Skip to main content
x
‹‹በከተማችን ፍፁም የሆነ አስተማማኝ ሰላም አለ ማለት ይቻላል››

‹‹በከተማችን ፍፁም የሆነ አስተማማኝ ሰላም አለ ማለት ይቻላል››

አቶ ተቀባ ተባባል፣ የጎንደር ከተማ ከንቲባ

አቶ ተቀባ ተባባል ጎንደር ከተማን ለአንድ ዓመት በከንቲባነት መርተዋል፡፡ አቶ ተቀባ ከወራት በፊት ከተማዋ በፖለቲካና በፀጥታ ችግር ውስጥ በነበረችበት ጊዜ አብረው የነበሩ ናቸው፡፡ ጎንደር በቅርቡ ሰባተኛውን የከተሞች ፎረም ማስተናገዷ ይታወሳል፡፡ የከተሞች ፎረም ከመዘጋጀቱ ከወራት በፊት ተከስቶ የነበረውን የፀጥታ ችግርና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ ዳዊት እንደሻው ከአቶ ተቀባ ጋር ያደረገው ቃለ ምልልስ እንዲህ ተጠናቅሯል፡፡ 

ሪፖርተር፡- ዘንድሮ የከተሞችን ፎረም በጎንደር ከተማ አዘጋጅታችኋል፡፡ ሲጀመር በዋናነት ምን ዓላማ አንግቦ ነበር የተነሳው? አሁንስ ምን ዓይነት ውጤት ትጠብቃላችሁ?

አቶ ተቀባ፡- መልካም፡፡ እንግዲህ ሰባተኛው የኢትዮጵያ የከተሞችን ፎረም በውድድር እንድናዘጋጅ ከመሰየማችን በፊት በ2002 ዓ.ም. ጀምሮ የከተሞች ቀን፣ የከተሞች ሳምንት ከዚያ በኋላም ባለፈው ከስድስተኛው ድሬዳዋ ከተከበረው ጀምሮ አሁንም የኢትዮጵያ የከተሞች ፎረም በመባል የሚከበር በዓል ነው፡፡ እንግዲህ የዚህ ፎረም መሠረታዊ ዓላማ በአገራችን ከዚህ ከከተሞች መስፋፋት ጋር ተያይዞ በከተሞች የሚሰጡ አገልግሎቶች፣ የመሬት ማኔጅመንትና መሰል ተግባራትን በተመለከተ በብቃት በመፈጸም ከተሞች በንግድ፣ በኢንቨስትመንትና በቱሪዝም ምቹ ማዕከላት ሆነው እንዲያገለግሉ ለማድረግ ታስቦ የሚካሄድ በዓል ነው፡፡ ከተሞች እንዲያሳኩዋቸው የሚጠበቁ ጉዳዮች ጭምር ስላሉ፣ እነሱን በብቃት ማሳካት እንዲችሉና ልምድ የሚለዋወጡበት መድረክ ሆኖ እንዲያገለገል ማድረግ አንደኛው ዓላማ ነው፡፡ በከተሞች መካከል ያለው የዕድገት ልዩነት እንዲጠብ በማድረግና በዚህ ፎረም አማካይነት አንዱ ከተማ ከሌላው ከተማ ልምድ የሚወስድበትና የሚለዋወጥበት፣ ልዩነቱ የሚጠብበት፣ የኢትዮጵያ ከተሞች ቅድም ባልኩት መንገድ በሒደት ቀስ እያሉ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የሚችሉበትን መንገድ የሚፈጥር ነው፡፡ ሰባተኛው የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም በጎንደር ከተማ ሲከበር በርካታ ልዩ ሁኔታዎችና አጋጣሚዎች ነበሩ፡፡

እስካሁን ድረስ ከተካሄዱት የከተሞች ፎረሞች  በአገር ውስጥ የሚሳተፉት ከተሞች ቁጥር እጅግ በጣም ከፍተኛ የሆነበት፣ ከ200 በላይ ከተሞች ይሳተፋሉ ተብሎ የተያዘበት፣ ከሃያ በላይ ኩባንያዎችና እስካሁን ድረስ ተደርጎ በማይታወቅ ሁኔታ ከውጭ የሚገኙ እህትማማች ከተሞችም ጭምር የተሳተፉበት ነበር፡፡ ሁለተኛው ለየት የሚያደርገው ይህ ሰባተኛው የከተሞች ፎረም ከክልል ርዕሳነ መዲናዎች ወጥቶ ለመጀመሪያ ጊዜ ከተማችን የሚከበር መሆኑ ልዩ ያደርገዋል፡፡ ከዚያ ባሻገር በአገር ደረጃ በተለይ ካለፉት ሰባትና ስምንት ወራት በፊት በእኛ አካባቢ አጋጥሞ በነበረው መለስተኛ የሆነ የሰላም ችግርና ከዚህ ጋር ተያይዞ በነበሩት ችግሮች ማግሥት ተመልሰን ወደ ልማት በመግባት፣ ሰላማችንን አስከብረን የጀመርናቸውን የህዳሴ ጉዞዎች ተግባራዊ ለማድረግ ርብርብ በምናደርግበት ወቅት የሚከበር ፎረም መሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ ፎረም ቅድም ያነሳኋቸውን ዓላማዎች ከማሳካት ባሻገር እነዚህ ልዩ ገጽታዎች ለከተማችን ይዘውት የሚመጡ ዕድል ስላለ ዕድሎችን አሟጦ ለመጠቀም በሚያስችል መንገድ የቅድመ ዝግጅት እንቅስቃሴ ስናደርግ ነው የቆየነው፡፡ ራሱን የቻለ ዕቅድ የማዘጋጀት፣ አደረጃጀቶችን የመፍጠር፣ ለፎረሙ የሚያስፈልገውን አጠቃላይ ዝግጅት አጠናቆ እንግዶችን ለመቀበል የሚያስችል ሥራ ነው የሠራነው፡፡

በዚህ ፎረም አንደኛ ከተማችን ጎንደር ከ250 ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ መናገሻ ከተማ ሆና የቆየች ከተማ ነች፣ ጥንታዊ ከተማ ነች፣ የቅርስ ከተማ ነች፡፡ ስለዚህ ከቱሪዝም አኳያ ያለንን ዕምቅ አቅም የምናሳይበት ይሆናል ብለን ነው ያሰብነው፡፡ በከተማችን ጎንደር ለኢንቨስትመንትና ለንግድ ያለው ምቹ ሁኔታ ከአራቱም የኢትዮጵያ ማዕዘናት የሚገኙ እንግዶቻችንም ሆኑ ከውጭ የሚመጡት እንግዶቻችንና ኩባንያዎች እንዲያውቁት ማድረግ፣ በቀጣይም የንግድ፣ የኢንቨስትመንትና የቱሪዝም ሥራዎቻችን ውስጥ ተጨማሪ አቅምና ተጨማሪ ጉልበት የምናገኝበት ሁኔታ እንፈጥራለን ብለን ነው የነበረው፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ከተማችን ከሰባት ከስምንት ወራት በፊት አጋጥሟት ከነበረው መለስተኛ የሰላም ችግር ጋር ተያይዞ ተቀዛቅዞ የነበረውን የንግድና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ እንደገና እንዲነቃነቅ የምናደርግበትን ዕድል ይፈጥርልናል ብለን ነበር፡፡ እነዚህን ከማድረግ ጎን ለጎን የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች የሚገኙበት በዓል ጭምር ስለሆነ ከተሞች ብቻ ሳይሆን ይዘዋቸው የሚመጡ ሰዎች ከ12,000 በላይ እንደሚሆኑ ገምተን ነበር፡፡ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት የበለጠ እንዲጠናከር የሚያስችል ሥራ እንሠራለን፡፡ በዚህም የጎንደርን ሕዝብ እንግዳ ተቀባይነትና እንግዳ አክባሪነት በአግባቡ ለሌሎች ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ለማስተዋወቅ ዕድል ይፈጥራል ብለን ነበር ያሰብነው፡፡ እነዚህን ዓላማዎች በሙሉ ያሳካ ፎረም ነበር ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡ ይገኛሉ ተብለው ከታሰቡት 200 ከተሞች 231 ከተሞች ናቸው የተገኙት፡፡ ከሃያ በላይ ኩባንያዎች ናቸው የተሳተፉት፡፡ ከጎንደር እህት ከተሞች የአሜሪካ ሞንትጎመሪ ከተማ እዚህ ተገኝቶ ያለውን ዝግጅት ለማሳየት ጥረት አድርጓል፡፡ አልጋ ተዘጋጅቶ የመኝታ አገልግሎት ያገኛሉ ተብለው ከተመዘገቡና አገልግሎት ከተሰጣቸው ውስጥ ከ8,500 በላይ የሚሆኑ እንግዶች ተካፍለዋል፡፡

እኛ ሳንጠራቸው የተገኙ በጣም በርካታ ተወካዮች ነበሩ፡፡ ለምሳሌ ከአምቦ፣ ከጅማ፣ ከአዲስ አበባና ከሌሎችም ዩኒቨርሲቲዎችና ተቋማት በፎረሙ ላይ የታደሙ ነበሩ፡፡ ስለዚህ ይኼን ያህል ቁጥር ያላቸው ከተሞች ሲሳተፉ በአገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡ ስድስተኛው የከተሞች ፎረም ላይ ተሳታፊ የነበሩት ከ166 ከተሞች አይበልጡም ነበር፡፡ የዘንድሮው ግን በጣም በርካታ ከተሞች የተሳተፉበትና ጥሩ ልምድ ያገኘንበት ነው ብለን በእኛ በኩል የምንወስደው፡፡ ሁለተኛው እነዚህ የልዑካን ቡድኖች ከመጡ አይቀር የከተማችንን የቅርስ መስኅቦች በአግባቡ እንዲጎበኙ የሚያስችል ሥራ ሠርተናል፡፡ የጎንደርን ከተማ በእንግዳ አክባሪነቱና፣ እንግዳ ተቀባይነቱ በየክፍላተ ከተሞች ጭምር ሕዝቡ ራሱ ትልልቅ ድንኳኖችን እየጣለ እየደገሰ ሁሉንም ክልሎችና የልዑካን ቡድኖች ሲያስተናግድ፣ የስጦታ ዕቃዎችን ለክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ ለከንቲባዎችም መልዕክት ሲልክ የሰነበተበት ሁኔታ ነበር የነበረው፡፡ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ የበለጠ እንዲጠብቅ ምቹ ሁኔታ ጭምር መፍጠር ችሏል፡፡ ከዚያ ባሻገር ከተሞቹ ይዘዋቸው የቀረቡት የፈጠራ ራስን ከማስተዋወቅ አኳያ እኛም ልምድ ያገኘንበት ነበር፡፡ በተለይ በከተማ መሬት አስተዳደር ሥርዓት፣ በመሠረተ ልማት፣ በመኖሪያ ቤትና በመሳሰሉት ችግሮችን ከመፍታት አኳያ ከተሞች ያላቸውን ተሞክሮ፣ በተለይ ትልልቆቹ ከተሞች እንዴት እየተንቀሳቀሱ ነው ብለን ልምድ ያገኘንበት ነበር፡፡

