Skip to main content
x
‹‹የሕገ ሕክምና ጉባኤ ማቋቋም ያስፈልጋል››

‹‹የሕገ ሕክምና ጉባኤ ማቋቋም ያስፈልጋል››

ዶ/ር ወንድወሰን አሰፋ፣ የኢትዮጵያ የግሉ ዘርፍ ሐኪሞች ሕክምና ማኅበር ፕሬዚዳንት

በግሉ የጤና ዘርፍና በመንግሥት መካከል በልዩ ልዩ የሥራ አተገባበሮች ዙሪያ ለአንድ ዓመት የዘለቀ ድርድር ሲካሄድ ቆይቷል፡፡ በዚህ ድርድር ላይ የግሉ ዘርፍ በመንግሥት በኩል ሊሻሻሉና ሊስተካከሉ ይገባል ያላቸውን ጉዳዮች ያነሳ ሲሆን፣ መንግሥት ደግሞ የግሉ ዘርፍ ሊፈጽማቸው ይገባል የሚላቸውን አሠራሮች ጠቁሟል፡፡ በእነዚህም ጉዳዮችና አፈጻጸሞች ላይ ውይይት ከተካሄደበት በኋላ የጋራ ስምምነት ተደርጎበታል፡፡ ዶ/ር ወንድወሰን አሰፋ የኢትዮጵያ የግሉ ዘርፍ ሐኪሞች ሕክምና ማኅበር ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ የድርድሩን ጭብጥና የተደረሰበትን ስምምነት በተመለከተ ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ድርድሩ በምን መልኩ ተካሄደ? በድርድሩስ የግሉ ጤና ዘርፍ ያነሳቸው ጉዮች ምንድን ናቸው?

ዶ/ር ወንድወሰን፡- ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር የተደራደርነውና የተወያየነው ብቻችንን ሳይሆን ከሌሎች የጤና ባለሙያዎች ማኅበራት ጋር ተቀናጅተን ነው፡፡ በድርድሩም ወቅት የግሉ ጤና ዘርፍ መንግሥት ሊያሻሽላቸውና ሊያስተካክላቸው ይገባል ያላቸውን ጉዳዮች አንስቷል፡፡ ካነሳቸውም ጉዳዮች መካከል የጤናውን ዘርፍ ለማጠናከር የወጣው የጤና ተቋማት የቁጥጥር ደረጃ (ሄልዝ ፋሲሊቲ ሬጉላቶሪ ስታንዳርድ) ታካሚዎችን በማይጎዳ መልኩ እንዲሻሻል፣ የቅብብሎሽ (ሪፈራል) ሥርዓት የግል ጤና ተቋማትን ባካተተ መልኩ እንዲቀረፅ፣ የግሉን ጤና ዘርፍ እንደ ዋነኛ ባለድርሻ አድርጎ ማየት የሚሉ ይገኙባቸዋል፡፡ ከዚህም ሌላ ከፌዴራል እስከ ወረዳ ድረስ ያሉት የመንግሥት ባለሥልጣናት በግሉ የጤና ዘርፍ ላይ ያላቸው አመለካከት የሚሻሻልበትን መንገድ መፍጠር፣ ከመንግሥትና ከግሉ ዘርፍ ትብብር አኳያ በወባ፣ በቲቢ፣ በኤችአይቪና በሌሎችም የክትባት ሥራዎች ላይ በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ ቅንጅት እየተከናወኑ ያሉት ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ማድረግ የመንግሥት የሥራ ድርሻዎች ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- የውድድር መልክ በያዘው የሥራ እንቅስቃሴ ላይ ያነሳችሁት ጉዳይ የለም?

ዶ/ር ወንድወሰን፡- አንስተናል፡፡ በዚህም መንግሥት ከግል የጤና ተቋማት ጋር የውድድር ሥራ ማከናወን እንደሌለበትና ውድድር ውስጥ መሳተፍ እንደማይገባው አመልክተናል፡፡ አንዱና ዋንኛው ጉዳይ በመንግሥት ሆስፒታሎች የተጀመረው ፕራይቬት ዊንግ የሚባል አካሄድ ነው፡፡ ይህ ፍትሐዊ እንዳልሆነ ጠቁመናል፡፡ ከዚህ ይልቅ ሐኪሞች በመንግሥትና በግል ጤና ተቋማት ውስጥ ሊሠሩ የሚችሉበትን አካሄድ መቀየስና ማስፋፋት እንዲሁም የተለያዩ አዳዲስ የአሠራር ሞዴሎችን ዲዛይን ማድረግ አማራጭ ሊሆን እንደሚገባ አሳስበናል፡፡

ሪፖርተር፡- በመንግሥት የሕክምና ተቋማት ውስጥ ፕራይቬት ዊንግ ሊከፈት የቻለው ከፍተኛ ሐኪሞችን በሥራቸው ላይ ለማቆየት በማሰብ ነው፡፡ ይኼንን እንዴት አያችሁት?

ዶ/ር ወንድወሰን፡- ይኼ ጉዳይ እንኳን እኔን አይመለከተኝም፡፡ ነገር ግን ለጥያቄህ የማምንበትን መልስ መስጠት ይኖርብኛል፡፡ ፕራይቬት ዊንግ ከፍተኛ ሐኪሞችን በሥራ ላይ ለማቆየት ሲባል ተግባር ላይ የዋለ ዘዴ እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡ መንግሥት የተጠቀሱትን ሐኪሞች ማቆየት ከፈለገ ደመወዛቸውን ሊጨምርላቸውና ልዩ ልዩ ጥቅማ ጥቅሞችን ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ በተረፈ በመንግሥት መሠረተ ልማትና መሣሪያዎች የግል ሕክምና አገልግሎት መስጠት ፍትሐዊ ነው ብለን አናምንም፡፡

ሪፖርተር፡- በድርድሩ ወቅት በሥራ አጋጣሚ ስህተት ፈጽመው በተገኙ ሐኪሞች ላይ መወሰድ ያለበትን ሕጋዊ ዕርምጃ በተመለከተ አልተነጋገራችሁም?

ዶ/ር ወንድወሰን፡- በሚገባ ተነጋግረን የመፍሔ ሐሳቦችን አስቀምጠናል፡፡ አንድ ሐኪም የሕክምና ስህተት ፈጽሞ ከተገኘ መታየት ያለበት በወንጀል ሕግ ሳይሆን በፍትሐብሔር መሆን እንዳለበት ጠቁመናል፡፡ መታሰርም ካለበት በሕግ አግባብ ሊሆን ይገባል፡፡ በዚህ ዙሪያ ላይ ነገሮችን ትንትን አድርጎ የሚያሳይ የሕገ ሕክምና (ሜድኮ ሌጋል) ጉባኤ ማቋቋም አስፈላጊ መሆኑንም አሳውቀናል፡፡ ከዚህም ሌላ ፋርማሲዩቲካልና ሜዲካል አቅርቦት ላይ የውጭ ምንዛሪ በማግኘት በጉምሩክ፣ በመድኃኒት ምዝገባና በሌሎችም እንቅስቃሴዎች ዙሪያ የሚታዩት አካሄዶች እንዲስተካከሉ አመልክተናል፡፡ በተለይም የመድኃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ መድኃኒት ለግል የጤና ተቋማት የሚያቀርበው ለመንግሥት ጤና ተቋማት በቅድሚያ ካደረሰና ካከፋፈለ በኋላ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ አሠራር ፍትሐዊ አለመሆኑን ገልጸን የአቅርቦቱ ሥራ ለመንግሥትም ሆነ ለግል ጤና ተቋማት እኩል እንዲሆን አሳስበናል፡፡ የመሬት፣ የብድር አቅርቦትና ሌሎች ኢንቨስትመንቶችን በተመለከተ ለግሉ የጤና ዘርፍ ቅድሚያ እንዲሰጥ፣ ለግል ሐኪሞች ሲሰጥ የነበረውና በአሁኑ ጊዜ የተቋረጠው የአገር ውስጥ ትምህርት ዕድል እንደገና እንዲታይ የሚሉትንም ነጥቦች በድርድሩ ላይ አቅርበናል፡፡  

ሪፖርተር፡- በግሉ ጤና ዘርፍ መከናወን ይገባቸዋል ተብሎ ከመንግሥት የቀረቡት አካሄዶች ምን ዓይነት ናቸው?

ዶ/ር ወንድወሰን፡- ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ያወጣቸውን የጥራት መለኪያዎች ሥራ ላይ ማዋል፣ ርህራሄ፣ አክብሮትና ጥንቃቄን የተላበሰ አገልግሎት መስጠት፣ ታካሚዎች ገንዘብ ከጨረሱ በኃላ ሪፈር የሚባሉበትን አሠራር ማስቀረት፣ ግልጽነት የተላበሰ የዋጋ ትመናን ተቀብሎ ተግባራዊ ማድረግ ይገኙበታል፡፡

ሪፖርተር፡- በተለይ ግልጽነት የተላበሰ የዋጋ ትመናን ሥራ ላይ ለማዋል በእናንተ በኩል ምን የታቀደ አካሄድ አለ?

ዶ/ር ወንድወሰን፡- አግባብ ያልሆነ የዋጋ ትመና የግሉ ዘርፍ መገለጫ ባይሆንም የታካሚውን አቅም ያላገናዘበና ከመጠን በላይ ክፍያዎችን የሚጠይቁ አንዳንድ የግል ሕክምና ተቋማት እንዳሉ በማመን፤ ኅብረተሰቡም በዚህ ዙሪያ እሮሮ ማሰማቱን በመገንዘብ ለችግሩ መፍትሔ ይሆናል ብለን ያመንበትንና ‹‹የተቀናጀ የጤና አገልግሎት አቅርቦት በግሉ የጤና ዘርፍ›› የሚል ስያሜ የተቸረውን ዕቅድ አዘጋጅተናል፡፡ በዚህ ዕቅድ መሠረት በተመሳሳይ ስም፣ ዋጋ፣ የጥራት መለኪያና ደረጃ አገልግሎት የሚሰጡ 40 የግል ክሊኒኮችን በዚህ ዓመት መጨረሻ ላይ ይፋ እናደርጋለን፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ሜዲካል ፕላዛ ብለን ተርሼሪ ኬር የሚሠራ አንድ ማዕከል ለማቋቋም አስበናል፡፡ 

ሪፖርተር፡- በድርድሩ ላይ ከግሉ ዘርፍ የተጠቆሙ ማሻሻያዎችን ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንዴት ተቀበለው?

ዶ/ር ወንድወሰን፡- ሁሉንም ችግሮች ለማየት ተስማምቷል፡፡ በተለይም አመለካከት ላይ ለመሥራት፣ የጤና ተቋም የቁጥጥር ደረጃን ለማሻሻል፣ ለአንድ ዘርፍ ሁለት መለኪያ የለም ቢልም ካለ ለማየት፣ በአገር ውስጥ ላሉ የግል ሐኪሞች የተከለከለውን የትምህርት ዕድል ለመቃኘትና የሕገ ሕክምና ጉባዔን ተቀብሏል፡፡

ሪፖርተር፡- የተስማማባቸውን ጉዳዮች ተግባራዊ ለማድረግ ምን ታቅዷል?

ዶ/ር ወንድወሰን፡- ለተግባራዊነቱ የሚረዳ የጋራ ዕቅድ አውጥተናል፡፡ ዕቅዱ ግን ሳይፈረም የጤና ጥበቃ ሚኒስትር የነበሩት ዶክተር ከሰተብርሃን አድማሱ ከሥራቸው ተነሱ፡፡ ይህን ያለቀለትን ዕቅድ አዲሱ ሚኒስትር ዘንድሮ ፈርመውበት ወደ ተግባር እንድንገባ የግሉ ጤና ዘርፍ በጉጉት እየተጠባበቀ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የዕቅዱ ተግባራዊ መሆን ለግሉ ጤና ዘርፍ ምን ውጤት ያስገኛል ብለው ያምናሉ?

ዶ/ር ወንድወሰን፡- የዚህ ዕቅድ ተግባራዊነት በግሉ ጤና ዘርፍ ላይ መሠረታዊ ለውጥ ያመጣል የሚል ተስፋ አሳድሯል፡፡ ምክንያቱም ብዙ ችግሮችን ስለሚቀርፍ ነው፡፡