| ለውጥ የሚፈጥር እርምጃ ያስፈልጋል |
|
|
| Sunday, 23 March 2008 | |
|
ጠቅላይ ሚኒስተር መለስ ዜናዊ ባለፈው ማክሰኞ ባቀረቡት ሪፖርት ተጨባጭ የሚባልና የሚታይ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገባችንን ተናግረዋል፡፡ የኢኮኖሚ እድገት ሲኖር ምርትና አገልግሎት ይጨምራል፡፡ የምርትና የአገልግሎቶች መጨመር የዋጋ ንረትን ይቀንሳል፡፡ ሆኖም አለ በሚባለው የኢኮኖሚ እድገት ይህ አልታየም፡፡ በአገሪቱ ውስጥ የተከሰተው የምግብ እህሎች ዋጋ ጭማሪ ምክንያት ምርት ወደ ገበያ ስላልመጣ ነው፤ ምርት ቢመጣ ዋጋ ይቀንሳል ቢባልም ይበልጥ እየጨመረ ነው፡፡
አሁን የምግብ እህሎችን በተመለከተ አብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ታክስ መክፈሉን የማያውቅ ነው፡፡ ደረሰኝ የሚቀበለውም ጥቂት ነው፡፡ አሁንም ቢሆን በምርቱ ላይ ታክስ መኖር አለመኖሩን የሚያረጋግጥ በትክክል ተግባራዊ መሆኑን የሚከታተል ጠንካራ አካል የለም፡፡ ይህንንም ለማድረግ ሰፊ አቅም ይጠይቃል፡፡ መንግሥት የዋጋ ንረቱን ትክክለኛ ምክንያት በማጥናት ለውጥ ሊያመጣ የሚያስችል እርምጃ ለመውሰድ ቢያስብ መልካም ነው፡፡ (ሩት አዳነ፣ ከአዲስ ሰፈር) ባህላዊ እሴቶችን ለመጠበቅ ይረዳል በረቡዕ የኪንና ባህል አምድ ላይ የጉጂ ኦሮሞ ስነ ቃልን በሚመለከት የቀረበው ፅሑፍ እንደ ኢትዮጵያ በርካታ ብሔር ብሔረሰቦች በሚኖሩበት አገር ያሉ የተለያዩ የባሕል እሴቶችን በማስተዋወቅ ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡ የተለያዩ ብሔሮች ወይም የሕብረተሰብ ክፍሎች የሚከተሉትን የተለየ ባሕላዊ ሥርዓት የሚያሳይ ቀጣይ ኘሮግራሞች ቢሠሩ ባህልን ለማስተዋወቅና ታሪካዊና ባህላዊ እሴቶችን ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ይረዳል፡፡ (ሒሩት፣ ከቤላ) ተመራጭነት ለማን? በቅርቡ የቀድሞው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ የነበሩት ኮፊ አናን የኬንያን የምርጫ ውዝግብ በውይይት እንዲፈታ ካደረጉ በኋላ ከኒውስ ዊክ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ "በምዕራባውያን ሰዎች ሀብት ሲፈልጉ ወደንግድ ይሄዳሉ፡፡ በአፍሪካ ግን ሃብት የሚፈልግ ሰው ፖለቲካ ውስጥ ይሳተፋል" ብለዋል፡፡ የአናን ንግግር እውነታ ያለው በመሆኑ በሚያዚያ ወር ለመሳተፍ በእጩነት የተመዘገቡ እጩዎች ፖለቲካ ውስጥ ሲሳተፉ ለህዝብ ፍትህን ለማስገኘት ወይስ ሀብት ለማካበት አስበው መነሳታቸውን ልንመረምር ያስፈልጋል፡፡ (አቡሽ፣ ከሳሪስ) ራስ ሳይጠና ጉተና በአገራችን የዩኒቨርሲቲዎች በቁጥር መበራከት አስፈላጊ ቢሆንም የአሠራርና አመራር እንዲሁም የትምህርት ሥርዓቱን ለጥራት ማብቃት ብዙ እንደሚቀረው ማስተባበል የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ቁጥሩን የማብዛቱን ያህል በአንፃሩ በሌሎች የአቅም ግንባታ ገጽታዎች ላይም በትኩረት መሥራት ይገባል፡፡ አሁን ያለው እውነታ እንደሚያመለክተው ይኼኛው ገጽታ ለፖለቲካ ፋይዳ ሲባል ደብዝዞ ይስተዋላል፡፡ ይህን ግምት ተጨባጭ የሚያደርገው