Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Friday
May 09th
Home arrow Sections arrow መንግሥት፡-
መንግሥት፡- Print E-mail
Sunday, 23 March 2008
Image- የጀመረውን ማሻሻያና ጥበቅ እርምጃ አጠናክሮ ይቀጥል!
- መመሪያዎቹን ግልፅ ያድርግ!


በጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ሰሞኑን ለፓርላማ የቀረበው ሪፖርት ለኑሮ ውድነት የሰጠው ትኩረትና የነበረው ጥያቄና መልስ በመንግሥትም በፓርቲዎችም ዘንድ ትኩረት የሳበ አጀንዳ ሆኖ መገኘቱ በእጅጉ በአዎንታ የሚታይ ነው፡፡
 
መንግሥት በስግብግብና ሸፍጠኛ ነጋዴዎች ላይ ጥብቅ እርምጃ እንደሚወስድ በቃልም በተግባርም እያሳየ ያለው እንቅስቃሴም የሚበረታታ ነው የኑሮ ውድነቱን ለማቋቋም የሚያደርገው ድጎማና የተርን ኦቨር ታክስና የተጨማሪ እሴት ታክስ ቅነሳ በምግብ ዙሪያ ማድረጉም የሚያስመሰግን ነው፡፡

አንዳንድ ተቃዋሚ የፓርላማ አባላ የተቃውሞ ሃሳብ ቢያቀርብም ከልብና በአዎንታ ተነስተው ችግሩን በማየትና ለችግሩ የመፍትሔ ሃሳብ በማቅረብ የተናገሩ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት መኖራቸውም መድረኩን ተስፋ ሰጪ አድርጎታል፡፡

ይህን ያልነው ሃሳብ አዎንታዊነቱ በአፅንኦት የምናስቀምጠው ሆኖ ከዚሁ ጋር በተያያዘ የምናቀርበው ሃሳብ ግን ያው የተለመደው ነው፡፡ መንግሥትና ኢሕአዴግ እርምጃ የሚወስዱት ከአደጋ በኋላ ለምን ይሆናል የሚል ነው፡፡ ቢቻል አረንጓዴ እየበራ እያለ፣ ካልተቻለም ብጫ ላይ ይሁን እንጂ ቀይ ከበራ በኋላ መፍትሄ ለማፈላለግ መሞከር አደገኛ ነው፡፡ ከቁጥጥር ውጭ የሆኑ ነገሮች ሊያጋጥሙ የሚችሉ መሆናቸውንም  መገመት ይበጃል፡፡ እርምጃው ጥሩ ነው መዘግየቱ ግን ለምን? ለምን? ለምን? የሚያሰኝ ነው፡፡

በአሁኑ ጊዜ ለገንዘብ ሚኒስትር፣ ከፖሊስና ከአገር ውስጥ ገቢ፣ ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ኮሚቴ ተቋቆሞ ጉዳዩን እየተከታተለ ነው፡፡ ይህ ኮሚቴ ቀደም ብሎም መቋቋም ነበረበት፡፡ ለሬሳ ምርመራ ሳይሆን ለመጀመሪያ እርዳታ" ያም ሆነ ይህ ግን ጠንከር ያለ እርምጃ በሸፍጠኛ ላይ መወሰድና አንዳንድ ግብሮችን ላይ የማንሳት እርምጃ መወሰድ ቀጥሉበት የሚያሰኝ ነው፡፡    

እርምጃ አወሳሰድ ላይ ወጥነት እንዲኖረው ማድረግም ሌላው የሚታብበት ጉዳይ ነው፡፡ ሸፍጠኛ ነጋዴ በየትኛውም ክልል ቢሆን በየትኛውም የስራ ዘርፍ ይሰማራ፣ በየትኛውም ቀንና ሰዓት ይሰረቅ የፈለገው ባለሥልጣን ጋር ይተዋወቅ፣ ይዛመድ ጠንካራ እርምጃ ሊወሰድበት እንደሚችል ማድረግ ይገባል፡፡ ያኛው ጠንካራ ነው ያኛው እንኳ ችግር የለም የሚል ማስተዛዘን እንደማይኖር ግልፅ መልዕክት ሊተላለፍ ይገባል፡፡

ይህን ለማድረግም ኢሕአዴግ መጀመሪያ ራሱ ውስጡን ይፈትሽ፣ የላሉ ብሎኖችን ይቀይር፣ ወይም ያጥብቅ፣ ቢሮክራሲውን ያፅዳ፣ ሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያውን በሥራ ያሳይ፡፡ ያኔ ሙስናን መዋጋትና ሽፍጠኛውን ማሳደድ "ገጠመኝ" ሳይሆን "መርህ" ይሆናል፡፡

