አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!
አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!

‹‹ኦሊምፒክ ኮሚቴ በአራት ዓመት አንድ ጊዜ ከሚያደርገው ሩጫ ወጥቶ ከአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጋር በሙሉ አቅሙ ሊሠራ ይገባል››

ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በዘርፉ ሙያተኞች መመራት ከጀመረ የውድድር ዓመቱን ግማሽ ዓመት አስቆጥሯል፡፡ ፌዴሬሽኑ ከፊት ለፊቱ ለሚጠብቀው አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ውድድሮች አገሪቱን ወክለው የሚሳተፉ አትሌቶች ዝግጅቶቻቸውን ከአዲስ አበባ ውጭ እንዲያደርጉ ወስኖ እየሠራም ይገኛል፡፡ በዋናነትም አሰላ የሚገኘው የጥሩነሽ ዲባባ ማሠልጠኛ ማዕከል የመጀመርያው ተመራጭ ሆኗል፡፡ ከዚህም ባሻገር ፌዴሬሽኑ የሚስተዋሉበትን የአደረጃጀትና የአሠራር ክፍተቶች አትሌቲክሱ ከሚፈልገው ወቅታዊ ሁኔታ ጋር ለማጣጣም ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑም ይነገራል፡፡ በሌላ በኩልም የዓለም አቀፍ የፀረ አበረታች ንጥረ ነገሮች ኤጀንሲ (ዋዳ) ኢትዮጵያ ችግሩ ከሚስተዋልባቸው አምስት የዓለም አገሮች አንዷ አድርጎ መጥቀሱ ይፋ ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ በአገር ደረጃ የተቋቋመው ብሔራዊ የፀረ አበረታች ንጥረ ነገሮች ኤጀንሲ (ናዶ) በአሁኑ ወቅት ከአንድ መቶ በላይ አትሌቶች የደምና የሽንት ናሙና የዓለም አቀፍ ተቋም ለምርመራ ወደ መረጠው አገር ኳታር የላከ ቢሆንም፣ ከጥራት ጋር በተያያዘ የኳታሩ የምርመራ ማዕከል እንዲታገድ ተደርጓል፡፡ በምትኩ በፈረንሣይ የሚገኘው የምርመራ ማዕከል ተመርጧል፡፡ ወደ ኳታር የተላከው የደምና ሽንት ናሙና በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል? የሚሉትንና በሌሎችም ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ ጋር ደረጀ ጠገናው ቆይታ አድርጓል፡፡  

ሪፖርተር፡- አዲሱ የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ወደ ኃላፊነት ከመጣ ለውጥ አምጥቻለሁ የሚለው ካለ፣ ተቋሙስ በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል?

ኃይሌ፡- ቀደም ሲል ጀምሮ ለእኛም የዘርፉ ባለሙያተኞች ነን ለምንለው ወደ ፌዴሬሽኑ እንድንመጣ ምክንያት የሆኑ በርካታ ነገሮች ነበሩ፡፡ ከነዚህ ውስጥ የተቋሙ አደረጃጀትና አሠራር የውጤት ጉዳይና ሌሎችም ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እስካሁንም ብዙ ነገሮችን ደረጃ በደረጃ እየፈታን እንገኛለን፡፡ ያልተጀመሩ በርካታ ሥራዎች ይጠብቁናል፡፡  በእኛ እምነት ሥራችንን እየሠራን ነው የምንለው፣ ሁሉ ነገር ተጠናቆ ውጤት ማምጣት ስንችል ብቻ ነው፡፡ ይኼ ባልታየበት ከወዲሁ እንዲህና  እንዲያ ማለቱ የሚጠቅም አይመስለኝም፡፡

ሪፖርተር፡- ከውጤት ጋር ተያይዞ ችግር ብላችሁ እስካሁን መሬት ላይ ያገኛችሁት አለ?

ኃይሌ፡- የፌዴሬሽኑ ባለሙያተኞች በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ሄደው የተለያዩ ጥናቶችን ሠርተዋል፡፡ በጥናቱ መሠረትም እምቅ ክህሎት የሚገኝባቸው አካባቢዎች ተለይተው ታውቀዋል፡፡ የመፍትሔ አቅጣጫው ምን መሆን እንዳለበት ሳይቀር ለማስቀመጥ ጥረት አድርገናል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን በአትሌቶች መካከል የጠፋውን ብሔራዊ ስሜት ወደ ነበረበት ለመመለስ መሄድ እስካለብን ለመሄድ ጥረት አድርገናል፣ ይቀጥላል፡፡ እንደሚታወቀው ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በብዙ ነገር ወደ ኋላ ቀርቷል፡፡ በዋናነት ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር አስፈላጊውን ግንኙነት በመፍጠር ማግኘት የሚገባንን ያህል ሳናገኝ ቆይተናል፡፡ አሁን ግን መጠየቅ ያለብንን ሁሉ ለምን ማለት ጀምረናል፡፡ ምክንያቱም ማን ምን እንደሆነ እንተዋወቃለን፡፡ የምንደመጥበት ሁኔታም አለ፡፡ አይኤኤኤፍ በየጊዜው አዳዲስ ሕጎችን ያወጣል፡፡ ለምን የሚል ጥያቄ እያቀረብን ተገቢውን መልስም እያገኘን ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- ሕጎች ሲባል ምን ዓይነቶች እንደሆኑ መጥቀስ ይቻላል?

ኃይሌ፡- ኢትዮጵያ በዶፒንግ ከተጠረጠሩ አምስት አገሮች አንዷ እንደሆነችና ከዚያ  አኳያ የሚወጡ ሕጎች ይጠቀሳሉ፡፡ የዓለም አቀፉ ተቋም የጠየቀውን ምንም እንኳ ባናሟላም በቅድመ ሁኔታ የሚታዩ ችግሮች ሊኖሩ እንደሚገባ ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የፌዴሬሽኑ ሙያተኞች በአገሪቱ በተለያዩ ክልሎች ተንቀሳቅሰው ጥናት ማድረጋቸውም ተነግሯል፡፡ በጥናቱ መሠረት የክህሎት አካባቢዎች ተብለው የተለዩ ካሉ ቢገለጽ?

ኃይሌ፡- የጥናቱ ጠቅላላ ሪፖርት በቅርቡ ለኅብረተሰቡ ይፋ ይደረጋል፡፡ እስከዚያው ግን ፌዴሬሽኑ ብዙ ጊዜ ውጤት የማያመጣባቸው የሜዳ ተግባራት ዝላይ፣ ውርወራና የመሳሰሉት የውድድር ዓይነቶች በጋምቤላና በደቡብ በብዛት ይገኛሉ፡፡ ታዳጊ ወጣቶቹ ቢኖሩም ከአኗኗር ዘይቤያቸው በመነሳት እኛ ወደ ምንፈልገው ሥርዓት ለማምጣት ደግሞ የዚያኑ ያህል ቀላል ሥራ እንዳልሆነ ጭምር ነው ለመረዳት የቻልነው፡፡ በእርግጥ የማነሳሳትና የማግባባት ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡ ሌላው በረዥም ርቀት ትልቅ አቅም እንዳለ በጥናቱ የተደረሰበት ጉጂ ዞን ነው፡፡ እኔን ጨምሮ ብዙዎቻችን ረዥም ርቀት ሲነሳ እስካሁን ድረስ የምናወራው ስለ አሰላ በቆጂ ነው፡፡ አሁን ትልቁ ችግር የሚሆንብን ፌዴሬሽኑ ያለው አቅም ውስን ስለሆነ የፈለገውን ያህል በጀት መድበን መንቀሳቀስ አለመቻላችን ነው፡፡ የፌዴሬሽኑ ትልቁ ገቢ ከአዲዳስ የሚገኘው ገንዘብ ብቻ ነው፡፡ የእኛ እምነት ፌዴሬሽኑ ትልልቅ የስፖርት አካዴሚዎች እንዲኖሩት ነው፡፡ ይህንኑ መነሻ በማድረግ በአሁኑ ወቅት በወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር የሚተዳደረው የአሰላው የታዳጊ ወጣቶች የስፖርት ማዕከል ፌዴሬሽኑ እንዲጠቀምበት ከኃላፊዎቹ ጋር እየተነጋገርን ነው፡፡ በአሁኑ ወቅትም ማዕከሉን ለብሔራዊ ቡድን ዝግጅት እንድንጠቀምበት ተፈቅዶልናል፡፡ ሌላው ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በተሻለ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ጥሩ ገቢ አለው፡፡ ነገር ግን ተቋሙ ትልቅ የሚባል እንቅስቃሴ ሲያደርግ የሚታየው በአራት ዓመት አንድ ጊዜ፣ እሱም ኦሊምፒክ ሲደርስ ነው፡፡ ስለሆነም ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው ለሚቀጥለው የቶኪዮ ኦሊምፒክ ከወዲሁ ከፌዴሬሽኑ ጋር አብሮ እንዲሠራ እንፈልጋለን፡፡ ምክንያቱም አትሌቲክሱ ከሌለ የኦሊምፒክ ተሳትፎ የለም፡፡  

