| አይ ኤስ ኦ 9000 የጥራት... |
|
|
| Sunday, 23 March 2008 | |
|
አይ ኤስ ኦ 9000 የጥራት ማረጋገጫ ወይስ የጥራት ጭምብል?
አይሶ (ISO) አህጽሮተ ቃል አይደለም፡፡ በግሪክ ቋንቋ እኩል ማለት ነው፡፡ አለም አቀፉ የደረጃዎች መዳቢ ድርጅት በአህጽሮተ ቃል አፃፃፍ አይሶ ማለት ሲገባው አይ ኤስ ኦ ማለቱ እስከምን ድረስ እንደሚያዛልቀው አጠያያቂ ነው፡፡ በጄኔቭ በ25 አገሮች እ.ኤ.አ በ1947 የተቋቋመው አይሶ ዋነኛ መርሁ አድርጎ የተነሳው "የአለም ሁሉ ደረጃዎች እኩል ይሁኑ" የሚል ነበር፡፡ ዛሬ አባል አገሮቹ ከ155 አልፈዋል፡፡ አይሶ በአብዛኛው ደረጃዎችን ከሙያ ማኅበራት፣ ከኢንዱስትሪዎች፣ ከምርምርና ከትምህርት ተቋማት በመውሰድ፣ በሚያዋቅሯቸው ረቂቅ መስፈርት በሌላቸው የቴክኒክ ኮሚቴዎቹ አስገምግሞ፣ በአባል አገሮቹ ከፀደቀ በኋላ እንዲተገብሩት ያበረታታል፡፡ ሩ በአሁኑ ጊዜ የፀደቀውና በሂደቱ ላይ ያሉ ደረጃዎቹ ወደ 26"000 ደርሰዋል፡፡ ይህ ለጊዜው የመጨረሻ የሆነው ደረጃ "በማኅበራዊ ኃላፊነት ላይ" ያተኮረ ነው፡፡ ደረጃው ከምን እንደደረሰ ባናውቅም፣ በዝግጅቱ ኢትዮጵያ እንደተሳተፈች በዚሁ ጋዜጣ ላይ ተዘግቦ እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ ጥራትን ለመጥራት የሚወጡ አለም አቀፍ ደረጃዎች 9000 የቁጥር ቤትን በመያዝ አይሶ 9000፣ አይሶ 9001፣ አይሶ 9004 በመባል ይታወቃሉ፡፡ በተለምዶ ግን የወል ስማቸው አይሶ 9000 ነው፡፡ የጥራትን ጥሪ ለማድመቅ አጋዥ ሰነዶች በ10"000 የቁጥር ቤት ተሰይመው ይገኛሉ፡፡ 14"000 ቤት ደግሞ ለአካባቢ ጥበቃ ተጠብቋል፡፡ አይሶ "ካሳተማቸው" ደረጃዎች እንደ አይሶ 9000 በስፋት የተተገበረና በወረት የደመቀ ደረጃ የለም፡፡ ከእንግሊዝ የተወሰደውና ቢ ኤስ 5750 በመባል ይታወቅ የነበረው የጥራት ዘዴ ደረጃ እ.ኤ.አ በ1978 በጄኔቭ ከተማ ስሙን ቀይሮ አይሶ 9000 ተባለ፡፡ በወቅቱም በነበሩ 90 በሚደርሱ የ አይሶ አባል አገሮች እደግ ተመንደግ ተባለ፡፡ በጥቂት አመታት ውስጥም በከፍተኛ ፍጥነት ከቆሻሻ ሰብሳቢዎች እስከ ሶፍት ዌር አምራቾች በ አይሶ 9000 ሰርተፍኬት ተመረቁ፡፡ ፈጥነውም ምርቃታቸውም ለዓለም አበሰሩ፡፡ ጥራታችን በእጅጉ ተሻሻለ፣ ወጪያችን አሽቆለቆለ፣ አቀላጠፍን፣ አፈጠንን፣ ወዘተ. የሚሉ ድርጅቶች ቁጥራቸው በዛ፡፡ በተቃራኒው ደግሞ አይሶ 9000 ውጥኑም፣ ለውጡም ጭብጡም አልታየንም ያሉ አልጠፉም፡፡ ደረጃው የወረቀት ሥራና ቢሮክራሲን ያበዛል የሚሉ አቤቱታዎችም በስፋት ይደመጡ ነበር፡፡ በትህትናም፣ ደረጃው "ቁቨሽቃሸ by the ሯቄቄቀ" የሚል ስያሜ በስውር ወጥቶለት በአደባባይ ይታማበት ጀመር፡፡ ሆኖም ግን በሶስተኛ ወገን ኦዲት ይደረጋል በሚል ሰበብ ቅሬታው ለተወሰነ ጊዜ ችላ መባሉ አልቀረም፡፡ በ አይሶ 9000 ሰርተፍኬት የተመረቁ ድርጅቶች "በየሶስት ዓመቱ" በጥራት ኦዲተሮች ሰርተፊኬታቸውን ማሳደስ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በመላ ኢትዮጵያ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በጥራት ኦዲተር ተመርምረው በ አይሶ 9000 ሰርተፊኬት የተመረቁ ድርጅቶች ከ10 አይበልጡም ነበር፤ ምንም እንኳ ጩኸታቸው የ10"000 ያህል ድርጅቶች ያህል ቢሰማም፡፡ በአዲስ አበባ የድርጅቶችና የ አይሶ 9000 ሰርተፊኬት አርማ የያዙ መልከኛ ሲቲከሮች በየቦታው ማየት የተለመደ ነው፡፡ በአብዛኛው ሲተከሮቹ በግሮሰሪ በር፣ በመጠጥ ቤት ባልኮኒ፣ በሆቴል ቤት መስኮት፣ በመኖሪያ ቤት አጥር፣ በሊስትሮ ሳጥን እና በኮንዶም ፖስተር ላይ ተለጥፈው ይታያሉ፡፡ በቅርብም ስልጠና ለመስጠት ወደ መዲናችን የመጡ የውጭ ዜጋ የ አይሶ 9000 የተቀበለ ድርጅት ማስተዋወቂያ በቴሌቪዥን በማየታቸው በእጅጉ እንዳስደሰታቸው የተናገሩት በጋዜጣ ላይ አስመዝግበው በማየታችን አድንቀውናል፡፡ አሥር የሚሆኑ የኮንስትራክሽን ድርጅቶች ረፋዱ ላይ በ አይሶ 9000 ተመርቀው ማምሻቸውን የውጭ አገር የሥራ ኮንትራት አገኘን ሲሉ ሰምተን ተደምመን ነበር፡፡ ኮንትራቱ ጎረቤት አገር መሆኑ በጀ፡፡ ያም ቢሆን በ አይሶ 9000 ባለመመረቃቸው ወይስ እስካሁን ድረስ ከአቅም በታች በመስራታቸው? የሚል ጥያቄ ሳያጭርብን አላለፈም፡፡ ለማንኛውም የማስታወቂያውን ጎራ እንደሚያጨናንቁት አንጠራጠርም፡፡ የሚገርመው ግን ስቲከሮች አይሶ ሰርተፊኬቱ መቼ ኤክስፓየር እንደሚያደርግ አይናገሩም፡፡ ምስጢር ይሆን ወይስ ሸፍጥ? የውስጥ አዋቂ ምንጮች ድርጅቶች ሰርተፊኬቱን ለንግድ ማስተዋወቂያነት እንዲጠቀሙበት አይሶ ብዙ መላዎች እንዳሉት ይናገራሉ፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥም በአለም ላይ ሰርተፊኬቱን የተቀበሉ ድርጅቶች 700"000 መድረሳቸው ከማስደነቅም አልፎ ጥርጣሬን አጭሯል፡፡ ለምሳሌ የተጠቀሰው ቁጥር ኤክስፓየር ያደረጉ፣ የተሰረዙ እና የተነጠቁ ሰርተፊኬቶችን እንዳቀፈ ይታማል፡፡ እስካሁን ድረስ የተሰረዙትን አይሶ 9002 እና 9003 በየጋዜጣውና መጽሄት ማየት የተለመደ ነው፡፡ በእርግጥ አይሶ ችግሮቹን ለመቅረፍ ያላሰለሰ ጥረት ከማድረግ አልቦዘነም፡፡ በከፍተኛ ደረጃ ይታማበት የነበረውን የወረቀት ሥራ የማብዛት ችግር እ.ኤ.አ ከ2000 ጀምሮ አስወግዷል፡፡ ይህ ትልቅ እርምጃ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በ አይሶ 9000 ለመመረቅ ያስፈልጉ የነበሩትን ከ30 በላይ የሚሆኑ የግዴታ ሰነዶች ወደ ስድስት አውርዷቸዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የ አይሶ 9000ን መስፈርቶች መሰረት ያደረጉበትን መርሆዎች አውጥቻለሁ ብሏል፡፡ በእርግጥ መርሆዎቹ በግልጽ አይቀመጡ እንጂ ወትሮም ከሞላ ጎደል በምስጢር የሲስተሙ አካሎች ነበሩ፡፡ ፈፃሚው አካል በወል ስላልተነዘባቸው ደረጃውን በአግባቡ ለመተግበር ሲቸገር ተስተውሏል፡፡ ል የአሰራር ለውጥ ያደረጉ አይመስልም፡፡ በመሆኑም ሳንካዎች አላጡትም፡፡ ለምሳሌ አስገዳጅ ዶክመንቶቹ ወደ 6 ዝቅ ማለታቸው መካኒካል የሆነና ክንውን ላይ ያተኮረ የኳሊቲ ሲስተም በድርጅቶች ላይ ተንሳፎ እንዲቀመጥ እያበረታታ ነው፡፡ ሁሌም "በአጭር ግብ" ላይ የሚንሰፈሰፉት በርካታ ማኔጀሮቻችን ሳይመቻቸው አይቀርም፡፡ ቢህም ረገድ ጥራዝ ነጠቅ አማካሪዎችና ግልብ ኦዲተሮች ለችግሩ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ አለም አቀፍ ተሞክሮዎች ያስጠነቅቃሉ፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን የ አይሶ 9000 ተመራቂዎች ቁጥር ባልተጠበቀ ሁኔታ እየቀነሰ መሄዱን ከተለያዩ ቦታዎች የሚወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ምክንያቱም በሌላ አማራጭ ወይም ግኝት አልያም አዲስ ወረት ይሆን ወደፊት የምናየው ይሆናል 700"000 ደርሰዋል የሚባለው ግን ጅምላ ቁጥር እንደሆነ ሊዘነጋ አይገባም፡፡ ነገር ግን "የጥራት ኦዲት አገልግሎት ሰጪ" ከፍተኛነት ከምክንያቶቹ አንዱ እንደሆነ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ኦዲቱ ቢያንስ በየስድስት ወሩ ሶስት ተከታታይ አመታት መከናወን ይኖርበታል፡፡ ይህ ካልሆነ በአይሶ 9000 መመረቅ የለም፡፡ መውደቅ አለ፡፡ መነጠቅም አይቀርም፡፡ አንድ ድርጅት አይሶ 9000 ሰርተፊኬት የለውም ማለት የጥራት ዘዴ አሰራር የለውም ማለት እንዳልሆነ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ በደንብ ሊኖረው ይችላል፡፡ ገበያውና ደንበኞቹ እስካላስገደዱት እንዲሁም የድርጅቱ ማኔጅመንት እስካመነበት ድረስ አይሶ 9000 መሠረት ያደረገ ነገር ግን በውጭ ኦዲተሮች ያልተመረመረ የጥራት ዘዴ መተግበር ይችላል፡፡ እንዲያውም ያዋጣል፡፡ ካዩኝ አላዩኝም ነፃ ይሆናል፡፡ ግን ይህ አሰራር ለጥራት ከፍተኛ ቁርጠኝነትና ተነሳሽነት ያለው ሠራተኛና ማኔጅመንት ግድ ይላል፡፡ ለዚህ የበቃ ድርጅት ከ9000 በላይ ተጉዟል ማለት ይቻላል፡፡ በዘመኑ የማኔጅመንት እሳቤ ትልቁ ቁም ነገር የዚህን አይነት ማኅበረሰብ መፍጠር ነው፡፡ አንድ ድርጅት በ አይሶ 9000 ተመርቋል ማለት በደፈናው ጥራት ያለው ምርትና አገልግሎት አለው ማለት አይደለም፡፡ ሠርተፊኬቱ የሚነግረን ድርጅቱ አለም አቀፍ እውቅና ያለው የጥራት ሲስተም አለው ማለት ነው፡፡ ለዚያውም ብቃትና ተአማኒነት ባለው የጥራት ኦዲተር ከታየ ነው፡፡ አይሶ ራሱ ስለ ጥራት ዘዴ የሰጠው ትርጉም የሚያረጋግጠውም ይህንኑ ነው፡፡ የጥራት ሥራ አመራርን ለመተግበር የሚያስፈልጉ መዋቅር፣ መመሪያ ሂደትና ግብአቶች ማለት ነው፡፡ የጥራት ኦዲተሩ አይሶ 9000 መስፈርት የሚያሟላ ሲስተም መኖሩን አንጂ የሚመሰክረው፣ ድርጅቱ ጥራት ያለውን ምርት ማምረቱን አይደለም የሚያረጋግጠው፡፡ በመሆኑም ነው በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ አይሶ 9000 ተመራቂዎች ጥራት የሌላው ምርት ሲያመርቱ የሚታዩት፡፡ በዚህ ላይ አይሶ 9000 የሚረዳቸው ያንኑ ጥራት የሌለው ምርት በማያቋርጥና በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲያመርቱ ነው፡፡ ሆኖም ግን አይሶ 9000 ጥራትን አማራጭ ወይም አጋዥ እንጂ ጥራትን ፈጣሪና አረጋጋጭ አይደለም፡፡ በሌላ አገላለጽ በአግባቡ የተተገበረ አይሶ 9000 ያላቸው ድርጅቶች፣ ጥራት ያለው ውጤት ለማምጣት እድላቸው ከዜሮ በላይ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ጃፓንን ልብ ይሏል፡፡ አይሶ 9000 ባልተፈጠረበት ዘመን የጥራት ቁንጮ ለመባል በቅታለች፡፡ ይህ ማለት ኢንዱስትሪዎቻቸው የጥራት ዘዴ የላቸውም ማለት አይደለም፡፡ ይልቁኑ የምርት ሂደታቸውን ስታንደርዳይዝድ ማድረግ አንዱ ጥራትን ለማምጣት የሚጠቀሙበት ስትራቴጂ ነበር፡፡ በተግባር አይሶ 9000 ማለት ሂደትን ስታንደርዳይዝ ማድረግ ማለት ነው፡፡ አለም በሙሉ እኩል ወይም አንድ አይነት የሆነ የጥራት ዘዴ ይኑረው ማለትም ነው፡፡ ይህ ከሆነ የውድድር ትርጉም ምን ሊሆን ነው? ስሙስ? አይሶ ውድድር ወይስ እኩል ውድድር ለማንኛውም የሥራ አመራር ልሂቃን አይሶ 9000 የውድድርን መንፈስ ያቀናል የሚል አስተያየት ሲሰነዘሩ ይደመጣሉ፡፡ ደረጃው ሂደቱ ላይ እንጂ ውጤቱ ላይ እምብዛም ነው የሚሉም አሉ፡፡ ትችቱ ይቀጥላል፡፡ መሰረታዊ የአሰራር ለውጥ (BPR) እንዴት ከግትሩ ስታንዳርዳይዜሽን ጋር ይስማማል? በፈጠነ እድገት የሚጓዘው የኮንስዩመር ማኅበረሰብ የሚፈልገውን ፈጣን ለውጥ በ አይሶ 9000 ማሟላት ይቻላል? ልብ ይበል፡፡ አይሶ 9000 ጥሩ የጥራት ሥራ አመራር ላለው ድርጅት የጎጆ ክዳን ላይ እንዳለችው አንዲቷ ሰበዝ ነው፡፡ ለምሳሌ በአውሮፓ እየገነነ ያለውን 'Conformity Europena (CD)' ምልክት ለማግኘት አይሶ 9001ን ጨምሮ ከ200 የማያንሱ ደረጃዎችን መተግበር ይጠይቃል፡፡ አለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ባለስልጣን (IATA) ምን ያህል ደረጃዎችን እንደሚጠይቅ ልብ ይሏል፡፡ እዚህ ላይ ሌሎች የኳሊቲ ቴክኒኮች፣ ጽንሰ ሃሳቦች አሰራሮችና ስትራቴጂዎች መዘንጋት የለባቸውም፡፡ ስለዚህ አይሶ 9000 "የኳሊቲ ጭምብል" እንዳይሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ጭምብል በተለያየ ቀለምና ቅርጽ በዘመናችን የመረጃ ቴክኖሎጂ እየተገዛ በገፍና ያለ ርህራሄ እየቀረበ ነው፡፡ አይሶ 9001 አንዱ የኳሊቲ መዳረሻ እንጂ በራሱ ግብ ወይም የጥራት ማረጋገጫ አይደለም፡፡ ይልቁኑ የጥራት ማደናቀፊያ ሊሆን ስለሚችል በቅርበት ልንክታተለው ይገባል፡፡ በጥራት ሥራ አመራር እንቅስቃሴዎች በሙሉ ጥራት አምጪ አይደሉም፡፡ በወንድራድ ሰይፉ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |