Skip to main content
x
‹‹በዘረመል ምሕንድስና ላይ የሚነሱ ትችቶች በዕውቀት ላይ የተመሠረቱ ናቸው ለማለት ያስቸግራል››

‹‹በዘረመል ምሕንድስና ላይ የሚነሱ ትችቶች በዕውቀት ላይ የተመሠረቱ ናቸው ለማለት ያስቸግራል››

ዶ/ር ካሳሁን ተስፋዬ፣ የኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር

በቅሎ ቤት ጠብመንጃ ያዥ ንግድ ባንክ አጠገብ የሚገኘውንና የቀድሞውን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሕንፃን የተረከበው አዲሱ መሥሪያ ቤት ከተመሠረተ አንደኛ ዓመቱን አስቆጥሯል፡፡ ውስጣዊ አደረጃጀቱ ለዘመናዊነትና ለዘመናዊ አሠራር ያለውን ተነሳሽነት የጀመረው ጉዞ መገለጫ ይመስላል፡፡ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ያልተለመደ የሥራ ቦታ አደረጃጀት፣ ምቹነትና የሠራተኞችን የሥራ ፍላጎት የሚቀሰቅስ የውስጥ ዲዛይን የገነባው ኢንስቲትዩቱ፣ በአገሪቱ ሳይንሳዊ ምርምሮች ውስጥም የቢሮውን ዓይነት ዘመናዊነት እንደሚያመጣ ይጠበቃል፡፡ ከ90 ያላነሱ ተመራማሪዎች የሚገኙበት አዲሱ የባዮቴክኖሎጂ ኢንስቲዩት፣ በኢትዮጵያ የግብርናና የኢንዱስትሪ ዘርፎች ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ እንደ ናኖ ቴክኖሎጂ ያሉና ሌሎች ወደፊት እያደጉ እንደሚሄዱ የሚታመንባቸውን ቴክሎጂዎች ጥቅም ላይ ለማዋል የሚደረጉ ምርምሮችን ለመምራትና ለማስተባበር፣ በራሱ ላቦራቶሪዎችም ልዩ ልዩ የምርምር ውጤቶችን ለማቅረብ ታስቦ እንደ ተመሠረተ ዋና ዳይሬክተሩ ዶ/ር ካሳሁን ተስፋዬ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በባዮቴክኖሎጂ መስክ አንዱ አካል በመሆን የሚጠቀሰው የዘረመል ምሕንድስና ነው፡፡ በኢትዮጵያ የዘረመል ምሕንድስና ዘርፍ ምርምር የሚደረግበት የጥጥ ምርት ከላቦራቶሪ አልፎ በተከለለና ጥብቅ በሆነ መስክ ሙከራ እየተደረገበት ይገኛል፡፡ ይሁንና ተቃውሞ ሲቀርብበት የቆየ አካሄድ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በእዚህ ነጥብና በሌሎችም የቴክኖሎጂ መስኮች ብርሃኑ ፈቃደ ከዶ/ር ካሳሁን ጋር ቆይታ በማድረግ የሚከተለውን ቃለ ምልልስ አጠናቅሯል፡፡

ሪፖርተር፡- ስለእርስዎ በጥቂቱ ለማወቅ ሲሞከር ‹ሪሰርችጌት› የተባለው የተመራማሪዎች ድረ ገጽ ላይ የሠፈሩ በርካታ የምርምር ሥራዎችዎን ተመልክቻለሁ፡፡

ዶ/ር ካሳሁን፡- ከመጀመርያው ዲግሪዬ ጀምሮ በዋናነት የምርምር ሥራዎቼን የሠራሁት ከዕፅዋት ጋር በተያያዙ የግብርና ሥራዎች ላይ ነው፡፡ በማስትሬት ዲግሪም በአፕላይድ ጄኔቲክስ ላይ በማተኮር በዕፅዋት ላይ እየሠራሁ ሲሆን፣ የዶክትሬት ዲግሪዬን ከቡና ጋር በተያያዘ ቡናን ወደፊት ማሻሻል ስለሚቻልበት የምርምር ሥራ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ በብዛት የምርምር ውጤቶችን ለማውጣት ያስቻለኝም በአብዛኛው ከምሠራው ሥራ ጋር ተጓዳኝነት ስላላቸው ነው፡፡ ሥራዎቼ የሚያጠነጥኑት እንደ ቡና፣ እንደ ዳጉሳ በመሳሰሉት ሰብሎች ላይ ነው፡፡ ቡና የተገኘው በኢትዮጵያ ነው፡፡ ዳጉሳም እንደዚሁ በኢትዮጵያ የተገኘ ነው፡፡ ከጤፍ ጋር የተያያዙ የታተሙ የምርምር ሥራዎችም አሉኝ፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ባለቤት እንደሌላቸው የሚታሰቡ ወይም ‹ኦርፋን ክሮፕስ› የሚባሉ የሳይንስ ማኅበረሰቡ ትኩረት ሰጥቷቸው ምርምር የማያደርግባቸው መስኮች ላይ አተኩራለሁ፡፡ ምክንያቱም እነዚህን ዕፅዋት ከእኛ አገር አኳያ ስናስባቸው በምግብ ራሳችንን ለመቻል ትልቅ ጠቀሜታ እንዳላቸው ስለማምን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ገናና ከሚባሉና አብዛኛው ዓለም አቀፍ የሳይንስ ማኅበረሰብ ትኩረት ከሚያደርግባቸው ይልቅ ወደ ሌሎቹ ብዙም ወዳልታዩት ሰብሎች አደላለሁ፡፡ አንጮቴ ላይ እየሠራሁ ነው፡፡ የኦሮሞ ድንች ላይ ወይም የወላይታ ዶኖ የሚባለው ሰብል ላይ ጥናቶችን አካሂዳለሁ፡፡ በአብዛኛው መነሻቸው ከኢትዮጵያ የሆኑና በማኅረሰብ ባህል የተለመዱት ላይ ትኩረት አደርጋለሁ፡፡ ተማሪዎችንም በዚሁ መስክ በሚያደርጉት ምርምር ላይ እከታተላለሁ፡፡ የምርምር ሥራዎቹ መበራከትም ከዚህ አትኩሮት የመነጨ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከእርስዎም ከሌሎችም የሳይንስ ባለሙያዎች መበራከት አኳያ የሳይንስ ውጤቶች ወደ ታች ወርደው ሕዝቡ ዘንድ ሲሰርፁ አለመታየታቸው የሚያስቆጭ ይመስለኛል፡፡ በእርስዎ ዘንድ እንዲህ ያለው ቁጭት አለ?

ዶ/ር ካሳሁን፡- እውነት ነው እንደ አገር የሳይንስ ማኅበረሰቡን ስናይ በቂ ሥራ ተሠርቷል ለማለት ቢቸግርም፣ የተሠራውም ቢሆን በበቂ መጠን ወደ ማኅበረሰቡ ወርዷል፣ በበቂ ሁኔታ ጥቅም ላይ ውሏል ለማለት ይቸግራል፡፡ ለዚህ ዋና ምክንያት ሊሆን ይችላል ብዬ የማስበው በከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና በተለያዩ ሚኒስቴሮች መካከል ያለው ግንኙነት ደካማ መሆን አንዱ ነው፡፡ ለምሳሌ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በግብርና ዘርፍ በርካታ ምርምሮች ያካሄዳሉ፡፡ ከግብርና ምርምር ተቋማት ባሻገር ግን ከሌሎች እንደ ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር፣ ከደንና አካባቢ ጥበቃ ሚኒስቴር፣ አሊያም ከእንሳስትና ዓሳ ሀብት ሚኒስቴር ጋር ተያይዘው የሚሠሩት ነገር ብዙም አይደለም፡፡ የእነዚህ መሥሪያ ቤቶች መዋቅር እስከ ታች እስከ ቀበሌ ድረስ የወረደ ነው፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ወይም ደግሞ የግብርና ምርምር ተቋማት በተወሰነ ደረጃ ምናልባት እስከ ወረዳ ቢዘረጋ ነው፡፡ የዚህ ቁርኝት ጠንካራ አለመሆን የምርምር ውጤቶች በተፈለገው መጠን ወደ ታች እንዳይወርዱ አድርጓል ብዬ አስባለሁ፡፡ ሌላው ደግሞ ሚኒስቴሮች ብቻም ሳይሆኑ የምርምር ጣቢያዎችና ተቋማት፣ ዩኒቨርሲቲዎችም ሊሆኑ ይችላሉ፣ ከኢንዱስትሪው ጋር ያላቸው ግንኙነት ደካማ መሆኑም የሚካሄዱት ምርምሮችስ በኢንዱስትሪው ውስጥ፣ በሚታየው የምርት ማነቆ ላይ፣ እንዲሁም በግብርናው ዘርፍ ወይም በኢንዱስትሪው ምርታማነት ችግር ላይ ያጠነጥናሉ የሚለውም አንቆ የያዘን ሌላው ችግር ነው፡፡ በአገራችን ያለው የግሉ ዘርፍ ደካማ መሆንም ሌላው ችግር ነው፡፡  ምርምር ለውጥ ያመጣል ብሎ አምኖ የግሉ ዘርፍ የምርምር ውጤቶችን በመቀበል ወደ ምርት የመግባት አቅም ላይ ችግር ያለ ይመስለኛል፡፡ የኢንኩቤሽን ማዕከላት አለመኖርም ለምርምር ሥራው አስቸጋሪ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ በላቦራቶሪ ደረጃ ጥናትና ምርምር የተካሄደባቸው ሥራዎች መደርደሪያ ላይ ይቀራሉ፡፡ ምክንያቱም ጥናቶቹን ወደ ኢንኩቤሽን ማዕከላት በመውሰድ ጥቅም ላይ የማዋል ችግሮች የሚታዩት፣ ማዕከላቱ ቀድሞውንም ስለሌሉ ይመስለኛል፡፡ በተወሰነ ደረጃ ምንም ያህል ከፍተኛ ሥጋት ባለባቸው መስኮች ላይ ኢንቨስት የሚደረገው የቬንቸር ካፒታል አለመኖርም ችግር ያመጣ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም በምርምር ማኅበረሰብ ዘንድ ዕውቀት፣ ቴክኖሎጂና ሌላውም ነገር ይገኛል፡፡ ይህንን ግን ይዞ ለመውጣትና ጥቅም ላይ ለማዋል ካፒታል ይጠይቃል፡፡ ይህ ባለመሆኑም ደፍረው ተግባር ላይ እንዳያውሉ ሲገድባቸው ይታያል፡፡ በመሆኑም የእነዚህ ሁሉ ጥርቅም ውጤት ይመስለኛል የእኛ አገር ችግር፡፡ 

ሪፖርተር፡- እርስዎ ወደሚመሩት ተቋም እንምጣ፡፡ የኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የሚባል ተቋም መመሥረት ለምን አስፈለገ? መሠረታዊ ተልዕኮውስ ምንድነው?