ሪፖርተር፡- የሚሳካላችሁ ይመስላችኋል?

ኃይሌ፡- የሚገርመው ከሚኒስቴሩ እስካሁን ያለው ግብረ መልስ በጣም ጥሩ ነው፡፡ በቅርቡ በኡጋንዳ ካምፓላ ለሚዘጋጀው የዓለም አገር አቋራጭ ውድድር ዝግጅት የአሰላውን አካዴሚ ስንጠይቅ ወዲያው ነው አወንታዊ መልስ ያገኘነው፡፡ በእርግጠኝነት በዚህ መንገድ ተናበን መሥራት ከቻልን ይሳካለናል፡፡ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴውን ስንመለከት በአትሌቶቻችን ተሳትፎ የማይታመን ገንዘብ እንዳለው እናውቃለን፡፡ ገንዘቡን ሕዝባችን ለሚፈልገው ነገር ማዋል ያስፈልጋል፡፡ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በአራት ዓመት አንድ ጊዜ ከሚያደርገው ሩጫ ወጥቶ ከአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጋር በሙሉ አቅሙ ሊሠራ ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከሁለት አሠርታት በፊት የተረከበው የሰንዳፋ አትሌቲክስ መንደር አለ፡፡ ነገር ግን ያ ቦታ ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም?

ኃይሌ፡- እውነት ነው፡፡ ለዚያ እኮ ነው ፌዴሬሽኑ አቅም ያስፈልገዋል የምለው፡፡ በዚህ አጋጣሚ የሰንዳፋ አትሌቲክስ መንደር ሲነሳ አንድ ነገር እያሰብኩ ነው፡፡ ከተለያየ አገር የሚመጡ ማናጀሮች ቦታው ላይ ማዘውተሪያዎችን ሠርተው ታዳጊዎች ቢጠቀሙበት በሚል እያሰብኩ ነው፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አሁን ባለው አቅም ውድድሮችና መሰል ዝግጅቶችን ለማከናወን ካልሆነ እኛ እንደምናስበው በአካዴሚ ደረጃ የሚያስኬድ አቅም የለውም፡፡

ሪፖርተር፡- በውድድር ዓመቱ ከሚደረጉ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ከካሪቢያን አገሮች አንዷ በሆነችው በሐማስ ከምታስተናግደው ሻምፒዮና የኢትዮጵያ ቡድን ራሱን አግሏል?

ኃይሌ፡- ትክክል ነው፣ በዚህ ሻምፒዮና እንሳተፍ ብንል ፌዴሬሽኑ ለአንድ አትሌት ለትራንስፖርት ብቻ አንድ መቶ ዘጠና ሺሕ ብር ማውጣት ይጠበቅበታል፡፡ ለዚያ ነው ለመሰረዝ ውሳኔ ላይ የደረስነው፡፡  ከጥቅሙ ጉዳቱ ስለሚያመዝን ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ፌዴሬሽኑ ችግር ከማውራት ባለፈ ስፖርቱን መሸጥ እየቻለ አይደለም?

ኃይሌ፡- ጥቆማው ጥሩ ነው፡፡ የዚህ ፌዴሬሽን አንዱ ዕቅድ ራሱን በመሸጥ ገቢ ማግኘት ነው፣ እየተንቀሳቀሰም ነው፡፡ በግንዛቤ እጥረት አንዳንድ ችግሮች እንዳሉ እሙን ቢሆንም እኛ ግን እየሞከርን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አዲዳስ የፌዴሬሽኑ ስፖንሰር ነው፡፡ ያንን ተሞክሮ ወደ አገር ውስጥ ማምጣት ችግሩ ምንድነው?

