Skip to main content
x

ድርድሩ ሽል ከሆነ ይገፋል ቂጣ ከሆነም ይጠፋል

ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲ የሚታወቀው በሕገወጥነቱ ነው፡፡ ምርጫ በነበረበትና የምክር ቤት እንደራሴዎችን በመምረጥ ረገድ እየተሻሻለ የመጣ አሠራር በታየበት በንጉሠ ነገሥት ጊዜም ቢሆን ፓርቲ ብሎ ነገር አልነበረም፡፡ ፓርቲ ብሎ ነገር የመጣው በድኅረ ንጉሠ ነገሥታዊው አገዛዝ ነው፡፡ ከደርግ የሥልጣን ዘመን መባቻ ጀምሮ በኅቡዕ ተደራጅተው የወጡትም፣ ከዕልቂትና ከመበታተን ብዙ አልተረፉም፡፡ በደርግ ኢማሌድህና በኢሕአፓ መካከል ኢትዮጵያ ተቀስፋ የነበረችበት (ተቃዋሚ አናርኪስት፣ ከመንግሥት የተጎዳኘ ባንዳ የተባሉበት) ወቅት አልፎ ሃምሳ ዓመታት ያህል ቢነጉድም፣ በሐሳቦች መንሸራሸር ሁሉንም የፖለቲካ አዝማሚያዎችና የአስተሳሰብ ዝንባሌዎች ማስተናገድ የሚያስችል ሥርዓት ግን ገና አልገነባንም፡፡

በዚያን ዘመን ፓርቲ ወይም አማራጭ የሌለው ብቸኛና ሥልጣን የያዘው ድርጅት ነው፡፡ አለዚያም ሕገወጥ ነው፡፡ ሕገወጥ ብቻ አይደለም፡፡ ሕገወጥም ሆነውና ተብለው ተቃዋሚዎች አይባሉም፡፡ ስማቸው ገንጣይ/አስገንጣይ፣ ጠላት፣ የጠላት መሣሪያ ነበር፡፡ በደርግ የአሥራ ሰባት ዓመታት ታሪክ ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተቃዋሚ ለመባል፣ በዚህ ስም እንኳን በቅጡ ለመጠራት የታደሉት ወታደራዊው መንግሥት እያለቀለት ከመጣ በኋላ በየካቲት 1982 ዓ.ም. የኢሠፓ ማዕላዊ ኮሚቴ ስብሰባ፣ ከሌሎች መካከል ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ አንድነት የቆሙ ተቃዋሚዎች ለውይይት ቀርበው በሚደርስበት ስምምነትና የኢትዮጵያ ሕዝብ በሚሰጠው ውሳኔ መሠረት በአገሪቱ ፖለቲካ ተሳታፊ እንዲሆኑ በተወሰነ ሰሞን ነው፡፡

እናም ያሁሉ ስም ቀርቶ ሳይሆን፣ ከእሱም ጋር አብሮ ተቃዋሚዎች የመባል ዕድል አገኙ፡፡ ይህ ግን ረዥም ዕድሜ አላገኘም፡፡ ደርግ የኢሠፓ አሥራ አንደኛ ማዕከላዊ ኮሚቴው ያሳለፈው ውሳኔ እንደወጣ ሕወሓትን፣ ኢሕዲንን፣ ወዘተ ይዞ አዲስ የተቋቋመው ኢሕአዴግ ቀደም ሲል በሕወሓትነት ዘመን አቅርቦት የነበረውን የሽግግር መንግሥት ሐሳብ አስፋፍቶ በኅብረት የመታገል ጥሪ ለሁሉም ተቃዋሚ አቀረበ፡፡ ይኼ ‹‹የኢሕአዴግ ሰላማዊ ዴሞክራሲያዊ የሽግግር መድረክ ፕሮግራም›› (የካቲት 1982 ዓ.ም.) በቅርፁ ኢሠፓን እስከማሳተፍ ድረስ ሆደ ሰፊ ነበር፡፡ ኢሕአዴግ ተቃዋሚ ፓርቲ ሆኖ፣ ተቃዋሚም የመባል በኢትዮጵያ ያልተለመደ ‹‹ዕድል›› አግኝቶና ተሰምቶ ያቀረበው የሽግግር ሐሳብ፣ የሽግግር መድረኩ ደርግን እንደማያገል በሕዝብ በተመረጠ ጉባዔ ሕገ መንግሥት ተረቅቆ በዚያው መሠረት በሚካሄድ ምርጫ ያሸነፈ ሥልጣን ላይ የሚወጣበት ትልም እንዳለው የሚገልጽ ነበር፡፡ እንዲህ ያለውን የደርግም የኢሕአዴግም የ1982 ዓ.ም. የካቲት የሽግግር ህልም ቅዠት አድርጎ ያስቀረው ከሌሎች መካከል የደርግ እንቢታ ጭምር ነው፡፡ በደርግ አንፃር የተሠለፉ እርስ በርስም የሚፋለሙ ታጣቂዎችም የአገሪቷን፣ የራሳቸውንና የደርግን የራሱን ችግሮች በየፈርጁ ለማስተናገድና ለመቋቋም አቅም ያለው ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ መፍትሔ በኅብረት ደቅነው በይፋ የማፋጠጥ አርቆ አስተዋይነት ያልፈጠረባቸው ነበሩ፡፡

ሕወሓት መጀመሪያ በመጋቢት 1981 ዓ.ም ድኅረ ሽሬ ድል የሰላም ጥሪ፣ በኋላም የኢሕአዴግ የ1982 ዓ.ም. የሽግግር መድረክ ፕሮግራም ጥሪ ያቀረበው እነ ሕወሓት (ከእነ ሕወሓትም እኩል ጎን ለጎን ሌሎች ማለትም እነ ኢዲሕ፣ ኢፒዲኤ፣ ኢሕአፓ፣ ኢሕዲን፣ . . .) ተቃዋሚዎች ሆነው ነው፡፡ ገብሩ አሥራት (2006) እንደሚሉትም፣ ‹‹በኢትዮጵያ ጦርነት የተበራከተውና አላስፈላጊ ደም መፋሰስ የተከሰተው ሰላማዊ የትግል አግባብ ዝግ ስለነበር ነው፡፡ ደርግ የፖለቲካ ምኅዳሩ ጠባብ ሆኖም ሰላማዊና ሕጋዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ ቢፈቅድ ኖሮ የእርስ በርስ ጦርነቱና የከፋ ዕልቂቱ ባልተከሰቱ ነበር፡፡ ዜጎች በሰላማዊ መንገድ ተወዳድረው ሥልጣን የሚይዙበት ሁኔታ በመዘጋቱ ትጥቅ ለማንሳትና ሥርዓቱን ለመፋለም በሰሜን ኢትዮጵያ ሕወሓት፣ ኢሕአፓ፣ ግገሓት፣ ኢዴሕና የኤርትራ ድርጅቶች ትጥቅ አንግበው ነበር፡፡ በምሥራቅና በምዕራብ ኢትዮጵያም ኦነግ፣ ኢነአድ፣ ምሶነአድ፣ ኦእነግ፣ ሲነአድ፣ ጋሕነአድ፣ ቤነአድ፣ ወዘተ ትጥቁ ትግል ያካሂዱ ነበር፡፡ መኢሶንም በመጨረሻ ሰዓት ወደ ትጥቅ ትግሉ አምርቶ ነበር፡፡››

ለማንኛውም ይህን ያህል ተቃዋሚ ነበር፡፡ ችግሩ ግን ተቃዋሚዎች በዚህ ስም አለመጠራታቸው፣ በዚህ ስም የመጠራት ክብር አለማግኘታቸው፣ ገንጣይ አስገንጣይ፣ አሸባሪ፣ የውክልና ጦርነትና የውክልና ወረራ መባሉ ብቻ አይደለም፡፡ ከጦርነት ቀጣናው ውጪ የሚገኙ እንደ አዲስ አበባ የታደሉት ጥቂቶቹ በሚኖሩበት፣ አንፃራዊ ደህነኛ ቦታዎች ጭምር በሻዕቢያነትና በወያኔነት የተጠረጠረን መልቀም፣ አብሮም መርዘኛና አሸባሪ ወሬዎች በየሥርቻው መነስነስ፣ የውስጥ አርበኞቻቸው ጥቃት ሊያደርሱ ነው እየተባለ ሥውርና ግልጽ ቁጥጥር ማጥበቅ የመንግሥት ዋነኛ ሥራ ሆነ፡፡ ትግሬ መሆን እስኪያሸማቅቅ ድረስ የእርስ በርስ መጠራጠር ተራባ፡፡

በተለይ በመጨረሻው ወቅት በጥቅምት 1982 ዓ.ም. የኢሠፓ ማዕከላዊ ኮሚቴና የብሔራዊ ጉባዔ አስቸኳይ ጉባዔ ወቅት ጦርነቱም የሰላም ጥረቱም እንዲቀጥል ተወስኖ አገር የመጨረሻውን መጨረሻ መታዘብ ያዘ፡፡ ገና ከሸንጎው ዕለት አንስቶ በአገሪቱ የብሔረሰብ እኩልነትና በቋንቋ የመጠቀም መብት ያለ ለማስመሰል እንደራሴዎች በኦሮሚኛ፣ በትግርኛ፣ በአፋርኛ እየተናገሩ ወደ አማርኛ የሚተረጎምበት ቴአትር ተሠራ፡፡ የእስልምናና የክርስትና እምነት የሃይማኖት ሹማምንትም ቡራኬያቸውን ሰጡ፡፡ የኦርቶዶክስ እምነት ተወካዩ ስመ ኢትዮጵያን ከመጽሐፍ ቅዱስ እያጣቀሱ፣ ከአብርሃ ወአጽብሃ ዘመን አንስቶ ቤተ ክርስቲያን አብራ እየዘመተች ለነፃነት ያደረገችውን ተጋድሎ እየዘረዘሩ ጦርነቱን አፀደቁ፡፡ የእስልምና ተወካዩም ‹‹አገርህን የደፈረ ውጋ›› ተብሎ ከላይ መታዘዙን እየጠቀሱና በኢትዮጵያ ያለውን የሃይማኖት እኩልነት እያሞካሹ መዝመትን ሰበኩ፡፡ በዘወትሩ የባንዲራ፣ የሦስተኛ ሺሕ ዓመት ሥልጣኔና ገናናነት አምልኮት ላይ ‹‹አገሪቱ ልትገነጣጠል ነው፣ . . . አማራንና ኦሮሞን ሊያጠፉት ነው . . .›› የሚል ሽብርም ተቸለሰ፡፡ በየቦታው ሕዝብን እየሰበሰቡ በእንዲህ ያለ ሽብርና ፀረ ትግሬ ስሜት ከትቦ ለማነሳሳትም ሲሞክር አየን፡፡ ‹‹ዘራፍ ትግሬ ገዳይ›› ብሎ በሬዲዮ እስከ ማስፎከር ድረስ ቅስቀሳው ልክ ሲያጣ መሰከርን፡፡

የኢትዮጵያ የተቃውሞ አስተነጋገድ አጠቃላይና አጭር ታሪክ ይኼንን ይመስላል፡፡ የተቃውሞው መስተንግዶ ብቻ ሳይሆን የተቃውሞው ዓይነት ብልሽትና ጭንጋፍነትም ከራሳችን አይወርድም፡፡ የእኛው ፖለቲካ ጥፋት ውጤት ነው፡፡

ፓርቲዎች ሕጋዊ በሆኑበት፣ የባለ ብዙ ፓርቲዎች ሥርዓት ተቋቁሟል በተባለበት ድኅረ 1983 ዓ.ም. እንኳን ኢሕአዴግ ታሪክ መሥራትና ማስመዝገብ የሚያስችለውን ዕድሉን ደግሞ ደጋግሞ አስጨንግፏል፡፡

ኢሕአዴግ ደርግን አሸንፎ ሥልጣን መያዝ መቻሉን የትክክለኛነቱ ማስረጃ በሥልጣን የመቆየት የድካምና የደም ዋጋው አድርጎ መውሰዱ አልቀረም፡፡ ይኼ ግን እስትንፋሱ አልሆነም እንጂ፣ ለአንደበት ወግ ያህል የሽግግሩ ምዕራፍ ከግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም. በኋላ ሲከፈት ከተባለው ጋር አብሮ አይሄድም፡፡ ደርግ ተሸነፈ፣ ሽግግር ጀመረ ማለት ትግል አበቃ ማለት አለመሆኑ ተገልጾ ነበር፡፡ ኢሕአዴግ የተፈተነው፣ የተሞከረውና ተሞክሮም ገና ከመጀመሪያው ፈተናውን ማለፍ ያልቻለው ይኼን ሰላማዊና ፖለቲካዊ ትግል ማካሄድ አልችል ሲል ነው፡፡ ተደማጭነት ያገኘ ሐሳብ አለኝ ወይ? በአብኛዛው በኅብረተሰቡ ውስጥ ሐሳቦቼ ተቀባይነት አግኝተው አሸናፊ ሆኑ ወይ? ማለቱን ትቶ በትጥቅ ትግሉ ማሸንፉን፣ በዚህ ዘርፍ ብቻ ከሁሉም በላይ ገዝፎ መገኘቱን ለትክክለኛነቱ ማስረጃ አድርጎ አቀረበ፡፡ በዚያውም ቀጥሎ ጫካ ውስጥ ከለመደው የጦርነት ሥልት በመውጣት ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ ተፎካካሪነት መለወጥ አቃተው፡፡

ከተቀናቃኞች ጋርም ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ማካሄድ እንቢ አለው፡፡ እንዲያውም ያን ሁሉ መከራ አይቶ፣ ደምቶና ሞቶ፣ የተጎናፀፈውን አሸናፊነት ያለ ተቃዋሚ ማጣጣም አለመቻሉን እንደ ሴራና ክፋት አየው፡፡ በገዛ ራሱ ጥፋትና ብልሽት ሰላማዊ የፖለቲካ ተፎካካሪነት የሚጠይቀውን አስተሳሰብና ምግባር ይዞ መገኘት አቅቶት ከተቃዋሚዎች ጋር ደመኛ ግንኙነት ጀመረ፡፡ ከዚህ የተነሳ የተቀናቃኞች ትግል በሰላማዊ ክልል ውስጥ እንዲቆይ፣ በዚያውም እንዲገታ ማድረግ አልፈቅድ ብሎ ተቃውሞ ውስጥ ለውስጥ እየተገነባ እንዲሄድ እየገፋፋ እነሆ አሁን ለደረሰበት ደረጃ በቃ፡፡

ከ25 ዓመታትና ከአምስት አጠቃላይ ምርጫ በኋላ ዛሬም ምርጫና የሕዝብ ፈቃድ በጭራሽ አልተግባቡም፡፡ እስከ ዛሬ የተካሄዱት ምርጫዎች የፖለቲካ ድርጅቶችን እውነተኛ ውድድርና የሕዝቡን እውነተኛ ምርጫ ለማሳየት አልቻሉም፡፡ በዴሞክራሲ ጨዋታ የሚወሰኑትም ውሳኔዎች የሕዝብን ፍላጎትና የኢሕአዴግን ፕሮግራም የመገጣጠም ደረጃ የማመልከት አቅም የላቸውም፡፡ ኢሕአዴግና አጋር ድርጅቶቹ የወደዱትን በሕዝብ ስም መጫን ይችላሉ፡፡ አጋር ድርጅቶችም በኢሕአዴግ ዙሪያ የሚሽከረከሩ ናቸው፡፡ ምሪት የሚያገኙትም ከኢሕአዴግ ነው፡፡ የምሪት እጁም የመሪዎቻቸውን በሥልጣን መቆየት አለመቆየት ላይ እስከመወሰን ሊረዝም የሚችል መሆኑ ተደጋግሞ ታይቷል፡፡

የእስካሁኑ የ25 ዓመታት ልምድ እንዳረጋገጠው አሁን ሥልጣን ላይ ያለው የገዢው ፓርቲ የገዢነት ሥልጣን ማንዴት የመነጨው ከምርጫ ሳይሆን፣ ከጥንት ከጠዋቱ የኢሕአዴግ የትጥቅ ትግል አሸናፊነት ነው ማለት ተራ አሉባልታ አይደለም፡፡ የዚህ ምክንያት የተገነቡት የመንግሥት አውታሮች ለኢሕአዴግና ለአንድ ፓርቲ ብቻ ያዘነበሉ፣ ካለሱ አሸናፊነት ሌላውን የማይቀበሉና አፈናጥረው የሚጥሉ በመሆናቸው ነው፡፡ ብዙ ፓርቲዎች አሉ እየተባለና ምርጫ እየተደረገም ኢሕአዴግ ብቸኛው አሸናፊ ሆኖ የቀጠለው፣ ከደርግ ውድቀት በኋለ የተገነባው አውታረ መንግሥት በውስጠ  ተፈጥሮው ለአንድ ፓርቲ አገዛዝ ሆኖ የተዋቀረ በመሆኑ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ የትኛውም ፓርቲ አማራጭ ሆኖ ወጥቶ በምርጫ አሸንፎ ሥልጣን ላይ የሚወጣበት፣ እስካሁን ገዢ ፓርቲ ሆኖ የቆየው ኢሕአዴግም በተራው ተቃዋሚ ፓርቲ ሆኖ በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ውስጥ ገብቶ የሚሠራበት ነፃነትም ሆነ ዕድል ሲበዛ የጨለመ ነው፡፡

ይኼንን ጉዳይ ትንሽ ዘርዘር አድርገን እንየው፡፡ ተቃዋሚዎች የሌሉ ያህል በሆኑበት ገዢው ፓርቲም ሁሉን ነገር ለራሱ ሥልጣን መሣሪያ ከማድረግና ‹‹ከእኔ ያልገጠመ ፖለቲካ የጠላት ነው›› ማለትን ርዕዮቱ ባደረገበት በዚህ ሁኔታ፣ ዋናው ጉዳት የሚተርፈው ለአገሪቱ ሕዝቦች ነው፡፡ በምዕራብ አገሮች እንደሚታየው ወግ አጥባቂም ሥልጣን ላይ ወጣ ሶሻሊስት፣ ባለመናጋት የአገርና የሕዝብ የተረጋጋ ጉዞ የሚቀጥልበት ሁኔታ ለእኛ ሩቅ እንደሆነ ነው፡፡ የኢሕአዴግ መንግሥትነት በምርጫና በአማራጭ ፓርቲ የሚቀየር ስለመሆኑ እምነት የሚያሳድር ነገር የለም፡፡ መጀመሪያ በአማራጭነት ኢሕአዴግን በምርጫ የሚፈታተን ብርቱ ፓርቲም አይታይም፡፡ አሉ የሚባሉት ተቃዋሚዎች እንዳሉ ተባብረው ቢመጡ እንኳ ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ ወገናዊነት ነፃ የሆነ የምርጫ ውድድር ሜዳ የመገኘቱ ጉዳይ ሌላ ፈተና ነው፡፡ በምርጫም ማሸነፍ ከዕለታት አንድ ቀን ቢቀና እንኳ ትርምስም ሆነ አፈራርሶ መገንባት በማይኖርበት ሁኔታ ጉዞውን ማስቀጠሉ መተማመን አይቻልም፡፡ ገዢው ፓርቲ እኔ ነኝ ያሸነፍኩ ብሎ በጉልበት የማይቀማበት፣ ወይም አሸናፊ ነን ባለ ወገንና አልለቅም ባለ ወገን ሕዝብ ተከፋፍሎ ቀውስ ውስጥ የማይገባበትና የተለፋበት የልማት ሥራ ለውድመት የማይጋለጥበት ሁኔታ አልተደለደለም፡፡ ነባሩ ገዢ እንደምንም ወርዶ ተቃዋሚው ሥልጣን ሊጨብጥ ቢችል እንኳ የነባሩን ገዢ ቡድናዊ አሻራና ቁጥርጥር ለማፅዳት ሲል መንግሥታዊ አውታራትን ማበራየቱ አይቀርም፡፡ ይኼን ችግር አይቀሬ የሚያደርገው ከቡድናዊ ወገናዊነት ነፃ የሆኑ አውታራትን የመገንባቱ ተግባር አለመከናወኑ ነው፡፡ ሥልጣን ላይ ያለው ስብስብና ተቃዋሚዎቹ በጠላትነት የፖለቲካ ወጥመድ ውስጥ እስከተሰነካከሉ ድረስም ይህን ተግባር መወጣት አይቻልም፡፡

አሁን ባለንበት ደረጃ ገዢው ፓርቲ ነፃ ዴሞክራሰያዊ ምርጫንና ውጤቱን ለማክበር የራሱ ፍላጎትና የተቃውሞ ሥጋት ካላስገደደው በቀር፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የአውታረ መንግሥት አተካከል ‹ቢፋጅ በማንኪያ ቢበርድ በእጅ› ለመግዛት የሚያስችል ነው፡፡

የተጀመረው የድርድርና የመግባባት ሒደት ለሕዝብ የሚተርፍ ቁም ነገር የሚኖረው፣ ገዢው ፓርቲ የሕዝብ ውሳኔን በመፃረር በመንግሥት ሥልጣን ላይ ላለመቆየትና ሕገወጥ የሥልጣን አወጣጥንም ላለመቀበል ሲስማማ፣ ከልቡ ሕዝቡን ከመቆጣጠር ፋንታ በሕዝብ ቁጥጥር ውስጥ ለማደር መልካም ፈቃዱ ከሆነና በመንግሥት አውታሩ ውስጥ ያለውን ለኢሕደዴግ አዘንባይነትም ወደፊት ለማቅናት ዝግጁ ከሆነ ነው፡፡ ኢሕአዴግ እንዲህ ያለ ፍላጎት ይኖረው ይሆን? እንዲህ ያለስ ጥያቄ ያስተናግድ ይሆን? ወደፊት ይታያል፡፡ ወይም በዘመኑ ልማታዊ ጋዜጠኝነት አስቀያሚ ቋንቋ ‹‹ወደፊት የሚታይ ነው የሚሆነው››፡፡ እኛ ደግሞ ‹ሽል ከሆነ ይገፋል ቂጣ ከሆነም ይጠፋል› እንላለን፡፡

ይኼንን የሚወስነው አሁን ድርድር የተቀመጡት ኢሕአዴጎችና ተቃዋሚዎች ግንኙነታቸውን የሚመሩበት ድባብና ከባቢ አየር ነው፡፡ ኢትዮጵያን ያስቸገራት የኢሕአዴግ በተከታታይ ገዢ ፓርቲ ሆኖ መቆየት ወይም ወደፊትም ሥልጣን ላይ መቆየት መቻሉ አይደለም፡፡ ያን ያህል እኩል የተቃዋሚዎች መኖር፣ ኢሕአዴግ ገና ሲጀምር እምነቱ አድርጎ እንደያዘው ችግራችን አይደለም፡፡ እንዲያውም የጎደለን የአገሪቷ የፖለቲካ አየር አለመጥራቱ፣ የፖለቲካ ኃይሎች ትግልም (እርስ በርሳቸው ጭምር) ሰላማዊ ግብግብ ውስጥ አለመግባቱ ነው፡፡ ከሁሉም የበለጠ መከራ ያሳየንና አገሪቷንም ያስቸገራት፣ የኢሕአዴግና የተቃዋሚዎች ትንቅንቅ ከሰላማዊና ከሕጋዊ መድረክ ውጪ መሆኑ ነው፡፡ የአገሪቷ የፖለቲካ ሰላም ፈተናም ይኼው ነው፡፡

ሁሉም ተደራዳሪዎች በሰላማዊውና በሕጋዊው መድረክ ውስጥ መዋል አለባቸው፡፡ ይኼ የሚመለከታቸው በሕጋዊነት መቀጠል ወይም ወደ ሕገወጥ መዞር እየተባሉ የጫካን መንገድ በሚያመላክት ፕሮፓጋንዳ የሚቀሰቅሱትንና የሚገፉትን ተቃዋሚዎችን ብቻ አይደለም፡፡ ተቃዋሚዎች ተመርረው ወደ ስደትና ወደ ጫካ ቢሄዱ እንደተገላገላቸው የሚቆጥረውን ኢሕአዴግን ጭምር ነው፡፡ ከሕገወጡ ይበልጥ ሕጋዊውን መንገድ ተመራጭና ቀላል የሚያደርግ የፖለቲካና የባህል አሠራር ማልማት ያቃተውንና ጥቅሜም አይደለም ያለውን ኢሕአዴግን ይጨምራል፡፡ ተቃውሞን በመበተን ሕገወጥነት ውስጥ መገኘቱን የማያውቀው ኢሕአዴግ ጭምር፣ በሕጋዊና በሰላማዊ መድረክ ውስጥ መዋል ማደር አለበት፡፡ ኢሕአዴግ ከሕግ በላይ ሆኖ ተቃውሞን ማስተዳደር ብቻ የመንግሥት ሥራው አድርጎ ከተጠመደበት ጣጣ መውጣት አለበት፡፡ የውስጥ ተቃውሞን ማዳከም ለኢሕአዴግ ጥንካሬ አለመሆኑን፣ የውስጥ ተቃውሞን አስደንግጦ ወደ ውጭ እንዲፈረጥጡ ማድረግም መገላገል አለመሆኑን ገና ዛሬም አልተማረም፡፡

በተያዘውና ገና ባልለየለት በዚህ ድርድርም ውስጥ ዋናው ቁም ነገር የሁሉም ልብ አንድ የሰላማዊ መንገድ ላይ መገናኘቱ ነው፡፡ ሰላማዊ የሐሳብ ትግልን ከተቀናቃኞች ጋር ማድረግና ማካሄድ ከሕግ በታች መሆንን፣ የፓርቲንና የመንግሥትን ሥራና ሚና ለይቶ ማወቅንና በሕግ መገዛትን ይጠይቃል፡፡ በአገሪቱ ውስጥ የሚርመሰመሰውን የተቃውሞ ብዛትና ዓይነት በዴሞክራሲያዊና ራስንም በሚያስገዙበት በሕጋዊ መንገድ ለመፍታት መሰናዳት ሕገ መንግሥቱ ፀንቶ በሥራ የሚቆይበትን ዘመን፣ አውታረ መንግሥትን ከአንድ መንግሥት ዕድሜ ጋር እንዲቆራኝ ካደረገው የእስከ ዛሬና የረዥም ጊዜ ችግራችን ይገላግለናል፡፡

አለበለዚያ ልዩነታችን አብሮ ለመሥራት አያስችለንም ብለው በ1960ዎቹ ማለቂያ ዓመታት ላይ በደረሰባቸው ዕልቂትና ጥፋት ዓይነት ብቻ የምንገላገለው አደጋ አይኖርም፡፡ እንደነሱ ከዕልቂትና ከመበታተን በኋላ እንደገና የመጎዳኘት ዕድል ሊኖር እንደማይችል ከወዲሁ መሥጋትና መፍራት ተገቢ ነው፡፡  

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