መንግሥት ከሚወስዳቸው እርምጃዎች ጋር ተያይዞ መታየት ያለበት ሌላው ጉዳይ የመመሪያዎቹ ግልፅነት ምን ያህል ነው? የሚለው ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ወርቅና ባሌስትራ አንድ ነው ብለው ለማመሳከር የሚሞክሩ "ጭልፊቶች" ባሉበት ሁኔታ መመሪያዎች በግልፅ ካልተቀመጡ ተግባር ላይ ለማዋል አስቸጋሪ ነው፡፡

መንግሥት ሰሞኑን ያወጣው መመሪያ እንዲህ ይላል፡-
"የምግብ እህል እና የስንዴ ዱቄትን በሚመለከት ከመንግሥት የተሰጠ ውሳኔ
የዋጋ ግሽበት ከሚታይባቸው የሸቀጥ ዓይነቶች አንዱና ዋነኛው የምግብ እህል በመሆኑ የምግብ እህል ማለትም (ጤፍ፣ ስንዴ፣ በቆሎ፣ ማሽላ፣ ጥራጥሬ እና የመሳሰሉት) እንዲሁም የስንዴ ዱቄት ዋጋን ለማረጋጋት ሲባል ከተጨማሪ እሴት ታክስ እና ከተርን ኦቨር ታክስ ነፃ እንደሆኑ መንግሥት መወሰኑን የገንዘብና የኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

በዚህም መሰረት ከመጋቢት 10 ቀን 2000 ዓ.ም ጀምሮ የምግብ እህል (ጤፍ፣ ስንዴ፣ በቆሎ ማሽላ፣ ጥራጥሬ እና የመሳሰሉት) እንዲሁም የስንዴ ዱቄት ከተጨማሪ እሴት ታክስ እና ከተርን ኦቨር ታክስ ነፃ የተደረጉ መሆኑንን እንገልፃለን፡፡
የፌዴራል አገር ውስጥ ገቢ ባለስልጣን"

ይህ ነው የመንግሥት መመሪያ ቃል በቃል ሲነበብ "የመሳሰሉት" ማለት ምን ማለት ነው? ይህ ሁኔታ በግልፁ ተብራርቶ ካልተቀመጠ የዋህ የሚጎዳበትና ሽፍጠኛና ጉበኛ የሚጠቀምበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፡፡ አንድ ሰራተኛ በአንድ ትርጉም ሌላ ሰራተኛ በሌላ ትርጉም የሚተረጎምበት መንገድ መፈጠር የለበትም፡፡

ሌላው ችግር ያጋጠመው የግልፅነት ሁኔታም አለ፡፡ የምግብ እህል ከተጠቀሱት ታክስ ነፃ ናቸው፣ ሲባል ሆቴል ገብቶ ከእነዚህ ጥራጥሬዎች የተሰራ ምግብ የበላ ሰው ቫት ይከፍላል ወይስ አይከፍልም? በአንዳንድ ቦታዎች ይህ ችግር አጋጥሟል፡፡ ተመግበው ቫት ያለበት ሂሳብ ሲመጣላቸው ከስንዴ የተሰራ ምግብ ስለበላሁ ቫት አልከፍልም፣ ትከፍላለህ የሚል ጥያቄና "ጥል" የተነሳባቸው ምግብ ቤቶች አጋጥመውናል፡፡

ለዚህ ነው መመሪያው ግልፅ ይሁን የምንለው፡፡ ባለፈው "የቅንጦት ዕቃ" የሚል ትርጓሜ ችግር ፈጥሮ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ "የመሳሰሉት" የሚለው ቃል ችግር ፈጥሯል፡፡ መንግሥትና በነካ እጁ እነዚህንና አሻሚ ጉዳዮች ግልፅ ሊያደርግ ይገባዋል፡፡

ዋናው ችግር ግን የቃላትና የመመሪያ አይደለም፡፡ በአንድ በኩል በቅንነት ሰርተው መኖርና መበልፀግ የሚፈልጉ አሉ፡፡ በሌላ በኩል አጭበርብረው ለመበልፀግ የሚሯሯጡ አሉ፡፡ የአመለካከትና የስብዕና ችግር ያለባቸው በተፈለገው መንገድ ቃላት በግልፅ ቢቀመጥላቸው አይሰሙም፡፡ በእነዚህ ላይ ጥብቅ እርምጃው ተጠናክሮ ይቀጥል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የማሻሻያው ጉዳይ ሰፋ ብሎ ይቀጥል፡፡ በጥናት ላይ ግን ይመስረት፡፡ 
 
< Prev   Next >