ማንም ሰው እንደሚገምተው ይኼ የዋናው ድርድር አጀንዳ ሆኖ ነው መቅረብ የነበረበት፡፡ ይኼም ቢሆን ጥያቄው እንደ አንድ አንገብጋቢ ጉዳይ የሚቀርብ አይደለም፡፡ ቅድመ ሁኔታ አያስፈልግም እየተባለ አንደ አንድ ማሳመኛ ለዋናው ድርድር መቅረብ ያለበትን ጉዳይ ያለቦታው ሰንቅሮ ድርድሩን ማቋረጥ ተገቢ አይደለም፡፡

ለድርድሩ ዋና አጀንዳና ለዘላቂ ሰላም መደላደል የሆኑ ብዙ ጉዳዮች አሉን፡፡ እየጠበበ ስለሚሄደው የፖለቲካ ምኅዳር፣ ስለዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች፣ ስለፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል፣ ስለመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ ስለምርጫ ሕጎች፣ ስለመገናኛ ብዙኃን አጠቃቀም፣ ወዘተ . . . ላይ ስለሚነሱ ጭብጦችና ድምዳሜዎች ለማወቅ ነው የሕዝቡ ዋና ጉጉት፡፡ በዚሀ ሒደት ውስጥ ይኼ በቅድመ ሁኔታነት የተቀመጠው ጉዳይም መፍትሔ ያገኛል፡፡ የታሰሩት አባሎቻችሁማ በትግል ውስጥ እስካሉ ድረስ ከዚህ በላይ የሆነ መስዋዕትነት ለመክፈል ቆርጠው ነው ወደ ትግሉ የተቀላቀሉት፡፡ ስለዚህ እነሱን በቅድሚያ ለማስፈታት ሳይሆን የእነሱን ዓላማ ለማሳካት ነው የትግሉም፣ የድርድሩም መነሻና መድረሻ ሐሳብ መሆን የነበረበት፡፡ ሌላው ጉዳይ ብቁ ተወዳዳሪዎቻችንና ተደራዳሪዎቻችን እነሱ ብቻ ስለሆኑ ሌላ የለንም ካላችሁ ደግሞ ሌሎችን የማሳነስ ሞራላችሁን በእጅጉ ይፈታተናል፡፡

ብዙ ጊዜ አንዳንድ አጋጣሚዎችን በወቅቱ ካልተጠቀምንባቸው ተመልሰው አይገኙም፡፡ ሁሉም ማለት በሚቻል ደረጃ የአገራችን የፖለቲካ ኃይሎች ካለፈው መማር በእጅጉ ይከብዳቸዋል፡፡ በ1997 ዓ.ም. ምርጫ ተቃዋሚዎች ከ150 በላይ የፓርላማ ወንበሮችንና በርካታ የክልል ወንበሮችን አሸንፈው አዲስ አበባን የማስተዳደር ሙሉ ዕድል አግኝተው ነበር፡፡ በዚህ ዕድል ተጠቅመው ለተሻለ ድል መዘጋጀት ሲገባቸው፣ ኢሕአዴግ ሙሉ ሥልጣኑን ካልለቀቀልን በሚል ቀቢፀ ተስፋ ያን ሁሉ የሕዝብ ጥረትና ተስፋ እንዲሟጠጥ አደረጉ፡፡ ከዚያ ወዲህ ኢሕአዴግ መቶ በመቶ የማሸነፍ ቀመር ሠርቶ እስከ ዛሬ ባዶ እጃቸውን አስቀራቸው፡፡ ሕዝቡንም የዴሞክራሲ ተስፋ አሳጡት፡፡

የአሁኑ የድርድር መድረክ ሊገኝ የቻለው ባለፈው ዓመት የተፈጠረው ሕዝባዊ ተቃውሞ አገሪቱን የማጥለቅለቅ አዝማሚያ ስላሳየና የማይቀር መሆኑም ስለተገመተ ነው፡፡ የፖለቲካ መፍትሔም ያሻዋል የሚል አስገዳጅ ሁኔታም ስለተፈጠረ ነው፡፡ ተቃዋሚዎችማ ከበፊት ጀምሮ የድርድር መድረክ እንዲከፈትላቸው ሲጠይቁ ነው የኖሩት፡፡ ግን አላገኙትም፡፡ ዕድሉን አጋጣሚዎች ሲያመጡት ደግሞ በተገኘው መድረክ ተጠቅሞ የሚቻለውን ሁሉ አድርጎ የተገኘውን ትርፍ ይዞ፣ ከአቅም በላይ የሆነውን ደግሞ ለሕዝብ መተው ሲገባ ‹የእናቴ መቀነት . . . . › ዓይነት ነገር ማቅረብ ተገቢ አይደለም፡፡

በዚህ መድረክ ላይ ኢሕአዴግ ይፈጥራል ተብሎ የሚጠበቀው ጫና ቀላል አይደለም፡፡ ከእሱ ፍላጎት ውጪ የሆነ ሌላ ፍላጎት፣ እሱ ከያሚቀርበው ሐሳብ ውጪ ሌላ ሐሳብ ተቀባይነት እንዳይኖረው በትጋት እንደሚሠራ ይታወቃል፡፡ ምናልባትም የኋላ ኋላም ቢሆን ለውድቀት ከሚዳርጉ ዋና ዋና ምክንያቶች የመጀመሪያው ምክንያት ይኼ ሊሆን ይችላል፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ይኼን ፀባዩን ስለሚያውቁ ለእልህ አስጨራሽ ትግል ተዘጋጅተው ነው ወደ መድረኩ መግባት ያለባቸው፡፡ በተለይም የመድረክ አመራሮች ከኢሕአዴግ ጋር በውስጥም በውጭም ሆነው ላለፉት 25 ዓመታት አብረው የተጓዙ ስለሆነ ከሁሉም በላይ ባህሪውን ጠንቅቀው የሚያውቁ ናቸው፡፡

የታሰሩት አመራሮች መፈታትን እንደ ቅድመ ሁኔታ ሲያስቀምጡ ይኼንን እንደማያደርግ በሚገባ ያውቃሉ፡፡ ነገር ግን ከውስጥም ከውጭ ይኼ ድርድር ብዙ ጫና ስላለበት አጣብቂኝ ውስጥ መግባታቸው ግልጽ ነው፡፡ ልክ እንደ 1997 ዓ.ም. ቅንጅት ማለት ነው፡፡ ለመሆኑ ከድርድሩ ቢወጡ የታሰሩት አባሎቻቸውን  የማስፈታት ዕድል አላቸው? የማይፈቱ ከሆነ ደግሞ በድርድሩ ለማስፈታት መሞከር አይሻላቸውም? መቼም እነሱ በተሳታፊነት አመራሮቻቸውን ለማስፈታት ፈቃደኛ ባልኑበት ሁኔታ ሌሎች ተደራዳሪዎች የእነሱን ጥያቄ ያቀርላቸዋል ተብሎ አይገመትም፡፡ እንግዲህ መድረኮች በድርድሩ የማይሳተፉ ከሆነ በፎርፌ ተሸንፈዋል፡፡

ኢሕአዴግ ለዋናው ድርድር የሚያቀርባቸው አባላት የገነተረና የማይታኘክ ደረቅ አቋም የሚያራምዱ ግለሰቦች መሆን የለባቸውም፡፡ ድርድሩ እነሱ ለሚመሩት ሕዝብ ሰላም ተብሎ እንጂ፣ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር የሚደረግ የርዕዮተ ዓለም ክርክር እንዳልሆነ መጤን አለበት፡፡ ከድርጅታቸው የሚሰጣቸው አቅጣጫም ሆነ ግለሰቦቹ በባህሪያቸው ነገሮችን ቀለል አድርገው አስተያየቶችን የመቀበልና በራስ የመተማመን አቅም ያላቸው መሆን አለባቸው፡፡

ጎበዝ ይኼ ሕዝብ እኮ በዚህ ቢል በዚያ ችግሩን የሚፈታለት ወገን አጣ፡፡ ግማሹ ችግሩ ባለበት እንዲቀጥል የሚያደርግ፣ ግማሹ ችግሩ እንዲባባስ በማድረግ መፍትሔ ይመጣል ብሎ የሚያምን ሆነ፡፡ ኢሕአዴግ ደግሞ የ25 ዓመታት የቆየ ታሪኩንና የጥንት ፖሊሲው ላይ ሙጭጭ ብሎ ጊዜውና ሕዝቡ እየቀደመው የዘመኑን እርሻ በዱሮ በሬ ለማረስ የሚዳክር ነው፡፡ ሕዝቡ ደግሞ ግራ በመጋባት ላለፉት አርባ ዓመታት በል ሲል በመጨራረስ አሊያም በመናቆርና በመዘላለፍ እየኖረ ነው፡፡ ሹሞቹም ሆኑ ሹመት ፈላጊዎቹ ብዙውን ጊዜያቸውን የሚያጠፉት ሴራ ሲወጥኑ፣ ማምለጫ መንገድና ማጥቂያ መንገድ ሲፈልጉ፣ ወገን ሲያበጁና እርስ በርሳቸው ሲካካዱ እንጂ፣ መክረውና ዘክረው ሰላምን ለማምጣት አይደለም፡፡ በአሁኑ የድርድር መድረክ ይኖራል ወይም አይኖርም ለማለት ከኢሕአዴግ ተዓምርን ከሌሎች ታሪክን እንጠብቅ፡፡ ለካስ ለሕዝብ የሚበጅ በጎ ነገር መሥራት ይኼን ያህል ከባድ ነው!     

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