| በወርቅ ማጭበርበር በተጠረጠሩት... |
|
|
| Sunday, 23 March 2008 | |
|
በወርቅ ማጭበርበር በተጠረጠሩት ላይ ክስ ሊመሰረት ነው
ከወርቅ ማጭበርበር ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው በእስር ላይ የሚገኙት የብሄራዊ ባንክ ሰራተኞች፣ የጂኦሎጂካል ሰርቬይ ሠራተኞች፣ ነጋዴዎችና ግለሰቦች ክስ እስኪመሰረትባቸው ድረስ በማረሚያ ቤት እንዲቆዩ፣ የፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ለከፍተኛው ፍርድ ቤት አንደኛ ወንጀል ችሎት መጋቢት 12 ቀን 2000 ዓ.ም በዋለው ችሎት ላይ ቀርቦ ለፍርድ ቤቱ አመለከተ፡፡ የኮሚሽኑ መርማሪ በተጠርጣሪዎቹ ላይ ሲያደርግ የነበረውን ምርመራ አጠናቆ ለኮሚሽኑ ዐቃቤ ሕግ ማስረከቡንም ተናግሯል፡፡ የኮሚሽኑ መርማሪ ለፍርድ ቤቱ ቀርቦ እንዳስረዳው፣ ምርመራውን ማጠናቀቁን፣ መጋቢት በ12 ቀን 2000 ዓ.ም ለኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ መስጠቱን ገልጾ፣ ዐቃቤ ሕግ ክስ መመስረቱ ወይም አለመመስረቱ እስኪታወቅ ድረስ ተጠርጣሪዎቹ በማረሚያ ቤት እንዲቆዩ ሲል ለፍርድ ቤቱ አመልክቷል፡፡ የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች በበኩላቸው፣ የኮሚሽኑ መርማሪ ምርመራውን ያጠናቀቀ በመሆኑ፣ ደንበኞቻቸው በዋስ ሊለቀቁ እንደሚገባ ለፍርድ ቤቱ አመልክተው፣ ክስ የሚመሰረትናበማረሚያ ቤት የሚቆዩ ከሆነ በ15 ቀናት ውስጥ ክሱን እንዲመሰርት ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡ የአቶ አምሳሉ አሰፋ ጠበቃ ደንበኛቸው ተጠርጥረው የታሰሩት ከአቶ ዳንኤል ዋቅጅራ ጋር መሆኑን አስታውሰው፣ አቶ ዳንኤል ዋቅጅራን ኮሚሽኑ በነፃ ስላሰናበታቸው አቶ አምሳሉም ሊሰናበቱ እንደሚገባ ለፍርድ ቤቱ አመልክተዋል፡፡ የኮሚሽኑ ዐቃቤ ሕግ በተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች የተነሱትን ጥያቄዎች ላይ በሰጠው ምላሽ፤ አቶ አምሳሉ አሰፋና አቶ ዳንኤል ዋቅጅራ ተጠርጥረው የተያዙ መሆኑን አስታውሶ፣ አቶ አምሳሉ አሰፋ ሐሰተኛ ሰነድ መስራታቸውን በማስረጃ በማረጋገጡ ክስ ሊመሰረት የሚያስችለው እንደሆነ፣ ነገር ግን አቶ ዳንኤል ዋቅጅራ የተጠረጡበት ጉዳይ አነስተኛ በመሆኑ ኮሚሽኑ ሊለቃቸው እንደቻለ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ ዐቃቤ ሕግ ክስ የሚመሰርት ከሆነ በ15 ቀናት ውስጥ እንዲመሰርት ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ይስጥልን በማለት የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች ያነሱት ጥያቄ፣ "በኛ በኩል ምርመራውን አጠናቀናል" በማለት ተቃውሞ እንደሌለው አመልክቷል፡፡ በየትኛው አንቀፅ እንደሚከሰሱ የሚያውቀው ዐቃቤ ሕግ ነው፡፡ ክሱ የዋስትና መብት ይከልክል ወይም አይከልክል አናውቅም፡፡ እኛ ግን ዐቃቤ ሕግ የሚመሰርተው ክስ ዋስትናን የሚከለክል ይሆናል ብለን እናምናለን" በማለት፣ የጠየቁት የዋስትና መብት ውድቅ እንዲሆን ለፍርድ ቤቱ አመልክተዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ግራና ቀኝ የተነሱትን ጥያቄና አስተያየቶች ካዳመጠ በኋላ "ተጠርጣሪዎቹ በአንድ የወንጀል ድርጊት ተባብረው ወንጀል መፈፀማቸውን ደርሸባቸዋለሁ" በማለት በአንድ ላይ መቅረቡን እንጅ በተነጣጠለ የክስ መዝገብ አለመቅረቡን ገልፆ፣ የተጠረጠሩበት ወንጀል አስር ዓመትና ከአስር ዓመት በላይ የሚያስቀጣ ሊሆን ስለሚችል በማለት የዋስትና ጥያቄውን እንዳልተቀበለው ገል"ል፡፡ ፍርድ ቤቱ ዐቃቤ ሕግ በ15 ቀናት ውስጥ አጠናቆ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቶ ለመጋቢት 29 ቀን 2000 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ በታምሩ ጽጌ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |