|
Wednesday, 19 March 2008 |
|
ኢትዮጵያና የመን በትብብር ለመሥራት መከሩ
የንግድ ሰዎችን ማበረታታት የጋራ ፕሮጀክቶችን ነድፎ የኢኮኖሚ ትብብርን በሁለቱ ሃገሮች ለማስፋፋት እንደሚረዳ የየመን ፓርላማ አፈ ጉባኤ ገለፁ፡፡
አፈ ጉባኤው ያህያ አል ሬይ ይኸን የገለፁት ባለፈው እሁድ በየመን የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው ከተሾሙት ቶውፊቅ አብደላህ ጋር ባደረጉት ውይይት በኢትዮጵያና በየመን መካከል ስላለው የፓርላማዎች ትብብርና በኢኮኖሚ፣ በንግድና በኢንቨስትመንት ግንኙነት ስላለው የቅርብ እድገት ባነጋገሩዋቸው ወቅት ነው፡፡
መንግሥት 100 ሚሊዮን ዶላር ሊበደር ነው
የኢትዮጵያ መንግሥት ለከተሞች መሠረተ ልማት አገልግሎት የሚውል 100 ሚሊዮን ዶላር ብድር ለማግኘት ከዓለም ባንክ ጋር ስምምነት ላይ መድረሱን የሥራና ከተማ ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የብድር ስምምነቱ በባንኩና በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር መካከል በሚቀጥለው ሳምንት ይፈረማል፡፡
ገንዘቡ አዲስ አበባን፣ ባሕርዳርን፣ አዋሳን፣ ድሬዳዋን፣ ሐረርንና መቀሌን ጨምሮ 19 ከተሞችን ለደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻ አስተዳደር፣ ለመሬት ልማት፣ ለፍሳሽ ማውረጃዎችና ለገበያ ማዕከላት ግንባታ፣ ለውሃ አቅርቦትና ለሌሎችም የመሠረተ ልማት ግንባታዎች እንደሚውልም ተጠቁሟል፡፡
ኢዜአ
የሬዲዮ ፈቃድ እየተሰጠ ነው
የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን የማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያ ለማቋቋም ለአመለከቱ ፈቃድ የመስጠት ሥራ እያከናወነ መሆኑን ገለፀ፡፡
የማህበረሰብ ሬዲዮ አስፈላጊነት በመንግሥት ትኩረት ተሰጥቶት የተለያዩ አበረታች ተግባሮች እያከናወነ እንደሚገኝ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የብሮድካስት አገልግሎትን አዋጅ እንደገና አሻሽሎ ሲያወጣ፣ የማህበረሰብ ሬዲዮ ሕጋዊ መሠረት እንዲኖረው ማድረጉ ተጠቃሽ መሆኑን ገል"ል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 9 ቀን 2000 ዓ.ም
በ326 ሚሊዮን ብር የተለያዩ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው
በአማራ ክልል ከተለያዩ ለጋሽ አገሮችና ዓለም አቀፍ አበዳሪ ድርጅቶች በተመደበ 326 ሚሊዮን ብር በላይ የተለያዩ የልማት ሥራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን የክልሉ ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡
ከለጋሾችና ከልማት አጋሮች የሚገኘውን ሀብት ከብክነት ለመጠበቅና በተገቢው መንገድ ጥቅም ላይ ለማዋል የክልሉ መንግሥት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ መሆኑን በተያዘው የበጀት ዓመት ከ21 ለጋሽ አገሮችና ዓለም አቀፍ አበዳሪ ድርጅቶች በተመደበ 326 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር በላይ የተለያዩ የልማት ሥራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን ገል"ል፡፡
ዋኢማ
በሕገወጥ ንግድ የተሰማሩ 18 ድርጅቶች ታሸጉ
በጅማ ከተማ በህገወጥ ንግድ ሥራ ላይ በተሰማሩ ነጋዴዎች ላይ የሚወስደው እርምጃ ተጠናክሮ መቀጠሉን የከተማው ንግድ ኢንዱስትሪና ትራንስፖርት ጽሕፈት ቤት ገልፆ፣ 18 የንግድ ድርጅቶች መታሸጋቸውን ተናግሯል፡፡
በጨውና በተለያዩ ሸቀጣሸቀጦች ላይ አግባብ ያልሆነ ጭማሪ ባደረጉት ሕገወጥ ነጋዴዎች ላይ የሚወስደው እርምጃ በሕዝብ ተሳትፎ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል፣ ጽህፈት ቤቱ ባደረገው ክትትል አስር የእህል፣ የህንፃ፣ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች መሸጫና የማከፋፈያ ድርጅቶችን ማሸጉንና በሸቀጦች ላይ መጠነኛ ቅናሽ መደረጉን ገል"ል፡፡
ኢዜአ |