ዶ/ር ካሳሁን፡- ኢንስቲትዩቱ የተቋቋመው የዛሬ ዓመት በሰኔ ወር የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ በሚያዘው መሠረት ነው፡፡ ማቋቋም ያስፈለገበት ዋናው ምክንያት በአሁኑ ወቅት መንግሥት ለሚያካሂዳቸው በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ዕድገት እንዲኖር በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ቴክኖሎጂ መገንባት አለብን፡፡ ስለዚህ መንግሥት የባዮቴክኖሎጂን ብቻም ሳይሆን፣ ሌሎችንም ቴክኖሎጂዎች ለመጠቀም በመወሰኑ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ የተለያዩ ሥራዎች ሲካሄዱ ቆይተዋል፡፡ ኢንስቲትዩቱን ለማቋቋም የሚኒስትሮች ጊዜያዊ ኮሚቴ በማቋቋም፣ በሥሩ ስድስት አባላት ያሉት ግብረ ኃይል በመመሥረት ሲያስጠና ነበር፡፡ ግብረ ኃይሉ ለመጪዎቹ አሥር ዓመታት ለአገሪቱ የሚያገለግል ፍኖተ ካርታ አዘጋጅቷል፡፡ ለምሳሌ ያህል በግብርና ባዮቴክኖሎጂ፣ በኢንዱስትሪያል ባዮቴክኖሎጂ፣ በአካባቢ እንዲሁም በሰው ኃይል ሥልጠና ዘርፍ በመጪው አሥር ዓመት ውስጥ ምን ያስፈልጋል የሚለው በፍኖተ ካርታው ተቀምጧል፡፡ በዚህ ፍኖተ ካርታው ጥናት መሠረት ነው ኢንስቲትዩቱ የተቋቋመው፡፡ የፍኖተ ካርታው ጥናት በዋናነት ያመለከተው ነጥብ በተለያዩ የምርምር ተቋማትና ዩኒቨርሲቲዎች የተለያዩ ጥናቶች ሲደረጉ ቢቆዩም የተበጣጠሱ ናቸው፣ እርስ በርስም አይናበቡም፡፡ አንዱ የሠራውን ሌላው የመድገም ዓይነት ችግሮች ይታዩ ነበር፡፡ ስለዚህ በአገር አቀፍ ደረጃ እንዲህ ያለውን አካሄድ አስተባብሮ የሚመራ ተቋም ያስፈልጋል በመባሉ ይህ ኢንስቲትዩት ተቋቁሟል፡፡ የኢንስቲትዩቱ አንዱ ዓላማም የባዮቴክኖሎጂ ምርምርና ሥርፀትን ማስተባበርና መምራት ነው፡፡ ከዚህ ባሻገርም በዋና ዋና የባዮቴክኖሎጂ ዘርፎች ውስጥም ዕውቀትን መሠረት ያደረገ ጥናትና ምርምር ማካሄድም ይጠበቅበታል፡፡ ኢንስቲትዩቱ ይህንን ሲያከናውን ብቻውን ግን አይደለም፡፡ ከበላዩ በአንድ መስክ የተቋቋመ የኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጂ ምክር ቤት አለ፡፡ ይህንን ምክር ቤት በበላይነት የሚመሩት ጠቅላይ ሚኒስትራችን ናቸው፡፡ በውስጡ ደግሞ የባዮቴክኖሎጂ ዘርፍ የሚመለከታቸው የተለያዩ ሚኒስቴሮች በሚኒስትሮቻቸው ይወከሉበታል፡፡ ምክር ቤቱ የሚያስፈልግበት ምክንያትም ባዮቴክኖሎጂ ዘርፈ ብዙ እንደመሆኑ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በእንስሳት ሀብት፣ በአካባቢና በሌሎችም መስኮች ውስጥ የሚተገበር በመሆኑ፣ በእነዚህና በሌሎች ዘርፎች ውስጥ የሚካሄዱ ምርምሮችን ከማስተባበር አንፃር፣ እነዚህ ሚኒስቴሮች የምክር ቤት አባላት መሆናቸው ጠቃሚ ነው፡፡ ከዚያም ሲያልፍ ደግሞ በአገር ደረጃ ልናተኩርባቸው የሚገቡ ጉዳዮችን ታች ድረስ አውርዶ ለመተግበር እንዲቻል ተቋማቱ የባዮቴክኖሎጂ ምክር ቤት አባላት መሆናቸው የታሰበበት ነው፡፡ ኢንስቲትዩታችን ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ተጠሪ ቢሆንም በተጨማሪነት በምክር ቤቱ በበላይነት ይከታተለዋል፡፡

በአጠቃላይ ከማስተባበርና ከመከታተል ባሻገር ተቋማችን አገራዊ መመርያዎችን የማዘጋጀት፣ በተለያዩ ሥፍራዎች የሚካሄዱ ምርምሮች ተያይዘው እንዲራመዱ ያደርጋል፡፡ ሥልጠናዎችና አቅም ግንባታዎች ላይ ይሠራል፡፡ ከሌሎች በዘርፉ ልምድ ካካበቱ አገሮች ጋራ የተለያዩ ግንኙነቶችን ይመሠርታል፡፡ የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፎችን ይሰጣል፡፡ ስሙ ባዮቴክኖሎጂ ይሁን እንጂ በሥሩ ሁለት ማዕከላት አሉት፡፡ አንደኛው የባዮቴክኖሎጂ ማዕከል ሲሆን እስካሁን ያብራራሁት የሚመለከተው ነው፡፡ ሌላኛው በማደግ ላይ ያሉ ወይም የኢመርጂንግ ቴኮኖሎጂዎች ማዕከል የሚባል ነው፡፡ ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ እንደ አገሩ ነባራዊ ሁኔታ ይለያያል፡፡ ለአንዳንዶች ባዮቴክኖሎጂ ኢመርጂንግ ሲሆን ለሌሎች ግን ላይሆን ይችላል፡፡ ከእኛ አገር ነባራዊ ሁኔታ አኳያ ኢመርጂንግ ብለን የለየናቸው የናኖ ቴክኖሎጂ፣ ከአውቶሜሽንና ከሮቦቲክስ ጋር የተገናኙ ሥራዎች የሚሠሩበት የአርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ፣ የኢቨርስ ኢንጂነሪንግ፣ እንዲሁም ማቴሪያል ሳይንስ የሚባሉ አራት የተለያዩ ዘርፎች ላይ አትኩሮ የሚሠራ ማዕከል ነው፡፡ ሁለቱን አንድ ላይ ማዋቀር ያስፈለገው አንደኛ ተደጋጋፊ በመሆናቸው ነው፡፡ አንደኛው በባዮቴክኖሎጂ ላይ ሲያተኩር ሌላኛው በብዛት በፊዚካል ሳይንስ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ በዕውቀት ደረጃም የሚመጋገቡ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ብንጠቅስ የካንሰር በሽታን ለመከላከል በአደጉ አገሮች እንደሚደረገው ባዮ ሳይንስ መድኃኒቱን ይሠራል፡፡ ናኖ ሳይንስ ደግሞ መድኃኒቱ መዳረስ የሚችልበትን ይሠራል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ መድኃኒቱ ተሠርቶ በአግባቡ መሠራጨት እስካልቻለ ድረስ የሚፈለገውን ውጤት አይሰጥም፡፡ ስለዚህ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው አካሄድም የባዮ ሳይንስና የሥነ ሕይወት ሳይንስን ምርምር ሥራዎች አቀናጅቶ መሄድ ነው፡፡ እኛ ምንም እንኳ ጀማሪም ብንሆንም በኢመርጂንግ ሳይንስ ላይ መሠረት መጣል ይጠበቅብናል፡፡ መሠረቱን ስንጥልም ሁለቱን አያይዘን ለመሄድ ነው ሁለቱን ያጣመርነው፡፡ ይሁንና ዋናው ትኩረት ግን በባዮ ሳይንስ ላይ ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- የአገሪቱ ፍላጎት ምንድን ነው? በባዮ ሳይንስ ምን ማሳካት ትፈልጋለች?

