Skip to main content
x
‹‹የዜጎች መብትና ፍላጎቶች ቅድሚያ እንደሚያገኙና እንደሚከበሩ ዳግም መተማመን የሚፈጥር ማኅበራዊ ውል መፈጸም አስፈላጊ ነው››

‹‹የዜጎች መብትና ፍላጎቶች ቅድሚያ እንደሚያገኙና እንደሚከበሩ ዳግም መተማመን የሚፈጥር ማኅበራዊ ውል መፈጸም አስፈላጊ ነው››

ሰለሞን አየለ ደርሶ (ዶ/ር)፣ የአፍሪካ የሰብዓዊና የሰዎች መብቶች ኮሚሽነር

ሰለሞን አየለ ደርሶ (ዶ/ር) ለአኅጉሪቱና ለአፍሪካ ኅብረት ዋነኛ የሰብዓዊ መብት አካል በሆነው የአፍሪካ የሰብዓዊና የሰዎች መብቶች ኮሚሽን በኮሚሽነርነት እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ የአፍሪካ ኮሚሽን ኤክስትራክቲቭ ኢንዱስትሪስ፣ አካባቢ ጥበቃና ሰብዓዊ መብት የሥራ ቡድን ሊቀመንበርም ናቸው፡፡ ለኮሚሽኑ በግጭቶች ውስጥ ስላለ የሰብዓዊ መብት ሁኔታና በድረ ግጭት የመሸጋገሪያ ፍትሕና በሰብዓዊ መብት መካከል ስላለው ግንኙነትም የመከታተል ኃላፊነት ተቀብለዋል፡፡ ከሰብዓዊ መብት ጋር የተያያዙ ኮርሶችንና ሌክቸሮችን በተለያዩ አገሮች ከመስጠት በተጨማሪ መቀመጫውን አዲስ አበባ ያደረገው የፖሊሲ ጥናት አማካሪ ቲንክ ታንክ አማኒ አፍሪካ ኢንስቲትዩት ኃላፊም ናቸው፡፡ ኢንስቲትዩቱ በአፍሪካ ኅብረትና በአኅጉሩ ሰላምና ደኅንነት ላይ አተኩሮ የሚሠራ ነው፡፡ አፍሪካን በተመለከቱ በርካታ ጉዳዮች ላይ በመደበኛነት ትንተና ያቀርባሉ፡፡ ሰለሞን ጎሹ በአዲስ አበባ እያቋቋሙት ባለው አማኒ አፍሪካ ኢንስቲትዩት ቢሮ በመገኘት በአብዛኛው በአፍሪካ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- እስኪ በአዲስ አበባ እያቋቋሙት ስላለው ኢንስቲትዩት በጥቂቱ ይንገሩን፡፡

ዶ/ር ሰለሞን፡- አማኒ አፍሪካ ኢንስቲትዩት በአፍሪካ ኅብረት ላይ በዋናነት ትኩረት አድርጎ የሚሠራ ብቸኛ የፖሊሲ ጥናት አማካሪ ቲንክ ታንክ ነው፡፡ የአፍሪካ ኅብረት ራዕይን በመጠቀም የአፍሪካ ሰላምና ደኅንነትን፣ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደርንና ልማትን የተመለከቱ ጉዳዮች ላይ በዓይነቱ ለየት ያለና መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት ያለመ የፖሊሲ ጥናትና ትንታኔ ለመሥራት እንዲሁም ሥልጠና ለመስጠት ያለመ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ ቀደም እንደ ተመራማሪ የኮሚሽኑን እንቅስቃሴ ጨምሮ በአፍሪካ ኅብረት ላይ ትንታኔ ሲያቀርቡ እንዴት መሻሻል እንደሚችልም ሃሳብ ያቀርቡ ነበር፡፡ አሁን ኮሚሽነር ነዎት፡፡ በሌሎች መገምገምን እንዴት አገኙት? የአፍሪካ ኅብረትን በአጠቃላይ ኮሚሽኑን በተለይ ውስጥ ገብተው አሠራራቸውን በቅርበት ሲያዩ ቀድሞ ከነበረዎት ግምገማ የተለየ ነገርስ አግኝተዋል?  

ዶ/ር ሰለሞን፡- ይኼ ደስ የሚል ጥያቄ ነው፡፡ እኔ የተለያዩ ኮፍያዎች አሉኝ፡፡ አንዱ ኮሚሽነርነቴ ነው፡፡ ሌላኛው ግን በአፍሪካ የሰላምና ደኅንነት ጉዳዮች ላይ ትንታኔ የምሰጥ የሕግ ምሁር መሆኔን መቀጠሌ ነው፡፡ በመሠረቱ ኮሚሽነር ስትሆን የተቋሙን ውስጣዊ አሠራር በጥልቀት ለመረዳት ዕድል ታገኛለህ፡፡ በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ነው በአፍሪካ ኮሚሽንና በአፍሪካ ኅብረት፣ በአፍሪካ ኮሚሽንና በአባል አገሮች፣ እንዲሁም በአፍሪካ ኮሚሽንና በሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች መካከል ያለውን የተወሳሰቡና የተለያዩ ተቋማዊ፣ ሕጋዊና ግለሰባዊ ግንኙነቶች በአግባቡ መረዳት የሚቻለው፡፡ ይህ ደግሞ የአፍሪካ ኅብረት አካላት እንዴት እንደሚሠሩና የተቋማቱን ጥንካሬና ድክመት፣ እንዲሁም አቅም፣ መጠንና ቅርጽ የሚወስኑ የተለያዩ ኃይሎችን አሠላለፍ ለመረዳት ያስችላል፡፡

በውጭ አካላት መገምገም በተወሰነ መልኩ አስደሳች ነው፡፡ የተወሰኑ ጉዳዮች ለምን እንደሚከሰቱና እንደማይከሰቱ ሰዎች ቢያውቁና ቢረዱ የምትመኝበት ጊዜ አለ፡፡ ምክንያቱም ብዙ እንዲፈጸሙ የሚጠበቁ ነገሮች አሉ፡፡ ኮሚሽኑ ነፃና ገለልተኛ አካል መሆኑ ጠቃሚ ነው፡፡ ይህን በመጠቀም ከሰብዓዊና ከሰዎች መብቶች ጋር የተያያዙ የተወሰኑ ጉዳዮችንና አጀንዳዎችን ለማራመድ ይችላል፡፡ ኮሚሽኑ ይህን አስቸጋሪ ተግባር በአግባቡ ለመወጣት ከሌሎች አካላት ጋር በአጋርነት በመሥራት የድጋፍ መሠረቱን ማስፋቱ የግድ ነው፡፡ ይህም ከሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች፣ ከሚዲያ፣ ከፖሊሲ ተመራማሪዎች፣ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን፣ እንዲሁም እንደ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ካሉ ብሔራዊ ተቋማት ጋር መሥራትን ይጨምራል፡፡

የኮሚሽኑ ስኬት በዋነኝነት የሚለካው ዜጎች ፍላጎታቸውንና ጥቅሞቻቸውን ከአገራቸው ድንበር ባሻገር ለማስከበር እንዲችሉ በሚፈጥረው ዕድል አማካይነት ነው፡፡ የአባል አገሮችን ባህሪ ለመቅረጽ የሚጫወተው ሚናም ወሳኝ ነው፡፡ በአጠቃላይ የኮሚሽኑን ሥራ በሦስት መንገድ ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ የመጀመሪያው ከሰብዓዊ መብት አንፃር ኮሚሽኑ ምን ያህል የሕግ ማዕቀፎችን አዘጋጅቷል? የአፍሪካውያንና የአባል አገሮች እንዲሁም የሌሎች በርካታ ባለድርሻ አካላት አረዳድና ግንዛቤን ለማሳደግ ምን ያህል ጥሯል? ከሚለው ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ይህ በአኅጉሩ ሰብዓዊ መብት እንዴት ዓይነት ግንዛቤ እንደተያዘበት፣ እንዴት እንደሚተረጎምና ተግባር ላይ እንደሚውል በሠራው ሰብዓዊ መብትን የማስፋፋት ሥራ ጋር ይያያዛል፡፡ በተለይ ከሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ሚና፣ ከፕሬስ ነፃነትና ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት፣ ከማኅበራዊ ሚዲያ አመራር፣ ከድህነትና ያልተመጣጠ ዕድገት፣ እንዲሁም ከተፈጥሮ ሀብቶች አስተዳደር ጋር በተያያዘ የሚሠራቸው የማስፋፋት ሥራዎች ወሳኝ ናቸው፡፡

በሁለተኛ ደረጃ በብሔራዊ ደረጃ መፍትሔ ላላገኙ ዜጎች አማራጭ ፍትሕ ማግኛ መድረክ ሆኖ ማገልገል አለበት፡፡ ኮሚሽኑ ይህን ለማድረግ እንዲያስችለው ከዜጎች ጋር ግንኙነት የሚያደርግበትና መረጃ የሚሰበስብበት አሠራር አለው፡፡ የመጨረሻው ሚና ኮሚሽኑ ምን ያህል የአገሮቹን ባህሪ ይገራል ከሚለው ጋር የተገናኘ ነው፡፡ የኮሚሽኑ ሥራ መታየትና መገምገም ያለበት ከእነዚህ አንፃር ነው፡፡ በኮሚሽኑ እየለመድኩ ባለሁበት በአሁኑ ወቅት የተረዳሁት ከውጭ የሚታየውና ውስጥ የሚገኘው ሁሌም አንድ እንዳልሆነ ነው፡፡ ነገር ግን በአኅጉሩ የሰብዓዊ መብት ይዞታ ላይ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት ኮሚሽኑ ትልቅ ሚና መጫወት ይችላል፡፡ የኮሚሽኑን ውጤታማነት ከገደቡ ውስንነቶች አንደኛው እኔና ሌሎች ኮሚሽነሮች በትርፍ ጊዜ የምንሠራ መሆናችን ነው፡፡ ስለዚህ በሌሎች ተግባራት ተጠምደን ነው የቀረውን ጊዜ የምንገፋው፡፡ ይህ ኮሚሽኑ በሚጠበቅበት ደረጃ እንዳይሠራ ጫና ይፈጥራል፡፡

ሪፖርተር፡- የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ወደ አፍሪካ ኅብረት ሲሸጋገር ለዜጎች በበርካታ ጉዳዮች ላይ ለውጥ እንደሚደረግ ተነግሮ ነበር፡፡ ከእነዚህ ጉዳዮች መካከል ተደጋግሞ የተነገረው ‘ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔዎች’ የሚለው ነው፡፡ ነገር ግን የአፍሪካ ኅብረትና አካላቱ አሁንም በፋይናንስና በአሠራር ሒደት በሌሎች የውጭ አካላት ላይ ጥገኛ ናቸው ተብለው ይተቻሉ፡፡ በዚህ አስተያየት ይስማማሉ?

ዶ/ር ሰለሞን፡- ይህን ቃል በተግባር ለማዋል በርካታ ውስንነቶች አሉ፡፡ ከፋይናንስ አንፃር ኅብረቱ አሁንም ቢሆን በውጭ ኃይሎች ላይ ጥገኛ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ኅብረቱ በሚሠራቸው ሥራዎች ላይ ሙሉ ቁጥጥር እንዳይኖረው ያደርጋል፡፡ አሁን ይህን ለመቀየርና ኅብረቱ ሥራዎቹን በራሱ ወጪ ለመሸፈን የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎች በመደረግ ላይ ናቸው፡፡ ኅብረቱ ጥሩ የሚባሉ ውሳኔዎችን የማሳለፍ ችግር ባይኖርበትም፣ ብዙዎቹ ውሳኔዎች ተግባር ላይ አይውሉም፡፡ የውሳኔዎቹ ተግባራዊነት በአባል አገሮቹ ፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ይህ ሀብትን፣ ግለሰቦችንና የዲፕሎማቲክና የፖለቲካ ካፒታልን ማንቀሳቀስ ይጠይቃል፡፡ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ደግሞ የአመራር ክፍተት አለ፡፡ ‘ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔዎች’ ማለት አፍሪካ ለሁሉም ችግሮቿ ብቻዋን መፍትሔ ትሰጣለች ማለት አይደለም፡፡

አሁን ባለንበት ዘመን አፍሪካ ውስጥ የምናያቸው ቀውሶች ሁሉ በአፍሪካ ድርጊቶች አማካይነት የመጡ አይደሉም፡፡ ከፊሎቹ በውጭ ኃይሎች ድርጊቶች የመጡ ናቸው፡፡ ለነገሩ በተመድ ቻርተር ላይ የተመሠረተው ዓለም አቀፋዊ የጋራ የደኅንነት ሥርዓትን የማስጠበቅ ኃላፊነት በአፍሪካም ላይ የወደቀ ነው፡፡ ‘ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔዎች’ ሲባል አፍሪካ በራሷ ጉዳዮች ላይ ትንታኔ በማቅረብም ይሁን መፍትሔ ከመስመት አኳያ የመሪነት ሚና መጫወት አለባት ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ የሌሎችን ተሳትፎ አይገድብም፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ሰላምና ደኅንነት በቅርቡ ችግር ውስጥ ገብቶ ነበር፡፡ በእርስዎ ዕይታ ወደዚህ ችግር ለመገባቱ መንስዔው ምንድነው?

ዶ/ር ሰለሞን፡- ያለፉት ሁለት ዓመታት ለኢትዮጵያና ለሕዝቦቿ በከፍተኛ ሁኔታ ፈታኝ ጊዜያት ነበሩ፡፡ በጊዜ ሒደት ሁኔታዎቹ ወዴት እንደሚያመሩ ሁላችንንም ጨንቆንና አሳስቦን ነበር፡፡ ለተከሰተው ችግር አንድ ነጠላ ምክንያት የለውም፡፡ ከግንዛቤ ውስጥ ልንከታቸው የሚገቡ በርካታ ተዋንያንና ምክንያቶች አሉ፡፡ አንደኛው ጉዳይ በአገሪቱ ውስጥ ካለው የዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ጋር የሚገናኝ ነው፡፡ ይህም በዋነኛነት የዜጎች ፍላጎቶችና መብቶች በአግባቡ በመሰማታቸውና መፍትሔ በማግኘታቸው የሚገለጽ ነው፡፡ በድኅረ 1983 ዓ.ም. የአገሪቱ የፖለቲካ ሥርዓት ዋነኛ መገለጫ ከሆነው የፌዴራል ሥርዓት አፈጻጸም ጋር የተገናኙ ጉዳዮችም አሉ፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት የፌዴራል ሥርዓቱ ችግር ውስጥ ገብቶ ነበር፡፡

ሌላኛው ችግር ከመድበለ ፓርቲ ሥርዓቱ ጋር የተገናኘ ነው፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሥርዓቱ ራሱ ስለመኖሩ ጥያቄ እየቀረበበት ነው፡፡ ይህ ይበልጥ ጉልህ የሆነው ገዥው ፓርቲና አጋሮቹ የፓርላማውን ወንበሮች ሙሉ በሙሉ ካሸነፉ በኋላ ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባለ ብዝኃነት ባለበት አገር ፓርላማው የአገሪቱን የፖለቲካ ብዝኃነት የሚወክል ስለመሆኑ ጥያቄ እየቀረበበት ነው፡፡ በአገሪቱ የብሔር ብዝኃነት ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ብዝኃነትም አለ፡፡ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በተለይም ወጣቱ ላይ ጫና ያሳደሩ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችም ተነስተዋል፡፡ ሥራ የማግኘት ዕድል ዕጦት ከመገለልና ካለመሰማት ስሜት ጋር ተዳምሮ ባለፉት ሁለት ዓመታት ለነበረው ችግር ዳርጓል፡፡

በመንግሥትና በሕዝቡ መካከል የነበረው ግንኙነት በጊዜ ሒደት እየተሸረሸረ መጥቷል፡፡ የነበራቸው እርስ በርስ መተማመንም ጥያቄ ውስጥ ገብቷል፡፡ ይህ ደግሞ በሙስና፣ በተጠያቂነት ዕጦት፣ እንዲሁም በፓርቲ፣ በመንግሥትና በአገር መካከል ልዩነት ባለመኖሩ ይበልጥ ተወሳስቧል፡፡ እነዚህ ሁሉ ጉዳዮች ችግሩን ፈጥረዋል፡፡ በዚህ ሁኔታ ችግሩን ለመቆስቆስ አንድ ምክንያት በቂ ነው፡፡ የአዲስ አበባና ኦሮሚያ የተቀናጀ ማስተር ፕላን ዕቅድ አንድ ቆስቋሽ ምክንያት ብቻ የሆነው ለዚህ ነው፡፡  የገዥው ፓርቲ አባል ፓርቲዎች የውስጥ ልዩነትም ችግሮችን የማባባስ ሚና ነበረው፡፡

ሪፖርተር፡- ተፈጥሮ ለነበረው ችግር ዘላቂ መፍትሔ ከመስጠት አኳያ ከመንግሥትና ከገዥው ፓርቲ ጨምሮ በርካታ ሐሳቦች ተሰንዝረዋል፡፡ እነዚህን ችግሮች ከመሠረቱ ለመፍታት ምን መደረግ አለበት ይላሉ?

ዶ/ር ሰለሞን፡- ማሻሻያው በተቻለ መጠን ከላይ ያነሳናቸውን ጉዳዮች ሁሉ ቢያካትት መልካም ነው፡፡ የገዥው ፓርቲ አባል ፓርቲዎች የውስጥ ልዩነታቸውን ቶሎ መፍታት አለባቸው፡፡ የዜጎች መብትና ፍላጎቶች ቅድሚያ እንደሚያገኙና እንደሚከበሩ ዳግም መተማመን መፍጠር የሚያስችል ማኅበራዊ ውል መፈጸም አስፈላጊ ነው፡፡ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ለሥራቸው ተጠያቂ መሆን አለባቸው፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱን አፈጻጸም መገምገምና ድጋሚ ማጤንም ያስፋልጋል፡፡ በሥርዓቱ ላይ የተወሰኑ ማሻሻያዎች ማድረግ አለብን ወይስ የለብንም የሚለውን ጥያቄ የምናቀርብበት ነጥብ ላይ ደርሰናል፡፡ ለቡድን መብት እንደተሰጠው ትኩረት ሁሉ ለግለሰቦች መብትም ተመሳሳይ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ዜጎች የትም ሆኑ የት መብታቸው ሊከበርላቸውና ከጥቃት ሊጠበቁ ይገባል፡፡ ዜጎች መብታቸው የሚከበረው በአንድ ክልል ችሮታ መሆን የለበትም፡፡ የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እኩልነት በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠበትን መንገድ ድጋሚ ማጤን ይኖርብናል፡፡

በቡድን መብትና በግለሰቦች መብት መካከል ሚዛን መጠበቅ አላስፈላጊ ሁከትና ብጥብጥን ለማስወገድ ይጠቅማል፡፡ የብሔሮች እኩልነት በመንግሥት መዋቅር ውስጥም መታየት አለበት፡፡ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓቱ ሊተገበርና ዕውን ሊሆን ይገባል፡፡ የአገሪቱን ብዝኃነት በመንግሥት መዋቅሮችና በፓርላማው ለማንፀባረቅ የሚያስችሉ ሕጋዊና ፖለቲካዊ ምኅዳሮች ሊፈጠሩ ይገባል፡፡ ከዚህ አንፃር በዓመቱ መጀመሪያ ላይ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) ያቀረቡት የምርጫ ሕግ ማሻሻያ ሐሳብ ተግባራዊ መሆን አለበት፡፡ ለአገሪቱ ጥቅምና መረጋጋት ሲባል ይህ ተግባራዊ መደረግ አለበት፡፡ ከኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች አንፃር የልማታዊ መንግሥት ሞዴል ለኢትዮጵያ አዋጪ ቢሆንም፣ አፈጻጸሙ ላይ በርካታ ጥያቄዎች ይነሳሉ፡፡ አፈጻጸሙ ዜጎችን የሚጎዳና የመገለል ስሜት የሚፈጥርባቸው መሆን የለበትም፡፡ ይህ ተገቢ ያልሆን አካሄድ ዜጎች በልማት ፕሮጀክቶች ላይ ለተቃውሞ እንዲነሱ ማድረጉንም አይተናል፡፡ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ጠቃሚ ቢሆንም፣ ከሕዝቡ ዘላቂ ፍላጎት ጋር ሊጣጣም ይገባል፡፡ ማሻሻያው እነዚህን ሁሉ ከግምት ውስጥ ሲያስገባ ነው ችግሮቹን በዘላቂነት መፍታታችንና አገሪቱ ሰላማዊ፣ የተረጋጋና ሕዝብን መሠረት ያደረገ ሥርዓት እየገነባን ስለመሆኑ መደምደም የሚቻለው፡፡