ምክንያት ተገቢው የዝግጅት ሂደት ሳይጠናቀቅ ሕንፃዎቹ ተዋቅረዋል በማለት ብቻ ተማሪዎች ገና በመሠራት ላይ ወደ አሉት "ዩኒቨርስቲዎች" ተመድበው መታየታቸው ነው፡፡ ሠመራ፣ ሚዛን ቴፒ፣ ወላይታ ዩኒቨርሲቲዎች ወዘተን. መጥቀስ በቂ ይሆናል፡፡ ጉዳዩ ባለቤት የሌለው ይመስላል፡፡ ትምህርት ሚኒስትርና ዩኒቨርስቲዎቹ አንዱ በሌላው ላይ እያመኻኙ በቂ መልስ ለጠያቂዎች አይሰጡም፡፡ መፈራራት አለ፡፡ የነገ የአገር ተስፋ የሆኑት ተማሪዎች ደግሞ ዝምታውን እስከ መቼ ሊሸከሙት ይገባል? የመታደል ጉዳይ ሆኖ ወደ ነባርና ዝግጅታቸው ወደተጠናቀቀ አዳዲስ ዩኒቨርስቲዎች የተደለደሉት እኩዮቻቸው የግማሽ ዓመት የትምህርት ሂደት ሲያገባድዱ ጥሪ የሚጠባበቁት ተማሪዎች ቀንን ሲቆጥሩ ለመቆየት መገደዳቸው ምን ያህል እንደሚያስጨንቅና እንደሚከብድ ወላጅ ይፍረደው፡፡ በዚህ ዐቢይ የትውልድ ጉዳት ዙሪያ ብዙ ማለት ቢቻልም የሚመለከታቸው አካላት ዝምታውን ትተው ለችግሩ ተግባራዊ ምላሽ ይስጡ፤ ልብን ከማንጠልጠል ትክክለኛውን የጥሪ ወቅት በብዙሃን የመገናኛ ዘዴ ጊዜ ሳይወስዱ ለተማሪዎች ይግለፁ እላለሁ፡፡ (ምርከና፣ ከአዲስ አበባ) በነጋዴዎች ላይ የሚደረገው ቁጥጥር ይቀጥል ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ባለፈው ማክሰኞ ባቀረቡት የስድስት ወር ሪፖርታቸው ከተርን ኦቨርና ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነፃ እንዲሆኑ በተደረጉ የምግብ እህሎች ላይ የፃፋችሁትን አንብቤያለሁ፡፡ በጣም ጥሩ ውሳኔ ነው፡፡ ነገር ግን ነጋዴዎችን እንዴት ነው መቀነስ አለመቀነሳቸውን ማረጋገጥ የሚቻለው? ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል ሥለሚያስፈልጋቸው አስፈፃሚ አካሎች፣ እባካችሁ ለህዝባችሁ ስትሉ ተግባራዊ መሆኑን በተለያየ ዘዴ ተጠቅማችሁ አረጋግጡ፡፡ (ፍሥሐፅዮን፣ ከተክለሃይማኖት) የፖለቲካ ተቋማትን ማጠናከር ግድ ነው ያለፈው እሮብ በፖለቲካ አምድ ላይ ያወጣችሁት የፖለቲካ ተቋማት በዴሞክራሲ ግንባታ ሂደት ውስጥ ያላቸውን ሚና በተመለከተ ሰፋ ያለ ምሁራዊ ትንታኔ ቀርቧል፡፡ ትንታኔው የሚወደድ ነው፡፡ በአንድ ሀገር ውስጥ የፖለቲካ ተቋማትን ማጠናከር ለዴሞክራሲ ግንባታው አስፈላጊ ሆኖ ሳለ በሀገራችን ያለውን እውነታ ከተመለከትን ግን አሳዛኝ ነው፡፡ ተቋማት ነፃ ካልሆኑ ዲሞክራሲን መገንባት አስቸጋሪ ነወ፡፡ በሌላ በኩል ፓርቲዎች በተለይ ገዢው ፓርቲ የዴሞክራሲ የዕከላዊነት በሚል አባላቱ ዲሞክራሲያዊ አስተሳሰቦችን በነፃነት የሚያራምዱበት ክፍተት ማጣታቸው ግልፅ ነው፡፡ ሀገራችን ከሶሻሊስት አስተሳሰብ የምትላቀቀው መቼ ይሆን? (ፍቅሩ፣ ከጃንሜዳ) መንግሥት ሙስናንም ያስቁም በአሁኑ ወቅት እየከበደ ከመጣው የኑሮ ውድነት ይበልጥ በአስደናቂ ሁኔታ እየረቀቀ እየተስፋፋ የመጣው ሙስና እጅግ አሳሳቢ ነው እላለሁ፡፡ ሙስና በተንሰራፋበት አገር ደግሞ መልካም አስተዳደር፣ የሕግ የበላይነት፣ እኩልነት ጨርሶ ሊታሰብ አይችልምና መንግሥት ጉዳዩን የአንድ ኮሚሽን ጉዳይ ከማድረግ በላይ የኔም ነው ብሎ ለንቀሳቀስ ይገባል፡፡ (መሀሪና ጓደኞቹ፣ ከሽሮ ሜዳ) |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |