Skip to main content
x
53 የተሻሻሉ የማሽላ ዝርያዎች ተለቀቁ

53 የተሻሻሉ የማሽላ ዝርያዎች ተለቀቁ

  • 23ቱ ዝናብ አጠር ለሆኑ አካባቢዎች የሚስማሙ ናቸው
  • ድርቅና አቀንጭራን ይቋቋማሉ

የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በኢትዮጵያ ደረጃ 53 የተሻሸሉ የማሽላ ዝርያዎችን መልቀቁን ከእነዚህ ውስጥ 23ቱ ዝናብ አጠር ለሆኑ አካባቢዎች የሚስማሙ መሆናቸውን አስታወቀ፡፡

ኢንስቲትዩቱ ላለፉት አራት ዓመታት ከስድስት ወራት የተገበረውን አይማሽላ (imashilla) የተባለውን ፕሮጀክት ማጠናቀቂያ አውደ ጥናት ከሚያዝያ 25 እስከ 26 ቀን 2009 ዓ.ም. ባካሄደበት ወቅት እንደተገለጸው፣ ዝርያዎቹ የተሻሻሉና በሄክታር እስከ 50 ኩንታል መስጠት የሚችሉ ናቸው፡፡

በኢንስቲትዩቱ የብሔራዊ ማሽላ ምርምር ፕሮግራም አስተባባሪ ዶ/ር ታዬ ታደሰ እንዳሉት፣ ፕሮጀክቱ የተሻሻሉና ድርቅንና አቀንጭራን መቋቋም የሚችሉ የማሽላ ዝርያዎችን በማፍለቅ ውጤታማ ሆኗል፡፡ እስከ 10 ዓመት የሚፈጀውን የማሽላ ዝርያ የማፍለቅ ሒደትም ወደ ስድስትና ሰባት ዓመት ዝቅ ማድረግ ተችሏል፡፡

የምርምር ውጤትን በተሻለ ደረጃ ለማምጣት የሚያስችሉ ቴክኒኮችን በመጠቀምም፣ ከዚህ በፊት  በአንድ ሙከራ ውስጥ ከ20 እስከ 30 ዝርያዎችን ይገመግሙ የነበረውን፣ አሁን ላይ እስከ 500 ዝርያዎችን በአንድ ጊዜ ለመገምገምና የተሻለ ዝርያ ለመምረጥ የሚያስችል አቅም ጎልብቷል፡፡

ለረዥም ጊዜ ለአርሶ አደሩ የተለቀቁት ዝርያዎች ባዮማሳቸው አነስተኛ በመሆኑ ተቀባይነታቸው ዝቅተኛ እንደነበር በማስታወስም፣ ማሽላው የተሻለ ባዮማስ እንዲኖረውና አርሶ አደሩ የሚፈልጋቸውን ዝርያዎች ባህሪያት በመለየትም በአጭር ጊዜ ውስጥ የተሻሉ ዝርያዎችን ለመፍጠር እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ በአብዛኛው ማሽላ የሚመረትባቸው አካባቢዎች ድርቅ የሚከሰት በመሆኑ ለዚህ የተመቸ ቴክኖሎጂ አለ ወይ? ተብለው የተጠየቁት ዶ/ር ታዬ፣ ቴክኖሎጂዎቹ በቂ እንዳልሆኑ ተናግረዋል፡፡ የተወሰኑ ቴክኖሎጂዎች ቢኖሩም ባለፉት ሦስት ዓመታት የተከሰተው ድርቅ አብዛኛው ማሽላ የሚበቅልባቸው አካባቢዎች ላይ በመሆኑና አርሶ አደሩ ለረዥም ዓመታት ሲጠቀምበት የነበረውን ባህላዊ አሠራርና የአመራረት ዘዴ ተጎጂ ስላደረገው አሁን ላይ ወደ ተሻሻሉ ዝርያዎች እየመጣ መሆኑንም አክለዋል፡፡

ዝርያዎቹ በአጭር ጊዜ መድረሳቸውና ድርቅን መቋቋማቸው ተቀባይነታቸውን እንደጨመረ በማውሳትም፣ በርሶ አደሩ ዘንድ ፍላጎት መታየቱንና የአርሶ አደሩን ፍላጎት ለማድረስም ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አክለዋል፡፡ ሆኖም የቴክኖሎጂ እጥረቶች ባሉባቸው አካባቢዎች ችግሩን ለመፍታት በአይማሽላ ፕሮጀክት እየተሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ያለው ማሽላ ረዣዥም መሆኑ ምርቱ ሲደርስ እንዲወድቅ ምክንያት ነው፣ ፕሮጀክቱ ለዚህ ምን መፍትሄ ይዟል? ለሚለውም፣ አርሶ አደሩ በተወሰነ መልኩ ረዥም መሆናቸውን እንደሚፈልግ፣ በተቋሙ የወጡ ዝርያዎች አጭር በመሆናቸው ተቀባይነትና ፍላጎት ቀንሶ እንደነበርና ለዚህም የተሻለ ቁመት እንዲኖራቸው መሠራቱን ዶ/ር ታዬ ተናግረዋል፡፡

ከቁመቱ ጋር ተያያይዞ የሚወድቅበት ምክንያት ቢኖርም፣ ድርቅና አቀንጭራ ዋና ችግሮች ስለሆኑ ትኩረት የተሰጠው ለእነዚህ ነው፣ የመውደቅን ባህሪ ገበሬው በተለያዩ መንገዶች ይከላከለዋልም ብለዋል፡፡

የሚጠየቁት የተሻሻለ የዘር መጠን በየጊዜው እየጨመረ መሆኑን፣ ከሦስት ዓመት በፊት በተደረገ ጥናት በተለይ የተሻሻሉ ዝርያዎችን በመጠቀም ረገድ መሻሻል ማሳየቱን፣ በተለይ ዝናብ አጠር በሆኑ አካባቢዎች የተሻሻሉ ዝርያዎችንና የራሱን ዝርያ ቀላቀሎ የሚጠቀም አርሶ አደር ቁጥር 29 በመቶ መድረሱንና ድርቁ እየፈጠረ ያለው ጫናም አርሶ አደሩ የራሱን ቴክኖሎጂ ከመጠቀም ይልቅ የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀም ጫና ማሳደሩንም ገልጸዋል፡፡

ትልቁ የአርሶ አደሩ ችግር ያመረተውን የሚሸጥበት አለማግኘቱ ነው፡፡ ያመረተውንም በአብዛኛው ለራሱ እየተጠቀመ ይገኛል፡፡ ዶ/ር ታዬ እንደሚሉት፣ ይህንን ለመቀየር ሥራዎች የተጀመሩ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ወስጥ ማሽላን ለቢራ የሚቀጠሙ ፋብሪካዎች መኖራቸውና ለዶሮ መኖነት ማዋል የሚቻልበት አጋጣሚም ስላለ ኢንዱስትሪዎቹን በማጠናከር ማሽላው ወደገበያው እንዲገባ እየተሠራ ነው፡፡

ምርታማነትን በተመለከተ ነባር ከሚባሉት ዝርያዎች በሄክታር 24 ኩንታል ሲገኝ፣ ተሻሽለው በቅርቡ የተለቀቁት ዝርያዎች በሄክታር እስከ 50 ኩንታል ይሰጣሉ፡፡ አሁን ያሉትን ቴክኖሎጂዎች ብቻ በመጠቀምም የማሽላ ምርታማነትን በሁለት እጥፍ ማሳደግ የሚቻል ሲሆን፣ በሄክታር እስከ 80 ኩንታል ምርት ማግኘት የሚቻልበት ዕድልም አለ፡፡

ማሽላ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የሚከሰቱ ችግሮችን በተወሰነ መልኩ የመቋቋም ባህሪ ቢኖረውም፣ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚመጣውን ድርቅና ሌሎች ችግሮች ለመቋቋም የሚችሉ ዝርያዎችን ለመፍጥር እየተሠራ ነውም ብለዋል፡፡

ትልቁ የማሽላ ችግር ለምግብነት ሲውል ካለው ጠቀሜታ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በሆድ ውስጥ ቶሎ የመፈጨት ዕድሉ ዝቅተኛ ስለሆነ ይህንን ማሻሻል፣ ጥራቱንም በተመለከተ ክፍተት እንዳይፈጠር ማድረግና ከአመጋገብ ሥርዓቱ ጋር ላለው ችግር የተሻሻለ የምግብ ይዘት ያላቸውን መፍጠርና ማስተዋወቅ የፕሮጀክቱ አካል ነው፡፡

አይማሽላ ፕሮጀክት በኢትዮጵያ የማሽላ ምርምርን በተሻለ ደረጃ ለማዘመንና የተለያዩ አሠራሮች ተቀናጅተው ውጤት የሚያመጡ የማሽላ ዝርያዎችን ለማፍለቅ የሚሠራ ፕሮጀክት ሲሆን፣ በአውስትራሊያ የኩዊንስ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ከኢንስቲትዩቱ ጋር ይሠራሉ፡፡