በአጠቃላይ ፎረሙ በተሳካ ሁኔታ የተከናወነ ነው ብሎ መውሰድ የሚቻለው፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ይኼ ፎረም በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ለማድረግ ዋነኛውን ድርሻ የወሰደው ሕዝቡ ነው፡፡ እንግዶችን ከ140 ኪሎ ሜትር ጀምሮ ተቀብሎ ከየከተሞች እየተቀበለ ከማምጣት ጀምሮ ቆይታቸውም ምቹና ደኅንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆንና አይረሴ ትዝታ ይዘው እንዲሄዱ ለማድረግ የሠራው ሥራ ጥሩ ነበር፡፡ የፀጥታ ሥራችን ላይ ኅብረተሰቡ ትልቁን ድርሻ ተወጥቷል፡፡ የፀጥታ ኃይሉ የሠራው ሥራ እንደተጠበቀ ሆኖ፡፡ ስለዚህ ሰባተኛው የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም በብዙ መልኩ ያስቀመጥናቸውን ዓላማዎች ያሳካ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡ ፎረሙ የሚካሄድበትን ቦታ ስናዘጋጅም ወደፊት ለወጣቶች መዝናኛ እንዲሆን አድርገን ነው፡፡ በቀጣይም ፓርክ ሆኖ ነው የሚያገለግለው፡፡ ስለዚህ ስኬታማ ነበር ብሎ ማንሳት ይቻላል ጠቅለል ባለ መልኩ፡፡  

ሪፖርተር፡- ከፀጥታ ጋር በተያያዘ ምናልባት ከዚህ ከከተሞች ፎረም በፊት በከተማዋ ችግሮች እንደነበሩ ይታወቃል፡፡ በከተማዋ በተለያዩ ቦታዎች ቦምብ እንደሚጣል በተለያዩ ሚዲያዎችም ሲዘገብ ነበር፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም አሜሪካ ዜጎቿን ወደ ጎንደር እንዳይሄዱ ማስጠንቀቂያ ሰጥታ ነበር፡፡ ይኼንን ድርጊት ማነው የሚፈጽመው? የተደራጀ ቡድን አለ? በቁጥጥር ሥር የዋሉና ኃላፊነቱን የወሰዱ አካላትም ካሉ እስኪ ያብራሩልኝ?

አቶ ተቀባ፡- ቅድም እንዳነሳሁት ካለፉት ስምንትና ዘጠኝ ወራት በፊት አጋጥሞ የነበረውን የሰላምና የፀጥታ ችግር ለመፍታት ሕዝቡ ከመንግሥት ጋር በመመካከር ሲሠራ ቆይቷል፡፡ ሰላም ሲደፈርስ እያስከተለ ያለውን ችግር ሕዝቡ በደንብ ተገንዝቦ ይኼን አለመረጋጋት የሚፈልጉ ኃይሎች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ለማድረግ ሰፊ ሥራ በመሠራቱ፣ በከተማችን ፍፁም የሆነ አስተማማኝ ሰላም አለ ማለት ይቻላል፡፡ አሁን የተረጋጋ ሁኔታ ነው ያለው፡፡ የንግድ፣ የኢንቨስትመንትና የቱሪዝም እንቅስቃሴው እየጨመረ መጥቷል፡፡ በጣም መሻሻሎች ይታያሉ፡፡ እንደዚያም ሆኖ ግን ወንጀሎች ይፈጸማሉ፡፡ እነዚህ ወንጀሎች ወዲያው እንደተፈጸሙ በቁጥጥር ሥር ለማዋል፣ ከተቻለም ለመከላከል የሚያስችል አደረጃጀት በየክፍላተ ከተሞቹ እየተደረገ ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ቶሎ ብሎ ባለቤቶችን የመለየት፣ በቁጥጥር ሥር አውሎ ጉዳያቸው በሕግ እንዲታይ የሚያስችል ሥራ ተጠናክሮ እየቀጠለ ነው ያለው፡፡ ቅድም ካነሳኸው ጉዳይ አኳያ አልፎ፣ አልፎ በከተማችን የሚጣሉ ፈንጂዎች አሉ፡፡ በተለይ በሰውና በንብረት ላይ የደረሰው ጉዳት ብዙ ባይሆንም አልፎ አልፎ ወንጀሎች አሉ፡፡ እነዚህን ወንጀሎች የፈጸሙ ሰዎችን ሁሉንም በቁጥጥር ሥር ለማዋል ተችሏል፡፡ ይህንን ድርጊት የሚፈጽሙት ፀረ ሰላም የሆኑ የኤርትራ ተላላኪዎች ናቸው፡፡ ይህንን ተልዕኮ ለመፈጸም ግለሰቦቹ የሚሰጣቸው ጥቅም እንዳለ ይነገራሉ፡፡ እነዚህን ፈጻሚዎች ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ለማድረግ የሚያስችል ሥራ በክልሉና በፌደራል የፀጥታ አካሎች ጥብቅ ክትትል እየተደረገበት በዚያ መንገድ እየተፈጸመ ነው ያለው፡፡ እስካሁን ድረስ በእኛ ከተማ ደረጃ እንደዚያ ዓይነት ችግር አድርሶ ያመለጠ ሰው የለም፡፡ ኔትወርኩም ጭምር በደንብ የተዘረጋ ነው፡፡

በአግባቡ በሕግ ሲጠየቁ ለሕዝብ የሚገለጽበት ሁኔታ እንዳለ ማንሳት ይቻላል፡፡ እንደሚታወቀው አሁን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ነው ያለነው፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተግባራዊ ለማድረግ ሕዝቡ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ነው፡፡ በከተማው ውስጥ ትልልቅ ዝግጅቶች ይሰናዳሉ፡፡ የስፖርት ዝግጅቶች አሉ፡፡ ሃይማኖታዊ የሆኑ ዝግጅቶች አሉ፡፡ ትናንትናና ከዚያ ወዲያ እንዳየነው በጣም ከፍተኛ ቁጥር ያለው እንግዳ ነው የተስተናገደው፡፡ ምንም ዓይነት የፀጥታ ችግር አልተፈጠረም፡፡ ይኼ የሚያመላክተው እንደዚህ ዓይነት ፀረ ሕዝብ የሆኑ ኃይሎችና ተላላኪዎች የአካባቢው ሰላም እንዳልሆነና እንዳልተረጋጋ ለሌሎቹ አካባቢዎች ያልተገባ መልዕክት እንዲተላለፍ በመፈለጋቸው ነው፡፡ ይህ ዓላማ ስላላቸው አካባቢው ተመልሶ ወደ ትርምስ ይገባል በሚል ቀቢፀ ተስፋ ጭምር ነው በዚህ መንገድ መልዕክት ለማስተላለፍ የሚያደርጉት፡፡ ከዚህ በቀር መሠረታዊ የሚባል የሰላም ችግር የለም፡፡ ቅድም እንዳልኩህ ሕዝቡ ባለቤት ስለሆነ፡፡ ይህንን ድርጊት የፈጸሙ ሰዎች ወዲያውኑ በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ይደረጋል ወይም ደግሞ ጥቆማዎችን ሰጥቶ ይኼንን የፈጸሙ ሰዎችና አካላት እንዲያዙ እየተደረገ ነው ያለው፡፡ በዚያ መንገድ የሚወሰድ ቢሆን ነው ጥሩ የሚሆነው፡፡

ይህን ተከትሎ አንዳንድ ኤምባሲዎች በከተማችን፣ በአካባቢያችንና በክልላችን ጭምር የሚያወጡት መረጃ ትክክል አይደለም፡፡ እንደተባለው የአሜሪካ ኤምባሲ አሜሪካዊያን ወደ ጎንደር በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የሚያመላክት መልዕክት አስተላልፏል፡፡ እውነታው ሲታይ ግን ቅድም ባልኩት መንገድ በጣም በርካታ ቱሪስቶች እየመጡ ነው ያለው፡፡ በቀጣይም ከኤምባሲዎች ጋር የምንነጋገርበት ሁኔታ ይኖራል ብለን ነው የምናስበው፡፡ እነዚህን በአጠቃላይ ከከተማው ሰላም ነጥሎ ማየት ነው ትክክል የሚሆነው፡፡ ሕዝቡ በሰላም ወጥቶ የማይገባ፣ ኢንቨስትመንት፣ ንግድና ልማት የቆመበት ተደርጎ የሚወሰድበት አተያይ ትክክል አይደለም፡፡ ፍፁም አስተማማኝ የሆነ ሰላም ያለበት አካባቢ ነው ተብሎ መውሰድ ነው በእኛ በኩል የሚቻለው፡፡

ሪፖርተር፡- በአገር አቀፍ ደረጃም፣ በክልልም፣ በከተሞችና በዞኖችም የፀጥታው ችግር ከተከሰተ በኋላ ጥልቅ ተሃድሶ ተጀምሯል፡፡ በእናንተ ጥልቅ ተሃድሶ የአመራሮች መሸጋሸግና ሌሎች ጉዳዮች ነበሩ፡፡ ወደታች ደግሞ የሚነሳው ጥያቄ ወጣቱ በጥቃቅንና አነስተኛ ለመደራጀት ቢሮክራሲው በዝቶብኛል ይላል፡፡ የሥራ ዕድል ፈጠራውና ሌሎች ችግሮችም እንዲሁ፡፡ ከዚያ ውጪ ደግሞ ወደ ገጠር ሲገባ የመሬት ችግር ይነሳል፡፡ እዚህም ጎንደር ከተማ ውስጥ የመኖሪያ ቤት አለማግኘትና የተለያዩ በሕዝቡ የሚነሱ ቅሬታዎች አሉ፡፡ ከዚህ አንፃር የሕዝቡን ትክክለኛ ጥያቄ ተረድታችሁ እየመለሳችሁ ነው ማለት ይቻላል?

አቶ ተቀባ፡- እንግዲህ በጥልቅ ተሃድሷችን መሠረታዊ ጭብጥ ባለፉት አሥራ አምስት ዓመታት በአገራችን የተመዘገቡ አንኳር አንኳር የሆኑ ውጤቶች አሉ፡፡ ግልጽ የሆኑ ፖሊሲዎቻችንና ስትራቴጂቻዎችን ነድፈን ወደ ተግባር ከገባን በኋላ በኢኮኖሚውም ሆነ በማኅበራዊ የተመዘገቡ ውጤቶች መኖራቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ አሁንም በሕዝቡ ዘንድ የሚነሱና ሕዝቡን ያማረሩ ጉዳዮች አሉ፡፡ እነዚህን ጥያቄዎች ከመመለስ አኳያ ዋነኛው መሠረታዊ ችግር ከአመራር ሰጪነት ጋር ተያይዞ ያለ ችግር ነው የሚል አቋም በድርጅታችን ብአዴንና በልማታዊ መንግሥታችን ተወስዷል፡፡ በዚህ መንገድ ወደ ጥልቅ ተሃድሶ ገብተናል፡፡ በተለይ ለጥልቅ ተሃድሷችን መሠረታዊ መነሻ የሆነው ከአመራር ሰጪነትና ከሥልጣን ጋር ተያይዞ ያለው ዕይታ ነው፡፡ የሕዝብ አገልጋይነት ስሜት እየጠፋ ለግልና ለራስ የመጠቀም ሁኔታ ስላለ፣ እሱን ለማስተካከል ከሥልጣን ጋር ያለን አተያይ በተገቢው መንገድ መታረም እንዳለበት ተወስዷል፡፡ በእነዚህ ጭብጦች ላይ በመመሥረት አመራሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ እንዲያስችለው የተደረገ እንቅስቃሴ ነው ወደ ተግባር የተገባው፡፡ መሠረታዊ ችግሮችን በአግባቡ ለይተን በችግሮቹ ዙሪያ ሕዝቡ ተጨማሪ ናቸው ብሎ የሚያነሳቸውን ነገሮች ጨምረን፣ እነዚህን ለማረም የሚያስችል እንቅስቃሴ እያደረግን ነው፡፡ የጥልቅ ተሃድሶ እንቅስቃሴያችን በአመራር መቀያየር የሚቆም ስላልሆነ፣ ዋነኛ ግቡም አመራሩን መተካት ወይም ማሸጋሸግ ሳይሆን፣ የሕዝብን ችግር ከመፍታት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ዕቅዶችን በአግባቡ አዘጋጅቶ እነዚህ ተፈጻሚ እንዲሆኑ ከሕዝብ ጋር መሥራት የሚያስችል የአመራር መዋቅርና ጠንካራ መንግሥት የመፍጠር ጉዳይ እንደሆነ ግምት ውስጥ በማስገባት፣ በእኛም ከተማ ደረጃ ይኼንን ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት ተደርጓል፡፡

የጥልቅ ተሃድሶ እንቅስቃሴያችንን ተከትሎ በተለያዩ መድረኮች ከሕዝቡ ጋር ተነጋግረዋል፡፡ ለቦታው የሚመጥኑ አዳዲስ አመራሮች እንዲቀላቀሉ ለማድረግ ጥረት ተደርጓል፡፡ በአፈጻጸማቸው ደካማ የነበሩ ወይም ደግሞ ሕዝቡ እነዚህ አመራሮች ሊቀጥሉ አይገባቸውም ያላቸውን ደግሞ ከአመራርነት እንዲሸጋሸጉ ለማድረግ የሚያስችል ሥራ ተሠርቷል፡፡ በዚህ ማግሥት ወደ ተግባር ለመግባት ዕቅድ አዘጋጅተን ነው ወደ ሥራ የገባነው፡፡ እንግዲህ ከተማችን ውስጥ የሚታዩ መሠረታዊ የሚባሉ ችግሮች ትልቁ ከሥራ አጥነት ጋር የሚያያዙ ናቸው፡፡ በከተማችን ከፍተኛ የሆነ የሥራ አጥ ቁጥር አለ፡፡ ጎንደር ደግሞ የዞን ዋና ከተማ ሆና የምታገለግል በመሆኗ ብቻ ሳይሆን፣ በዙሪያ ካሉ ወረዳዎችም ጭምር በርካታ ወጣቶች፣ የአርሶ አደሩ ልጆችና ሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎች ይገባሉ፡፡ በጣም በርካታ ሥራ አጥ ወጣት አለ፡፡ ሁለተኛው ችግር ሕዝቡን ያማረሩት የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች አለመመለስ ነው፡፡ ከመንገድና ከንፁህ መጠጥ ውኃ ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች አሉ፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ከሕዝቡ ከዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ መሠረታዊ ናቸው የሚባሉ አቅርቦቶችን፣ የመኖሪያ ቤት የመሳሰሉትን በተመለከተ የሚነሱ ጥያቄዎች አሉ፡፡ ከምንም በላይ ሕዝቡ ደጋግሞ የሚያነሳቸው ከአገልግሎት አሰጣጥና ከአገልጋይነት ስሜት ጋር ተያይዞ ያለው ችግር ፈጣን ምላሽ አለማግኘት ነው፡፡ እነዚህን ለመፍታት የሚያስችል ዕቅድ አዘጋጅተን ወደ ተግባር ገብተናል፡፡

በዚህ ዓመት ወደ 23,000 የሚሆኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል ይፈጠርላቸዋል ብለን ነበር ዕቅድ ይዘን የነበረው፡፡ ባለፉት ሰባት ወራት ያከናወነውን ለመገምገም ሞክረን ነበር፡፡ ወደ 11,000 ለሚሆኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል እንዲፈጠርላቸው ለማድረግ ተችሏል፡፡ በተለይ በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ በአመለካከት ረገድ ከወጣቶችና ከወላጆቻቸው ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡ በዚህ ረገድ በአመለካከት ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎችን አድርገናል፡፡ የፈጠርነው የሥራ ዕድል በጣም ብዙ ነው ብለን አንወስድም፡፡ ከሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር ተያይዞ በወጣቶች ዘንድ የሚስተዋለው በተለይ ደግሞ እነዚህ አድካሚ የሚባሉ ሥራዎችን ለመሥራት አለመፈለግ፣ ወደ አገልግሎት ሰጪ ዘርፎች አለመሰማራት፣ ዕድገት ተኮር ወደሆኑ ዘርፎች፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ የከተማ ግብርና፣ ኮንስትራክሽንና በመሳሰሉት ለመሰማራት ብዙም ያለመፈለግ ችግሮች አሉ፡፡ እነዚህን ችግሮች ተከታታይነት ባለው የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ አመለካከቱ እንዲስተካከል የሚያደርግ እንቅስቃሴ ነው እያከናወንን ያለነው፡፡

በሰባት ወራት ውስጥ ወደ 33 ሚሊዮን ብር የሚሆን ብድር ለወጣቶች ለማቅረብ ተሞክሯል፡፡ ይኸም ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ከምንም ነገር በላይ የሥራ ዕድል ፈጠራ ሥራችን መቋጫ የሚያገኘው መንግሥት በሚፈጥሯቸው የሥራ አማራጮች ላይ የተመሠረተ ይሆናል የሚል እምነት የለንም፡፡ እንደኔ አመለካከት በከተማችን ውስጥ ኢንቨስትመንት ሊያስፋፋ የሚያስችል ሥራ ማከናወን ስላለብን የሥራ ዕድል ፈጠራ ሥራችንን ከኢንቨስትመንት መስፋፋት ጋር ተያይዞ እንዲያድግ ርብርብ እያደረግን ነው ያለነው፡፡ የግል ኢንቨስትመንቶች ጠንክረው እንዲወጡ የሚችሉበትን ሁኔታ እየፈጠርን ነው፡፡ ገበያ ኖሯቸው ማደግ የሚችሉበት ሁኔታ ከተፈጠረ ሥራ አጦችን የሚይዙት እነዚህ የግል ድርጅቶች ናቸው፡፡ ለወጣቶች አስተማማኝ የሥራ ዕድል የሚፈጥሩት እነዚህ የግል ድርጅቶች ናቸው የሚል እምነት አለን፡፡ በእኛ በኩልም ይህንን ተግባራዊ የሚያደርግ ሥራ እየሠራን ነው፡፡ ለምሳሌ በዚህ ዓመት 126 የሚሆኑ አዳዲስ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች እንክፈት የሚል የሚል ጥያቄዎች ቀርበዋል፡፡ አራት የኢንዱስትሪ መንደሮች አሉ፡፡ ከእነዚህ ጥያቄዎች መካከል 51 የሚሆኑትን በአንድ ቀን ነው የወሰድነው፡፡ በደረጃ ለይተን ለማስተናገድ የሚያስችል ሥራ እየሠራን ነው፡፡ 39 ሔክታር መሬት አስረክበናል፡፡ አንዳንዶች በግንባታ ሒደት፣ አንዳንዶች ደግሞ ማሽን በማዘዝ ላይ ነው ያሉት፡፡ ስለዚህ እንደዚህ ያሉ ኢንቨስትመንቶችን ማበረታታትና መደገፍ አለብን ብለን ነው በእኛ በኩል የምንወስደው፡፡ መንግሥት የሚፈጥረው የሥራ ዕድል እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በእነዚህ ላይ ያለውን ዕድል አሟጠን እንጠቀም በማለት እየሠራን ነው ያለነው፡፡

ከመሠረተ ልማት ጋር ተያይዞ በተለይ በከተማችን ጎንደር የአስፋልት መንደር መሠረተ ልማቶቻችን ያረጁ ናቸው፡፡ እነዚህ እንዲቀየሩ ሕዝቡ ደጋግሞ ይጠይቅ ነበር፡፡ አዳዲስ መንገዶች እንዲሠሩለት እየጠየቀ ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ ዓመት በከተማ አስተዳደሩ በኩል የተበላሹ አስፋልቶችን የመጠገን ሥራ ጀምረናል፡፡ በፌዴራል መንግሥት በኩል ከአዘዞ እስከ ጎንደር የሚሠራው የአስፋልት ግንባታ በጨረታ ሒደት ላይ ነው ያለው፡፡ የቆዩ የሕዝብ ጥያቄዎችን ለመፍታት እንቅስቃሴ እያደረግን ነው ያለነው፡፡ አንተም ተዘዋውረህ ዓይተህ ይሆናል፡፡ የጀማመርናቸው የአስፋልት ጥገና ሥራዎች ጭምር አሉን፡፡ ሕዝቡን ላለፉት ስድስት፣ ሰባት ዓመታት ሲያማርሩ የነበሩ ጉዳዮችን ለመፍታት እንቅስቃሴ እያደረግን ነው፡፡ ከዚያ ባሻገር የከተማውን የንፁህ መጠጥ ውኃ ለመፍታት የሚያስችል ፕሮጀክት ላይ ርብርብ እያደረግን ነው፡፡ አሁን የመብራቱ ጉዳይ አልቋል፡፡ በቅርቡ የከተማዋ የንፁህ ውኃ አቅርቦት ችግር በአስተማማኝ ሁኔታ ለመፍታት የሚያስችል ርብርብ እያደረግን ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ሕዝቡን ያማረሩ ጥያቄዎችን ለመመለስ የሚደረገው እንቅስቃሴ በመሠረታዊነት በአገልግሎት አሰጣጣችን ችግሮች የሚስተካከል ስለሆነ ለእያንዳንዱ የከተማ ነዋሪ ተገቢ አገልግሎት መስጠት የሚቻልበት ሁኔታ ለመፍጠር ጥረት እያደረግን ነው፡፡ የቆዩና የተንከባለሉ ለስምንትና ለአሥር ዓመታት ያህል ያልተፈቱ ችግሮችን እየፈቱ የመሄድ እንቅስቃሴ እያደረግን ነው፡፡ ይህንን አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡ ተሃድሷችን የአንድ ወቅት ስላልሆነ ከዚህ እየተማርንና ከሕዝቡ ጋር እየተመካከርን፣ ይበልጥ የጎደሉትን ነገሮች ደግሞ እያየን፣ የሠራናቸውን ነገሮች እያቀረብን፣ የከበዱንን ከሕዝቡ ጋር በትብብር እየሠራን፣ ከእኛ አኳያ ማስተካከል የሚገቡንን እያስተካከልን የሕዝቡን ጥያቄ የምንመልስበት የመልካም አስተዳደር ሥራዎቻችን እያከናወንን ነው፡፡ ስለዚህ የጥልቅ ተሃድሷችን አነሳሱ ቅድም ባልኩት መንገድ ነው፡፡ ማጠቃለያ የሚሆነው ግን የሕዝቡን እርካታ በጥልቅ ለመገመት የሚያስችል ደረጃ ላይ ነን ብዬ አልወስድም፡፡

ሪፖርተር፡- ከተሃድሶው ጋር በተያያዘ አሁንም አንዳንድ የሚነሱ ጉዳዮች አሉ፡፡ በሥራ አመራራቸው ወይም ደግሞ በአገልግሎት አሰጣጣቸው፣ በሙስና የሚጠረጠሩትንና ሕዝብ የተማረረባቸውን ከአንድ ቦታ አንስቶ ወደ ሌላ ቦታ መውሰድ እንዳለ ሕዝቡ አሁንም ያነሳል፡፡ የከተማዋን መሬት ወረው የያዙ አሁንም አልተጠየቁም ሲል ሕዝቡ  ይሰማል፡፡ ከዚህም አንፃር ጥልቅ ተሃድሶው ለዚህ ብዙ ትኩረት አልሰጠም ይባላል፡፡ እስኪ እዚህ ላይ የተሠራ ነገር ካለ ይግለጹልኝ?

አቶ ተቀባ፡- እንግዲህ ቅድም እንዳልኩህ ሥልጣንን ለራስ ጥቅም ከመዋል ጋር በተያያዘ ችግር አለ፡፡ ሕዝቡን ማዕከል አድርገው የማይሠሩ ኃላፊዎች አሉ፡፡ አጠቃላይ በጥልቅ ተሃድሶው አመራር ሆነው መቀጠል መቻል የለባቸውም ተብለው የተለዩት አመራሮች አሉ፡፡ በእኛ ደረጃ 49 በመቶ የሚሆነው አመራር ከሥልጣኑ እንዲወርድ ተደርጓል፡፡ ከዚህ ውስጥ ከሙስና፣ ሥልጣንን ያላግባብ ከመገልገል ጋር በተያያዘ 22 አመራሮች ጉዳያቸው በሕግ እንዲታይ እየተደረገ ነው፡፡ ከመሬት ማኔጅመንት ጋር ተያይዞ፣ የመንግሥት ሀብትና ንብረትን በአግባቡ ከመያዝ ጋር ተያያዞ፣ ሥልጣንን ያላግባብ ከመገልገል ጋር ተያይዞ ያሉ ጉዳዮችን በመለየት የማጥራት ሥራ ጀምረናል፡፡ አንዳንዶች በሕግ ቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ተደርጓል፡፡ ፈጻሚ ባለሙያዎችም፣ አመራሮችም ጭምር፡፡ ማስረጃዎች በደንብ እየታዩ ነው ያለው፡፡ ችግሩ እዚህ አካባቢ ትንሽ ገዘፍ ይል ስለነበር ከሙስና ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩትን በአግባቡ ለይተንና ተገቢውን የሕግ ሥርዓት ተከትለን የማጥራት፣ በቁጥጥር ሥር የማዋልና የመሳሰሉትን ሥራ እያከናወንን ነው ያለው፡፡ የሕዝቡን ችግር ከመፍታት ጋር የአቅም ማነስ ያለባቸው ኃላፊዎች እንዲነሱ ተደርጓል፡፡ በሙያተኛ መደብ እንዲመደቡ የተደረጉም፡፡ ችግር ኖሮበት ወደ ሌላ አካባቢ የወሰድነው የለም፡፡ እውነቱን ለመናገር ሕዝቡን በማሳተፍ ነው የተተኩትን አዳዲስ  አመራሮች ለማስተቸት የተሞከረው፡፡

ሪፖርተር፡- በቱሪዝም ሴክተሩ ጎንደር ከተማ አንዷ መሆኗ ይታወቃል፡፡ ከቱሪዝም ጋር በተያያዘም የፋሲል ግንብን ማንም የሚያውቀው ነው፡፡ የፋሲል ግንብን ለማደስ ችግር እንዳለ ይሰማል፡፡ ቶሎ ቶሎ ያለማደስ ችግር አለ፡፡ በእዚህ ላይ ምን ተሠራ? ለማደስስ ያስቸገራችሁ ነገር ምንድነው?   

አቶ ተቀባ፡- መልካም፡፡ እንግዲህ የፋሲል አብያተ መንግሥትና የፋሲል ግንብ በዓለም አቀፍ ቅርስነት ከተመዘገቡ ዘጠኝ የአገራችን ቅርሶች አንዱ ነው፡፡ ይህ ቅርስ የጎንደር ከተማ ብቻ አይደለም፡፡ የአማራ ክልል ወይም የኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ ንብረትም አይደለም፡፡ ይልቁንም የዓለም ሕዝብ ንብረት ነው፡፡ ስለዚህ ይኼንን ቅርስ በአግባቡ መጠበቅና መንከባከብ የእኛና የሌላውም ድርሻ ነው ብለን ነው የምንወስደው፡፡ ቅርሱ ረዥም ዓመታትን ያስቆጠረ በመሆኑ አንፃራዊ በሆነ መንገድ ትኩረት ያለው ዕድሳት ከማግኘት አንፃር ውስንነቶች አሉ፡፡ እዚህ ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይገባል የሚል አቋም አለኝ፡፡ ይህ ቅርስ በአግባቡ ተጠብቆ ከቆየ ለጎንደር ብቻ ሳይሆን፣ ለአገራችን ብሎም ለዓለም ትልቅ አስተዋጽኦ ሊያበረክት የሚችል ነው፡፡ ስለዚህ በእኛ በኩል ያደረግነው እንቅስቃሴ አንደኛው ቅርሱ ውስጥ ያሉ የመሬት አቀማመጥና ተያያዥ ሥራዎች እንዲስተካከሉ ማድረግ ነው፡፡ ይህን ሥራ ከኢትዮጵያ ቱሪስት ድርጅት ጋር በመተባበር አምስት ሚሊዮን ብር በጀት ተመድቦ እንቅስቃሴ ጀምረናል፡፡ ለዓይን ዕይታ ማራኪ መሆን መቻል አለበት፡፡ እዚያ አካባቢ ያለውን ነገር ማስተካከል አለብን ብለን ነው እየሠራን ነው ያለነው፡፡ ሁለተኛው ቅርሱን ማሻሻል የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን ከአምቦ ድረስ ሄዶ ገዝቶ የማምጣት ሥራ ሠርተናል፡፡ እንደሚታወቀው ለአምስት፣ ለስድስት ዓመታት ከኖራ ተቦክቶ ከምድር በታች ተቀብሮ የሚሠራ ሥራ ነው፡፡ ይህን ለማድረግ የማቃጠል ቴክኖሎጂ፣ ኖራ የሚገኝበትን አካባቢ ጭምር ለመለየት የሚያስችል ሥራ ሠርተናል፡፡ ስለዚህ ከአውሮፓ ኅብረትና ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በመሆን ወደፊት እንሠራለን፡፡ ፕሮጀክቶችን እየቀረፅን ይኼንን ልንሠራ የምንችልበትን መንገድ እናመቻቻለን፡፡ ቅርሱን ለማሻሻል በእኛ በኩል የሚቻል አይደለም፡፡ ከፍተኛ የሆነ በጀት ያስፈልገዋል፡፡ በቅርቡ የዓለም ቱሪዝም ድርጅት ዋና ዳይሬክተር፣ ምክትላቸውና አምባሳደሮች ከተማችንን ጎብኝተው ነበር፡፡ ይህንን ጉዳይ አንስተን ለመወያየት ጥረት አድርገናል፡፡ ስለዚህ እነሱም ለእድሳቱ የሚያግዙበት ዕድል እንዳለ ነው የገለጹልን፡፡

ሪፖርተር፡- ከወልቃይት የማንነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ መንግሥት ጉዳዩ የትግራይ ክልል መንግሥት እንደሆነ ጠቁሟል፡፡ አንዳንድ ወገኖች ደግሞ የአማራ ክልል ብሎም የጎንደር ሕዝብና የከተማው አስተዳደር ገብተው ሊፈቱት እንደሚችሉ ይናገራሉ፡፡ ይኼንን ችግር ለመፍታት የከተማ አስተዳደሩ እየሠራው ያለው ምንድነው? እናንተ ለችግሩ ቅርበት ያላችሁ ስለሆነ፡፡

አቶ ተቀባ፡- አጋጥሞ በነበረው የሰላም ችግር ሕዝብ ያነሳቸው የነበሩ የልማት ጥያቄዎችን በእኛ በኩል ለመመለስ ቅድም ባልኩት መንገድ እየሠራን ነው፡፡ በክልሉ መንግሥትና በፌዴራል መንግሥት የሚፈቱ ጥያቄዎችን ደግሞ ለሚመለከተው አካል ተላልፎ ሁሉም አካላት በራሳቸው በኩል እየሠሩ ነው፡፡ ከዚህ በላይ ጉዳዩ ከእኛ ከተማ ጋር የሚያያዝ አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- በጎንደር ከተማ ሁከትና ብጥብጥ ከተከሰተ ማግሥት ጀምሮ በፌዴራል መንግሥቱና በከተማ አስተዳደሩ በኩል የመረጃ ክፍተት እንደነበረ አንዳንድ ሚዲያዎች ሲገልጹ ነበር፡፡ በከተማውና በፌዴራል መንግሥቱ የሚሰጡ መግለጫዎች ተመሳሳይነት ይጎድላቸው እንደነበር አንዳንድ ወገኖች ሲናገሩ ይደመጣል፡፡ ስለዚህ አሁን የፌዴራል መንግሥት እዚህ ያለውን ችግር በደንብ በመገንዘብ መፍትሔ አሰጣጡ እንዴት ነው?

አቶ ተቀባ፡- ቀደም ሲል በፌዴራል መንግሥት፣ በክልሉ መንግሥትና በከተማ አስተዳደሩ በአቋም ደረጃ የተለየ ጉዳይ አልነበረም፡፡ የተለየ ችግርም አልነበረም፡፡ በወቅቱ ተፈጥሮ የነበረውን ችግር ለመፍታት ሁሉም አካላት ተንቀሳቅሰዋል፡፡ የክልል መንግሥታት ድጋፍ እያደረጉ ነው፡፡ በፌዴራል መንግሥት በኩል የሚሠሩ ሥራዎች አሉ፡፡ እነዚህ ሥራዎች ተግባራዊ እንዲደረጉ ከፍተኛ የሆነ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው፡፡ ችግሩ በተፈጠረ ማግሥት ይሰጡ የነበሩ መግለጫዎች አሉ፡፡ የሚሰጡ መግለጫዎች በአግባቡ እንዲተላለፉ ሲደረግ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ያለው እንቅስቃሴ እየተጠናከረ ነው የሄደው ብሎ መጥቀስ ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- ከአሁን በፊት ከአጎራባች ክልሎችና ከሱዳን ጋር የፀጥታ ችግሮች ነበሩ፡፡ ችግሮቹ ከተፈጠሩ በኋላም ንግግሮች ነበሩ፡፡ በተለይ የሁለቱ ክልሎች ከፍተኛ አመራሮች ፀጥታውን በተመለከተ መነጋገራቸው ይታወቃል፡፡ እናንተም እንደ ዞን የፀጥታ ችግሮችን ለመፍታት ምን እየሠራችሁ እንደሆነ ይግለጹልኝ?

አቶ ተቀባ፡- ምናልባት እንግዲህ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ከዞኑ የተለየ ነው፡፡ ትልቅ የከተማ አስተዳደር ነው ያለው፡፡፡ ይህ ጉዳይ ዞኑን ነው የሚመለከተው፡፡ ዞሮ ዞሮ ተከስተው የነበሩ ችግሮችንና ሕዝቡ ያነሳቸውን ጥያቄዎች ለመፍታት በሁለቱም ክልል መንግሥታት የተጀመሩ ጉዳዮች አሉ፡፡