ዶ/ር ካሳሁን፡- በተለያየ የባዮ ሳይንስ ዘርፍ ምን እንደሚያስፈልግ በፍኖተ ካርታውም የተቀመጡ ነገሮች አሉ፡፡ ኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጂን እንደ ምርምርና ቴክኖሎጂ ማጎልበቻ ዘርፍ ስትለይ በዋናነት ታሳቢ የተደረገው የአገሪቱ የተለያይነት ሀብት ነው፡፡ ሜጋ ተለያይነት አላቸው ተብለው ከሚታሰቡ አገሮች አንዷ ኢትዮጵያ ነች፡፡ ባቢሎቭ የተባለው ተመራማሪ ከለያቸው 12 ዕፅዋት ተለያይነት አኳያ ኢትዮጵያ አንዷ ሆና ትገኛለች፡፡ ኢትዮጵያ ከዕፅዋት ተለያይነት አኳያ ከሌሎች አገሮች ይልቅ ንፅፅራዊ የሀብት ብልጫ አላት፡፡ በእንስሳትም ተለያይነት እንዲሁ ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህን ሀብቶች ይበልጥ ወደ ጠቃሚነት ለመቀየር መሣሪያው ባዮቴክኖሎጂ ነው፡፡ እንደስሙ የባዮ ሀብቶችን በቴክኖሎጂ አማካይነት ወደሚፈለገው ጥቅም ማምጣት ነው፡፡ ስለዚህ በዋናነት እዚህ ላይ ያተኩራል፡፡ በተለያዩ ዘርፎች ውስጥ የተለዩ ቴክኖሎጂዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ኢንዱስትሪያል ቴክኖሎጂን እንደ ዘርፍ ካየነው፣ በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያ በዚህ ዘርፍ ተጠቃሚ እንድትሆን በአትኩሮት መሥራት ያለብን፣ ኢንዛይም ቴክኖሎጂ ላይ እንደሆነ በፍኖተ ካርታው ተቀምጧል፡፡ ከዚያም ባለፈ ከማይክሮ ኦርጋኒዝም አኳያ እርሾ ወይም ይስት ላይ አተኩረን ብንሠራ ውጤታማ እንደምንሆን ተቀምጧል፡፡ ይህ የተባለበት ምክንያት ምንድነው በስምጥ ሸለቆ ውስጥ በርካታ ሐይቆች አሉ፡፡ እነዚህ ሐይቆች በሚገኙባቸው ከባቢያዊ ሁኔታ አማካይነት ልዩ ልዩ ማይክሮ ኦርጋኒዝሞችን ለመያዝ ችለዋል፡፡ በአፋር ዝቅተኛው ቦታ ደንከል ዲፕሬሽን ውስጥ የጨው ሐይቆች ይገኛሉ፡፡ በእነዚህ ሐይቆች ውስጥ ደግሞ ልዩ ማይክሮ ኦርጋኒዝሞች አሉ፡፡ ወደ መሀል አገር ስንጠጋ በውስጣቸው በርካታ ማይክሮ ኦርጋኒዝም ያላቸው የተለያዩ ፍልውኃዎችን እናገኛለን፡፡

ስለዚህ ለዳቦ መጋገሪያ ብቻም ሳይሆን ለተለያዩ ተግባራት ከውጭ የምናስገባቸውንና ለማፍላት አሊያም ለማብላላት የምንጠቀምባቸውን እርሾዎች በአገር ውስጥ እንደ ልብ ለማምረት የሚያስችለን ሀብት ስላለ እዚህ ላይ ብናተኩር ውጤታማ እንሆናለን የሚል ሐሳብ አለ፡፡ በኢንዛይም ቴክኖሎጂ አማካይነት ለተለያዩ የኢንዱስትሪ ሥራዎች ይውላሉ፡፡ በአገራችን ከግብርና ወደ አግሮ ኢንዱስትሪ ኢኮኖሚ ለማሻገር እየተሞከረ ስለሆነ፣ ከውጭ የምናስገባቸውን ኬሚካሎች ወይም ኢንዛይሞች የሚተካና ለአገር አቅም የሚሠራ የኢንዛይም ቴክኖሎጂ ማልማት እንችላለን በማለት ትኩረት የሚደረግበት ነው፡፡ ከጤና አኳያም ለክትባት የሚውሉ ቴክኖሎጂዎች ላይ ትኩረት ቢደረግና ከውጭ የሚገቡትን በራሳችን ምርቶች ብንተካ የሚል አቋም አለ፡፡ ኢንዱስትሪዎች ሲስፋፉ የአካባቢ ብክለትም ይኖራል፡፡ ይህንን ለመቋቋምስ እንዴት ነው ቀድመን መዘጋጀት ያለብን የሚል ተልዕኮም አለ፡፡ በግብርና መስክም የማዳቀል ሥራውን የዘረመል መለየት ሥራዎችን በመለየት የመሥራት ትኩረት አለ፡፡ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪውን ለመደገፍ ጥጥ ላይ ትኩረት በማድረግ መሥራት እንደሚያዋጣ ተለይቷል፡፡ ወደፊት ከውጭ የሚገባውን የጥጥ ምርት ቢቲ ኮተን የተባለውን የዘረመል ጥጥ በማምረት፣ በቀጣዮቹ አሥር ዓመታት ውስጥ ለውጥ ለማምጣት የታሰበበት አካሄድ አለ፡፡

ሪፖርተር፡- ቢቲ ኮተን ስለሚባለው የዘረመል ጥጥ ከመነጋገራችን በፊት ግን በተቋሙ አመሠራረት ላይ አንድ ነገር እንመልከት፡፡ መንግሥት ለጥናትና ምርምር፣ ለድጋፍ ሰጪነትም ጭምር በርካታ ኢንስቲትዩቶች አቋቁሟል፡፡ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት፣ የቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት፣ የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት፣ ወዘተ አቋቁሟል፡፡ እርስዎ የሚመሩት ተቋም እንዲሁ ማቋቋም ስለፈለገ ብቻ መንግሥት የመሠረተው ተቋም እንዳልሆነ ከማብራሪያዎ መረዳት ይቻላል፡፡ ይሁንና መንግሥት ይህንን ተቋም አስፋፍቶ ወደተባሉት ውጤቶች ለማድረስና ሥር ሰድዶ እንዲጓዝ ለማድረግ ምን ያህል ፍላጎቱ አለው? የባዮቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዓምና ይቋቋም እንጂ ከአሥር ዓመት በፊት ሊመሠረት ሽር ጉድ ይባል እንደነበር የሚያሳዩ መረጃዎች አሉ፡፡

ዶ/ር ካሳሁን፡- ባዮቴክኖሎጂ ላይ የተለያዩ ጥረቶች ሲደረጉ ነበር፡፡ የእነዚያ ጥረቶች ውጤት ነው፡፡ በሆለታ የሚገኘው የግብርና ምርምር ውስጥ የተመሠረተው የባዮቴክኖሎጂ ማዕከልም የዚህ ጥረት ውጤት ነው፡፡ በተለይ ዩኒቨርሲቲዎች በመጀመርያ በሁለተኛ ዲግሪ ደረጃ በዘርፉ ለማስተማር የተነሳሱበት ምክንያትም የጥረቱ ውጤት ነው፡፡ ባዮቴክኖሎጂ ለረዥም ጊዜ የመንግሥት አጀንዳ ሆኖ ቆይቷል፡፡ አሁን ግን በተቋም ደረጃ በሰፊው እንዲወጣ የተደረገበት ሆነ እንጂ ቀደም ብሎም እንቅስቃሴዎች ሲደረጉ ነበር፡፡ እስከ 12 ዩኒቨርሲቲዎች የባዮቴክ የመጀመርያ ዲግሪ ትምህርት ጀምረዋል፡፡ ሰባት ዩኒቨርሲቲዎች በማስተርስ ደረጃ ማስተማር ጀምረዋል፡፡ የዶክትሬት ዲግሪ ፕሮግራም ለመጀመር የተዘጋጁና የጀመሩ ዩኒቨርሲቲዎችም አሉ፡፡ ይህ ሁሉ ምን ያህል ትኩረት እንደተሰጠው የሚያሳይ ነው፡፡ የኢንስቲትዩቱ ምሥረታን ስንመለከት ቀደም ብሎ በአገር አቀፍ ደረጃ እንዲህ ያለ ተቋም ሊኖር እንደሚገባው ይታሰብ ነበር፡፡ ባዮቴክ ከሌሎች ቴክኖሎጂዎች አኳያ ብዙ ካፒታል የሚጠይቅ ነው፡፡ የመሠረተ ልማት አውታሮች በብዙ የሚያስፈልጉትና ጥልቀት ያለው ዕውቀት የሚፈልግ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የበርካታ ጥናት ዘርፎችን ዕውቀት የሚፈልግ ነው፡፡ ባዮሎጂስት፣ አግሮኖሚስት፣ ባዮኬሚስት፣ የኮምፒዩተር ሳይንስ ባለሙያዎችንና የመሳሰሉትን ባለሙያዎች የዕውቀት ጥርቅም ይፈልጋል፡፡ ስለዚህ እንዲህ በጣም ብዙ መሠረተ ልማት የሚጠይቅ ዘርፍ በየቦታው ማዳረስ አይቻልም፡፡ አገራችን ለዚያ አቅም የላትም፡፡ በማዕከልነት እነዚህን የሚመራና የሚያስተባብር ተቋም ስላስፈለገ ነው ኢንስቲትዩቱ የተመሠረተው፡፡ ላቦራቶሪዎቹም በጣም ውድ ናቸው፡፡ እዚህን በአንድ ጊዜ ሁሉ ቦታ ማቋቋም ስለማይቻል በማዕከል አገልግሎት እየሰጠ ለመምራት ተቋሙ ተዋቅሯል፡፡ ኢንስቲትዩት ያስፈልገናል ተብሎ ሳይሆን፣ የባዮቴክኖሎጂ ዘርፍ እንዲያድግ እንቅፋት የሆኑ ጉዳዮች ተጠንተው፣ ዋና የላቦራቶሪ ሥራዎችን በማዕከል የሚመራ ተቋም ባለመኖሩም ጭምር ነው ይህንን ተቋም ለመመሥረት ያበቃው፡፡  

ሪፖርተር፡- በቢቲ ኮተን ብቻም ሳይሆን በባዮቴክኖሎጂ ዘርፍ በርካታ የሚነሱ ተቋውሞዎች አሉ፡፡ የዘረመል ምሕንድስና ብዙ ሽኩቻ የሚታይበት ዘርፍ ነው፡፡ በእኛ አገር የዘረመል ጥጥ ለማልማት የምርምር ሥራዎች እየተካሄዱ ነው፡፡ ይሁንና ዘረመል ምሕንድስናን በሚመለከት በአካባቢ ተቆርቋሪዎች ብቻም ሳይሆን በባለሙያዎች መካከልም አለመግባባት ይታያል፡፡ ከዚህ አኳያ የእርስዎ ሐሳብ ምንድነው?

ዶ/ር ካሳሁን፡- ባዮቴክኖሎጂ ሰፊ ነው፡፡ የዘረመል ምሕንድስና በጣም ጥቂቱ ክፍል ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ወደ ዘረመል ምሕንድስና የሚኬደው ሌሎቹን የባዮቴኮኖሎጂ ዘዴዎች አሟጠን ተጠቅመን መፍትሔ ማምጣት ሲያቅተን ወደዚህኛው አማራጭ ይኬዳል፡፡ አስገዳጅ ሁኔታ እስካልተፈጠረ ድረስ የሌሎች የባዮቴክኖሎጂ ዘዴዎችን እንከተላለን፡፡ ነገር ግን በአንድ የዕፅዋት ዝርያ ውስጥ የሚፈለገው ልዩ ባህሪይ የማይገኝ ከሆነና በማዳቀል ዘዴም የማናመጣው ከሆነ፣ ወደ ዘረመል ምሕንድስና በመሄድ ያንን ልዩ ባህሪይ ከሌሎች ዕፅዋት ዘር በማምጣት ለመሥራት ይሞከራል፡፡ የዘረመል ምሕንድስና የተለያየ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሳይንስ ነው፡፡ ምንም ዓይነት ግንኙነት ከሌላቸው ዝርያዎች ዘር የሚፈጠርበት፣ ተቀራራቢ ከሆኑና በማንኛውም የማዳቀል ዘዴ የማይመጡትን ዝርያዎች የማምጣት ሒደቶች አሉ፡፡ በባህሪያቸው ወይም ደግሞ በአንድ ዘር ውስጥ የሚመደቡ ነገር ግን ዝርያቸው የሚለያዩ እንዲገናኙ የሚደረግበት አሠራርም አለ፡፡ በዘረመል ምሕንድስና ጥያቄ የሚነሳው ከሌላ ዝርያ የሚመጣውን ባህሪይ በማዋሀድ የሚሠራበት ላይ ነው፡፡ በአንድ ዝርያ ውስጥ የሚገኙት ላይ የሚሠራው የዘረመል ምሕንድስና ሥራ ብዙም ችግር ያስከትላል ተብሎ ስለማይታሰብ ብዙም ጥያቄ አያስነሳም፡፡ የባዮሴፍቲ ሕግም ያስፈለገው በዚህ አግባብ ነው፡፡ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2009 ጀምሮ የባዮሴፍቲ ሕግ ሥራ ላይ አውላለች፡፡ በ2015 ይህንኑ ሕግ አሻሽላ የዘረመል ምሕንድስናና የቴክኖሎጂ ሥራ ለምርምርና ለማስተማር እንዲውል አድርጋለች፡፡ የባዮሴፍቲ ሕግ በአብዛኛው ከሌላ ቦታ የሚመጣውን ዘረመል በምን መልኩ መጠቀም እንደሚገባና ጉዳት እንዳያስከትልም ለመከላከል ነው፡፡ ቴክኖሎጂዎች የራሳቸው ጥሩም መጥፎም ጎኖች አሏቸው፡፡ በትክክል ሥራ ላይ ካልዋሉ አደጋ ማስከተላቸው ስለማይቀር ነው የባዮሴፍቲ ሕግ ያስፈለገው፡፡

ቴክኖሎጂዎች ሲመጡ አብረዋቸው ሕጎች ይወጣሉ፡፡ የጥቅማቸውን ያህል ጉዳት ሊኖራቸው ስለሚችል ነው፡፡ መኪና ጠቃሚ ነገር ነው፡፡ ነገር ግን በአግባቡ እስካላሽከረከርነው ድረስ አደጋ አለው፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይል ጠቃሚ ነው፡፡ በሕጉ መሠረት እስካልተጠቀምንበት ድረስ አደጋ አለው፡፡ እሳትም እንዲሁ ነው፡፡ የጥቅሙን ያህል ሊጎዳ ይችላል፡፡ የባዮቴክኖሎጂ ጠቀሜታ የጎላ የመሆኑን ያህል  በላቦራቶሪም ሆነ በጥቅም ላይ ስናውለው በአግባቡ ካልሆነ በቀር ጉዳት የለውም፡፡ ቴክኖሎጂው በሰው ላይ የሚያደርሰው ጉዳት በሚገባ ተፈትሾ ነው ጥቅም ላይ የሚውለው፡፡ የማይጠቅሙ፣ ጉዳትና አደጋ ሊያደርሱ  እንደሚችሉ ሲታመንባቸው ከላቦራቶሪ እንዳይወጡ የሚደረጉ በርካታ የምርምር ውጤቶች አሉ፡፡ በተለያዩ ደረጃዎች ተገምግመው ነው ጥቅም ላይ የሚውሉት፡፡ በዓለም ደረጃ የዘረመል ምሕንድስና ወይም የባዮቴክኖሎጂ ውጤቶች በምዕራቡ ዓለም ትልቅ ዕውቅና ያላቸው የሳይንስ ማዕከላትና የሳይንቲስቶች ስብስብ ያሏቸው የላቦራቶሪ ማዕከላት፣ ለአሥር ዓመታት ያህል ቴክኖሎጂውን በማጥናት የደረሱበት ድምዳሜ አለ፡፡ ለምሳሌ የዘረመል ዕፅዋቶችን በተመለከተ በማዳቀል ከመጡ ዝርያዎች ብዙም የተለዩ እንዳይደሉ አጥንተዋል፡፡ አውሮፓም፣ አሜሪካም ያሉ አጥኚዎች ይህንን አረጋግጠዋል፡፡ ስለዚህ በርካታ ሥጋቶች ዕውቀት ላይ የተመሠረቱ ናቸው ለማለት ይቸግራል፡፡ ሰዎች በውስጣቸው ካለው ፍርኃት ተነስተው የሚናገሯቸው እንጂ በጥናትና በምርምር ላይ ተመሥርተው እንዲህ ያለ አደጋ ተከስቷል የሚሉበት ግልጽ ጥናት ሲቀርብ አይታይም፡፡ የባዮቴክኖሎጂ ዘዴዎች እያደጉ መጥተዋል፡፡ አሁን ከሌላ ቦታ ዘረመል ከመውሰድ ይልቅ ዘረመልን ሳይለውጡ ባለበት የማስተካከል ቴክኖሎጂ ተፈጥሯል፡፡ ከአንዱ ወደ ሌላው ዘረመልን የማስተላለፍ አሠራር ወደፊት የሚቀርበት አዝማሚያ እየታየ ነው፡፡  እርግጥ ጂን ኢዲሽን ወይም ዘረመል የማስተካከል ዘዴ በአንዳንድ አገሮች እንደ ዘረመል ምሕንድስና ይታይ የሚል ክርክር አለ፡፡  

ሪፖርተር፡- ከኢትዮጵያ የብዝኃ ሕይወት ጥበቃ ሕግ አኳያ የጥጥ ዘረመል የምሕንድስና ሙከራ ላይ የሚነሳ ቅሬታ አለ፡፡ ይኸውም ሕጉ ከተሻሻለ በኋላ የቢቲ ኮተን ሙከራው ተገባዶ ጥቅም ላይ ወደ መዋሉ መቃረቡ ሲሰማ፣ የምርምር ሥራው ሕጉን ቀድሟል፣ ይህ አግባብ አይደለም የሚሉ ቅሬታዎች ተነስተዋል፡፡

ዶ/ር ካሳሁን፡- በተከለለና በዝግ ሥፍራ የዘረመል ምርምር ማካሄድን ሕጉ ይፈቅዳል፡፡ ሕጉ ከፀደቀ በኋላ ነው የግብርና ምርምር የዘረመል ምሕንድስና በጥጥ ላይ የጀመረው፡፡ ስለዚህ እስካሁንም የሚካሄደው ምርምር በዝግ ሥፍራ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የሚያስተች ነገር አለ ብዬ አላምንም፡፡ በዝግ የተጠናው ነገር አዋጭነቱ ከታየ በኋላ ነው ጥቅም ላይ የማዋሉ ጉዳይ የሚነሳው፡፡ ጥቅም ላይ ስለሚውልበት አግባብ ለማውራትና በምን መልኩ ጥቅም ላይ እንደምናውለው ለመወሰን አሁንም ብዙ ጊዜ አለን ብዬ አምናለሁ፡፡ ጥጡ ለምክክር ገና ይመስለኛል፡፡ ጥቅም ላይም መዋል አልጀመረም፡፡ የአንድ ዓመት የቤተ ሙከራ ሥራ ተካሂዶበታል፡፡ ተጨማሪ ሙከራዎች የሚያስፈልጉ ይመስለኛል፡፡ መረጃው በእጃቸው ያለው የግብርና ምርምር ባለሙያዎች ስለሆኑ እነሱ ብዙ ሊያስረዱ ይችላሉ፡፡ ከቢቲ ኮተን ጋር በተገናኘ ማለት የምፈልገው ቢቲ የሚለው ባሲለስ ትራንስጂንሰስ ከሚለው ከአንድ ባክቴሪያ የተወሰደ ስምን ነው፡፡ ይህ ባክቴሪያ ምናልባት በ1900 ዓ.ም. መጀመርያዎቹ ጀምሮ እነሱን በማባዛት ከውስጡ ተባዮችን የሚገድል ኬሚካል በመውሰድ ጥቅም ላይ ሲውል የነበረበት አሠራር ነበር፡፡ የባክቴሪያው አደገኛ ኬሚካል ጥቅም ላይ መዋል የጀመረው ዘመናዊ ግብርና ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ቢሆንም፣ አሁን የተሻሻለው ነገር ቢኖር ይህ ባክቴሪያ ወደ ጥጥ ውስጥ እንዲገባ ተደርጎ ጥጡ በሽታ እንዲቋቋም ያደረገበት አሠራር መፈጠሩ ነው፡፡ ቢቲ ባክቴሪያ በኢትዮጵያ አፈር ውስጥ አለ፡፡ እንዲሁ ከሌላ ቦታ የመጣ ብቻም ሳይሆን በእኛ አፈር ውስጥም የሚገኝ ነው፡፡ ለየት ያለው ነገር ያንን ዘረመል ወደ ጥጥ ማምጣታችን ብቻ ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር የቢቲ ጥጥ በብዙ አገሮች ዘንድ ለረዥም ጊዜ ጥቅም ላይ የዋለ የዘረመል ጥጥ ነው፡፡ ለምሳሌ የህንድ 95 በመቶ አርሶ አደሮች ሲያመርቱት የቆዩት የጥጥ ዝርያ ነው፡፡ ጎረቤታችን ሱዳንም ጥቅም ላይ እያዋለችው የሚገኝ ቴክኖሎጂ ነው፡፡ ዝም ብለን እንቀመጥ ብንል እንኳ ከውጭ የምናስገባቸው ምርቶች በተለይም አልባሳት በዚሁ የተመረቱ በመሆናቸው ጥቅም ላይ እያዋልነው ስለሆነ፣ ከዚህ ይልቅ እኛው አምርተን ኢንዱስትሪዎቻችንን ብንጠቅማቸው የሚሻል ይመስለኛል፡፡

ሪፖርተር፡- የዘረመል ምሕንድስና ውጤት የሆነ የጎመን ዘር ህንድ ውስጥ ሰሞኑን ሲያጨቃጭቅ ሰንብቷል፡፡ ቴክኖሎጂው ጥቅም ላይ እንዲውል የሚያፀድቀው አካል ይሁንታው ሲጠየቅ፣ የግብርና ሚኒስትር ናቸው የዘር መል ቴክኖሎጂ ውጤት የሆነው ጎመን ዘር ጥቅም ላይ እንዳይውል የከለከሉት፡፡ እንዲህ ያሉ ሥጋቶች እዚህ አገር እንዴት ነው የሚስተናገዱት? ግልጽ ውይይቶችስ ይታሰባሉ? በተለይ ተቃውሞ የሚያሰሙ አካላት መድረኩን አግኝተው፣ ሐሳባቸውን አቅርበው የሚደመጡበት ማዕቀፍ አለ?

