Skip to main content
x
‹‹ወላጆች ልጆቻቸው በርትተው እንዲያጠኑ ከመደገፍ በስተቀር ሰርቀው የሚያመጡትን ውጤት ማውገዝ አለባቸው››

‹‹ወላጆች ልጆቻቸው በርትተው እንዲያጠኑ ከመደገፍ በስተቀር ሰርቀው የሚያመጡትን ውጤት ማውገዝ አለባቸው››

አቶ አርዓያ ገብረ እግዚአብሔር፣ የአገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር

የዘንድሮ የአጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ማጠናቀቂያ ፈተና ከግንቦት 23 ቀን እስከ ግንቦት 25 ቀን፣ እንዲሁም የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ከግንቦት 28 ቀን እስከ ሰኔ 1 ቀን 2009 ዓ.ም. በአገር አቀፍ ደረጃ ወጥነት ባለው መመርያና የሥራ ፕሮግራም ይካሄዳል፡፡ በመላ አገሪቱ በሚካሄዱ የብሔራዊና የክልል ፈተናዎች ከ2.8 በላይ ተፈታኞች ሲቀመጡ፣ ለፈተና ዝግጅትና ማስፈጸሚያ 250 ሚሊዮን ብር በጀት ተመድቦ ነው ሥራው የተጀመረው፡፡ በፈተና ጣቢያ ኃላፊነት፣ ተቆጣጣሪነትና ኃላፊነት 52 ሺሕ መምህራን ይሳተፋሉ፡፡ ፈተና በመመርያና በፕሮግራም አማካይነት መካሄዱ የፈተናዎቹን አሰጣጥ አስተማማኝ በማድረግ፣ በተፈታኞች ውጤት ላይ የተመሠረተ ቀጣይ ትምህርታዊ የጥናትና ምርምር ሥራ በማካሄድ ተገቢ የማሻሻያ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል ተብሏል፡፡ በፈተና አዘገጃጀትና አሰጣጥ፣ አሳሳቢ በሆነው ኩረጃ፣ እንዲሁም በተዛማጅ ጉዳዮች ላይ ታደሰ ገብረማርያም፣ ከአገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ አርዓያ ገብረ እግዚአብሔር ጋር ያደረገው አጭር ቃለ ምልልስ እንዲህ ተጠናቅሯል፡፡

ሪፖርተር፡- ፈተና ሲደርስ የኩረጃ አሳሳቢነት ከፍተኛ ደረጃ ላይ መገኘቱ ይሰማል፡፡ በዚህ ችግር ላይ ምን ይላሉ?

አቶ አርዓያ፡- ኩረጃ በብሔራዊ ፈተና ላይ ብቻ ሳይሆን ከሥር ጀምሮ ካልጠፋ ፈተና ባለ ቁጥር አለ፡፡ ይህም ሲባል ኩረጃ መኖር አለበት በማለት ማድነቄ አይደለም፡፡ በየደረጃው የሚሰጡ ፈተናዎች ከካሪኩለሙ ጋር አያይዞ በቀጣይ ወደ ትምህርትና ሥልጠና የሚሄዱ ተማሪዎች እነማን ናቸው ተብሎ ለመለየት የሚያስችሉ ወይም የመለየት ሥራ ናቸው፡፡ የአንደኛ ደረጃ ትምህርትን ስምንተኛ ክፍል፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርትን አሥረኛ ክፍል አጠናቅቀዋል ብለን ‘ሠርቲፋይድ’ ለማድረግ ነው፡፡ ስለዚህ በተቻለ መጠን በትምህርት ቤትም ሆነ በሌላ አካባቢ ኩረጃ እንዳይኖር ሰፋ ያለ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ በመካሄድ ላይ ነው፡፡ ኩረጃ የዝግጅት ማነስ ይመስለኛል፡፡ ወይም ፍርኃት ነው፡፡ በኩረጃ የተገኘ ውጤት የትም አያደርስም፡፡ ኩረጃን በመጠቀም ወደ ዩኒቨርሲቲ የገባ ተማሪ በሳምንቱ ሻንጣውን ይዞ ወደ ቤቱ ሲመለስ እየታየ ነው፡፡ አሥረኛን አታሎ መሰናዶ ሊገባ ይችላል፡፡ ግን ይወጣል፡፡ ወደ ዩኒቨርሲቲም አልፎ ከሆነ ተስፋ የለውም፡፡ የዩኒቨርሲቲዎች ቁጥር ጨምሯል፡፡ ከዚህ አኳያ ሰፊ ዕድል አለ፡፡ ነገር ግን አንድ ተማሪ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት በቂ የሆነ ቅርስ (ዳራ) ሊኖረው ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- ኩረጃን ሊያስቀር የሚችለው ማን ነው?

አቶ አርዓያ፡- ኩረጃን ማስቀረት የሚችለው አንደኛ ተማሪው፣ ሁለተኛ መምህሩ (ፈታኙ) እና ሱፐርቫይዘሩ ናቸው፡፡ ከዚህ የበለጠ ደግሞ የአካባቢው ማኅበረሰብና ወላጆች ናቸው፡፡ በተለይ ወላጆች ልጆቻቸው በርትተው እንዲያጠኑ ከመደገፍ በስተቀር ሰርቀው የሚያመጡትን ውጤት ማውገዝ አለባቸው፡፡ ይህ ሁሉ ቢሆንም መስረቅ እፈልጋለሁ ብሎ የተዘጋጀን ሰው ለመቆጣጠር በጣም ያስቸግራል፡፡  

ሪፖርተር፡- ፈተና ሲኮርጅ በተገኘ ተማሪና ኩረጃው መፈጸሙን እየተመለከተ እንዳላየ ባሳለፈው ፈታኝ ላይ ምን ዓይነት ዕርምጃ ነው የሚወሰደው?

አቶ አርዓያ፡- ለዚህ የሚሆን ደንብና መመርያ ወጥቷል፡፡ በተጨማሪም የአገር አቀፍ ፈተናዎች አሰጣጥ ማኑዋል ተዘጋጅቷል፡፡ በፈተና አሰጣጡ ላይ በፈታኝነት፣ በሱፐርቫይዘርነት፣ በፈተና ጣቢያ ኃላፊነት፣ በክላስተር ማዕከል አስተባባሪነትና በመልስ ወረቀት የማደራጀት ሥራ ላይ በርካታ የትምህርት ባለሙያዎች ይሳተፋሉ፡፡ ማኑዋሉ እያንዳንዱ የትምህርት ባለሙያ በየተመደበበት የሥራ መስክ ያለበትን ኃላፊነትና ተግባር በዝርዝር አስቀምጧል፡፡ ተፈታኙ ወይም ተማሪው ምን ስህተት ሲፈጽም ነው የሚቀጣው የሚለው ማኑዋል ላይ አሉ፡፡

ከዚህም በላይ ፈተናውን በተመለከተ በፕላዝማና ፊት ለፊት ማብራሪያ ይሰጣል፡፡ ይህንን ሁሉ አልፎ ሲኮርጅ የተገኘ ተማሪ በማኑዋሉ መሠረት ፈተናው ሙሉ ለሙሉ ይሰረዝበታል፡፡ ለምሳሌ አንዳንድ ልጆች ሞባይል ይዘው ይገባሉ፡፡ ይዘውም የገቡት ሁለተኛው ፈተናቸው ላይ ሊሆን ይችላል፡፡ ሞባይል ይዞ የገባው ተማሪ በተያዘበት ወቅት የተፈተናቸው ፈተናዎች በሙሉ ወዲያውኑ ይሰረዛሉ፡፡ ከዚህ አኳያ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃ፣ ሞባይል፣ ወዘተ ይዞ መግባት አይፈቀድም፡፡ እርሳስ፣ ላጲስና መቅረጫ ግን ይዞ ሊገባ ይችላል፡፡ ፈታኞችን በተመለከተ ግን በዲሲፕሊንና በሕግ ይጠየቃሉ፡፡ ሊከሰሱም ይችላሉ፡፡ ምክንያቱም ማጭበርበርና ወንጀል ነው የፈጸሙት፡፡

ሪፖርተር፡- አንዳንድ ክልሎችና ትምህርት ቤቶች ለስማቸው ዝና ሲሉ ተፈታኞቻቸው ኮርጀውም ቢሆን እንዲያልፉ ጥረት እንደሚያደርጉ ይሰማል፡፡ ይህ በእናንተ ዘንድ ይታወቃል? በዚህ ላይ ያለዎት አስተያየት ምንድነው?

አቶ አርዓያ፡- አሉ ይባላል፡፡ እኔም እሰማለሁ፡፡ አንዳንዴ ግን ውሸት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ተደራጅተው ገንዘብ በማዋጣት ፈታኞችን አግባብተውና ጉቦ ሰጥተው ውጤት ሊያስቀይሩ የሚሞክረ አካባቢዎች እንዳሉ በወሬ እንሰማለን፡፡ በተጨባጭ ግን አላገኘንም፡፡ ይህንን ነገር ለመከላከል እንዲቻል ከመምህራን፣ ከተማሪዎችና ከመምህራን ማኅበር ጋር አብረን ልንሠራ እየሞከርን ነው፡፡ ስለዚህ ጥርጣሬው ተጨባጭ እየሆነ ከመጣ የማስተማሪያ ዕርምጃ ልንወስድ እንችላለን፡፡ ዕርምጃውን ከመውሰድም ወደ ኋላ አንልም፡፡

ሪፖርተር፡- የፈተና ወረቀቶች ወደ ፈተና ጣቢያዎች ወይም ወደ ክልሎች እንዴት ነው የሚሠራጩት?

አቶ አርዓያ፡- እስካለፈው ዓመት ድረስ የፈተና ጥያቄዎች፣ የመልስ መስጫ ወረቀቶችና ሌሎች ሎጂስቲኮችን በፈተና ጣቢያዎች የሚያሠራጩት የኤጀንሲው ሠራተኞች ነበሩ፡፡ በዚህ ሁኔታ የተከናወነውን ሥርጭት የፈተና ጣቢያዎች ኃላፊዎች መረከባቸውን ካረጋገጥን በኋላ እንመለሳለን፡፡ ዘንድሮ ግን ይህ ዓይነቱን አካሄድ መከተል ትተን፣ በፈተና አሰጣጥ ላይ የሚሳተፉ የትምህርት ባለሙያዎች ኤጀንሲው ድረስ እየመጡ እንዲረከቡና እንዲወስዱ አድርገናል፡፡ ከዚያም የፈተናው ጥያቄና የመልስ መስጫው ወረቀት በፖሊስ አካባቢ በጥበቃ ሥር እንዲቆይ ይደረጋል፡፡

ሪፖርተር፡- የአጠባበቁ ሁኔታ ምን ይመስላል?

አቶ አርዓያ፡- አይ! ይኼ የራሱ አሠራር አለው፡፡ አሠራሩን በሚዲያ መግለጽ ደግሞ ትንሽ ይከብዳል፡፡  

ሪፖርተር፡- በሥርጭት ወቅት የፈተና ጥያቄዎች ለስርቆት አይጋለጡም?

አቶ አርዓያ፡- የፈተና ጥያቄዎቹ ደኅንነት በሚገባ የተጠበቀ ነው፡፡ በትምህርት ባለሙያዎች ከመያዛቸው ባሻገር፣ በፖሊሶችና በፀጥታ ኃይሎች በቂና አስተማማኝ የሆነ ጥበቃና ከለላ ይደረግላቸዋል፡፡  

ሪፖርተር፡- ባለፈው ዓመት ለተፈጸመው የፈተና ስርቆት ተጠያቂው አካል ማን ነው? ትምህርት ሚኒስቴር ወይስ ኤጀንሲው?

አቶ አርዓያ፡- በበኩሌ ማንንም አልወቅስም፡፡ ለመውቀስ እኮ አንድ መነሻ ነገር ያስፈልጋል፡፡  

ሪፖርተር፡- ፈተናው ተሰርቋል እኮ? ከዚህ የበለጠ ምን መነሻ ያስፈልጋል?

አቶ አርዓያ፡- አዎ ተሰርቋል፡፡ አልተሰረቀም እንዳልልህ እኔም፣ አንተም እኩል በፌስቡክ ዓይተነዋል፡፡ ስለዚህ ተሰርቋል፡፡ መንግሥትም ይህንን ጉዳይ የሚመረምርና የሚያጣራ ቡድን አቋቁሞ የምርመራውና የማጣራቱ ሥራ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ በዚህም መሠረት ለስርቆቱ መከሰት ተጠያቂ የሚሆነው አካል ወይም ሰው ይለያል፡፡ በበኩሌ ግን መወቀስ ያለበት የፈተና ጥያቄውን በፌስቡክ እንዲለቀቅ ያደረገው ሰው ነው፡፡ ምክንያቱም በአገሪቱ ላይ ትልቅ ጠባሳ ከመጣሉም ባሻገር፣ አገሪቱ ፈተና ከተሰረቀባቸው አገሮች ተርታ እንድትሰለፍ አድርጓታል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ወላጆችና ተማሪዎች ለጉዳት መዳረጋቸውንም አላገናዘበም፡፡ በተለይ ከገጠር የመጣ ተማሪ ፈተናውን ቶሎ ጨርሶ ወደ ቤተሰቦቹ መመለስ ነው የሚፈልገው፡፡

ጥያቄው በመሠረቁና በዚህም የተነሳ ጊዜው በመጓተቱ ምክንያት ስንቅና ቀለብ በድጋሚ ቆርጦ እንደገና ከተማ እንዲቀመጥ ነው ያደረገው፡፡ እኛ ግን በተጠባባቂነት የተያዘ ፈተና ስለነበረን ሌት ተቀን ሠርተን በድጋሚ እንዲዘጋጅ አድርገናል፡፡ የትምህርት ሥርዓቱም አልተስተጓጎለም፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ሥራ በሦስትና በአራት ወራት ውስጥ ነበር ሠርተን ማስረከብ የሚጠበቅብን፡፡ ነገር ግን በነበረን ቁጭትና እልህ ተረባርበን በተጠቀሱት ቀናት ውስጥ ለማቅረብ ችለናል፡፡ ይህም ከፍተኛ የሆነ መጨናነቅ ቢያስከትልብንም ችለነው በአሸናፊነት ተወጥተነዋል፡፡  

ሪፖርተር፡- ፈተናው በመሰረቁ ኅብረተሰቡ አዝኗል፡፡ ማዘን ብቻም ሳይሆን በውል ተለይቶ ለምንድነው ዕርምጃ የማይወሰድ በማለት ጥያቄ አንስቷል፡፡

አቶ አርዓያ፡- ይህ ጥያቄ ትክክል ነው፡፡ እኔም አምንበታለሁ፡፡ ነገና ከነገ ወዲያ ይህ ነገር ዕውን ሊሆን የሚችል ይመስለኛል፡፡ ለማንኛውም ግን ታሪካችንን በየጊዜው እያበላሸን መሄድ የለብንም፡፡

ሪፖርተር፡- አሁንስ ላለመሰረቁ ምን ዋስትና አለ?

አቶ አርዓያ፡- አንደኛ ይህንን ስህተት የፈጸሙ ሰዎች ድጋሚ ስህተት ይፈጽማሉ ብዬ አላስብም፡፡ ህሊና ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ሁለተኛ ደግሞ እንዲህ ዓይነቱ እኩይ ተግባር በድጋሚ እንዳይከሰት፣ በየደረጃው ጉዳዩ የሚመለከታቸው ኃላፊዎችና ሠራተኞች ከኤጀንሲው ጋር በቅንጅትና በጋራ እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡ ይህን ያህል ጥበቃና ጥንቃቄ ቢደረግም አንዳንድ ቦታ ላይ የሚያሾልክ ሰው ካለ ችግሩ መፈጠሩ ስለማይቀር፣ ይህ እንዳይሆን ክትትል እያደረግን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በመካሄድ ላይ የነበረው ምርመራ ምን ደረጃ ላይ ነው ያለው?

