Skip to main content
x

ግንባታዎችና የትራፊክ ፍሰቶች የመንገድ ሕግ የሚያከብሩት መቼ ይሆን?

በአዲስ አበባ የተንሰራፋው የንግባታ ዘርፍ ለመንገዶች መጣበብ መንስኤ መሆኑ አሌ የሚባል አይደለም፡፡ የሚገነባው ሕንፃ መንገድ ከፍሎ፣ የእግረኛ መንገድ አጥሮ፣ ደህነኛውን መንገድ ቆፋፍሮና አበለሻሽቶ መተው እየተዘወተረ መጥቷል፡፡

ወትሮውንም የሦስት መንግሥት ተቋማት የሚመስሉት የቴሌኮም፣ የውኃና ፍሳሽ እንዲሁም የመንገድ ግንባታ የሚመለከታቸው ተቋማት አንዱ የሠራውን ሌላው እያፈረሰ፣ አንዱ የገነባውን ሌላው እየናደ፣ ያንዱን ሥራ ሌላኛው እንዳሻው እያዘበራረቀ አሁንም ድረስ በለመደ አሠራራቸው ቀጥለዋል፡፡

ከሰሞኑ የምናየውም ይህንኑ ያሳብቃል፡፡ በየቦታው የምናያቸው የእግረኛ መንገድ ቁፋሮችም ይህንን ይመሰክሩልናል፡፡ ተራ መንገዶች፣ ቀለበት መንገድ ውስጥ የሚገኙ የእግረኛ መንገዶች ሳይቀሩ ተቆፋፍረው አገሩን የምስጥ ኩይሳ የወረረው እስኪመስል ድረስ በየቦታው የአፈር ክምር ይታያል፡፡ ጉድባ እዚህም እዚያም ተቆፋፍሯል፡፡ አስቂኝ የሚሆነው ደግሞ የቆፈሩትን አፈር፣ ያወጡትን ድንጋይ እንደነገሩ እየመለሱ፣ የራሳቸውን ቱቦ ወይም የሽቦ መሥመር በሲሚንቶ እየለሰኑ የሚገኙት ተቋማት አድራጎት አስገራሚ የሚባል ነው፡፡

እንዲህ ያለው ያፈጀ አሠራር ዛሬም ድረስ የሚተገበር በመሆኑ መንገዶች ተጣበዋል፡፡ የተቆፈሩ መንገዶችን ሽሽት እግረኛው ወደ መኪና መንገዶች እየገባ ፍትጊያ ሲገጥም ይታያል፡፡ የትርምርስ አገር፡፡ ከመንግሥታዊ ተቋማቱ ባሻገር በየጥጉ ሽቅብ የሚፈሉት ሕንጻዎች የሚያደርሱትን ጉዳት ቁብ የሚለው አልተገኘም፡፡ ማዘጋጃ ቤትም ምን ቸገረኝ ያለ ይመስል ነገር አለሙን ትቶታል፡፡ መገንባቱ የሚደገፍ ሆኖ ሳለ፣ ጠጠርና አሸዋ የሚገለበጠው መንገድ ዳር ከሆነ፣ አሸዋና ሲሚንቶ የሚቦካው መንገድ ዳር ከሆነ፣ ብረታብረቱና አጠናው የሚኮለኮለው በመንገደኛው መንገድ ላይ ከሆነ ምን የሚሉት ግንባታ ነው? የጋራውን እያፈራረሱ የራስን መገንባት ምንኛ የዕድገት መገለጫ ይሆን?

ከዚህ ጎን ለጎን በመንገድ አጠቃቀም ላይ የሚታየው የአሽከርካሪው ባህርይ ሳይጠቀስ አይታለፍም፡፡ የትራፊክ ባለሙያዎች እንዲገልጹት በእውነትም በአብዛኛው አሽከርካሪ ችግር የበዛበት፣ እግኛን ማስቀደም ነውር የሚመስለው ነው፡፡ ያለጥሩንባ መኪና የነዳ የማይመስለውም ስንቱ ነው፡፡ አንዳንዱማ እንኳንና በመንገዱ ገብተውበት፣ በትክክለኛው የእግኞች ማቋረጫ መንገድ (ዜብራ) ሳይቀር እየተሻገረ ያለውን እግረኛ ሸርፎ በማጠምዘዝ ቀድሞ ለማለፍ የሚሽቀዳደም ነው፡፡ ይባስ ሲልም በዜብራ ማቋረጫው ላይ የሚተላለፉትን በጡሩምባ የሚያደናብር፣ በሚጋልብበት ፍጥነት እየከነፈ መጥቶ በግድ የሚቆም የትዬ ለሌ ነው፡፡

ለዚህ ሁሉ ችግር የተለያየ ምክንያት ሊቀርብ ይችላል፡፡ የሾፌሮች ማን አለብኝነት፣ የእግረኛው ደንታ ቢስነት፣ የመንገዶች ጠባብ መሆን ወዘተ. ሊጠቀሱ ከሚችሉት ችግሮች መካከል ናቸው፡፡ በሬዲዮና በቴሌቪዥን የሚለፈፈው መሠረቱን የሳተ ትምህርት አሰጣጥና አደጋ ዲስኩር እንዳለ ይቆይና አንዳንድ አባባሎችን ግን እንፈትሽ፡፡

የትራፊክ ፖሊስ ባልደረቦችም ሆኑ አጉራ ዘለል ሾፌሮች እግረኛ መንገድ ሲያቋርጥ በፍጥነት መሻገር አለበት የሚሉት ፈሊጥ ተደጋግሞ ይደመጣል፡፡ በመሠረቱ እግረኛ ለራሱ ደኅንነት ሲል ይህን ማድረጉ መካሪ ባላሻው ነበር፡፡ ነገር ግን ደንብ የሚያከብረውም አሽከርካሪውም ተባብረው እግረኛው በዜብራ መንገድ ሲያቋርጥ በፍጥነት አይደለም የሚለው አነጋገራቸው እርምት የሚሻ ይመስለኛል፡፡ ተደጋግሞ መባል ያለበትና መከበርም የሚገባው አባባል የሚሻገር እግረኛ ኖረም አልኖረ አሽከርካሪው እግረኞች ወደ ሚያቋርጡበት መንገድ ሲቃረብ ፍጥነቱን ቀንሶ መሆን እንዳለበት የሚያሳስበው ነው፡፡

የመንገድ ሕግ እግረኛው ሲያቋርጥ በፍጥነት በሩጫ ወዘተ. ይሁን የሚል ተቀጥላ የለውም፡፡ ይህ ማለት በመንገዱ የሚጠቀሙ አካል ጉዳተኞች፣ አቅመ ደካሞች፣ ነፍሰ ጡሮች፣ ህጻናት እንዲሁም የቤት እንስሳት ወደ ክፍለ አገር ሲወጣ እንደሚታየው የዱር እንስሳት በትራፊክ አደጋ እንዲያልቁ ከበየን የማይተናነስ የአንድ ወገን አገላለጽ ነው፡፡ እንደ እውነቱ መሆን የነበረበት በእግረኛ ማቋረጫ መንገዶች ላይ ፍጥነቱን የማይቀንስ፣ እግረኞችን በጡምሩምባ የሚያተራምስ፣ መሪ እየጠመዘዘ የሚያሸማቅቀው በሙሉ መቀጣትና አደብ መግዛት እንዲችል የሚያደርገው አሠራር መተግበር ነበር፡፡

ሩቅ ሳንሄድ ቅርባችን ሩዋንዳ ውስጥ የዚህ ዓይነት አሠራር አላቸው፡፡ እግረኛው በትክክለኛው የማቋረጫ መንገዱ መሠረት እስከተሸገረ ድረስ ለምን አትሮጥም፣ አትከንፍም ብሎ ነገር የለበትም፡፡ ይልቁንም የተገላቢጦሹን እግረኛው ሲያቋርጥ በነበረበት ወቅት ዝግ የማይል ሾፌር፣ ለእግረኛ ክብር የማይሰጥ አሽከርካሪ በትራፊክ ደንብ ተላላፊነት ይከሰሳል፡፡ ይቀጣል፡፡ እርግጥ በዚህ አገር የማይከበሩ የእግረኛ ሕጎች ከሆኑት ውስጥ የትራፊክ መብራት ማክበር ተጠቃሽ ነው፡፡ ማንም ጉዳዬ ሳይለው ቀይና አረንጓዴ ሲያበራ የሚውለው የእግረኛ መብራት እንዲከበር፣ እንዲለመድ ማድረግ ተገቢ ይሆናል፡፡ ሌሎች አገሮች ስለወደዱ ብቻም ሳይሆን ሕግ ስለሚያስገድዳቸው፣ ባያከብሩት ስለሚቀጣቸው የእግረኛ መብራቶችን አክብረው ይጠቀማሉ፡፡ የሚያልፍ መኪና ኖረም አልኖረ፣ ቀይ የበራበት እግረኛ እስኪለቀቅ ድረስ ቆሞ የሚጠባበቅባቸው አገሮች እዚሁ አፍሪካችንም ውስጥ አሉ፡፡

ስለዚህ ሕግ የማስከበር ግዴታ ያለበት አካል ሕግ ማስከበር ያለበት በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት እንጂ በልምምጥ መሆን የለበትም፡፡ እግረኛም ሆነ አሽከርካሪ አደጋ ቢደርስ ተጎጂነቱን በማሰብ ጥንቃቄ ማድረግ የህልውና ጉዳይ ስለመሆኑ በነጋሪ ሊደሰኮርለት አይገባውም፡፡ በዚህ ሳያበቃ ግን በሕግ ተጠቃነት እንዳለበት አውቆም መንቀሳቀስ ግዴታው እንደሆነም ሊገነዘብ በሚገባው መልኩ እንዲንቀሳቀስ መደረግ አለበት፡፡

(ያንታለም በሰማይ፣ ከአዲስ አበባ)