ዶ/ር ካሳሁን፡- የዘረመል ምሕንድስና ውጤት የሆኑ ዕፅዋቶችን ሥራ ላይ ከማዋል አንፃር ሙሉ በሙሉ የሚደግፍ ሰው ወይም ደግሞ ከዚህ ክርክር ነፃ የሆነ ነገር ማግኘት ይቸግራል፡፡ አንዳንዱ ክርክር ዕውቀትን መሠረት ስለማያደርግ በዚህ አግባብ የሚነሳውን ተቃውሞ የሚደግፍ የኅብረተሰብ ክፍል ሊኖር ይችላል፡፡ ነገር ግን በአገር ደረጃ ያለን የባዮሴፍቲ ሕግ በተወሰነ ደረጃ፣ ደኅንነታቸው የተጠበቁ ውጤቶችን ጥቅም ላይ ለማዋል ሕጉ ጥሩ ማዕቀፍ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ክርክሩ ግን የሚቆም አይደለም፣ ይቀጥላል፡፡ ምክንያቱም ቴክኖሎጂውን የሚፈልገው አካል የመኖሩን ያህል የማይፈልገውም ወገን ስላለ ማለት ነው፡፡ አንዳንዱ ከጀርባው ሌላ ፍላጎት ያለው ቡድን ይኖረዋል፡፡ ለክርክሩ በርካታ መነሻ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በአገር ደረጃ የወጣ ሕግ ስላለ ሕጉን በአግባቡ መተግበር እስከቻልን ድረስ ደኅንነታችን የተጠበቀ ይሆናል ብዬ አስባለሁ፡፡ የጎመን ዘር አሁንም ድረስ በህንድ እያጨቃጨቀ ነው፡፡ ጥቅም ላይ መዋል የለበትም አለበት የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ ነገር ግን የጎመን ዘርን በዘረመል ምሕንድስና አማካይነት በማልማት ጥቅም ላይ የሚያውሉ አገሮችም አሉ፡፡ እያንዳንዱን ጉዳይ በፈርጅ ፈርጁ ማየት ይገባል፡፡ በእያንዳንዱ ነገር ላይ በግልጽ መነጋገር ያስፈልገናል፡፡ ጥቅም አለው የለም ይጎዳል የሚለው አካል በግንባር መነጋገር አለበት፡፡ ቴክኖሎጂዎች ግን ያስፈልጉናል፡፡ ለመጪው ጉዟችን እንደ አገር ብቁ ሆነን ለመራመድ ዕውቀትንና ቴክኖሎጂን ጥቅም ላይ ማዋል ግድ ይለናል፡፡ ዘመኑ የውድድር እንደ መሆኑ ከሌሎች አገሮች ጋር መፎካከር አለብን፡፡ ለዚህ የሚረዱንን ቴክኖሎጂዎች መጠቀም አለብን፡፡ ይሁንና ሁሉንም ቴክኖሎጂ በጥቅል መደፍጠጥ ወይም በጥቅል መቀበል ሳይሆን፣ እያንዳንዱን ነገር በየደርዙ እያየን የሚጎዳንንና የሚጠቅመንን በመለየት መጠቀም አለብን፡፡

ሪፖርተር፡-  ከጥጥ ባሻገር ሌሎች በቴክኖሎጂው እንዲፈጠሩ የሚታሰቡ መስመር ላይ ያሉ ነገሮች አሉ?

ዶ/ር ካሳሁን፡- እስካሁን ከጥጥ ባሻገር በዘረመል ምሕንድስና አማካይነት ጥቅም ላይ እንዲውሉ የተለዩ የሉም፡፡ ነገር ግን ከጥጥ በተጨማሪ በሌሎችም መስኮች መሥራት ይኖርብናል፡፡ ይህንን ለማድረግ ግን አገር አቀፍ ምክክር ያስፈልገናል፡፡ ደኅንነቱ የተረጋገረጠውን ቴክኖሎጂ ወደ ተግባር ለማስገባት የሁሉም ተሳትፎ ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- ኢንስቲትዩቱ በመጪው ዓመት የሚሠራቸው ቀዳሚ ተግባራት ምንድን ናቸው?

ዶ/ር ካሳሁን፡- ልንሠራ የምናስባቸው ዋና ዋና ሥራዎች የተበጣጠሱትን የባዮቴክኖሎጂ ሥራዎች የሚናበቡበትን መንገድ መፍጠር ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር እዚህም እዚያም የተንጠባጠቡትን ላቦራቶሪዎች እንዴት ለተጠቃሚ ክፍት እንደሚደረጉ ለማቀናጀት ሥራ እንሠራለን፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከምርምር አንፃር የራሳችንን የላቦራቶሪ መሠረተ ልማት መገንባት ስላለብን በአሁኑ ወቅት ጥሩ የሰው ኃይል አቅም አጎልብተናል፡፡ ድጋፍ ሰጪዎችን ጨምሮ 109 ሠራተኞች አሉን፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 90 ተመራማሪዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ተመራማሪዎች የእኛ ላቦራቶሪዎች እስኪሟሉ ድረስ በተለያዩ ተቋማት ውስጥ በሚገኙት ላቦራቶሪዎች የምርምር ሥራዎቻቸውን እንዲያካሂዱ ማድረግ ጀምረናል፡፡ ከዚህ ባሻገር በ2008 ዓ.ም. ውጤታማ የምርምር ፕሮጀክቶች ከመሆን አልፈው ወደ ተግባር ለመሻገር ጫፍ የደረሱ አሥር ፕሮጀክቶች ተለይተው በፋይናንስ ለመደገፍ የማጣራት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡ ሌሎችንም ለመደገፍ የማጣራት ሥራዎች እየተካሄዱ ነው፡፡ ከአሥሩ ፕሮጀክቶች መካከል አንደኛው ቢቲ ጥጥ ላይ የሚደረገው ጥናት ነው፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚካሄድ የኢንዛይም ቴክኖሎጂ ጥናትን በገንዘብ እየደገፍን ነው፡፡ በጎንደር ዩኒቨርሲቲም እንደዚሁ የጠጅ አጣጣል፣ እንዲሁም ጠጅ የሚፈላበት ሒደት ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን ለማድረግ በዩኒቨርሲቲው የሚደረገውን ምርምር እያገዝን እንገኛለን፡፡