አቶ አርዓያ፡- አላውቅም፡፡ አንዱ ተመርማሪ እኔ ነኝ፡፡  

ሪፖርተር፡- በመላ አገሪቱ ለሚገኙ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ትምህርት በፕላዝማ እንዲሰጥ ቢደረግም ከፊሉ ትምህርት ቤቶች ተጠቃሚ ናቸው፡፡ ከፊሎቹ ደግሞ አይደሉም፡፡ ይህ ዓይነቱ ሁኔታ በትምህርት ጥራትና በተፈታኞች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አያሳድርም?

አቶ አርዓያ፡- ሁሉም ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ፕላዝማ እንዲኖራቸው ነው የማፈለገው፡፡ አንዳንድ ቦታ ላይ ግን ክፍተት ሊኖር ይችላል፡፡ ይህም በትምህርት አሰጣጡ ላይ ልዩነት መፍጠሩ አይቀሬ ነው፡፡ ፕላዝማው ቀርቶ መምህሩ ብቻ አስተምሮአቸው እኮ ልዩነት ሊፈጠር ይችላል፡፡ ከዚህ ሁሉ ይልቅ ጥሩ እየሆነ የመጣው አንድ ለአምስት የሚባለው አደረጃጀትት ነው፡፡ በተረፈ ልዩነቱ በፕላዝማ ስለተማረና ፕላዝማ ስለሌለው ብቻ ሳይሆን ግብዓትም፣ መጻሕፍትም፣ ሌሎች፣ ሌሎች ክፍተቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ እኛ ግን መሠረት አድርገን የምንሠራው በካሪኩለም ነው፡፡ በመንግሥትና በግል ትምህርት ቤቶች ልዩነት አለ፡፡ ይህን ልዩነት ሊጠፋ አይችልም፡፡ ወይም ደግሞ ምንጊዜም ቢሆን ሊጠፋ የሚችል አይመስለኝም፡፡

ሪፖርተር፡- ለታዳጊ ክልሎችና ለሴቶች በተለየ አሠራር በኮታ ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚገቡበት አካሄድ እንዳለ ይታወቃል፡፡ በዚህ አሠራር ዕድሉን ያገኙ ተማሪዎች በሚገቡባቸው ተቋማት የሚሰጡዋቸውን ትምህርቶች ለመቀበል አያዳግታቸውም ወይ? ይችሉታል ወይ?

አቶ አርዓያ፡- እየቻሉት ነው፡፡ የዚያን ያህል የመረረ ነገር የለም፡፡ ተስፋ የማደርገው ደግሞ ተጨማሪ የመማሪያ ጊዜ እየተሰጣቸው ውጤት ይዘው የሚወጡ ልጆች አሉ፡፡ አንድ የፈተና ውጤት ተፈታኙ አሁን ያለበትን ደረጃ የሚገልጽ እንጂ፣ የበለጠ ይሠራል ወይም አይሠራም የሚል የመጨረሻ መገለጫ አይደለም፡፡ ወይም ተማሪውን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚወስን አይደለም፡፡ ሰዎች ራሳቸውን ቶሎ ቀይረው የሚያጠኑና የሚማሩ ከሆነ ምንም ነገር መያዝ የሚያቅታቸው አይመስለኝም፡፡  

ሪፖርተር፡- ለኅብረተሰቡ የሚያስተላልፉት መልዕክት አለ?

አቶ አርዓያ፡- ኅብረተሰቡ ለተፈታኞች አግባብ ያለው ድጋፍ ቢሰጣቸው ጥሩ ነው፡፡ ይህም ማለት የፈተና መግቢያ (አድሚሽን) ካርድ የያዘና የፈተናው ሰዓት የደረሰበት ተፈታኝ ካለ፣ የታክሲ ወረፋ ሳይጠብቅ በቅድሚያ እንዲሳፈር በማድረግ ረገድ ኅብረተሰቡ ሊተባበር ይገባል፡፡ ምክንያቱም በትራንስፖርት እጥረት ሳቢያ የፈተናው ጊዜ ሊያልፍበት ይችላል፡፡ የፈተናው ዕለት የልጆቹ የአሥርና የ12 ዓመት የመጨረሻ ልደታቸው ስለሆነ፣ ልንደግፋቸው ይገባል፡፡ ተፈታኞች ከኩረጃ ነፃ ሆነው ተረጋግተውና ጠንክረው እንዲሠሩ ያስፈልጋል፡፡