ኃይሌ፡- አዲዳስ የሚፈልገን ዓለም ላይ ባለን ስምና ውጤት ነው፡፡ ተሞክሮ ስለተባለው ያንን ግንዛቤ ለሌሎችም ለማስጨበጥ ጥረት እያደረግን ነው፡፡ አበረታች ነገሮችም እየታዩ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ተቋሙ ለስፖንሰርሽፕ ያለው ግንዛቤ እንዴት ነው?

ኃይሌ፡- በፌዴሬሽኑ የስፖንሰርሽፕ ኮሚቴ ሰብሳቢ እኔና አቶ በላይነህ ክንዴ ነን፡፡ በደንብ እየሄድንበት ነው፡፡ በአጠቃላይ የፌዴሬሽኑን አጠቃላይ እንቅስቃሴ የተቃናና ከውዝግብ የፀዳ ለማድረግ በየቀኑ ማለት በሚያስችል እየተገናኘንና እየሠራን ነው፡፡ ምን ወሰናችሁ? ምን አመጣችሁ? ለሚለው ወደፊት ውጤቱ የሚመልሰው ነው የሚሆነው፡፡   

ሪፖርተር፡- የቀድሞው አመራር ያዘጋጀው መሠረታዊ የሥራ ሒደት ለውጥ ጥናቱን አሁን ያለው አመራር እንደማያምንበት እየተነገረ ይገኛል፡፡ ችግሩ ምንድነው?

ኃይሌ፡- የፌዴሬሽን አደረጃጀት መሆን ካለበት አገር አቀፍ፣ አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ አደረጃጀቶችን መነሻ እንዲያደርግ ነው፡፡ ምክንያቱም የአትሌቲክስ ባለድርሻዎች ብዙ ናቸው፡፡ ከዚህ አኳያ እያንዳንዱ ምን ይፈልጋል? የሚለው መልስ ማግኘት ከቻለ ስፖርቱ ጤናማ አካሄድ እየሄደ ነው ብለን መውሰድ እንችላለን፡፡ በእኛ አትሌቲክስ ትልቁና አሁንም ያልተመለሰ የዓመታት ጥያቄ የአገሪቱ ክለቦች ከአትሌቶቻቸው እንዴት ነው ተጠቃሚ መሆን የሚችሉት? የሚለው ነው፡፡ የተባለው ጥናት ለዚህ መፍትሔ አላስቀመጠም፡፡ እርግጥ ነው ፌዴሬሽኑ ከሚችለው አቅም በላይ የሰው ኃይል አሸክሞታል፡፡ ቀጣዩስ ለሚለው ጥናቱ እንደገና የሚከለስበት ሁኔታ እየታየ ነው፡፡ እንደ ሥራ አስፈጻሚ በግምገማችን ጥናቱ የሚያሠራ ሆኖ ነው ያገኘነው፡፡

ሪፖርተር፡- ጥናቱ ያመጣው የሰው ኃይል እንዳለ ሆኖ ከሰሞኑ ፌዴሬሽኑ ከ50 የማያንሱ የብሔራዊ ቡድን አሠልጣኞችና ተያያዥነት ያላቸው ሙያተኞች ቅጥር ፈጽሟል፡፡ አቅምን ያገናዘበ ነው ማለት ይቻላል?

ኃይሌ፡- በእኛ እምነት በሙያተኞች ረገድ ቅጥሩ አቅምን ያገናዘበ ነው ብለን ነው የምንወስደው፡፡ ምክንያቱም የአገሪቱ አትሌቲክስ ትልቁ ችግር በባለሙያ መመራት አለመቻሉ እንደሆነ እናምናለን፡፡

ሪፖርተር፡- ከአዲዳስ ኩባንያ ጋር ያለው የስፖንሰርሽፕ ስምምነት ፌዴሬሽኑን አይመጥንም፣ በጣም ያሳንሳል የሚል ተቃውሞ ሲሰሙ ነበር፡፡ በዚያ ረገድ አሁን የተለወጠ ነገር አለ?

ኃይሌ፡- የሚገርመው የቀድሞ አመራር ስምምነቱን ያደረገው ለስምንት ዓመት ነው፡፡ ስለዚህ ጥያቄውን እናንሳ ብንል ጊዜ ገደቡን መጠበቅ ይኖርብናል ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በትክክል ገቢው ስንት ነው?

ኃይሌ፡- ለአንድ ዓመት 1.5 ሚሊዮን ዶላር ይደርሳል፡፡ ቦነሶችን ጨምሮ በአጠቃላይ በአገራችን ገንዘቡ ከ30 ሚሊዮን ብር የማያንስ እናገኛለን፡፡

ሪፖርተር፡- ከአበረታች ንጥረ ነገሮች ጋር በተገናኘ ዓለም አቀፉ ተቋም ዋዳ አዳዲስ መረጃዎችን ይፋ እያደረገ ነው፡፡ ኢትዮጵያ አሁንም ቀይ መብራት ላይ እንዳለች መረጃዎች እየወጡ ነው፣ ምን የታሰበ ነገር አለ?

ኃይሌ፡- ዋዳ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ብሔራዊ የፀረ አበረታች ንጥረ ነገሮች ኤጀንሲ እንድናቋቁም ጠይቆን አቋቁመናል፡፡ ይሁንና አሁንም ውሳኔያችሁ ግልጽ አይደለም የሚል ቅሬታ እንዳለው እያሳሰበን ነው፡፡ እኛ ደግሞ ይህን በሚመለከት የኢትዮጵያ ሕግ ቀድሞውንም ጠንካራ ነው እያልን ነው፡፡ የሚገርመው ዋዳ ኢትዮጵያ እንደ ሩሲያ ሁሉ አትሌቶቿን እየተከላከለች ቁጥጥሩን ችላ ብላለች የሚል ጥርጣሬ አለው፡፡ ውሸት መሆኑንና በአሁኑ ወቅትም አምስት አትሌቶች ማዕቀብ ላይ መሆናቸውን በመግለጽ እየተከራከርን ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- ዋዳ ለኢትዮጵያ በሰጠው መመርያ መሠረት በውድድር ዓመቱ እስከ 200 ለሚደርሱ አትሌቶች ምርመራ እንድታደርጉ ነው፡፡ እንዴት እየሄደ ነው?

ኃይሌ፡- ትክክል ነው፡፡ ለዚህ ተብሎ ከፌዴሬሽኑም ሆነ ከመንግሥት ነፃ የሆነ ብሔራዊ ኤጀንሲ ተቋቁሟል፡፡ በእሱ በኩል ምርመራው እየተከናወነ ነው፡፡ ወጪውም የሚሸፈነው በኢትዮጵያ ነው፡፡ ለአንድ አትሌት እስከ 500 ዶላር ይጠይቃል፡፡

ሪፖርተር፡- እስካሁን ሲደረግ የቆየው ምርመራ ኳታር ውስጥ ነበር፡፡ ኢትዮጵያም ወደ ኳታር የበርካታ አትሌቶችን የደምና የሽንት ናሙና ልካለች፡፡ በቅርቡ ግን የኳታሩ የምርመራ ማዕከል መታገዱ ታውቋል፡፡ ወደ ኳታር የተላከው የኢትዮጵያውያን አትሌቶች የምርመራ ውጤት በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል?

ኃይሌ፡- የሚገርመው የኳታሩ የምርመራ ማዕከል ዕገዳ ከተደረገበት ከሦስት ወር በላይ አስቆጥሯል፡፡ ኢትዮጵያም እያስመረመረች ያለው ፈረንሣይ በሚገኘው ማዕከል ነው፡፡ ዋጋውም በጣም ጨምሯል፡፡ ይህ ሳንወድ በግድ የምናደርገው ጉዳይ ነው፡፡ ምክንያቱም ዶፒንግ መከላከል ከማንም በላይ ጥቅሙ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን አትሌቶች ነው፡፡ ይፈቀድ ቢባል ከሌሎች አገሮች ዕድገትና አቅም አኳያ መቋቋም የማንችለው እኛ ነን፡፡ ኳታር ስለሚገኘው የምርመራ ውጤት አብሮ ከመታገዱ ውጭ ሌላ አማራጭ እስካሁን የለም፡፡ ዋዳ እንደገና የሦስት ወር ጊዜ ተጨማሪ ማስጠንቀቂያ እንዲሰጠን ምክንያት የሆነው ኳታር ላይ በታገደው ናሙና መነሻ ነው፡፡ ከመቶ በላይ አትሌቶች ናሙና ነው ወደ ኳታር የተላከው፡፡